ዛሬም በታላቅ ማንነታችን፣ በከበረውም ስማችን እንኑር!

ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ፊት፣ ቀና ብላ በኩራት እንድትራመድ ካደረጓት ደማቅ ገድሎች መሀል አድዋ አንዱ ነው፡፡ አድዋ እውነት ከማይመስሉ ግን ደግሞ እውነት ከሆኑ የዓለም ታላላቅ ገድሎች ውስጥ አንዱ ለመሆን የበቃ እልህ አስጨራሽ የሕልውና ፍልሚያ የፈጠረው አንጸባራቂ ድል ነው፡፡ በሁለት ጎራ ባሉ (ራስወዳድና ፍትሀዊ ነፍሶች) መሀል የተደረገ የባሕል፣ የታሪክ፣ የማንነት፣ የነጻነት፣ የክብር፣ የሉአላዊነት ተጋድሎ ነው፡፡

አንዱ በኃይል ሌላው በሕዝባዊነት ሉአላዊነታቸውን ለማስቀጠል ያደረጉት የማንነት ትንቅንቅ በስተመጨረሻም ሕዝባዊነትን ይዘው ለፍትህ በቆሙት ነፍሶች የበላይነት ተጠናቀቀ፡፡ እንደ አድዋ ያሉ ለሰው ልጅ ሁሉ ትንሳኤ በመሆን በዘመን ውስጥ ሳይንገዳገዱ ማለፍ የሚችሉ የታሪክ አንጓዎች እንዴት ተከሰቱ ብለን ስንጠይቅ፣ ከዘርፈ ብዙ ምክንያቶቹ ውስጥ በቀዳሚነት የምናገኘው ሕዝባዊነትን ነው፡፡

ሕዝባዊነት ከድልና እድል ባለፈ በትውልድ እና በታሪክ መሀል የሚቀመጥ የብዙሀነት ቀለም ነው፡፡ አድዋን ማን ፈጠረው? እንዴት ተፈጠረ? አላማውና አስተማሪነቱስ ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ እኚህን መልሶች በቀዳሚነት እናገኛለን፡፡ እናም አድዋን ማን ፈጠረው? ከሚለው ጥያቄ ብንጀምር አንድነትና ሕዝባዊነት ባበሩበት የፍትህና የሚዛናዊነት እሳቤ በኩል ተፈጠረ የሚል መልስን እናገኛለን፡፡

በግርድፉ ብንናገር የኢትዮጵያውያን የድል ብስራትን እንመለከታለን፡፡ ኢትዮጵያውያን ዝም ብለው ወደ ጦርነት አልገቡም፡፡ በተቻላቸው ሁሉ በፍቅርና በንግግር ለመፍታት ጥረት አድርገው ነበር።እብሪተኛው የጣሊያን ወራሪ ግን ይሄን የእንነጋገር ሀሳብ ሳይቀበል በአሸንፋለው መንፈስ ወደጦርነት ገባ፡፡ ሆኖም ግን እንዳሰበው የሆነ አልነበረም፡፡ ነጭ ለምንግዜም የሚያፍርበትን፣ ጥቁር ለሁልግዜም የሚኮራበትን የነጻነትና የእኩልነት ታሪክ ጽፈን አለፍን፡፡

ይሄ የታሪክ ምዕራፍ ገናናነት እንዴት ተፈጠረ? የሚለው ጥያቄ ማን ፈጠረው? በሚለው ስነልቦና የሚመለስ ነው፡፡ እንዴት ተፈጠረ የሚለው ጥያቄ በውስጡ ኢትዮጵያዊነትን ያቀለመ ሀሳብ ነው፡፡ አድዋ እንዴት ተፈጠረ? የሚለውን ጥያቄ “በሀሳብ በላቁ፣ በአንድነት በበረቱ፣ ስለሉአላዊነታቸው እንቅልፍ በማይተኙ ነፍሶች ተፈጠረ” ብለን መመለስ እንችላለን፡፡

አላማውና አስተምህሮቱ ለዚህኛውም ሆነ ለዛኛው ትውልድ አንድ አይነት መልክ ያለው ነው። የአድዋ መነሻ በክተት አዋጁ ላይ እንደተጠቀሰው ሀገርና ርስትን ሊቀማ የመጣ፣ ባህልን ሊበርዝ፣ ማንነትን ሊቀይጥ የመጣ ባዕድ እንደሆነ ይታወቃል። ይሄን መነሻ አድርገን ብንናገር የእኛ የተጋድሎ ዓላማና የአድዋ ውጤት መድረሻ ኢትዮጵያዊነትን መታደግ፣ ታሪክና ባሕልን ማስቀጠል፣ ነጻነትንና ሉዓላዊነትን ትርጉም መስጠት ከምንም በላይ ደግሞ አብሮነትንና ወንድማማችነትን ማስቀጠል እንደሆነ እንረዳለን፡፡

አድዋ ብለው የተናገሩ የትኛዎቹም ጠቢብ አፎች፣ አድዋ ብለው የጻፉ የትኛዎቹም በሳል ብዕሮች ሲናገሩም ሆነ ሲጽፉ መነሻቸውን ሀገር መድረሻቸው ሕዝብ አድርገው ነው፡፡ መነሻና መድረሻው ሀገርና ሕዝብ የሆነ አእምሮና ልብ የአባቶቹን መንፈስ ወርሶ አንዲት ሀገርን ይፈጥራል እንጂ በታሪክ ተወቃሽ ለመሆን የአድዋን የአብሮነት መልክ አያደበዝዝም። አድዋ ከእኛ አልፎ አፍሪካ፣ ከዛም ዓለም አቀፍ የሆነ የአስተሳሰብ፣ የርዮተዓለምና የጥቁርነት ገናና ማህተም ነው፡፡ በዚህ ማህተም ካላማርንና ካልደመቅን፣ ካልሻርንና ካልታከምን፣ ካልተቃቀፍንና ካላበርን ሌላ የኢትዮጵያዊነት ቀለም የለንም፡፡

አድዋ ኢትዮጵያዊነት የተሰበሰቡበት፣ የተሳሰ ቡበት፣ የተለቁበት፣ የተደማመጡበት፣ የመከሩበትና የተዋሃዱበት የታሪክ ዋርካ ነው፡፡ በዚህ ዋርካ ስር እኔነትና ዘረኝነት አልነበረም፡፡ ብሄርና ጎሳ፣ ዘርና ቋንቋ አልነጣጠሏቸውም፡፡ ጥላቻና መገፋፋት፣ ቂምና ቅራኔ አጥር አልሰሩም፡፡ እናም የዓድዋ ዋርካነት ሁሉንም በእኩል ያስጠለለ የእውነተኛይቱ የኢትዮጵ ስም ነበር፡፡ ይሄ ስም ለመላው ዓለም የነጻነት ብርሀንን ፈንጥቆ መላውን የሰው ልጅ ነጻ ያወጣ የጥቁርነት የጽናት ተምሳሌት ነው፡፡

በአድዋ የአንድነት ዋርካ ስር ኢትዮጵያዊነት ለምልሞ ነጻነት መጥቷል፡፡ የዘመናት የነጭ የበላይነት ተሽሮ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል መሆኑ እንደአዲስ የምስራች ተበስሯል፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ ዓለምና ሕዝቦቿ በተለይም ነጮቹ ከነበሩበት የኃይልና የአንባገነንነት እሳቤ ወጥተው እኩልነትና ሰብዐዊነት ያለበትን አዲስ የሕይወት ልምምድን እንዲለማመዱ ሆነዋል፡፡

ባርነትና ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሽረው ሰብዐዊነት የነገሰበት ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰው የሚሉት ፍጡር ከዘርና ከቀለም ርቆ በፍትህና በእኩልነት ሚዛን ብቻ እንዲለካ አስገዳጅ ስርዐትም ሰፍኖ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ አዲስ ስርዐት ከአድዋ በኋላ በኢትዮጵያውያን የተፈጠረ የብዙሀን ከእስራት ነጻ የመሆን የከእንደገና መወለድ ቀን ነበር፡፡

ለራስ ተርፎና በቅቶ ሌሎችን የነጻ ፋና መሆን ደስ ይላል፡፡ የነጻነት ምልክትነት በውስጡ በርካታ ሕብረብሄራዊ መልኮች ያሉት ማንነት ነው፡፡ አንድ ሀገር የነጻነት ምልክት ነው የሚባለው ለራሱ በቅቶ ራሱን ሲችል ነው፡፡ እኚህ ሂደቶች ደግሞ ብዙ መመዘኛዎች አሉት፡፡ ሌሎች ያልቻሉትን ችለን አፍሪካንና መላው ዓለምን ከባርነት ነጻ ስናወጣ አውቀንና ተረድተን፣ ተግባብተንና ተዋህደን፣ ተስማምተንና አብረን ቆመን ነው፡፡

እኚህ ውህደቶች ደግሞ ዝም ብለው አይመጡም ከታሪክና ከማንነት ጋር የተዋረሱ ሆነው የሚጠሩ ናቸው፡፡ ለሶስት ሺ ዘመን በሀገርነት ስንጠራ ምን ነበርን፣ እንዴት ነበር ሀገርና ሕዝብ የሆነው የሚለው ጥያቄ ይሄን ማንነታችንን የሚናገር እውነታ ነው። ከጥንት እስከዛሬ ብዙዎችን ከባርነት፣ ከጭቆና ነጻ እንዲወጡ መንገድ አሳይተናል፡፡ ለብዙ ሀገራት የሰላምና የመረጋጋት አስተዋጽኦ አድርገናል። ብዙዎች እንደሀገር እንዲቀጥሉ ከተሞክሯችን አካፍለናል፡፡ በዲፕሎማሲውና በመልካም ግንኙነት የራቀ ታሪክ አለን፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ አድዋ ተፈጠረ፡፡ እናም የነጻነት ፋናዎች ተባልን፡፡

የተጀመረው እንዲቀጥል፣ የቀጠለው ፍሬ እንዲያፈራ በአባቶቻችን የነጻነት መንፈስ መቀጠል አማራጭ የሌለው ግዴታችን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በአንድነት የደመቀው የድሮው አድዋዊ ስማችን ዛሬ ላይ በእኔነትና በራስወዳድነት ጨቅይቶ ክፍተት እያበጀ ነው፡፡ አሁናዊው የአንድነት መንፈሳችን መሸርሸር ነው ዛሬ ላይ ብሄር ወለድ ቁርሾዎች እንዲበረክቱ ያደረገው፡፡

እዚህጋ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፣ አንዳንድ ነገሮች ቀላል ይመስላሉ ግን ለትላልቅ ውድቀት መንገድ የሚጠርጉ ናቸው፡፡ ታላላቅ የሰውነት ስብራቶች ቀላል በሚመስሉ ነገሮች በኩል የመጡ ናቸው፡፡ እንደ ሀገር የምንሰቃይባቸው የብሄር አስተሳሰቦችም በነዚህ በኩል ሰርገው የገቡ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡ ለትናንሽ ነገሮች መንገድ ስንዘጋ ትላልቅ ሁነቶች እንዲቀጥሉ እድል እንሰጣለን፡፡ አድዋና መንፈሱ በዚህ ትውልድ ላይ እንዲደገም እነዚህ ትንሽ የሚመስሉ የልዩነት አስተሳሰቦች መደብዘዝ አለባቸው፡፡ ከብዙሀን የተሰጠን የነጻነት ዓርኣያነት ስም እንዲቀጥል በትንንሽ ሀሳብ መቧደናችንን ትተን ሀገር በሚጠቅም ትልልቅ ሀሳብ ስር መውደቅ አለብን፡፡

አድዋ የትልቅ ሀሳብ ውጤት ነው፡፡ በእኛ ትልቅ ሀሳብ በኩል የተንጸባረቀ የብዙሀን የትንሳኤ ጮራ ነው። በመሳፍንቶች መሀል ያሉ ትንንሽ አለመግባባቶች ተዘግተው ስለኢትዮጵያ በአንድነት የተከፈለ መስዋዕት ነው፡፡ ከዚህ ሀሳብ ተነስተን አድዋንና የዛን ዘመን አስተሳሰብ ብንዳስስ በመሳፍንቶች መሀል የነበረው አለመግባባትና ቅሬት ከሀገር የማይበልጥ ትንሽ ሀሳብ መሆኑን እንደርስበታለን፡፡ እነዛን ትናንሽ ውስጣዊ ችግሮች ትተን ስለሀገር ስለተቧደንን ነው አድዋን የፈጠርነው። ከሀገራችን ቅሬታዎቻችን በልጠው ቢሆንና ለቅሬታዎቻችን ቅድሚያ ብንሰጥ ኖሮ አድዋን ውሀ አይኖርም ነበር፡፡

ይሄ እውነታ ለዚህኛውም ትውልድ የሚሰራ ነው። በዚህኛው ትውልድ ስር መንገድ ያልተዘጋባቸው ለትልቁ ሕዝባዊ ጉዳይ መንገድ የከለከሉ ጥቃቅን ሀሳቦች እዚም እዛም አሉ፡፡ በትርክት ተደናግረን ሀገር ለሚጠቅሙ፣ ትውልድ ለሚያሻግሩ ጠቃሚ ጉዳዮች ኋለኞች ሆነን የቆምን አለን፡፡ የማይጠቅሙንን ሽረን ለሚጠቅሙን ስንደክም ብቻ ነው ዳግማዊ አድዋን የምንፈጥረው፡፡ መንገድ ያልዘጋንባቸው ትናንሽ ሀሳቦች ትልቁን ሀሳብ ሽረው ዋጋ እያስከፈሉን እንደሆነ ሊገባን ይገባል፡፡

አሁን ላለው ትውልድ ዳግማዊ አድዋን መፍጠሪያ ቁልፉ ተነጋግሮ መግባባት፣ ተግባብቶ አብሮ መኖር ነው፡፡ በእርቅና በምክክር ተጽዕኖ ፈጣሪነታችንን ማስቀጠል ከቻልን ያኔ የእኛ አድዋ ነፍስ ይዘራል፡፡ በመሀከላችን ገብተው ላደበዘዙን ትርክቶችና አፍራሽ አስተሳሰቦች ሁነኛ መልስ ስንሰጥ ያኔ ነጻ አውጪ ስማችን ይመለሳል፡፡ ጥበብ የትም አለ፤ ሆኖም እንደሚነጋገርና እንደሚወያይ ማኅበረሰብ ግን ጥበብ መልህቁን የጣለበት ስፍራ የለም፡፡ የሀሳብ ልዩነት መቼም ይኖራል፣ በምክክር አቃንቶና አስተካክሎ ለሀገር የሚበጅ ማድረግ ግን የዚህ ዘመን ቀዳማይ የቤት ስራው ሊሆን የሚገባ ነው፡፡

ታላላቅ ማኅበራዊ ተጽዕኖዎች ከመደማመጥ እንደሚመጡ የገባኝን ያክል ምንም ገብቶኝ አያውቅም፡፡ አለመደማመጥ ከፍ ሲልም ተነጋግሮ አለመግባባት ያኛውንም ይሄኛውንም አድዋ የሚሰውር ተግዳሮት ነው፡፡ የአባቶቻችን አድዋ አንድ ሁለተኛው የመደማመጥ ውጤት ነው፡፡ የእኛም አድዋ በመደማመጥ እንደሚጀምር ስናገር ከልቤ ነው፡፡ ያኛው ትውልድ በአንድነትና በወዳጅነት ተሳስሮ ኢትዮጵያዊነትን ሳያስነካ ከትውልድ ትውልድ አሻግሯል፡፡ ይሄኛው ትውልድም በተመሳሳይ አንድነቱን አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ግዴታ አለበት፡፡ አድዋ ትርጉም ያለው የሚሆነው የአባቶቻችንን መንፈስ ተቀብለን በአባቶቻችን መንፈስ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ስንችል ነው፡፡

በተለይ አሁን ላለነው ለእኛ የአድዋ መንፈስ ከምንም በላይ ያስፈልገናል፡፡ በኢትዮጵያዊነት መሀል የተሰገሰጉና ለመከፋፈል እድል እየፈጠሩ ያሉ ወይባ መልኮችን ለማጽዳትና ለማከም አድዋ መነሻችን መሆን ይችላል፡፡ ሕብረታችንን ለማጠንከር፣ አንድነታችንን አስቀጥለን ለመጓዝ አድዋን የፈጠረ የአባቶቻችንን መንፈስ እንደወኔና እንደመንደርደሪያ ልንጠቀመው ይገባል፡፡ ያለፉ የታሪክ ዳናዎቻችን ለሚደነቃቀፍ ማንነታችን ሁነኛ መማሪያ ነው። ካለፈው ተምረን መጪውን የተሻለ ማድረግ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ የጋራ ጉዳያችን ነው፡፡

አድዋ መነሻው ነጻነት፣ መድረሻው ደግሞ ሰብዐዊነት ነው፡፡ እኚህ ጥንድ የማንነት ደማቅ መልኮች ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ካልሆኑ የትም የሉም። ማንም በሌለው ክብር ውስጥ የቆምነው ማንንም በማይመስሉ አባቶቻችን ነው፡፡ በምን ኃይል፣ በምን ጥበብ፣ በምንስ ብቃት ነጭ በጥቁር ተሸነፈ ብለን ብናስብ ማረፊያችን የሚሆነው ኢትዮጵያዊነት የሚለው ሕብረ ውህድ ትልቅ ስም ነው፡፡

የጥቁሮች የአይበገሬነት በትር ያረፈበት የጣሊያን ጦር ተበታትኖና ፈርጥጦ ወደሀገሩ ሲመለስ የወቅቱ የጣሊያን ንጉስ አማኑኤል ኡምቤርቶ የልደት ቀን በመላ ሀገሪቱ የሀዘን ቀን እንዲሆን ያስገደደ የታሪክ ጀብዱ ነበር፡፡ ዋና ከተማዋን ሮምን ጨምሮ የጥቁሮቹን ንጉስ ስም በመጥራት “ምኒሊክ ለዘላለም ይኑር” በሚሉ ቁጣ በወለዳቸው ሕዝባዊ መፈክሮች እንዲጥለቀለቅም ምክንያት ሆኗል፡፡ እኚህ ሁሉ እውነታዎች አፈ ታሪክ ሳይሆኑ ከአድዋ ድል በኋላ የተከሰቱ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬም ይሄን መሰል ገናን ታሪክ ለመከተብ እንድንችል በትናንቱ ማንነትና ስማችን ከፍታ ልክ መገኘትን የግድ የሚለን፡፡

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You