የትምህርት ተቋማት የሁሉም ነገር ማእከላት፤ የእውቀት መከማቻዎች፤ የክሂሎት ማዳበሪያዎች፤ የአብሮነት መናኸሪያዎች፤ የነገ ሀገር ገንቢ ትውልድ ማፍሪያዎች ወዘተ ናቸው። በመሆኑም በሁሉም ይፈለጋሉ፤ የቻለ ሁሉ በእነሱ ውስጥ ያልፋል።
በትምህርት ተቋማት ውስጥ ከመማር-ማስተማር ተግባርና መደበኛው የቀለም ትምህርት በተጨማሪ በተጓዳኝ ትምህርትነት የሚታወቁ በርካታ እንቅስቃሴዎች ያሉ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም ቀዳሚ ተጠቃሾቹ ክበባት ናቸው። ከክበባቱም አንዱ ደግሞ የሙዚቃ ክበብ ሲሆን፣ እንደየ ትምህርት ተቋማቱ አቅምና ባህርያት፣ የክበቡ ከፍተኛ የእድገት ደረጃም “ማርሽ ባንድ″ (ማርቺንግ ባንድ) እና እውቅ ባለ ሙያዎችን ማፍራት ሲሆን፤ በዳግማዊ ምኒልክ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ያየነው ይህንኑ ነው።
በመላው ዓለም በሙያዊ ስልጠና የተቃኘ የዘንግ ማሽከርከር፣ አሰላለፍ እና ውህድ የሙዚቃ ጣዕም በማውጣት ለተለያዩ ዝግጅቶች ማድመቂያ የሚውለው፤ በተለይም በወታደራዊ ተቋማት ውስጥ አንዱ የተቋሙ አካልና ተግባር በመሆን ሲሰራበት የሚታየው ማርሽ (ማርቺንግ) ባንድ ዛሬ ዛሬ ከዛም አልፎ በትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ተማሪዎች አማካኝነት እየተከናወነ ይገኛል።
ለዚህ ጽሑፍ ግብአት ይሆኑን ዘንድ መረጃዎችን ፍለጋ ስናነፈንፍ ያገኘነውና “በንጉስ ሚካኤል ልጅ በወይዘሮ ስህን፣ በ1922 ዓ.ም በተመሰረተው የቀለም ትምህርት ቤት ጎን ለጎን፣ በ1956 ዓ.ም ደግሞ የሙዚቃ ባንድ ተቋቋመ። ባንዱ ስራውን ሲጀመር 40 ተማሪዎችን በመያዝ ሚስተር ሮናልድ ቤል በሚባሉ አሜሪካዊ ትምህርቱ መሰጠት ተጀመረ። ሙሉ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በማሟላት ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት የተሟላ የሙዚቃ ባንድ እና ማርሽ ባንድ ያቋቋመ የመጀመሪያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመሆን ለሀገራችን ለኢትዮጵያ የሙዚቃ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል።″ የሚለውም እዚህ ቦታ ይጠቀስ ዘንድ ታሪክ ያስገድዳልና እነሆ ክፋት የለውም።
ማርሽ ባንዱ በአጠቃላይ ሀገሪቱ ባደረገው አስተዋጽኦ በወቅቱ ከንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ሽልማትን ተቀብሏል። ታዋቂ ከሆኑ የሙዚቃ አባላት መካከልም እንደ መስፍን አበበ (ያዥልኝ ቀጠሮ) አይነት አንጋፋ ባለሙያዎችን ያፈራ ተቋም መሆኑም የብዙዎችን ምስክርነት ያገኘ ነው። ዛሬ “ያ ሁሉ ታላቅነት እና ዝና ጠፍቶ በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ትምህርት ቤቱ ወደ ነበረበት ዝና እንዲመለስ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል።″ ጥሪም ከዚሁ መረጃ ጋር ተያይዞ ይገኛልና ምን ያህል ምላሾችን እንዳገኘ ለጊዜው ማወቅ ባይቻልም፤ የዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማርሽ ባንድን እንደ ታደገው፣ እንደ ሌ/ኮ ሲሳይ አይነት ተቆርቋሪ እንዲገጥመው ግን ሳንመኝ አናልፍም።
ተሾመ ብርሃኑ የተባሉ ጸሐፊ “ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን በ1923 ዓ.ም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተብለው ሲነግሱ ያጀባቸው የኪቮርክ ናልባዲያን ሰልጣኞች፣ የተፈሪ ማርሽ ባንድ ነበር፡፡″ በማለት ለንባብ ያበቁትን እንደ መነሻ ታሪክ ይዘን፤ መነሻ ታሪኩንም “የአርመናዊያኑ የሙዚቃ ቡድን ወይም ባንድ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከሀገረ ሩሲያ ከመጡ የሙዚቃ መሳሪያዎች እና ጥቂት የሙዚቃ አሰልጣኞች ወዲህ፤ ከውጭ በመጡ ሙዚቀኞች የተደራጀ ቀዳሚ ባንድ ነው፡፡″ በሚለው አደንድነንና ወደ ኋላ ወስደን ስለ ማርሽ ባንዶች ታሪክ ስናወሳ በርካታ ጉዳዮችን የምናገኝ ሲሆን፣ አንዱም የትምህርት ቤቶች ማርሽ ባንድ ታሪክ ነው። (“ከውጪ የመጡ″ የተባሉት ኪቮርክ ናልባዲያን የተባለ የሙዚቃ አሰልጣኛቸውን ጨምሮ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ለእያንዳዳቸው የመርከብ ወጪያቸውን ከፍለው ከኢየሩሳሌም የአርመን ገዳም ያመጧቸው አርባ አርመናውያን ወጣቶች (በዘመኑ ድንቅ የሚባለውን የብራስ ባንድ የፈጠሩ) መሆናቸው በዚሁ በተሾመ ጽሑፍ ውስጥ ተጠቅሷል።)
ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉትና የዳግማዊ ምኒልክ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማርሽ ባንድ አሰልጣኙ ሌ/ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ከበፊት ጀምሮ ትምህርት ቤቶች፤ በተለይም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማርሽ ባንድ የነበራቸው ሲሆን፤ እሳቸው የተማሩበትና የማርሽ ባንዱ አባል በመሆን በውስጡ ያለፉበት የናዝሬቱ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤትን ጨምሮ፣ አሁን ተማሪዎችን እያሰለጠኑበት ያለው ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ኮከበ ፅባህ እና ሌሎችም ማርሽ ባንድ የነበራቸውና በርካታ የኪነጥበብ ሰዎችን ያወጡ ተቋማት ናቸው።
ሌ/ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱ እንዳጫወቱን በአሁኑ ሰአት የራሳቸው ማርሽ ባንድ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ እሳቸው ተማሪዎችን እያሰለጠኑ ከሚያስመርቁበት ምኒልክ በተጨማሪ የድሬዳዋው ከዚራ የሙዚቃ ክበብ አንዱና ሌላኛው ነው።
የሌ/ኮሎኔል፣ መምህርና አሰልጣኝ ሲሳይን ጥቆማ ተከትለን ስለ ድሬ ለማወቅ ካደረግነው ጥረት ለመረዳት እንደ ቻልነው የማርሽ ባንዱ መስራች መምህር ዳንኤል ሲሆኑ፤ በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙኃን እንደ ተናገሩት የድሬደዋ ትምህርት ቢሮ ማርሽ ባንድ ከጥቂት አመታት ወዲህ በመሳሪያ እና በሚያሳትፋቸው ልጆች መጠን ከፍ እያለ መቷል፡፡ በዚህም በመስተዳድሩ የሚሰሩ ማናቸውም ስራዎችን ሙሉ በሙሉ መስራት (ማጀብ) ችሏል።
እንደ መምህር ዳንኤል ማብራሪያ፣ ባንዱ ከትምህርት በኋላ ቀጣይ ሕይወታቸውን ለሙዚቃው ጥበብ የሰጡ ሞያተኞችን በማፍራት ለተለያዩ ተቋማት አበርክቷል። የተማሪዎችን ስብስብ ያቀፈው ማርሽ ባንዱ በአሁኑ ጊዜ ከድሬዳዋ መስተዳድር አልፎ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
“በጣም ጎበዝ እና ለድሬ ድምቀት ነህ″፤ የባንዱ አባላትም “የድሬ አለኝታ ናቸው″፤ በዚህ እድሜያቸው ለድሬ ብቻ ሳይሆን ለሌላ ክልልም ተርፈዋል፤ እነዚህን ተማሪዎች ማበረታታት ያስፈልጋል″ የሚል አድናቆትን ያገኙት መምህር ዳንኤልና የማርሽ ባንዱ አባላት ለሚዲያ ባለሙያዎች እንደ ተናገሩት ብዙ ፈተናዎችን አልፎ እዚህ የደረሰው የተማሪዎች ማርሽ ባንድ በየጊዜው አዳዲስ ተማሪዎች ይቀላቀሉታል፤ ይማሩበታል፤ ያገለግሉበታል። ኋላም ለተተኪው አስረክበው ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ይሄዳሉ፡፡
አንጋፋና ተተኪዎችን ያቀፈው፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በርካታ አስቸጋሪ ፈተናዎችን በፅናት ማለፉ የሚነገርለት የሐረር ከተማ የሙዚቃ ሙያተኞች ማህበር ማርሽ ባንድም የሀገራችን የማርሽ ባንድ ታሪክ አካል ነው። “የዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሊዲያ መለስን ጨምሮ 60 የሚሆኑ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ድሬዳዋ በሚገኘው የትምህርት ቢሮ የተማሪዎች ማርሽ ባንድ ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያዎች″ን (ሳክስፎን አንዱ ነው) በመጫወት ላይ መገኘታቸውም እንደዛው።
ወደ ምኒልክ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንመለስ፤
ከዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደ ሚያሳየው ከሆነ፣ ትምህርት ቤቱ በኢትዮጵያ የማርሽ ባንድ ከነበራቸው ጥቂት ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ነበር። ከ43 ዓመታት በፊት ተቋርጦ የነበረው የትምህርት ቤቱ የተማሪዎች የሙዚቃና ማርሽ ባንድ አሁን ትንሳኤውን ማግኘት ችሏል።
የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኪነ ጥበብ ክበብ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ እሸቱ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር አድርገውት በነበረ ቆይታ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከ43 ዓመታት በፊት ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ለውጥ በኋላ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት መቋረጡን ያስታወሱት መምህር ፍቃዱ፣ “የሙዚቃ ሙያተኛ እና መምህር የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱ ለትምህርት ቤቱ የሙዚቃና ማርሽ ባንድ ትንሳኤ ምክንያት ሆነዋል። የግል የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ተማሪዎች በነፃ እንዲጠቀሙባቸው በማድረግ እና ስልጠና በመስጠት የተማሪዎች ማርሽ ባንድ እንዲጠናከር ሰፊ ጥረት በማድረግ ላይም ይገኛሉ።″ በማለት ስለዛሬው እንግዳችን ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ43 ዓመታት በፊት የሙዚቃ ትምህርትን በማጠናከር ተማሪዎች በፍላጎታቸው በትምርት ቤት ውስጥ የተቋቋሙ የተማሪ የሙዚቃ እና ማርሽ ባንዶችን እንዲቀላቀሉ በማድረግ በዘርፉ ለአገር ፈርጥ የሆኑ ታዋቂ ሙዚቀኞችን ማፍራት መቻሉን የተናገሩት መምህር ፍቃዱ ከዚህ ትምህርት ቤት የወጡ ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያዎችና የኪነጥበብ ሰዎች እንዳሉም ገልፀዋል። ተማሪዎች ባገኙት ስልጠና መሠረት በተማሪዎች ማርሽ ባንድ መቋቋም ላይ የድርሻቸውን በመወጣትም ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
“የዚህ የማርሽ ባንድ ጉዳይ፣ ከሰብእና ቀረፃም ሆነ ለኪነጥበብ እድገት ሲባል በሌሎች ትምህርት ቤቶች ላይም እንዲስፋፋ በትኩረት ሊሠራበት″ የሚገባ መሆኑን የሚናገሩት እንግዳችን የመምህር ፍቃዱን ሃሳብ በማጠናከር በአሁኑ ሰአት እሳቸው ያሰለጠኗቸው ተማሪዎች በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ “አንቱ″ እየተባሉ የሚገኙ ሲሆን፣ ቲክቶክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይም ስራዎቻቸውን በማቅረብ ከ35ሺህ በላይ ተከታዮች ያሏቸው ወጣት ሙያተኞች እንዳፈሩም ይናገራሉ።
በቀድሞው (ቅድመ 1983 ዓ∙ም) በነበረው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ውስጥ በዚሁ ስራ ላይ ያገለግሉ የነበሩት፤ አንጋፋው ባህር ኃይል እንዲፈርስ የተፈረደበት መሆኑን ተከትሎ ከስራቸው የተፈናቀሉት፤ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በሙያቸው ተፈልገው ዳግም መከላከያን በመቀላቀል የመከላከያ ማርሽ ባንድ አሰልጣኝ የነበሩት (ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ)፤ በዚሁ ስራቸው አማካኝነት ወደ ተለያዩ ሀገራት የተጓዙትና ከማርሽ ባንዱ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አካል በመሆን በሙያቸው ሲያገለግሎ የቆዩት፤ የአንጋፋው ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቅ ሌ/ኮሎኔል ሲሳይ ፍቃዱ እንዳጫወቱን ከሆነ ወደ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምጣት ይህንን፣ በራሳቸው ሙሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች የነፃ አገልግሎት ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ሊሰጡ የቻሉት ለሙያው ካላቸው ልዩ ፍቅርና ለሀገሪቱ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ማደግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ሲሆን፤ ተሳክቶላቸው እያደረጉትም ይገኛሉ።
ህልማቸው የራሳቸውን ማሰልጠኛ መክፈት መሆኑን የሚናገሩት መምህር ሌ/ኮሎኔል ሲሳይ ባለፈው ህዳር ወር ሁለተኛ ዙር ተመራቂዎችን ያስመረቁ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር ብቻ 35 ተማሪዎችን በማስመረቅ ለፍሬ ያበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የራሴን የሆነ ማሰልጠኛ ለመክፈትና ስልጠናውን ለብዙዎች ተደራሽ ለማድረግ ፍላጎቱ አለኝ። ምኞቴም በርካታ ስመጥር ሙያተኞችን ማፍራት ነው። ሙዚቃን በባንድ መስራቱ አስፈላጊ መሆኑን ስለማምንበት ያንን እውን ለማድረግ እነዛን ሙያተኞች ማፍራት እፈልጋለሁ።″ የሚሉት ሌ/ኮለኔሉ “ችግሬ የቦታ በመሆኑ ያንን የሚቀርፍልኝ አካል ባገኝ የበለጠ ለመስራት ዝግጁ ነኝ። መሳሪያዎችን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ እየገዛሁ ያጠራቀምኩ በመሆኑ ምንም ችግር የለብኝም። ችግሬ የማሰልጠኛ ስፍራ ነው። የዛሬ ቤት ኪራይ የሚቀመስ ባለ መሆኑ እገዛ ቢደረግልኝ ደስ ይለኛል።″ ሲሉም ያሉበትን ሁኔታና የወደፊት ፍላጎታቸውን ይናገራሉ።
እኔ ይህ ሙያ በየትምህርት ቤቶችም ሆነ ሌሎች ተቋማት ውስጥ እንዲስፋፋ ልምዴን ለማካፈል፣ እገዛ ለማድረግ፤ በምችለው ሁሉ ለመተባበር ዝግጁ ነኝ የሚሉት የሙዚቃ መሳሪያዎች ባለሙያው ሌ/ኮለኔሉ ሲሳይ እንደሚናገሩት ከሆነ ኢትዮጵያ ለማርሽ ባንድ አዲስ አይደለችም። በጣሊያን ጊዜ ተቋርጦ አንዳንዶቹም በዛው ቀሩ እንጂ ማርሽ ባንድ በስፋት ነበር። ወታደራዊ፣ ክቡር ዘበኛ፣ ፖሊስ ማርቺን ባንዶችን ጨምሮ እንቅስቃሴው ከድሮ ጀምሮ የነበረ ነው። ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። ትምህርት ቤቶች ደግሞ ለዚህ ምቹ ናቸው። መሳሪያዎቻቸውን በሙሉ ይዘው በመምጣት ምኒልክ ትምህርት ቤትን “ትንሽ ቦታ ፍቀዱልኝ፤ በነፃ ላሰልጥን″ ብለው የጠየቁበትና ተሳክቶላቸው ወደ ስራ የገቡበት፤ ገብተውም ውጤታማ የሆኑበት ምክንያትም ይኸው ነው።
ሌ/ኮለኔል ሲሳይ ስልጠናውን በሚሰጡበት ምኒልክ ትምህርት ቤት በሙዚቃ መሳሪያዎች የተሞላ፣ ወጣት ሰልጣኞች የሚገኙበት፤ በኪነጥበባዊ ምስሎች በደመቀው መለስተኛ አዳራሽ ተገኝተን እንደ ተመለከትነው በከፍተኛ የሙያ ፍቅር የሚሰለጥኑ ወጣቶች አሉ። የሌ/ኮለኔል ሲሳይ ረዳቶችም በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል። ባንዱ ከሰልጣኝነትም አልፎ በተለያዩ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና መዘጋጃ ቤትን በመሳሰሉ መድረኮች ላይ ስራዎቹን እንደሚያቀርብም በሌ/ኮለኔል ሲሳይ አማካኝነት ተነግሮናል። በሚቀጥለው በዚሁ ገጽ ላይ ይዘናቸው ከምንመጣቸው ፍሬዎቻቸውም ሆነ ሰልጣኞቻቸው ዘንድ እጅግ የሚወደዱትና የሚወደሱት ሌ/ኮለኔል መምህር ሲሳይ ፍቃዱ እያደረጉት ያለው ተግባር ዳግማዊ ምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን አንድ እርምጃ ወደ ፊት እያስኬደና ስሙንም እያስጠራው መሆኑን ተገንዝበናል። በመሆኑም፣ ሁሉም ይህንን ልምድ ሊቀስም ይገባል ስንል በአክብሮት እንገልጻለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2016 ዓ.ም