የንቅናቄው ተስፋ ሰጪ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች

መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሄ ርምጃዎች መካከል በሚያዝያ 2014 ዓ.ም፣ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ይጠቀሳል።

የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፤ ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል፤ በዘርፉ ያለውን የስራ ባህል ማሻሻል እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው።

ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍና አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው። የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሰራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል። በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ ከፍ እንደሚያደርግ ተሥፋ ተጥሎበታል።

ንቅናቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ነው። ከንቅናቄው ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠርም ይጠበቃል። ሀገሪቷ በዘርፉ ያላትን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተጀመረው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ዋና ዋና ምሰሶዎቹ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ ናቸው።

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሃገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ተዋንያን በሆኑ በበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚተገበር ቢሆንም በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው። የሚኒስቴሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በንቅናቄው ትግበራ ለአምራች ዘርፉ ችግሮች መቃለል መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ንቅናቄው በተጀመረበት ዓመት ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላትን በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል፤ በዚህም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል። ከ352 በላይ ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል። 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል። አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል። ባለፈው የበጀት ዓመት በንቅናቄው በተከናወኑ ስራዎች፣ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትና የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 55 በመቶ ማድረስ ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎትና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በመያዝ አስተዋፅዖ እያደረጉ ይገኛሉ። የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል።

ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል። በሀገሪቱ በአምራች ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ ተቋማት በንቅናቄው እቅዶች ላይ ተመሥርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን፣ ንቅናቄውም ቀድሞ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው ይገኛል።

በ2016 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በንቅናቄው በኢንዱስትሪ ደረጃ ከተለዩ ሁለት ሺ167 ችግሮች (የግብዓት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመስሪያና የማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት … ችግሮች) መካከል፣ አንድ ሺ34 የሚሆኑት መፍትሄ እንዲያገኙ ተደርጓል፤ በቀሪዎቹ አንድ ሺ133 ላይ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፤ ችግሮቻቸው ከተፈቱላቸው አምራቾች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ አምራቾች ናቸው።

በርካታ ተሳታፊዎች የሚገኙባቸውና ከፍተኛ ግብይት የሚፈፀምባቸው እንዲሁም የአምራቾችን አቅም የሚያጎለብቱ የንግድና ግብይት ትስስሮች የሚፈጠሩባቸው ኤክስፖዎችም የንቅናቄውን ትግበራ የሚያሳልጡ መድረኮች ናቸው። ንቅናቄው የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የመጀመሪያው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት ሁለት ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ መካሄዱ ይታወሳል። ለአምስት ቀናት የተካሄደው ኤክስፖ ከ450 በላይ ተጋባዥ እንግዶች፣ ከ25 በላይ መገናኛ ብዙኃንና ከ53ሺ በላይ ጎብኚዎች የተሳተፉበት እና ከ125 በላይ የንግድ ስምምቶች የተፈረሙበት እንዲሁም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት የተፈፀመበት ነበር።

ዘንድሮም ሁለተኛው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኤክስፖ በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን ለዓለም አቀፍ ሸማቾች የማስተዋወቅና የገበያ ተደራሽነታቸውን የማስፋት፣ የውጭ ቴክኖሎጂዎችንና ኢንቨስትመንቶችን ወደ ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመሳብ እንዲሁም አምራችና የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ ባሉ ባለድርሻ አካላት መካከል ትብብር የመፍጠር ዓላማዎችን ይዞ ይካሄዳል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አማካሪና የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር አያና ዘውዴ እንደሚናገሩት፣ ንቅናቄው እስካሁን ያገለገሉት አሰራሮች የአምራች ዘርፉን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የማያስችሉ በመሆናቸው የተተገበሩ ይገኛሉ። በንቅናቄው ትግበራ ከ10 ዓመታት በኋላ የአምራች ዘርፉ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማድረስ፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢን አሁን ካለበት 500 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በማሳደግ ዘርፉ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የ45 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው ለማድረግ እንዲሁም ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል። በተጨማሪም የዘርፉን የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ ንቅናቄው እየተተገበረ ይገኛል።

ይሁን እንጂ የተለመዱ አሰራሮችን በመተግበር እነዚህን እቅዶች ማሳካት እንደማይቻል አማካሪው ጠቅሰው፣ አሰራሮቹ አምራች ኢንዱስትሪው ያሉበትን መዋቅራዊ ማነቆዎች ለመፍታት የማያስችሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፤ ሁሉንም የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን የሚያቀናጅ ተቋማዊ ንቅናቄ በመፍጠር መዋቅራዊ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ ንቅናቄው በ2014 ዓ.ም ይፋ ተደርጎ እየተተገበረ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

የንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ዘርፉን ማነቆዎች በመለየት በተደራጀና ተቋማዊ በሆነ አሰራር መፍታት፣ የዘርፉን ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ማሳደግና ዘርፉ ለኢኮኖሚ ሽግግሩ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ይገባል። አምራች ዘርፉ አሁን በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የሰባት በመቶ ድርሻ ወደ 17 በመቶ በማሳደግ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ማድረግ ይገባል።

የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ግንባታን ማሳደግ፣ መሪ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር፣ የጥናትና ምርምር ችግር ፈቺነትን ማሳደግ፣ ምቹ የቢዝነስ ከባቢ መፍጠርና ሀገር በቀል ምርቶችንና አምራቾችን ማሳደግ የንቅናቄው ዋና ዋና ምሰሶዎች ናቸው። የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ ግንባታን እውን ለማድረግ የኢንዱስትሪ ሰላምን ማረጋገጥና የስራ ባህልን ማሳደግ ይገባል። ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ትልቅ ድርሻ የሚኖራቸውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር የምርት መጠንና ጥራትን ያሳድጋል፡፡

ባለድርሻ አካላት የዘርፉን ችግሮች በባለቤትነት በመያዝ ለመፍትሄው በተቀናጀ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ተግባርም የንቅናቄው ምሰሶ አካል ነው። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጥናትና ምርምር ስራዎች ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው፤ ስለሆነም የጥናትና ምርምር ስራዎቹን ምርትንና የቴክኖሎጂ አቅምን ሊያሳድጉ በሚችሉበት ሁኔታ መተግበር ይገባል። ዘላቂ ተወዳዳሪነትን ለመገንባት ሀገር በቀል ምርቶችንና አምራቾችን ማሳተፍና ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡

‹‹ንቅናቄው በሚያዝያ 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ ከተደረገ በኋላ ንቅናቄውን የሚያስተባብርና የሚመራ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሟል። የችግሮቹን ዓይነትና ባህርይ መሰረት ያደረጉ አምስት ክላስተሮች ተደራጅተዋል። እነዚህ ክላስተሮች የመሰረተ ልማት፣ የግብዓት ልማት፣ የአቅም ግንባታና ምርምር፣ የኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የፋይናንስና የጉምሩክ ክላስተሮች ሲሆኑ፣ በእያንዳንዱ ክላስተር ውስጥ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ሚኒስቴሮች፣ ኮሚሽኖችና ባለስልጣኖች ይሳተፋሉ። ለአብነት ያህል የግብርና ሚኒስቴር በግብዓት ልማት ክላስተር፣ የትምህርት ሚኒስቴር በአቅም ግንባታና ምርምር ክላስተር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በፋይናንስና ጉምሩክ ክላስተር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ ክላስተር ውስጥ በተቀናጀ መንገድ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡

የክላስተሮቹ አደረጃጀት የተደራጀ እቅድን እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ስርዓትን መሰረት ያደረገ ሲሆን፣ በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች የሚተገበር ነው። በእያንዳንዱ ክላስተር ምን ምን ተግባራት እንደተከናወኑና ምን ውጤቶች እንደተገኙ ክትትልና ግምገማ ይደረጋል›› በማለት ዶክተር አያና ያብራራሉ።

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እንዳስገኘ ዶክተር አያና ያስረዳሉ። በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከንቅናቄው የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።

የኢንዱስትሪ ፖሊሲው ንቅናቄው ካስገኛቸው ውጤቶች መካከል አንዱ ነው። በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ከታኅሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል የተወሰነው ፖሊሲው፣ የግሉ ዘርፍ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ የመሪነት ሚና እንዲኖረው ያግዛል። ፖሊሲውን ለማስፈፀም የሚያስችሉ 18 ስትራቴጂዎች ይዘጋጃሉ። ከእነዚህ ውስጥ የአራቱ ስትራቴጂዎች ዝግጅት ተጠናቋል። ስትራቴጂዎቹን ከማዘጋጀት በተጨማሪ ወደ ተግባር የመቀየሪያ ስልት ተነድፏል።

ለአነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ለሊዝ ፋይናንስና ለስራ ማስኬጃ እንዲሁም ለከፍተኛ አምራቾች የተሻለ ብድር ማቅረብ ተችሏል። ክልሎች ከ12ሺ ሄክታር በላይ የለማ መሬት አዘጋጅተው ለአምራቾች አቅርበዋል። የኃይል አቅርቦት ተሻሽሏል፤ የማምረት አቅም አጠቃቀም አድጓል።

ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ አምርቶ በመተካት ረገድ፣ በ2015 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል። በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ደግሞ በተኪ ምርቶች ከ994 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል።

የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች እንዳሉ አይካድም። ይሁንና እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ለወቅቱ የሚመጥን ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ የማምረት አቅምን በማጎልበት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ተጨማሪ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለማቃለልና ተወዳዳሪ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ያስችላል ተብሎ የታመነበት የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ አማራጭ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው።

የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመፍታት ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅዖ የሚኖረውን ይህን ንቅናቄውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ ዘመቻው ምን ለውጥ እንዳስገኘ በየጊዜው ክትትል እያደረጉ መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ንቅናቄውን እንዲሁም ዘርፉን ውጤታማ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ምቹ የኢንዱስትሪ ከባቢን መፍጠር ይጠበቅበታል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን መጋቢት   5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You