ዜጎች ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆም አለባቸው

የአንድ ሀገር ብሄራዊ ጥቅም በዋናነት በራሱ ሀብትና አቅም ላይ የተመሰረተ፤ በራሱ ይሁንታና ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ነው። ሀገር የተፈጥሮም ይሁን የሰው ሀብቷን ተጠቅማ የማደግ መብቷ የማይሸራረፍ የሉዐላዊነት መገለጫም ነው። ከሀገር ሲያልፍ ከውጭ ሀገራት ጋር በሚኖር ግንኙነትም ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የተለመደ ነው።

ሁሉም ሀገራት ‹‹ብሔራዊ ጥቅሜ›› በሚል የሚይዙትና የሚታገሉለት አጀንዳ አላቸው። ሀያላን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሜ የሚሉት እና ይሄንኑ ማዕከል አድርገው ከሌላው ዓለም ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት አላቸው። በተለይ የአደጉ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሜን አስከብራለሁ ብለው ከተሳካ በዲፕሎማሲ መንገድ፤ አለፍ ካለም በኃይል ጫና ተጠቅመው በበርካታ ሀገራት የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲተጉ መመልከት የተለመደ ሆኗል። ዜጎቻቸውም የየሀገሮቻቸውን አጀንዳ በመደገፍ በጋራ ሲቆሙ ተመልክተናል።

ኢትዮጵያውያንም የሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉ በጋራ ተዋድቀው በጋራ ሞተዋል። ኢትዮጵያ ለሉዐላዊነቷ እና ለብሔራዊ ጥቅሞቿ ያደረገቻቸው ጥሪዎች ሁሉ በመልካም ምላሽ የተቃኙ ናቸው። ለዚህ ከታላቁ የአድዋ ድል እስከ ሕዳሴው ግድቡ የተመዘገቡትን ሁነቶች መጥቀስ ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት በተሻገሩ አጀንዳዎች ብዙ የልዩነት ሀሳቦች ቢኖሩንም፤ ሀገርን ስለሚያፀኑ ጉዳዮች በትብብር መቆም ግን ዛሬም የትውልዱ የቤት ስራ ነው።

ሁሉም እቅዶች የሚሳኩት፣ ሁሉም ሀሳቦች የሚሟሉት፣ ሁሉም ተስፋዎች የሚኖሩት ሀገር ሲኖር ነው። ለዚህም ነው ዜጎች የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ግድ ይላቸዋል የሚባለው። በእርግጥ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ጥቅም በአንድነት እና በፅናት መጠበቅ የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን የትናንት ታሪክና የቅርብ ጊዜ ሁኔታ ሁነኛ ማሳያም ናቸው። የሀገርን ልዕልና ማስጠበቅ ከትውልድ ትውልድ ከመንግስት መንግስት ሲሸጋገር የመጣ የኢትዮጵያ መለያ ባህሪ ነው።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በጥቂቶች ሀገር እና የአስተዳደር ሥርዓትን (ቢሮክራሲን) ያለመለየት ችግር፣ እንዲሁም ለግል ጥቅማቸው ባደሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሲንፀባረቅ ይታያል። ይህ የጥቂቶች የተዛባ እይታ ደግሞ እያደገ ሲሄድ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ነው። ሊታወቅ የሚገባው ሥርዓትና መንግስታት በአንድ ሀገር ውስጥ ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። ሀገር ግን ሕያው ሆና ትቀጥላለች። በመሆኑም ለማትለወጠው ሀገር ለጉዳዮቿ ዜጎች በአንድነት መቆም ካልቻሉ ደግሞ የሀገር ብሔራዊ ጥቅም ይጎዳል።

ከዚህ አኳያ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር ባለማቅረብ የሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታን ማጠናከር የኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ፤ ለዚህም አወንታዊ ድርሻን ማበርከት ደግሞ ከልሂቃንና ከፖለቲከኞች የሚጠበቅ፤ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር መሆን አለበት። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቆ ለማስቀጠል ሀገር እያጋጠማት ያለውን ፈተና በጋራ ለማለፍ ከመስራት ጎንለጎን፤ ሲቃወሙም ሀገርንና መንግስትን መለየት አስፈላጊ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በምታደርገው ጥረት ግለሰቦችና ቡድኖች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በአንድነት ከመቆም ይልቅ በተቃራኒ ጎን መታየታቸው ሀገሪቱ ወደ ግጭትና ጦርነት እንድትገባ አድርጓታል”፤ ብለው ነበር።

ይሄም ንግግር የሚያሳየው ደግሞ ግለሰቦች አልጣም ጥቂቶች በቡድን ተሰባስበውም ያሉ ከመንግስት ጋር ቅራኔ አለን ብለው ካሰቡ ተቃውሟቸውን በሁሉም መንገድ የማድረግ አካሄድ አሁን አሁን ላይ እየተለመደ መምጣቱን ነው። ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከተ መለያየት፣ ጫፍና ጫፍ መሳሳብ ኢትዮጵያ ላይ ያልተለመደ ነው። ምክንያቱም ቀደም ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ከሌላ ሀገር ጋር በምታደርገው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ራሳቸው የጀመሩትን የውስጥ ግጭት እንኳን ቢኖር ለጊዜው ቅራኔውን ትተው የውጭውን ጠላት እስኪያወድሙ ድረስ አንድ ይሆኑ ነበር። ይህ በአድዋ የታየ ነው።

የአድዋ ጦርነት ሊጀመር ትንሽ ቀን ሲቀረው ጭምር ከጣሊያን ጎን የነበሩ ኢትዮጵያውያን፣ በኋላ ላይ የሀገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ የተመለሱና የሰሩ ነበሩ። እንዲህ ማድረጋቸው ጦርነቱን ለማሸነፍ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ይህ ደግሞ የሁል ጊዜ ኢትዮጵያውያን የሀገር ወዳድነት የውስጥ ስሜት ነው። በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተቃዋሚ ሳይኖር ሁሉም በጋራ ተስማምቶ የመደገፉም ምስጢር ይሄው ከውስጥ የሚመነጨው የሀገር ወዳድነት መንፈስ ነው።

አሁን ግን አዲስ ልምምድ እየታየ ነው። በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ እዛና እዚህ የሚቆሙ ግለሰቦችን ማየት ተለምዷል። እንዲህ ማድረግም እንግዳ ያልሆነ ነገር እየሆነ ነው። ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለውንና ብሔራዊ ጥቅሟን ሊያስከብር የሚችለውን የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን እንቅስቃሴ የራሷ ዜጎች ሆነው የሚቃወሙ ቡድኖችንና ግለሰቦችን እየተመለከትን መሆናችንም የዚህ አብነት ነው።

ይህ አካሄድ ተገቢ ያልሆነና ተቀባይነት የሌለው ነው። ምክንያቱም፣ የሀገራችንን የወደብ ጥያቄ እንዳይሳካ አሸባሪው አልሸባብ እንኳ ከሱማሊያ መንግስት ጋር ባይስማማም ለሶማሊያ ጉዳይ በሚል በአንድነት ቆሟል። በአንጻሩ ግን የኢትዮጵያን መንግስት የተቃወሙ መስሏቸውም ይሁን አውቀው ከሀገር ጥቅም ተቃርነው የቆሙ ጥቂት ግለሰቦች ታይተዋል። ነገር ግን በብሔራዊ ጥቅም ላይ ይሄን መሰል አቋም ሊኖር አይገባውም። በዚህ መልኩ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ላይ በተቃርኖ መቆም ደግሞ ነውርም ነው፤ ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሆኑ እንኳን በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ቢለያዩም በተለይ በብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ በጋራ ሊቆሙ ይገባል። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። የሀገርን ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ላይ፣ የሀገርን ኢኮኖሚ በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ፣ የሀገርን ደህንነት በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የፖለቲካ አንቂዎች ሁሉም ዜጋ በጋራ መቆም ይገባዋል። ከዚህ በተቃራኒው ግን በሀገር ጥቅም ላይ ተቃርኖ መቆም ሀገርን አሳልፎ እንደመስጠት ይሆናል። መሰረታዊ በሆኑ በሀገራዊ እሳቤ እና በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ መቀራረብና መተባበር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሀገር ካለ ብቻ ነው ሁሉም ነገር ሊኖር የሚችለው።

ታሪክ እንደሚመሰክረውም፣ ኢትዮጵያውያን በታሪክ አጋጣሚ በጋራ በቆሙባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ሁሉ አሸናፊ ናቸው። ይሄ የሸናፊነት ልዕልና ደግሞ እንደ መንግስትም፣ እንደ ተቋምም የሚወርዱ የሀገርን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስጠብቁ አጀንዳና ጉዳዮችን የእኔ ብሎ ከመቀበል፤ ለአጀንዳና ጉዳዩ መሳካትም ትኩረት ሰጥቶ ከመስራት ጋር የሚተሳሰርም ነው።

በእርግጥ የትኛውም የሀገርን ጥቅም የሚያረጋግጥ አጀንዳ የሚወለደው ከመንግስት፣ ከፓርቲዎች፣ ከቡድኖች፣ ሲያልፍም ከግለሰብ ሊሆን ይችላል። ለአጀንዳው ተፈፃሚነት መስራት ግን የብዙሀኑን ትብብር ይሻል። አጀንዳውን የእኔ ብሎ ለመቀበልና ለመተግበር ታዲያ ጥያቄው መሆን ያለበት፤ የአጀንዳው ግብ የሀገርንና የህዝብን ብሄራዊ ጥቅም ያረጋግጣል ወይ? የሚል መሆን አለበት።

ለምሳሌ፣ እንደ ሀገር አሁን እየታሰቡ ያሉ ጉዳዮች አሉ። እነዚህ በገዢው መንግስት የሚመጡ ቢሆኑም፤ የሀገርን ጥቅም የሚያስከብሩ እስከሆኑ ድረስ መፈፀም እንዳለባቸው ሁሉም በአንድ ድምፅ ማመን አለበት። እንደዚህ አይነት የጋራ የሆኑ አጀንዳዎችን መያዝና የወል ትርክቶችን መፍጠሪያ አውዶችን መገንባት ከሁሉም ይጠበቃል። መንግስትም አቃፊ ሆኖ የጋራ ትርክት እንዲኖር ከሁሉ የበለጠ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚቀርቡ አጀንዳዎች የህዝቡን ስነ ልቡና፣ ሞራልና እሴት ያገናዘቡ ዘላቂ አብሮነትንም የሚያፀኑ መሆንም አለባቸው።

የትኛውም የበለፀገ ሀገር መነሻው ድህነት የወለደው የሰላም እጦትና ችግር ነው። ሆኖም የትኛውም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ቢኖር፣ በሀገር ተስፋ መቁረጥ ግን ከቶውንም አይቻልም። በሀገር ላይ በርካታ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት፣ መፈናቀል፣ግጭት ቢኖሩም፤ እነዚህን ችግሮች ብቻ እየመዘዝን ከሄድን ብዙ የሚያስኮርፉ ነገሮች አሉ። ነገር ግን በማን ነው የሚኮረፈው? የሚለውን ጥያቄ አንስተን በሀገር እንደማይኮረፍ በአግባቡ ሊገባን ይገባል።

ችግሮችን እየነቀሱ አኩራፎ ከመሆን ይልቅም፣ ችግሮቹ እንዲፈቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆንና መፍትሄ አማራጮችን ማቅረብ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ እንዳደረገቻቸው የነፃነት ትግሎች ሁሉ፤ አሁንም የተደራረበባትን የችግር ድሪቶ ገፍፎ ለመጣል የተለያዩ አጀንዳዎችን ቀርፃ እየሰራች ነው። እነዚህ አጀንዳዎች ከግብ እንዲደርሱ ደግሞ፣ የሂደቱ ፈተና የሆኑ ጉዳዮችን የማጥራት ስራ ያስፈልጋል።

የተለያየ አጀንዳ እና ፍላጎት ያላቸው አካላት/መንግስትም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ሌሎች አደረጃጀቶች/ነገሮችን የሚረዱበትና የሚተረጉሙበት፣ እንዲሁም የሚተነትኑበት መንገድ የተለያየ ነው። ይሄው የአረዳድ ልዩነት የሚፈጥርባቸውን ስሜትም ወደ ኅብረተሰቡ የሚያሰርጹት በየራሳቸው መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ይሄን ሲያደርጉ ቢያንስ በሚያቀራረብና ወደ ሚያስማማው ለመምጣት እንዲችሉ በማድረግ ሊሆን ያስፈልጋል።

በሌላ መልኩ ደግሞ የዴሞክራሲ ተቋማት እንደምርጫ ቦርድ፣ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ኦዲተር የመሳሰሉ ተቋማት በተቻለ መጠን ገለልተኛ ሆነው እኩል የሚዳኙ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትና ታማኝነት ሊኖራቸው ያስፈልጋል። ይሄን ታማኝነት ሲያገኙ በመንግስትና ሕዝብ መካከል ትምምነት ስለሚፈጥሩ እንዲተገበሩና እንዲኖሩ በሚታሰቡ ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ሁሉም ኃይሎች በጋራ የሚተባበሩበት አውድ ይፈጠራል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችውን የባህር በር የማግኘት ጉዞን ጨምሮ ሌሎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያረጋግጡ ጥያቄዎች በውጤት ለመደምደም፤ በተለይ መንግስት ችግሮችን በሆደ ሰፊነት የመሻገር ልምምዱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ በጋራ አለመቆም እና የሀገርን ገፅታ ለግል ጥቅም ለማዋል ሲባል ሆንብሎ ማበላሸት በሕግ ተጠያቂ ከማድረጉም ባሻገር የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ተግባር መሆኑንም መገንዘብ ይገባል።

በመሆኑም በሀገራችን ጉዳይ ላይ የምንሰጠው አስተያየትና በመንግስት ላይ የምንሰጠው አስተያየት ለየቅል መሆን አለባቸው። መንግስትን መተቸት፣ መውቀስ፣ ማመስገን ይቻላል። ነገር ግን ሀገርን ማሳነስ፣ ሀገርን ተዳፍሮ ለጠላት መረጃ መስጠት፣ የሀገርን ገፅታ ጥላሸት እየቀቡ እንጀራ መብያ ማድረግ ታሪክም ሕዝብም ህግም ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ናቸው።

ምክንያቱም ሀገር ከሁሉ ነገር ትበልጣለች። መንግስታት የሚቀያየሩት በቋሚዋ ሀገር ውስጥ ነው። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚኖረው እይታ ሁሉ ከዚህች ቋሚ ሀገር ጋር ሊሆን ይገባል። ስለ ኢትዮጵያ ስናስብ የቀደሙት ስለ እርሷ ራሳቸውን እንዴት አሳልፈው እንደሰጡ እናስብ፤ ገናን ታሪክና ዝናዋ፣ ስልጣኔና ጥበቧ ከምን የመነጨ እንደሆነ እናሰላስል። ይሄን ማድረግ ስንችል በታላላቅ ሰዎች የዘለቀችውን የታላቋን ሀገር ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ በመሆም አቅም እናገኛለን።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You