መዳብ የሆኑብን፤ በእጃችን የያዝናቸው “ወርቆቻችን”

ከወራት በፊት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዘጋጅቶት የነበረን አንድ መድረክ ለመዘገብ ወደ ጅማ ከተማ አቅንቼ ነበር። በወቅቱ የመድረኩ አጋፋሪ በከተማው ነዋሪ ዘንድ ‹‹ፔሌ›› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቁት አብዱልከሪም አባገሮ በእንኳን ደህና መጣችሁ!ንግግራቸው ስለ ጅማ ብዙ ቁምነገሮች እንዳነሱልንም አታውሳለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ጅማዎች ለእንግዳ ያላቸውን ክብር እና ትሕትና ስለ “ana cabsuu” ያነሱት ሃሳብ እጅጉን አስገርሞኝ ነበር፡፡

በአፋን ኦሮሞ “ana cabsuu ” ትርጓሜው ስበረኝ እንደማለት ነው። የቤቱ ባለቤት “አናጨብሱ” ብሎ ወደ ቤቱ በአክብሮት የመጣው እንግዳ ከእሱ የሚበልጥ መሆኑንና በትሑት መንፈስ ፍቅሩን አክብሮቱን የሚያሳይበት የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት ነው። የአብዱልከሪም አባገሮ ንግግር ስሰማ ከመገረም ባለፈ ለካስ ኢትዮጵያውያን በአብሮነት፣ በአንድነት፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀር…. ዘመናትን አብረው መኖር እንዲችሉ ያደረጓቸው፤ እንደ “አናጨብሱ” አይነት ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው” የሚለውን እንዳሰላስል አድርጎኛል፡፡

ኢትዮጵያውያን እንደ “አናጨብሱ” አይነት ለእንግዳ ያላቸውን ክብር፣ ፍቅርንና ትሕትናን የሚያሳይበትና የሚያስመሰክሩበት በርካታ እሴቶች አሏቸው፡፡ በየዘመናት ሂደት በባሕል ውርርስና ልውውጥ ምክንያት ሕዝቦቿ የበርካታ ሀገር በቀል ዕውቀቶችና ጥበቦች ባለቤቶች ሆነዋል፡፡

ታሪክ ስንመረምርም ኢትዮጵያ ከዚህ የደረሰችው በረጅም የውስጥና የውጭ ፈተና አልፋ እንደሆነ እንረዳለን። ይሁንና ሁሉም በሚባል መልኩ አንገዳግደዋት ይሆናል እንጂ አልጣሏትም፡፡ ለዚህ ጥንካሬዋ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችና ምርኩዞችን መዘርዘር ይቻላል።፡ እንደ “አናጨብሱ” አይነት ድንቅ ባሕላዊ እሴቶችም በተለይ በአንድነት ለመቀጠል ትልቅ አቅም እንደነበሩ መካድ የሚቻል አይደለም፡፡

በእኔ እምነት፤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል የዚህ ድምር ውጤት ነው ። ለዚህ እንደ ማስረጃም፤ መስከረም 17 ቀን 1888 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጣሊያን ለወረራ መሰማራቱን ተከትሎ ያስተላለፉት የክተት አዋጅን እናንሳ፡-

‹‹ …ሀገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ….ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።›› ሲሉ አዋጅ አስነገሩ ።

በወቅቱ አኩርፈው የነበሩ ንጉሦች አሻፈረኝ ብለው አኩርፈው አልቀሩም። ለሀገር ፍቅርና ክብር፣ ለእምነት፣ ለመሬት፤ ለንጉሥ ከፍ ያለ ክብር ይሰጣል። በሀገራችን በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ መሪ ይደመጣል፤ ይከበራል፣ ይፈራልም። የሀገር ክብር ከቁርሾም በላይ ነበርና፤ የንጉሡን ጥሪ አሻፈረኝ ብሎ የቀረ አልነበረም። በጊዜው በንጉሡ ላይ ጥያቄ የነበራቸው ጥያቄያቸውን በይደር አስቀምጠው ለሀገር ሉዓላዊነት በአንድነት ቆመዋል።

ታላቅን ማክበር፣ መደማመጥ፣ ለአባቶች ቦታ መስጠት፣ እርቅ መፈጸም፣ መታዘዝ፣ መረዳዳትና መሰል የሥነ ምግባር መርሆዎች የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች ናቸው። አባቶቻችን ይህን በመሰለ በጎ እሴት እጅ ለእጅ ተያይዘው ችግሮችን አልፈው ኢትዮጵያን ማጽናት ችለዋል።

አባቶቻችን እነዚህን የወል እሴቶች በመጠቀም ችግሮችን ፈትቶና አስታርቆ፤ የተበላሸን አቅንቶ፤ የነገውን መልካም ተስፋ አሳይቶ በይቅርታና በፍቅር መኖር እንደሚቻል አሳይተውናል። አሁንም በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ለሠላም፣ ለአብሮነት ፋይዳ ያላቸው አንድነትን የሚያጠናክሩ የመከባበር፤ አብሮ የመብላትና የመሥራት ዕሴቶች ግጭቶች እንዳይከሰቱ ወይም እንዳይባባሱ የማድረግ አቅም ያላቸው ባሕላዊ እሴቶች አሉ።

ምናልባትም ቢደበዝዙ እንጂ ጨርሶ አልጠፋም ማለት ይቻላል፡፡ “የጋሞዎች እርጥብ ሣር ” ገድልም ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን የሚችል ነው፡፡ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ለበቀል ተነስቶ የነበረውን የአርባ ምንጭና የአካባቢውን ወጣት ለምለም ሣር ይዘው ተንበርክከው በመለመን ቁጣውን አብርደው መልሰውታል። ይህን የሀገር ሽማግሌዎች ገድል በጥሞና ለተረዳው የአርባ ምንጩን እሳት ብቻ አይደለም ያጠፉት፤ ጥፋቱን ተከትሎ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሊዛመት የነበረውን የበቀል ሰደድ እሳት ጭምር እንጂ ።

ክስተቱና ቁጣ አብራጁ የጋሞ አባቶች ልመናም ከፍ ብሎ ሊገለጥ የሚገባው የትላንት ባሕላዊ የግጭት አፈታት፣ የእርቅ አውርድ እና የፍቅር ማስፈኛ አቅማችን ብሎም ጥበባችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ከምንም በላይ ጥሩ ማሳያ መሆን የሚችል ነው፡፡

ባሕላዊ ወረታችን ለበጎ ዓላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት፣ የሰው ልጆችንም ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል። እነዚህ የባሕል እሴቶች ትኩረት ቢያገኙ እንደ ሀገር ያሉብንን አለመግባባቶች፣ ያሉብንን ስብራቶች “የሀገሩን በሬ በሀገሩ ሰርዶ እንደሚባለው” መጠገን ይችላሉ የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እየፈተኗት የሚገኙ አስቸጋሪና እጅግ አሳሳቢ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል። ከሚበቃት በላይም ጦርነቶች የተካሄዱባት ሀገር መሆኗን፣ የታሪክ ድርሳናትን በማገላበጥ መረዳት ይቻላል፡፡ የድህነትና የኋላቀርነት መፈንጫ የሆነችውም ሠላሟ እየተናጋ መረጋጋት በመጥፋቱ ነበር፡፡ ዛሬም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ። የፖለቲካ ዝለት ብቻም ሳይሆን፣ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሚደረግ ጥረት ይልቅ ጠመንጃን ዋነኛ አማራጭ አድርጎ የመቁጠር አስተሳሰብ ጎልብቷል።

ይሑንና በመሰል አካሄድ አባቶቻችን በጥበብ ያቆዩልንን ሀገር እኛ በስሜት ለማፍረስ መሽቀዳደም የለብንም። ለመነጋገርና ለመደማመጥ ቦታ አለመስጠት መዘዙ የከፋ በመሆኑ፤ ከዚያ ዓይነቱ አስከፊ አዙሪት ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በ”አናጨብሱ” ባሕልና ትውፊት በተቃኘ መልኩ በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በመነጋገር የሠላምንና የዕርቅን ባንዲራ ከፍ ማድረግ ይኖርብናል። በትሕትና ዝቅ ማለትና በፍቅር የመሸነፍ የ‘አናጨብሱ’ ባሕል በፖለቲካችን መድረክም ሥፍራ ቢያገኝ አትራፊ እንሆናለን ።

በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉ ችግሮችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድም፤ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ አብሮነት በጉልህ የሚንጸባረቅባቸው የጋራ እሴቶቻችንን እንደ ዋነኛ አማራጭ መጠቀም ተገቢ ይሆናል። በዚህም ኅብረተሰቡን በማሳተፍ የቆዩ ሀገራዊ የጋራ እሴቶችና ልምዶች ቀምሮ ወደ ተግባር መግባት አስፈላጊ ነው። ሀገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ በየአካባቢው ያሉ ባሕላዊ እሴቶቻችንን መጠቀም ይኖርብናል። ስለሆነም በእጃችን ያሉት ወርቅ የሆኑት የወል እሴቶቻችን መዳብ እንዳይሆኑብን በልካቸው ተገንዝበንና ተጠቅመን ሀገርን ማጽኛ ልናደርጋቸው ይገባል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You