«እድለኞች ወደ ቤታቸው የገቡት ሁሉ ነገር ተሟልቶ እና ምቹ ሆኖ አይደለም» – ኢንጂነር ስጦታው አካለ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች/ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ሲሆኑ፤ ይህም ነዋሪዎች እየቆጠቡ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠባበቁበት ነው፡፡ ሆኖም በተለያዩ ወቅቶች ተገንብተው ለባለዕድለኞች በዕጣ የሚተላለፉ እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደ መብራት፤ መንገድ፤ ውሃ፤ አሳንሰርና መሰል የመሰረተ ልማት አለመሟላት ችግር፤ እንዲሁም የጥራት ጉድለት እንዳለባቸው ቅሬታዎች ሲነሱ ይደመጣል፡፡

ይሁን እንጂ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ከተጠናቀቁ በኋላ ለባለዕድለኞ ከመተላለፋቸው በፊት ከላይ የተጠቀሱት የመሰረተ ልማት አውታሮች ተሟልተው እንደሚተላለፉ መመሪያው ላይ ተቀምቷል። ነገር ግን እንደ ቦሌ በሻሌና መሰል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከአምስት ዓመት በፊት ለነዋሪዎቻቸው በዕጣ የተላለፉ ቤቶች መሰረተ ልማት ያልተሟሉባቸው ናቸው፡፡ ይሄም ለባለእድለኞች የመልካም አስተዳደር ችግር ብቻ ሳይሆን፤ ላልተገባ ወጪ መዳረግ ምክንያት ሆኗል።፡

እኛም ለዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችን በእነዚህና ሌሎችም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ ያዘጋጀን ሲሆን፤ በዚህም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግባታና የመሰረተ ልማት አቀርቦት ችግር ምክንያቶች፣ ችግሮቹን በምን መልኩ እየተፈቱ እንደሆነና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ስጦታው አካለ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ምንባብ፡፡!

አዲስ ዘመን፡- በተለያዩ ችግሮች ከአምስት ዓመታት በላይ ነዋሪዎች ያልገቡባቸው በርካታ ቤቶች አሉ፡፡ በከተማው ክፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ባለበት ሁኔታ ይህ ከአሰራር አንጻር እንዴት ይታያል?

ኢንጂነር ስጦታው፡– ነዋሪዎች እጣ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ በአስተዳደሩ በኩል በርካታ ጥረቶች የተደረጉ ቢሆንም፤ አሁንም ድረስ ያልገቡ የቤት እድለኞች እንዳሉ ይታወቃል። ይህም ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዘ ነው ፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ዋና ዋና የሚባሉ የመሰረተ ልማት አውታሮች የማሟላት ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የመሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በርካታ ችግሮች መኖራቸውን መውሰድ ተገቢ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በርካታ የተባሉት ችግሮች የትኞቹ ናቸው? እንዴትስ ለመፍታት ታስቧል?

ኢንጂነር ስጦታው፡– አንዱና ዋነኛው ችግር የፋይናንስ ዕጥረት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የኅብረተሰቡ ቁጠባ ሙሉ ቤቶችን ይገነባል ማለት አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ የሚቆጥበው 20 ወይም 40 በመቶ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግንባታ በምን ያህል ወጭ እንደሚገነባ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ከመንግስት ወይም ከባንክ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ እዳ ውስጥ ገብተን ነው ቤት እየገነባን ያለነው፡፡

አሁን ካለው የግንባታ ዋጋ አንጻር ኅብረተሰቡ ምንም እንኳን መቆጠብ የሚገባውን መቆጠብ ቢችል እንኳን በቂ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የፋይናንስ እጥረት ገጥሟል፡፡ እጥረቱን ለመሙላት የፋይናንስ ምንጭ እየተፈለገ መሰረተ ልማት እንዲሟላና ቤቶቹ ምቹ እንዲሆኑ የቀሩት ቤቶች እንዲጠናቀቁ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

በዚህ ረገድ አሁን ላይ አጫጭር እቅዶች ታቅደዋል። ችግር ያለባቸው ቤቶችን በየሳይቱ ምን እንደጎደላቸው ተለይተው ችግሩን የመፍታት ስራ 24/7 እየተሰራ ነው። በዚህም ኅብረተሰቡ ወደ ቤቱ መግባት የሚችል ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም ውስን ብሎኮች የሚቀሩ ሲሆን፤ በተያዘው ወር ይጠናቀቃል፡፡

ሌላው ችግር የተቋራጮች አቅም ውስንነት ነው። እንደሚታወቀው በጦርነት ውስጥ የቆየን ስለሆነ ተቋራጮች በቂ ስራ እየሰሩ ስላልሆነ ለሰሩት ስራ ጭምር የፋይናንስ ጥያቄ ሲጠይቁ ምላሽ መስጠት ባለመቻላችን ምክንያት በሙሉ አቅማቸው ስራ እየሰሩ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ክፍያ የሚጠባበቁ አሉ፡፡ አቅም ያለው ተቋራጭ ሲሆን ስራዎቹን በራሱ ገንዘብ አውጥቶ ሰርቶ አጠናቆ ክፍያውን ይጠብቃል፡፡

አቅም የሌላቸው ግን በኮንትራታቸው መሰረት እየሰሩ ክፍያ ይጠብቃሉ፡፡ ስለዚህ ሰርተው ክፍያ ካልተከፈላቸው ወደ ቀጣዩ ስራ መግባት አይችሉም። ከዚህ አኳያ ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ የፋይናንስ እጥረቱ በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን በተቋራጮች አቅም ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡

ሌላኛው፣ በኅበረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ ሁሉም ስራ በመንግስት የሚሰራና የሚጠናቀቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡ ራሱ ቤቱ ከተሰራለት ገብቶ ማልማት በጋራና በትብብር መስራትን ይጠይቃል። በርካታ ስራዎችን ሰርተን አጠናቀን ነዋሪዎች ገብተው የሚያለሟቸው ስራዎች ይጠበቃሉ፡፡ በዚህ ላይም መስራት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ችግሩ ከሚታይባቸው የጋራ መኖሪያ ሳይቶች መካከል የቦሌ በሻሌ ሳይት ነው። በዚህ ሳይት እንደ ውሃ መብራት፤ አሳሰንሰርና መሳሰል መሰረተ ልማቶች አልተሟሉም፡፡ ነገር ግን በ2011 በዕጣ ለነዋሪዎች የተላለፉ ቤቶች ናቸውና መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉ የሚተላለፉበት አሰራር አለ?

ኢንጂነር ስጦታው፡- የቦሌ በሻሌ ሳይት ከሌሎች ሳይቶች የተሻለ ሳይት ነው፡፡ ነገር ግን የጎደሉት ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ ሊፍት ሲሆን፤ ይሄን በቀጣይ የምናስተካክለው ነው። ሆኖም አሁን ካለው የዋጋ ንረት በተያዘ ትልቅ በጀት የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለዚህ ከውጭ የሚገባ በመሆኑ ጊዜ ወስዷል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ አቅራቢዎቹ ውል ገብተው ባስቸኳይ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ስለሆነ በቀጣይ አንድ ወይም ሁለት ወር ውስጥ የሊፍት ወይም አሳንሰር ገጠማ ስራ ይከናወናል፡፡

ሌላው ከውሃ ጋር ተያይዞ ብዙ ወለሎች ያሉት ሕንጻ ስለሆነ ፓምፕ ያስፈልገዋል፡፡ ፓምፕ አሁን ላይ ጨረታ ላይ ስለሆነ ባሉት ቀጣይ ወራት ይገጠማል። በሳይቱ ከሁለት ሺህ በላይ ሕንጻዎች ስላሉ እነዚህን የሊፍት ባለቤትና የፓምፕ ባለቤት ማድረግ ቀላል ነገር ተደርጎ አይወሰድም፡፡

ከዚህ ውጪ ከመንገድ አኳያ ውስጥ ለውስጥ ጭምር አስፓልት ሆኗል፡፡ የእግረኛና የመብራት መስመር አለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሳይት የጎደሉ ነገሮች አይሟሉም ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ባስቸኳይና ባጠረ ቀን ውስጥ የሚሟሉ ናቸው፡፡ ከፍሳሽ ጋር ትናንሽ መስመሮችን የማገናኘት ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከእያንዳንዱ ብሎክ ያለው የፍሳሽ መስመር ካልተገናኘ ፍሳሽ ማስተናገድ አይቻልም፡፡ እነዚህ ፍሳሾች መስተናገድ የሚችሉት የፍሳሽ መስመሮችን ከሰራን በኋላ የሚገናኝ በመሆኑ እየተሰራ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ቀሪ ስራዎችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ብቁ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው፡፡ አመራሩ ችግር የሚስተዋልባቸውን ግንባታዎች የክትትል ስርዓት በመዘርጋት እየሰራ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ነዋሪው እየቆጠበ ያለው ከ15 ዓመት በፊት በነበረው ዋጋ በመሆኑ አሁን ላይ ያለው የግንባታ ወጭ ከሚቆጥበው ዋጋ ጋር የሚመጣጠን አይደለም። ለምሳሌ፣ የሚቆጠበው ከሁለት መቶ ሺ እስከ 400 ሺ ብር ድረስ ነው፡፡ መቶ ሺህ ብር የቆጠበ ሰው ባለ ሶስት መኝታ ቤት እንዲደርሰው ይጠብቃል፡፡ እንደ ደረሰው ቤቱ ጥንቅቅ ብሎ አልቆ ቁልፍ ተረክቦ ወደ ቤቱ መግባት ይፈልጋል፡፡ በመቶ ሺ ብር ግን ቤቱ አይገነባም። ነገርግን እንደ ሀገር የገጠመንን ፋይናንስ ቀውስ በመቆጣጠር መንግስትም በብዙ ጫናዎች ውስጥ ሆኖ ቤቱ የሚያልቅበትን ብድር ጭምር እያመቻቸ ችግሩን የሚመጥን ስራ እየሰራ ነው፡፡

ስለዚህ ጊዜ የወሰደው በምክንያት ነው፡፡ እንዲሁ ቤት ለምን አላገኝም የሚል ቀላል ጥያቄ ይሰማል። ይህ እውነታውን ካለመገንዘብ የመጣ ነው፡፡ ቤቶቹ የሚተላለፉበት ዋጋም ከፍተኛው አምስት መቶ ሺህና ስድስት መቶ ሺህ ብር ነው፡፡ በግል ቤት ልማት ግባታ የተሰማራ ባለሀብት ቤቱን በስንት ሚሊዮን ብር እንደሚሰጥ ማሰብ ነው፡፡ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ስለዚህ ቀሪውን ገንዘብ መንግስት እየደጎመ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ይህም እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ የሚረጭ ሳይሆን ቅድሚያ በመስጠት የሚሰራ ስራ ነው፡፡ ስለሆነም የመንግስትና የግል አጋርነትን የመሳሰሉ በሌሎች አማራጮች ጭምር ቤቶችን ለመገንባት እየተሰራ ነው። የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር ያለባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች በጥቂት ወራት ይጠናቀቃሉ፡፡ የመንገድ ግንባታ ችግር ያለባቸው እንደ ሀያት ሁለት እና መሰል ሳይቶች እስከ ሰኔ ድረስ ተገንብተው ማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለ ዕድለኞች ከመተላለፋቸው በፊት የሚተላለፉበት መመሪያ ምን ይላል፤ በመንግስት በኩል መሟላት ያለባቸው መሰረተ ልማት የትኞቹ ናቸው? ከባለዕድለኞችስ ምን ይጠበቃል?

ኢንጂነር ስጦታው፡- ከተማ አስተዳደሩ የሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለዕለኞች ከመተላለፋቸው በፊት ምን ምን ነገሮች መሟላት እንዳለባው በግልጽ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ሁሉንም መሰረተ ልማቶች ማሟላት ግዴታ አለበት፡፡ ለመኖሪያ ምቹ የማድረግ ጉዳይ የግድ ነው፡፡ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ገብቶ ለመኖር ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን በብዙ ምክምያቶች ሳይሟሉ የሚቀሩ መሰረተ ልማቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሕንጻው አስገዳጅ አዋጅ የሚያመላክት ነው “አራት ወለለል እና ከዛ በላይ የሆኑ ሕንጻዎች ሊፍት የግድ” መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልቻልንም፡፡ ሕንጻዎቻችን ከአራት ወለል በላይ ናቸው። ነገር ግን ጥቂት ጊዚያት ቢዘገይ ማኅበረሰቡ ችግሩን ተቋቁሞ ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ መንግስትም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ተገንዝቦ መሰረተ ልማቱ እስኪገባ ድረስ መጠበቅ ግዴታ ሆኗል ማለት ነው፡፡

ከተማ አስተዳደሩም ከአቅሙ በላይ ባይሆን ኖሮ የሊፍት ጉዳዮችን ችላ እንደማይል መገንዝብ ይኖርብናል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ እጣ ቀድሞ ሊወጣ ይችላል፡፡ ዕጣው በሚወጣበት ወቅት ታሳቢ የሚደረገው ቤቶቹ መጠናቃቸውን ነው። መሰረተ ልማቶቹ ላይሟሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሂደት ዕጣ ከወጣባቸው ጊዜ ጀምሮ ቀሪ ስራዎች በፍጥነትና ባጠረ ጊዜ ውስጥ ኅብረተሰቡ እስኪገባ ድረስ ጎን ለጎን እናለማለን በሚል የተደረገ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በታሰበው ልክ ያልተሰራ ስራ እንዳለ ተገንዘበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የጋራ መኖሪ ቤቶች የግንባታ ጥራት ጉድለት እንዳለበት የአፍሪካ ከተሞች የምርምር ጥምረትና ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ የተሰኙ ተቋማት በጋራ ባደረጉት ጥናት ይፋ አድርገዋል፤ በኅብረተሰቡም ችግሩ እንዳለ ይነሳል፤ በጉዳዩ ላይ ምን ይላሉ?

ኢንጂነር ስጦታው፡– የጥራትን ጉዳይ በምንም ሁኔታ ችላ የሚባል አይደለም፡፡ የጥራት ወይም የደህንነት ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ግንባታዎች እንዲፈርሱ እያደረግን ነው፡፡ ተቋራጮችን ተጠያቂ እያደርግን ነው፡፡ ክፍተትና የጥራት ችግር የፈጠሩትን ተቋራጮችን ተጠያቂ እየተደረጉ ነው፡፡ ወደ ግንባታው የሚገቡ ግብዓቶን እንደ አፈር፤ ብረት፤ ሲሚንቶና ሌሎች ግብዓቶች ጭምር እየተፈተሸን ነው፡፡ አንዳንዶችን ግብዓቶች ደግሞ መንግስት በራሱ ያቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ የጥራት ችግር አይኖርም ማለት አይደለም፤ በሚሰራው የክትትል ስራ ግኝት ግን እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በተጨባጭ የተወሰደ እርምጃ ምንድን ነው?

ኢንጂነር ስጦታው፡- በጣም፡፡ በበርካታ ተቋ ራጮች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ እርምጃቸው ግን በተለያየ ደረጃ የተከናወነ ነው፡፡ የውል ማቋረጥ፤ የገነባው እንዲፈረስ ማድረግ እስከ ማገድ ድረስ የዘለቀ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች የተለያዩ ሳይቶች ከአሳንሰር፤ ውሃ፤ መብራት እና መሰል መሰረተ ልማት ችግሮች አሉ፡፡ ይህም የቅንጅት ክፍተት እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ውሃ፤ መብራትና መንገድ የቅንጅት ስራው መስራት ላይ ምን ይመስላል? ችግሩ መኖሩን ታምናላችሁ?

ኢንጂነር ስጦታው፡– በየሳይቶቹ ያሉ ቀሪ ስራዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከሊፍት ጀምሮ የአሉሚኒየም ስራዎች አሉ፡፡ በተለይ 40/60 ዎቹ ላይ የበር፤ የመብራት፤ የፓምፕ፤ የውሃ የፍሳሻ ማስወገጃ የመስመር ዝርጋታ ስራዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ዘርፉ በሚመለከታቸው ተቋማት የሚሰሩ ናቸው፡፡ መሰረተ ልማቶቹ በእነዚህ መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት የሚገነቡ ናቸው፡፡

ቅንጅትን በተመለከተ አቀናጅ መስሪያ ቤት አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ተቋም ስር ይገመገማል፤ በስሩ እየተመራ በሚመለከታቸው የመሰረተ ልማት አልሚዎች ጋር እየተከናወነ ነው፡፡ አሁን የምታነሳልኝ ጥያቄዎች አብዛኛዎቹ ከመሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ናቸው። ይሁን እንጂ እኛ እንደቤቶች አስተዳደር ቤቱን ገንብተን ጨርሰናል፤ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች እኛን አይመለከተንም ሂዱና የሚመለከታቸውን ተቋማት ጠይቁ አላልንም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የጋራ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እንደ መንግስት በመሰናሰል እና በመቀናጀት መስራት የግድ ነው፡፡ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ተከትለን ቀሪ ነገሮችን ለማሟላት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተናበን እየሰራን ነው፡፡

በውጭ ምንዛሬ፣ በበጀት እና በእቅድ ችግር ተቋማት ባሰቡት ልክ ላይሰሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ሲሆን እንደ መንግስት ተቋም አንዱ ተቋም ሌላኛውን ተቋም ይጠብቃል፡፡ ለምሳሌ፣ መንገድ መብራት እና ውሃን ሊጠብቅ ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁሉም ተቋማት የጋራ ኃላፊነቶች አሉባቸው፡፡ ለመዘግየቱ አንዱ ተቋም በሌላኛው ተቋም ማሳበቡ ለነዋሪው አይጠቅምም።፡ የሁሉም ተቋማት ችግሮች የእኛ ናቸው ብሎ ወስዶ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገዶች መፈለግ ይሻላል፡፡

አሁን ላይ በነባር ሳይቶች የነበሩ የመሰረተ ልማት ትያቄዎች ሁሉንም ብሎ መናገር በሚያስችል ተፈተዋል። በጣም ጥቃቅን የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ አሁን ደግሞ በሚቀጥሉት ወራቶች ሊፍት ከገጠምን ለመጨረስ እየሰራን ነው፡፡ “ፓንፕን” በተመለከተ ጨረታ አልቆ ቀርቧል፡፡ ስለዚህ የሚቀር ነገር የለም ማለት ነው፡፡ መንገድም በተመለከተ እንዲሁ መውጫ መግቢያ መንገድ ብቻ ሳይሆን አስፋልት ጭምር ተሰርቷል፡፡ ስለዚህ ነባር ሳይቶች ጥሩ የመኖሪያ መንደሮች በሚሆኑበት ልክ ዝግጁ እየሆኑ ነው፡፡ ቀሪ ነገሮችን ለማጠናቀቅ ቀንም ምሽትም 7/24 እየሰራን ነው፤ አሁንም እንሰራለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ መብራት የሰራውን መንገድ፣ መንገድ የሰራውን ውሃ፤ ወዘተ ሲያፈርሱ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ተናቦ አለመስራትን ያመለክታል፡፡ እናንተ በቅንጅት መስራታቸውን እንዴት ነው የምታረጋግጡት?

ኢንጅነር ስጦታው፡– አሁን እንደዚያ አይነት አሰራር የለም፡፡ አንዱ የአንዱን የመሰረተ ልማት አፍርሶ የራሱን መሰረተ ልማት መገንባት አይችልም፡፡ አሁን ላይ ያስጠይቃል፡፡ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ስታንዳርድ አለው፡፡ በስታንዳርዱ እንዴት አብረው መስራት እንዳለባቸው፣ መቼ ምን መስራት እንዳለባቸው ተቀምጧል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ወር ላይ የጋራ እቅድ አውጥተን፤ ተፈራርምን፡፡ ለምሳሌ፣ በዚህ ዓመት በአንድ ሳይት ላይ የመብራት፣ ውሃ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ሌሎችም መሰረተ ልማቶች እንሰራለን ብለን ካቀድን ሁሉም ተቋም እቅዱን ወደ ተቋሙ ይወስዳል፡፡ ስለሚሰራው ስራ ዲዛይን ያዘጋጃል፤ በጀት ያዘጋጃል፡ በእቅዱ መሰረት ገብቶ ይሰራል፡፡ ስለዚህ አሁን ምን አልባት አንዱ አንዱን መጠበቅ ካልሆነ በስተቀር እና በተለያዩ ችገሮች በስተቀር አንዱ አንዱ የመሰረተ ልማቶች የሚያፈርስበት መንገድ አስቀርተናል፡፡

አሁን ያለው ችግር መጠባበቅ ብቻ ነው። መጠባበቁ ደግሞ ሆን ተብሎ የመጣ አይደለም። በተለያዩ ከተቋማቱ አቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ምክንያት የሚፈጠር፡፡ አንዱ የተሰጠውን ስራ ካልጨረሰ ሌሎቹ ደግሞ መስራት አይችሉም፤ ቆመው የዘገየውን ይጠብቃሉ፡፡ የግድ ስለሆነ። ነገር ግን በፊት እንደነበረው አንዱ የሰራውን መሰረተ ልማት አንዱ አፍርሶ ሲካሰሱ እና ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት የሚያባክኑትን ሰዓት አስቀርተናል። ስራዎችን የምንገመግምበት የጋራ ፕላት ፎርም አለን። በወር አንድ ጊዜ ስራዎችን እና አፈጻጸማቸውን እንገመግማለን፡፡

ቴክኒካል ኮሚቴው በየሳምንቱ እና በየ15 ቀኑ ሳይት ላይ ወርዶ የሚሰሩ ስራዎችን ያያል፤ ይገመግማል፡፡ ያጋጠሙ ችግሮችን ለሚመለከተው ሪፖርት ያደርጋል። ስለዚህ የተቋም ኃላፊዎቹ ሁኔታውን ወይም ስራዎች እንዴት እየሄዱ ነው? የሚለውን በወር አንድ ጊዜ እንገመግማለን፡፡ ማን ምን ችግር ፈታ? ማን ምን ጨረሰ? ምን ቀረው? የሚለውን በጋራ እናያለን፡፡ በዚህም የተቀናጀ አካሄድ መሰረተ ልማት የማቅረቡን ስራ በተገቢው ሁኔታ እየተመራ ነው፡፡

ነገር ግን አሁንም የተለያዩ ምክንያቶች መሰረተ ልማት ማቅረብ ያልቻሉበት ሁኔታ ስላለ እሱን በቀጣይ እየገመገምን የምናስተካክለው ይሆናል፡፡ ምን አልባትም ካቅማችን ባላይ ከሆነ የበላይ አካላት ጭምር እያማከርን እየፈታን የምንሄድ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን ፡- ነባርም ሆነ አዲስ በተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ የወጣላቸው ዜጎች ምን ያህል ወደቤታቸው ገብተዋል?

ኢንጅነር ስጦታው፡- በመገንባት ላይ ከነበሩ አጠቃላይ 139 ሺህ ቤቶች ውስጥ 130 ሺህ ያህሉ ተጠናቀው እስከ ሰኔ 30 2015 ዓ.ም ድረስ እድለኞች ቤታቸው ገብተዋል፡፡ ባንድም በሌላ፣ ወደ ቤቶቹ ሰው ላይገባ ይችላል፡፡ ነገር ግን ቤቶቹ ለመኖሪያ ምቹ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ወደ 2016 ዓ.ም የተሻገሩት 7 ሺ ገደማ ቤቶች ነበሩ፡፡ ከእነኝህ ውስጥ አሁን ላይ አብዛኛዎቹን ጨርሰናል፡፡ ይህም የዘገየው በበጀት ችግር ነበር፡፡

አሁን ላይ ሰዎች ገብተው ቤታቸውን እያደሱ ነው፡፡ አሁንም አያት ሁለት የቀሩ ቤቶች አሉ፡፡ በሚቀጥሉት ወራት እነሱን ለማስገባት እየሰራን ነው። በጀት ተመድቧል፡፡ ተቋራጮችን፣ ማኅበራቶችን፣ የነዋሪ ማኅበራትን፣ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትን አወያይተናል፡፡ ችግሮቹ እንዴት ይፈቱ? የሚለውን ገምግመናል፡፡ እንዴት ይሰሩ? የሚለው ላይ ተግባብተናል፡፡ በሚቀጥሉት ወራቶች ችግሮች አሉባቸው የምንላቸው ሳይቶች ችግራቸው ተፈቶ የቤት እድለኞች ወደቤታቸው ይገባሉ የሚል ግምገማ ነው ያለን ፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በበርካታ ሳይቶች ሊፍት እና መሰል መሰረተ ልማቶች ባለመኖራቸው ልጆቻቸውን ለሰራተኛ ከፍለው በሽኮኮ የሚያስወጡ አሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ወደቤታቸው የገቡት ሰዎች ለመኖር ተመችቷቸዋል ለማለት ያስደፍራል?

ኢንጅነር ስጦታው፡– ልክ ነህ፤ እድለኞች ወደቤታቸው የገቡት ሁሉ ነገር ተሟልቶ እና ምቹ ሆኖ አይደለም፡፡ ሊፍት በሌለበት ምቹ ነው ልንል አንችልም። ግን ከአዲስ አበባ የነሮ ውድነት፤ በከተማችን ላይ ካለው የቤት እጥረት አንጻር ሰዎች ቤታቸው ገብተው እየኖሩ ነው፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶች አረንጓዴ ስፋራ፣ የልጆች መጫወቻ፣ በቅርብ የሚገኝ የልጆች ትምህርት ቤት እና መሰል ነገሮች ለማሟላት በከተማ አስተዳደሩ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲሟሉ ነው ምቹ ነው ልንል የምንችለው፡፡ እነዚህ ባልተሟሉበት ምቹ ልንል አንችልም፡፡

ነገር ግን በከተማችን ካለው የቤት ችግር አንጻር በእጅጉ የቤትን ችግር የሚያቃልል መሆኑን ታሳቢ ተደርጎ የቀሩ ነገሮችን በፍጥነት እንዲሟሉ ለማድረግ ኅብረተሰቡን እያሳተፍን እየሰራን ነው፡፡ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሲባል ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ በጉልበትም መሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በትብብር መልክ አካባቢውን የማጽዳት፣ ምቹ የማድረግ ጉዳይ በመንግስት ብቻ የሚሸፈን እንዳልሆነ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- መሰረተ ልማቶች ተሟልተው ቤታቸው ያልገቡ ሰዎች የግድግዳ እና የጣሪያ ግብር እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ይህን እንዴት ይገመግሙታል?

ኢንጂነር ስጦታው፡- የግብር ጉዳይ ከአገልግሎት ጋር አይገናኝም፡፡ ባለእድለኛው ሀብቱ የእነሱ ነው፤ ንብረቱ የእነሱ ነው፣ ያ ቤት የተገነባው ለእነሱ ነው፣ በስማቸውም ውል ተዋውለዋል፡፡ በስማቸው ውል ከተዋዋሉባት ጊዜ ጀምሮ ያ ቤት የእነሱ ነው፡፡ ቀሪ እዳ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ለዚያ ሀብት ደግሞ የግድግዳ እና የጣሪያ ግብር መገበር ግዴታ ነው፡፡ ሀገራዊ ኃላፊነትም ነው፡፡ ግብር ካልተሰበሰበ ለሌሎች በምንስ ይሰራል?

አዲስ ዘመን ፡- የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ቤታቸውን እስከምን ድረስ ማልማት ይችላሉ? አፍርሰው እንደገና መስራት ይችላሉ? መመሪያው ምን ይላል?

ኢንጂነር ስጦታው፡– ቤት ተረክበው ከገቡ በኋላ በተወሰነ ደረጃ ውስጥ ላይ “ኢንቴሬር ዲዛይን” ሰርተው ለራሳቸው በሚመቻቸው መልኩ አስተካክለው ሲሰሩ እያየን ነው፡፡ ዋናውን የቤት ስትራክቸር ሳይነኩ የውስጥ ፓርቲሽን የማስተካከል ስራ አይከለከልም። መንግስት በብዙ ሚሊዮኖች ያወጣበትን ግንባታ አፍርሰው መገንባት ግን አይችሉም፡፡ ነገር ግን ሰው በአቅሙ እና በሚመቸው ልክ ሊያድስ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በእድሳት ወቅት የሚያስወግዳቸውን ተረፈ ምርቶች በተገቢው ቦታ ማስወገድ ግዴታው ነው፡፡

ከዚህ ውጭ የጋራ መጠቀሚዎችን (ኮሚናል ቤቶችን) በጋራ ይጠቀማሉ፡፡ የጋራ መጠቀሚ የሌላቸውን ደግሞ በዲዛይኑ የተመላከተ የጋራ መጠቀሚያ ካለ ባለው ቦታ ላይ ኅበረተሰቡም ተሳትፎ ቢሆን ሰርቶ መጠቀም ይችላል፡፡ ካሁን በፊት ያልተሰሩ ካሉ ግን መንግስት የሚሰራ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ጭፈራ ቤቶች አሉ፡፡ ይህም የድምጽ ብክለት ያመጣል፡፡ ይህን እንዴት ይመለከቱታል? በጋራ መኖሪያ ቤቶች ያሉ የንግድ ቤቶች ለምን ለምን ንግድ ስራ እንዲውሉ መመሪያችሁ ይፈቅዳል?

ኢንጂነር ስጦታው፡- ኮንዶሚኒየም በተለይ 40/60ዎቹ እስከ ጂ+2 ያሉ ቤቶች የንግድ ቤቶች ናቸው። እነዚህ ቤቶች ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚሰሩት ለንግድ ተብሎ ነው፡፡ ቤቶቹ የሚተላለፉት በጨረታ ነው። ጨረታውን የሚያወጣው የቤቶች አስተዳደር ነው። ማንኛውም ሰው የንግድ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት መነገድ ይችላል፡፡ ነገር ግን የንግድ ስራዎች ሲሰሩ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማይረብሽ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ነዋሪውን የሚረብሹ ነገሮች ካሉ የነዋሪዎች ኮሚቴ አለ እሱ እርምጃ ይወስዳል፡፡

ከዚህ ባለፈ ሳይቱ የሚገኝበት ክፍለ ከተማ ወይም ወረዳም ተቆጣጥሮ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ነጋዴዎች ይህን ነገድ ይህን አትነግድ ማለት አይቻልም፡፡ የንግድ ሕጉን ተከትሎ ሰው የፈለገውን መነገድ ይችላል፡፡ የተጫረቱት ቤት ስታንዳርዱን ካላሟላ የንግድ ፈቃድም አያገኝም። ለምሳሌ አንድ ሰው ክሊኒክ ልክፈት ቢል ፈቃዱን የሚሰጡት የጤና ተቋማት ናቸው፡፡ ስለዚህ ብቁ ካልሆነ እዚህ ተቋማት ፈቃዱን አይሰጡትም፡፡ በአጠቃላይ ንግድ ማካሄድ የሚፈቀደው የነዋሪውን ደህንነት እና ጤና ባገናዘበ መልኩ ብቻ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለልማት ተነሺዎች ኮንዶሚ ኒየም ቤቶች ይሰጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ ቤት ለማግኘት የሚቆጥቡ ሰዎች ላይ ቅሬታ ይፈጥራል። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

ኢንጂነር ስጦታው፡-፡- በልማት የሚነሱ ሰዎች ለከተማው ልማት ቤት እና ንብረታቸውን ይለቃሉ። እነዚህ ሰዎች ከቤታቸው ሲነሱ የግድ ማረፊያ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሚሰጡት ቤቶች ነዋሪው ከቆጠበው ቁጠባ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም ለልማት ተነሺዎች ነገም ዛሬም ቤቶችን እንሰጣለን፡፡

አዲስ ዘመን ፡- በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ እድለኛ ያልሆኑ ሰዎች ቁልፍ ሰብረው እየኖሩ እንደሚገኙ ሰዎች ቅሬታ ያነሳሉ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነታ ነው? እናንተስ ጉዳዩን ታውቁታላችሁ?

ኢንጅነር ስጦታው ፡– በሕገ ወጥ ተያዙ የተባሉ ቤቶችን ትክክል ነው አግኝተናል፡፡ በየክፍለ ከተማው ካሉ የጸጥታ መዋቅሮች ጋር በመሆን ሕገ ወጦችን ከቤቶች እያስወጣ ነው፡፡ የተዘጋ ወይም ያልተላለፈ ቤት ሲያገኝ ሰብሮ ገብቶ የመቀመጥ ዝንባሌዎች አይተናል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕገወጦችን አስወጥተናል፡፡ አሁንም ክትትል እያደረግን ነው፡፡

አዲስ ዘመን ፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።

ኢንጂነር ስጦታው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ሞገስ ተስፋ እና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You