ስለ ኦቲዝም – ከግንዛቤ ባሻገር…

የቀድሞ የካቢን ሠራተኛ (የበረራ አስተናጋጅ) እና በአቪየሽን አካዳሚ መምህርት ነበረች። በትምህርት ራሷን ለማብቃት የተለያዩ ሥልጠናዎችን፣ ሴሚናሮችን እና ወርክሾፖችን በተለያዩ ሀገራት እና በኢትዮጵያ ወስዳለች- ወይዘሮ ትዕግስት ኃይሉ።

ወደ ትዳር ዓለም ከገባች በኋላ እርሷ እና ባለቤቷ አቶ ክንፈ ጽጌ የመጀመሪያ ልጃቸውን አገኙ። ልጃቸው ናታን ክንፈ ኦቲዝም እንዳለበት ሲያውቁ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋቡ። በተደጋጋሚ ‹‹ግን ለምን?›› የሚለውን ጥያቄ ከመጠየቅና ከብዙ መብሰልሰል በኋላ በአንድ ነገር እርግጠኛ ሆኑ። በመተጋገዝ እንዲሁም በመነጋገር ልጃቸውን መርዳትና ማገዝ እንደሚችሉ አመኑ፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት የልጇን ሕይወት ለመቀየር ለ14 ዓመት ያህል ከሠራችበት መሥሪያ ለቃ ልጇን በማስተማር ብዙ ለፍታለች። ዛሬ ልጃቸው የ15 ዓመት ታዳጊ እና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆናል። ብዙ ወላጆች ወደ እነ ወይዘሮ ትዕግስት ቤት እየመጡ ልምድ ይቀስማሉ። እነርሱም ከሌሎች ሃሳብ ይቀበላሉ። የመረጃ ልውውጡ አድጎ ‹‹ምሉዕ ፋውንዴሽን›› የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንዲመሠረት ምክንያት ሆነ።

የትዳር አጋሮቹ የመሠረቱት የበጎ አድራጎት ድርጅት በ2013 ዓ.ም በይፋ ሥራውን ጀመረ። የቴራፒ (ሕክምና መስጫ) ማዕከሉ ወደ ሥራ ከገባ ደግሞ ዘጠኝ ወራትን ተሻግሯል። ወይዘሮ ትዕግስት በአሁን ወቅት ፋውንዴሽኑን በማስተዳደር ላይ ትገኛለች።

ፋውንዴሸኑ እንደ ስሙ ምሉዕ እንዲሆን እና የተቀናጀ ማኅበረሰብን ለመፍጠር፤ በተለይም ኦቲዝም ያለባቸውና ሌሎች ልዩ ፍላጎት ለሚያስፈልጋቸው ሕጻናትና ወላጆች የሥልጠና ማዕከልን በማቋቋም፣ አካላዊ እና አዕምሯዊ ሕክምና መስጠትና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ማዘጋጀት ከዓላማዎቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት እንደሚያስረዱት፣ ፋውንዴሽኑ የቴራፒ አገልግሎቱን መስጠት ሲጀምር ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት እና ከዛ በላይ የሆኑ እና የትምህርት ዕድል ላላገኙ ሕፃናት ቅድሚያ በመስጠት ሲሆን፤ በሦስት ፈረቃ እገዛ ያደርግላቸዋል። ልጆቹንም እገዛ በደንብ የሚሹ፣ ትምህርት ቤት የገቡ ነገር ግን መጠነኛ እገዛ የሚሹ እና ትንሽ እገዛ የሚሹ ብሎ በመለየት በአሁን ወቅት እድሜያቸው ከሦስት እስከ 12 ላሉ 34 ልጆች አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል። ድርጅቱ ለአስተዳደራዊ ወጪ ብቻ ከወላጆች አነስተኛ ወጪ ይጋራል።

በማዕከሉ ያሉ ልጆች የዕለት ተዕለት እንቅሰቃሴቻው ስለሚመዘገብ ምን ላይ መሥራት እንደሚገባ እና ምን ላይ ጠንካራ እንደሆኑ ዳሰሳ በማድረግ እንዲሁም እቅድ በማውጣት ልጆቹ ላይ ይሠራል። ከዚህ በሻገር ወላጆች ልጆቻቸው በሌሉበት ሰዓት ቁጭ ብለው ሂደቱን እንዲከታተሉ እና ተመሳሳይ ክትትል በቤታቸው እንዲያደጉ ይደረጋል። አገልግሎት ሰጪ መምህራን ልዩ ፍላጎት ላይ የሚሠሩ እና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ ተቋሙ አገልግሎት በማይሰጥበት ቀን በተለያየ የሙያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን በማስመጣት ሥልጠና እንዲያገኙ ያደረጋል። በተጨማሪም ራሳቸውን እንዲያበቁ እና እርስ በእርስ እንዲማማሩ ይደረጋል።

በማዕከሉ ልጆች በሚፈለገው መልኩ እንዲጫወቱ፣ ራሳቸውን ችለው እንዲመገቡ፣ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ተግባቦት እንዲያዳብሩ እና ነገሮችን በራሳቸው ለማድረግ በቀላሉ በቤታችን ውስጥ የሚገኙ ማስተማሪያ መሣሪያዎችን እንዲሁም ቦታዎችን (ኮርነሮችን) በማዘጋጀት የትምህርት ሂደቱን እንዲያልፉት ይደረጋል። ይህን የሥነ ማስተማር ዘዴ በአገራችን ለማስፋፋት ወይዘሮ ትዕግስት የራሷ የሕይወት ተሞክሮ እና በተለያዩ አገራት ላይ ተዘዋውራ መሥራቷ ልምዶችን እንድትቀስም ረድቷታል።

ፋውንዴሽኑ በሥልጠና መርሐ ግብሩ እስካሁን ከሁለት ሺህ በላይ የልዩ ፍላጎት ወላጆች፣ ተንከባካቢዎች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች፣ በሕፃናት ማሳደጊያዎች፣ በሆስፒታሎች እና በተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ራሳቸውን ችለው ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ለማገዝ በእውቀት ላይ የተደገፈ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በፋውንዴሽኑ ቤተ መጽሐፍት በሁሉም እድሜ ክልል ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚገለገሉበት ከሦስት ሺ በላይ የተለያዩ መጽሐፍትን በውስጡ አካቷል። ለወደፊት ሲጠናከር ደግሞ ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 18 ዓመት ያሉ ታዳጊዎችን በማሠልጠን ወደ ማኅበረሰብ ተቀላቅለው እንዲሠሩ ለማድረግ ጥረት እንደሚደርግ ወይዘሮ ትዕግስት ይናገራሉ፡፡

ወላጆች ከበረቱ ልጆቻቸውን ማገዝ እና መቀየር ይችላሉ። ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ነገሮችን የሚረዱበት መንገድ የተለየ ነው። ‹‹ልጄ ነው አስተማሪዬ›› የምትለው የናታን እናት ትዕግስት፤ ልጇን ከንግግር በዘለለ ለማስተማር ሥዕላዊ መግለጫዎችን ትጠቀማለች። እንዲህ ያሉት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ እያንዳንዳቸውን በተለየ መንገድ ማስተማር አዳጋች እንደሚሆን በማንሳት፤ ትምህርት ቤቶች በእውቀት የተመሠረተ ትምህርት እንዲሰጡ ድርጅታቸው ሥልጠናዎችን በቻለው አቅም እንደሚሰጥ ያስረዳሉ፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ልጇን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ብዙ ተቸግራለች። ይሁን እንጂ በቻለችው ሁሉ ልጇን ለማስተማር ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ለብዙዎችን ለመድረስ እንደተቋም በሦስት ዓመት ውስጥ የአካቶ ትምህርት ቤት ለመክፈት ዕቅድ መኖሩን ገልፃለች። ፋውንዴሽኑ ከዚህ በተጓዳኝ መጋቢት 24 የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የኦቲዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ምክንያት በማድረግ ፋውንዴሽኑ ‹‹የማብቃት ታሪኮች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና በዘለቄታዊ የልማት ግቦች ከኦቲዝም ግንዛቤ ጋር በማጣጣም የተገኙ ድሎች›› በሚል መሪ ሃሳብ ያከብራል። በዚሁ ዕለት ‹‹እራት በምክንያት›› የተሰኘ መርሐ ግብር በማካሄድ ከግንዛቤ ባሻገር ወደ ተግባር እና ወደ ኃላፊነትን እንዲገባ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፡፡

ኦቲዝም በሕፃናት የነርቭና የእድገት ክትትል ላይ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ሲሆን ከሰው ጋር የሚደረገውን ግንኙነትና የመግባባት ችሎታ (ክህሎት) የሚጎዳ ወይም የሚቀንስ የሕመም አይነት ነው። በዋናነት ከሚታዩ ምልክቶች፤ ቋንቋ እና ምልክትን ለመግባባት መጠቀም አለመቻል፣ የሰው ዓይን አለማየት፣ በተደጋጋሚ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ወይም መደጋገም፣ በአንድ አይነት መጫወቻ ብቻ ራስን መወሰን፣ የትኩረት ማነስ፣ ከሰው ወይም ከሌሎች ልጆች ጋር አለመቀራረብ (ለብቻ መጫወት) እና የመሳሰሉት እንደሆነ የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስት እና ረዳት ፕሮፌሰር ከሆኑት ከዶክተር ፋሲል መንበረ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ለመረዳት ይቻላል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን መጋቢት   5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You