በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ችግሮችን የሚፈቱ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ያበረከቱ ሴቶችን በተለያየ ጊዜ ተመልክተናል። በሀገራችንም በተለያዩ ጊዜያት የፈጠራ ስራ የሰሩ በርካታ ሴቶች አሉ። በዛሬው ጽሁፋችን በ2015 ዓ.ም የብሩህ ኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ ውድድር የተለየ የፈጠራ ስራ በማቅረብ ተሸላሚ የነበረችውና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማቴሪያል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ክፍል መምህርት ከሆነችው ወይዘሮ ፋይዛ ሸምሱ ጋር ያደረግነውን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።
የተወለደችው በጉራጌ ዞን ቢሆንም ቤተሰቦቿ የመኖሪያ ቦታቸውን ቀይረው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመምጣታቸው ከሁለት ዓመቷ ጀምሮ እድገቷ በአዲስ አበባ ከተማ ሆነ። ትምህርቷንም የተከታተለችው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አንደኛ እና ሁለተኛ ክፍል በኮከብ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከሶስተኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ባሸዋም በመባል በሚጠራ ትምህርት ቤት፣ ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛ ደግሞ ክፍል ፒያሳ በሚገኘው አፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት ተከታትላለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በራዲካል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ባሽዋም ትምህርት ቤት በማጠናቀቅ የመሰናዶ ትምህርቷን በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ተከታተለች። ፋይዛ በነበራት የትምህርት ቤት ቆይታ የደረጃ ተማሪ የነበረች ሲሆን ለኬሚስትሪ ትምህርት የተለየ ፍቅር ነበራት። ለኬሚስትሪ ትምህርት የነበራት ፍቅር አሁን ላለችበት ሙያም ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ትናገራለች። የመሰናዶ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ወደ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገባች። እዛም ከኬሚስትሪ ትምህርት ጋር የሚገናኝ የትምህርት ክፍል ስትፈልግ የማቴሪያል ኢንጂነሪንግ ቀልቧን ስለሳበው ምርጫዋ አደረገችው።
በወቅቱ የትምህርት ክፍሉ ገና አዲስ የተቋቋመ በመሆኑ ብዙ ተማሪ ለመምረጥ ይፈራ ነበር። ፋይዛ ግን ይህ የትምህርት ክፍል በውስጧ ከነበረው ፍላጎት ጋር ይቀራረብ ስለነበር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምርጫዋ አደረገችው። በ2008 ዓ.ም በማቴሪያል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያዘች።
ፋይዛ ከምርቃት በኋላ ተከትሎ የሚመጣው የስራ ፍለጋ ውጣውረድ አላጋጠማትም 2008 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዋን እንደተመረቀች በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ሆና ተቀጠረች። በ2009 ዓ.ም እዚያው ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን የመከታተል እድል ስላገኘች ስራ ሳትጀምር በቀጥታ ወደ ትምህርት ገባች። ሁለተኛ ዲግሪዋንም የተከታተለችው ማቴሪያል ኢንጂነሪንግ ነበር። ሁለተኛ ዲግሪዋንም እንደጨረሰች እዚያው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስራዋን ቀጥላ በመምህርነት ሙያ ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።
ፋይዛ ከፍተኛ የምርምር ፍላጎት በውስጧ ስላለ በመምህርነት ሙያዋ እየሰራች የምርምር ስራዎችንም ታከናውናለች። የምርምር ውጤቶች መደርደሪያ ላይ ብቻ የሚቀሩ መሆን የለባቸውም የሚል አቋምም አላት። በወረቀት ላይ ተፅፈው ብቻ ከመቀመጥ አልፈው መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ የሚደረጉ ምርምሮችን የመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፏን ጨምሮ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ምርምሮችን ሰርታለች።
የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፏ ለግንባታ ስራ የሚያገለግል ጡብ (brick) ማምረት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። የድንጋይ ከሰል ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ የሚወጣው አመድ ከሲሚንቶ ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ያለው ነው የምትለው ፋይዛ፤ ይህ የድንጋይ ከሰል አመድ ያለ ጥቅም ተወግዶ አካባቢ ላይ ጉዳት ከሚያደርስ በድጋሚ ጥቅም ላይ ውሎ የሸክላ ጡብ ሊሰራበት ይችላል። ይህ ከድንጋይ ከሰል አመድ የሚሰራው የሸክላ ጡብ የመሰንጠቅ ሁኔታ ቢያጋጥመው እርጥበት በሚያገኝበት ወቅት ያለምንም ጥገና እርጥበቱን ብቻ በመጠቀም በራሱ ተመልሶ የመጠገን ባህሪ ያለው ነው ትላለች።
ጠንካራዋና አዳዲስ የምርምር ግኝቶችን ለመፍጠር ተኝታ የማታድረው ፋይዛ ታዲያ በተለያዩ የፈጠራ ስራ ውድድሮች ላይም ትሳተፋለች። በኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ዘርፍና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ቁልፍ ተግዳሮችን ለመፍታት እና በአካባቢያቸው ያለውን ሃብት በመለየት አዳዲስ ሃሳቦችን ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን ማበረታታትን ዓላማው አድርጎ ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የብሩህ ኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ ውድድርም ፋይዛ በ2015 ዓ.ም ተወዳድራ ሽልማት ያገኘችበት አንዱ ውድድር ነው።
በዚህ ውድድር ፋይዛ የምስክር ወረቀትን ጨምሮ 260 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ለማግኘት ችላለች። በውድድሩ ማሸነፏ እና የገንዘብ ሽልማት ማግኘቷ የሞራል መነሳሳት እንደፈጠረላት እና ወደፊትም በሌሎች የፈጠራ ስራዎች ላይም ጠንክራ መስራት እንዳለባት እንድታስብ ያደረጋት መሆኑን ትናገራለች። ከውድድሩ ባገኘችው የገንዘብ ሽልማትም የፈጠራ ስራዋን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚረዷትን ስራዎች ለመስራት እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ትናገራለች።
ይህንን ውድድር ለማሸነፍ ያበቃት፤ በፈረንጆቹ 2019 ኡጋንዳ ላይ በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ከአሜሪካ እንዲሁም ከኡጋንዳ ሴት ተማሪዎች ጋር በመሆን አፍሪካ ውስጥ ሴቶች በቀላሉ ሊሰሩት የሚችሉት የንፅህና መጠበቅያ እንዴት ማዘጋጀት እንችላለን የሚል ሃሳብ በማመንጨት ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የቪዲዮ ምስሎች በስፋት ይወጡ ነበር።
በኋላ ግን ይህ በጋራ የተጀመረ ሃሳብ ፋይዛ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሷ በጋራ የሚሰራ ሊሆን አልቻለም። ፋይዛ ታዲያ ወደ ሀገሯ ተመልሳም ሃሳቡን ከጭንቅላቷ አላወጣችውም ነበርና ከሃሳቡ ጋር የሚገናኙ የተለያዩ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን መመልከት ጀመረች።
የፋይዛ ወላጅ እናት ተወልደው ያደጉት በጉራጌ ዞን የገጠር አካባቢ ነው። የጉራጌ ዞን የምትታወቅበት የእንሰት ተክል ከምግብነቱ ባሻገር የጉራጌ ሴቶች ሲወልዱ ወይም የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት የእንሰት ቅርንጫፍ አድርቀው በማንጠፍ የሚተኙበት የንፅህና መጠበቂያ መሳሪያቸውም ጭምር ነው። የእንሰት ተክል ግንዱ ውሃ አያሳልፍም፤ የቅርንጫፉ ለስላሳ ክፍል ደግሞ ፈሳሽን አምቆ የመያዝ አቅም አለው።
ፋይዛ ይህንን የጉራጌ ሴቶች የእንሰት አጠቃቀም ከእናቷ በሰማች ጊዜ እጅጉን ተደነቀች፤ ነገሩ ቀልቧን ሳበው። የእንሰት ተክሉን እንድታመጣላት እናቷን ጠይቃ የተነገራትን መሞከር ፈለገች። በሙከራዋም ተክሉ ውሃ እንደማያሳልፍ ለማረጋገጥ ቻለች። ወዲያው ይህንን ነገር ወደ ምርምር መቀየር እንዳለባትና የእንሰት ተክልን በመጠቀም የንፅህና መጠበቂያ መስራት እንዳለባት አሰበች። በሃሳብ ብቻም አልቀረችም ባደረገችው ምርምር ከእንሰት ተክል የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ መስራት ቻለች። ለውድድሩ አሸናፊነትም ያበቃት ይሄው የምርምር ስራ ነው።
ይህንን የምርምር ውጤት በምትሰራበት ወቅት የተለያዩ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ለማየት ሞክራ እንደነበር የምትናገረው ፋይዛ፤ አብዛኞቹ ምርቶች ሙሉ ለሙሉ የተሰሩት ከፕላስቲክ እንደሆና እነዚህ ፕላስቲኮች የሚሰሩት ከነዳጅ በመሆኑ በጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው ትገልፃለች። ከዚህ ባሻገር እነዚህ ከፕላስቲክ የሚሰሩ የንፅህና መጠበቂያዎች በሙቀት ወቅት የማቃጠልና የማሳከክ ባህሪ እንዳላቸውም ታስረዳለች።
እነዚህ የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች የሚመረቱበት ጥሬ እቃ ከውጪ የሚገባ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እጅግ እየጨመረ ሄዷል። አገልግሎት ላይ ከዋሉ በኋላም ቶሎ የመበስበስ ባህሪ ስለሌላቸው አካባቢን የመበከል አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ከእንሰት የሚሰሩት የንፅህና መጠበቂያዎች እንደሀገር ገበያ ላይ ቢውል የሚሰራው ከባዮማስ(biomass) እንደመሆኑ ለጤና ተስማሚ ከመሆኑ ባሻገር ዋጋውም እንደሌሎች የፅህና መጠበቂዎች ውድ አይሆንም፤ አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላም ቶሎ የመበስበስ ባህሪ ስላለው የአካባቢ ብክለትን ይቀንሳል ትላለች።
አዕምሮዋ ሁሌም ለአዲስ ነገር ዝግጁ የሆነው ፋይዛ ምርምሯን በእንሰት ተክል ብቻ አላበቃችም። አንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ ውሎ ከሚጣለው የንፅህና መጠበቂያ ባሻገር ለረጅም ጊዜ እየታጠበ አገልግሎት መስጠት የሚችል የሴቶች ንፅህና መጠበቂያም ለመስራት ችላለች። ይህንን ስራዋን የስፌት ማሽን በመግዛት ቤት ውስጥ በማምረት የጀመረች ሲሆን ምርቱን ያስተዋወቀችው በአዲስ አበባ ብቻ ነበር። ነገር ግን አዲስ አበባ ውስጥ የንፅህና መጠበቂያን አጥቦ የመጠቀም ልምድ እስከዚም በመሆኑ ተቀባይነት ማግኘት አልቻለችም። ክልሎች እና በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ለማሰራጨት ብታስብም አብሯት የሚሰራ ተቋምም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ተቋማት ባለማግኘቷ ምርቱን ለተጠቃሚ ማድረስ አልቻለችምና ለጊዜው ማምረቷን እንዳቆመች ትናገራለች።
‹‹ትልቁ ሃሳቤ ምርቴ ሰው ጋር ደርሶ ተጠቃሚ እንዲያገኝ ማድረግ ነው››‹ የምትለው ፋይዛ ምርቶቹን ለማምረት የሚረዱ የተለያዩ ማሽኖችን ማቅረብ የሚችል አካል ካለ አብራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ትገልፃለች። በተጨማሪም ስራው ምርት የሚመረትበት ሰፊ ቦታ የሚያስፈልገው በመሆኑ ይህንን የሚያሟላልኝ አካል ቢኖር የፈጠራ ስራዬ በተግባር ተተርጉሞ ሰዎች ዘንድ መድረስ ይችላል ትላለች። ታጥበው በድጋሚ አገልግሎት ላይ መዋል የሚችሉ የንፅህና መጠበቂያዎች ተመርተው በእጇ ላይ የሚገኙ በመሆኑ እነዚህን ምርቶች ከበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በመሆን በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ለሚገኙ ሴቶች ማሰራጨት እንደምትፈልግ ጨምራ ትናገራለች።
ፋይዛ የዩኒቨርሲቲ መምህርት እንደመሆኗ በርካታ ተማሪዎችን የእውቀት እናት በመሆን ታሳድጋለች። እሷ ካላት የፈጠራ ችሎታ በመነሳት ተማሪዎቿ የሚሰሯቸው የመመረቂያ የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር የሚለወጡና በርካቶችን የሚጠቅሙ ሃሳቦች ላይ እንዲያተኩሩ ዘወትር ትመክራለች። በክፍል ውስጥ በምታስተምርበት ወቅትም ተማሪዎቿ በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን በተግባር ምን እንደሚመስል እንዲረዱ የተለያዩ ቪዲዮዎችን ይዛ በመግባት እንዲመለከቱ ታደርጋለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አዳዲስ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ሴቶች ይበረታታሉ የምትለው ፋይዛ፤ እንዳጠቃላይ ግን ሴት ልጅ በተለይም ልጅ ካላት ደካማ ተደርጋ የመቆጠሩ ነገር አሁንም አለ። ነገር ግን ይህንን ጫና ተቋቁማ ነጥራ ከወጣች በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት እድል አላት ትላለች።
በመንግስት በኩል ሴቶችን እናበረታታለን የሚሉ ነገሮችን በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነገር እንሰማለን፤ አሁንም ግን በፈጠራው ዘርፍ ሴቶችን በግንባር ቀደምትነት በመደገፍና በማበረታታት በኩል መንግስት ብዙ ሊሰራው የሚገባ ነገር እንዳለ ትናገራለች። በርካታ እድሉን ያላገኙ ነገር ግን እድሉን ቢያገኙ ሀገር መለወጥ የሚችል የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ሴቶች በየቤታቸው ተቀምጠዋል፤ ይህንን የሚለውጥ እድል ሊፈጠርላቸው ይገባል ትችላለች ፋይዛ።
ወደ መሬት ወርደው ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ ሃሳቦችን በማመንጨት በኩል ሴቶች የተሻለ ሀሳብ የማመንጨት ብቃት በተፈጥሮ ተሠጥቷቸዋል። ያሉባቸውን የተለያዩ ጫናዎች አሸንፈው ወደፊት መውጣትና ችሎታቸውን ማሳየት አለባቸው። እንደሀገር ያለንበት የኢኮኖሚም ሆነ የቴክኖሎጂ እድገት በብዙዎች ላይ የፈጠራ ስራቸውን ለማውጣትና ተግባራዊ አድርጎ ለማሳየት የሚያዳግት ቢሆንም ሴቶች በተቻላቸው አቅም ሁሉ በውስጣቸው የያዙትን እምቅ አቅም አውጥተው ማሳየትና ተግባር ላይ ማዋል አለባቸው ባይ ናት።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም