የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለቀጣናው ሠላምና ዕድገት ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ምሑር አስታወቁ

አዲስ አበባ፡-ለቀጣናው ሠላምና ለጋራ ዕድገት የኢትዮጵያ የምትከተለው ዲፕሎማሲ ወሳኝ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ሲሉ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሠላምና ፀጥታ ትምህርት ክፍል መምህር የኔነሽ ተመስገን (ዶ/ር) ተናገሩ።

መምህርት የኔነሽ ተመስገን (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለሠላምና ለጋራ ዕድገት ቅድሚያ የሰጠ በመሆኑ ለቀጣናው ሠላም ወሳኝ ነው። ኢትዮጵያ ባላት የዲፕሎማሲ ታሪክ ጦረኛ ሳትሆን ሠላማዊና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲን የምታራምድ ናት ያሉት ዶክተር የኔነሽ፤ ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የነበሯት መሪዎችና ዲፕሎማቶች የቀጣናውን ዲፕሎማሲ በጥንቃቄ ይዘው መምራታቸውን ጠቁመዋል።

በዲፕሎማሲ ረገድ ሁለት አይነት ዲፕሎማሲ መኖሩን የገለጹት ዶክተር የኔነሽ፤ ይህም “ለስላሳ ዲፕሎማሲና” እና “ጠንካራ ዲፕሎማሲ” መሆናቸውን አመላክተዋል። በኢትዮጵያ በሃርድ ዲፕሎማሲው የዓድዋ ጦርነትን አሸንፋ አቅሟን አሳይታለች፤ በለስላሳ ዲፕሎማሲውም የአፍሪካ ሀገራትን አንድ እንዲሆኑና ኅብረት እንዲፈጥሩ ማድረጓን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ የበለጠ በንግግርና በውይይት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲን ስትጠቀም መቆየቷን አስታውሰው፤ በዚህም የበለጠ ወጤታማ የምትሆንባቸውን መደላድሎች ማመቻቸቷን ተናግረዋል። ሀገሪቱ የራሷን ዲፕሎማሲ በሠላማዊና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከመያዝ አልፋ በሌሎች ጎረቤት ሀገራት አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የምታከናውነው የሠላም ጥረት የሚወደስ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ ዶክተር የኔነሽ ገለጻ፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ስለምትጠቀምባቸው ጉዳዮች ስምምነት መድረሷን የማይፈልጉ አካላት የሚያደርጉትን ጥረት ለማክሸፍ ጥረት ማድረግ ይገባል። ከባሕር በር ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጫናዎችም ኢትዮጵያ በቂ ዝግጅት አድርጋ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሱ ሀሳቦችን በማጤን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጋ ስለወደብ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት የህዳሴ ግድቡን የእኔ ነው ብሎ እንደያዘው ጉዳዩን በእኔነት ስሜት እንዲይዘው ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ጠቁመዋል። የባሕር በር አለመኖር በርካታ ነገሮች እንድታጣ አድርጓታል ያሉት መምህሯ፤ የሀገሪቱ የባሕር በር ማግኘት በጂኦ ፖለቲካ ተጠቃሚ እንድትሆንና በቀጣናው ጠንካራ ሀገር እንድትሆን ያስችላታል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር የኔነሽ አይይዘው እንደተናገሩት፤ ለረጅም ዓመታት ለሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ዕድገት ትልቅ ዋጋ የከፈሉበትን አካሄድ ይበልጥ በማጤን ለበለጠ ውጤት መሥራት ከማንኛውም ዜጋ ይጠበቃል።ከሀገር ውስጥ ሰላምና ዲፕሎማሲውን በማጠናከር በቀጣናው ያለውን ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አካሄዶች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባም መምህርቷ ጠቁመዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You