የዱር እንስሳት ጥበቃ ሚና ለተፈጥሮ ቱሪዝም እድገት

የተፈጥሮ ቱሪዝም በዓለም ላይ መስህብ ያላቸው ሁሉንም ማራኪ የተፈጥሮ አካባቢዎችን የመጎብኘት ልማድ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አንዳንዶች ከገጠር ቱሪዝም ጽንሰ-ሃሳብ ጋር ተጣጥሞ እንደሚሄድም ይገልፃሉ። በተፈጥሮ ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ቱሪስቶች ሊጎበኟቸው የሚችሏቸው ቦታዎች የባህር ዳርቻዎች፣ ደኖች ወይም ብሔራዊ ፓርኮች የመሳሰሉትን ነው። በተለይ ፓርኮችና ማራኪ መልከዓ ምድር በቱሪስቶች በስፋት ተመራጭ ናቸው።

በዓለማችን ላይ ጉዞ የሚያደርጉ ብዛት ያላቸው ቱሪስቶች ከሰው ሠራሽ የቱሪዝም መስህቦች ይልቅ በተፈጥሮ አካባቢዎች ላይ እንደሚያተኩሩ በየጊዜው የሚወጡ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ኮከቦችን፣ ፓርኮችን፣ ትላልቅ ወንዞችን፣ ተራሮችን፣ በረሃማ ሥፍራዎችን ለመመልከት እና በእግር ጉዞ ማድረግ ምርጫቸው ያደረጉ ቱሪስቶች በየጊዜው እየጨመሩ መምጣታቸው ይነገራል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለማችን ለተፈጥሮ ቱሪዝም ምቹ የሆኑ ቦታዎች በብዛት ይገኛሉ። በኔዘርላንድ መቀመጫውን ያደረገው ሲቢአይ ‹‹CBI›› (ከታዳጊ ሀገሮች የሚመጡ ምርቶችን የሚያስተዋወቅ ማዕከል) የተፈጥሮ ቱሪዝምን ‹‹በአካባቢው የተፈጥሮ መስህቦች ላይ የተመሠረተ ቱሪዝም ነው። የተፈጥሮ አካባቢዎችን እና መልከዓ ምድራቸውን፣ እፅዋትንና እንስሳትን ለመለማመድ፣ አካባቢን ለመጠበቅ እና የአካባቢውን ነዋሪዎች የኑሮ ጥራት ለማሻሻል ኃላፊነት የሚሰማው ጉዞን ያካትታል›› በማለት የተፈጥሮ ቱሪዝም ማራኪ ሥፍራዎችን ለመመልከት ከሚደረግ ጉዞም ያለፈ ለሀብቱ ኃላፊነትን የመውሰድ እና መንከባከብም ጭምር እንደሆነ ይገልጸዋል።

ለሰዎች የተፈጥሮ አካባቢያችንን ውበት እንዲያዩ እና እንዲያደንቁ ስለሚያደርግ የተፈጥሮ ቱሪዝም ምርጫቸው እንደሆነ አብዛኛዎቹ ጎብኚዎች ይናገራሉ። በዚህ ዓይነት የቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ከከተማ ሕይወት፣ ብክለት እና ጫና ማምለጥ እንችላለን በማለት የሚያስቡ ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም። ንጹህ አየር መተንፈስ እና አረንጓዴ ሥፍራ፤ ሰማያዊ ባህር ማየት ለአካላዊ እና አእምሯዊ ደህንነታቸው ጥሩ አማራጭ መሆኑን ያስባሉ። ሳይንሱም ይህንኑ በስፋት ሲመክር ይደመጣል። ከዚህ አንፃር የተፈጥሮ ቱሪዝም ጎብኚዎችን ለተፈጥሮ አካባቢ ፍላጎት እንዲኖራቸው ያበረታታል። በተለይ ጎብኚዎች የአካባቢ ጉዳዮችን በሚመለከት የበለጠ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ያሳስባል። የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል፣ ሕገወጥ የእንስሳት አደን እንዳይስፋፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት የጉብኚት ባህል እንዲኖር ግንዛቤ ያስጨብጣል።

ያም ቢሆን ግን የሰው ልጆች የተፈጥሮ ቱሪዝም አስኳል የሆኑ ሀብቶች ላይ ጥፋት ሲያደርሱ ይስተዋላል። በተለይ ሕገወጥ የዱር እንስሳት አደን፣ የደን ምንጠራና፣ ሕገ ወጥ ሰፈራ እንዲሁም የአየር ብክለትን የሚያባብሱ ኃላፊነት የጎደላቸው (የፕላስቲክና መሰል ቁሳቁሶችን መጣል) ርምጃዎች ላይ ሲሳተፉ ይስተዋላል። በተለይ ብርቅዬና አይተኬ የዱር እንስሳት ላይ የሚካሄደው አደን የተፈጥሮ ቱሪዝምን አደጋ ውስጥ እየጣለ ከሚገኝ ዋንኛ እኩይ ድርጊት የሚመደብ እየሆነ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ ለተፈጥሮ ቱሪዝም ምቹ ከሆኑ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ናት። በሌላው ዓለም የማይገኙ ብርቅዬ እንስሳት፣ መልከዓ ምድር (የ13 ወር ፀጋ የሚል ስያሜ ያሰጣት)፣ በርካታ ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም ማራኪ ወንዞች የሚገኙባት ነች። ይህንን ተከትሎ በቂ የሚባል ባይሆንም በርካታ ቱሪስቶች ተፈጥሮዋን መሠረት አድርገው ለጉብኚት ወደ ኢትዮጵያ በየዓመቱ እንደሚገቡ ይነገራል። የቱሪዝም ሚኒስቴርን የ2015 መረጃ ብንወስድ እንኳን 850 ሺ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ይሁን እንጂ የዱር እንስሳቶቿ እና የተፈጥሮ ሥፍራዎች በሕገ ወጦች በየጊዜው ይፈተናሉ። በተለይ በዱር እንስሳት ከሚፈተኑ ሀገራት ተርታ ቀዳሚዋ ነች። ዝሆኖች፣ አቦ ሸማኔ እና ሌሎች የዱር እንስሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥጋት ውስጥ መሆናቸው እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህ ምክንያት የዱር እንስሳቱ መጥፋት አደጋ፣ የሥነ ምህዳር መዛባትን ጨምሮ የተፈጥሮ ቱሪዝምን መሠረት አድርገው የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዳይመናመን ስጋት እየሆነ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ይፋ አድርጓል።

የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ የዱር እንስሳት ውስጥ አቦ ሸማኔ (Cheetah) በቀዳሚነት ይገኝበታል። አቦሸማኔ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቢገኝም በበርካታ ሰው ሠራሽና እና የተፈጥሮ ተግዳሮቶች ምክንያት ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣ በመሆኑ በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ህብረት (IUCN) የመጥፋት አደጋ ውስጥ ያሉ የዱር እንስሳት ዝርዝር ውስጥ ከተካተተ ዓመታት መቆጠሩን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ይናገራሉ።

በመጥፋት ላይ የሚገኘውን አቦ ሸማኔን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆኑን ይገልፃሉ። በመሆኑም ለሥነ ምህዳር ሚዛን መጠበቅ እንዲሁ ለተፈጥሮ ቱሪዝም መስፋፋት አስተዋጽኦ ያለውን አቦ ሸማኔ እንዲሁም መሰል ስጋት ያለባቸው የዱር እንስሳትን የመጠበቅ ኃላፊነት ሁሉም በድርሻው መወጣት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

አቶ ዳንኤል ጳውሎስ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ውስጥ የዱር እንስሳት ሕገ ወጥ ዝውውር ቁጥጥር ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በዓለም ላይ የአቦ ሸማኔዎች ቁጥር ባለፉት 100 ዓመታት 90 በመቶ በመቀነስ በእጅጉ እያሽቆለቆለ መጥቶ ከ100 ሚሊየን አሁን ላይ 10 ሚሊየን መድረሱን ያስረዳሉ። ይህ ስጋት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትንም እንደሚጨምር የሚናገሩት ባለሙያው የአቦ ሸማኔ ጥበቃ ፈንድ ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን ሀገራትን በማስተባበር በዓለም ላይ ለአቦ ሸማኔዎች ጥበቃ በማድረግ ላይ ይገኛል ይላሉ። ኢትዮጵያም ጥበቃውን ለማጠናከርና የዱር እንስሳትን ከስጋት ለመታደግ መሰል ርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ ያስረዳሉ።

የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሕገ ወጥ ዝውውር ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳንኤል፤ ለዱር እንስሳት መጥፋት ስጋት ከሆኑት ምክንያቶች መካከል በሕገ ወጥ ሰፈራ ምክንያት የዱር እንስሳቱ ከመኖሪያ አካባቢ መጥፋት፣ በሰው ሠራሽ ግጭት፣ በሕገ ወጥ አደን፣ ሕገ ወጥ ግድያ እና ለአስደናቂ የቤት እንስሳነት ንግድ በሚል የሚደረግ ዝውውር ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ያስረዳሉ።

የዱር እንስሳት ጥበቃን በሚመለከት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ቀርበው መፍትሔ አምጪ ውይይቶች በየጊዜው እንደሚካሄድ የሚያስረዱት ባለሙያው፤ ከዚያ በተጨማሪ ቀጣናዊ ትስስር በመፍጠር ሕገ ወጥ ዝውውርን እንዲሁም አደንን ለመከላከል የትብብር ስምምነቶች መደረጋቸውን ያስረዳሉ። እንዲሁም የዱር እንስሳትን በሚመለከት ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚተገበረው የመጥፋት አደጋ ላይ ያሉትን ሕይዎት ለመጠበቅ የሚያስችል የጥበቃ የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ይገልፃሉ።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦች፣ አጋሮች፣ መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለተፈጥሮ መጠበቅና ለተፈጥሮ ቱሪዝም እድገት ጉልህ ሚና ያላቸው የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ እየተሠራ መሆኑን ይናገራል። በተለይ በያዝነው ዓመት የመጥፋት ስጋት ውስጥ የሚገኘውን አቦ ሸማኔ ለመታደግና የተፈጥሮ ሚዛንን ለመጠበቅ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ የአቦ ሸማኔ ጉባኤ ከአቦ ሸማኔ ጥበቃ ፈንድ ጋር በመተባባር በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ተግባራዊ ርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችሉ ስምምነቶች መደረጋቸውንም ገልጸዋል።

‹‹ለዱር እንስሳት መጥፋትና መሰደድ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የደን ምንጣሮ፣ ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ንግድና ሌሎችም ዓይነተኛ ምክንያቶች ናቸው›› የሚሉት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ናቸው። የአቦ ሸማኔ የመጥፋት አደጋና የመከላከያ መንገዶች ላይ ያተኮረ በኢትዮጵያ የተካሄደ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በኢትዮጵያ ከሚገኙ በርካታ የዱር እንስሳት መካከል አቦ ሸማኔም መኖሩን ጠቅሰው፤ በተለያዩ ችግሮች እንዳይጠፉ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል። ለህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና ሁሉንም ያሳተፈ ጥበቃ ማድረግ እንዲሁም የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትና የፓርኮች ጥበቃ ሥራ ከሚወሰደው ርምጃ መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም ይገልፃሉ። የፓርኮችን ልማት ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለፈ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ለቱሪዝም ሀብት እንዲያገለግሉ እየተሠራ መሆኑንም ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ የዱር እንስሳትን ከጥፋት ለመታደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የአቦ ሸማኔ ጥበቃን የሚያግዘው የሲሲኤፍ ጥናት እንደሚያመለክተው ዓለም ባለፉት 100 ዓመታት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አቦ ሸማኔዎችን አጥታለች። እስካሁን በዱር የሚገኙ ያደጉ አቦ ሸማኔዎች ብዛት ከ7 ሺህ 500 እንደማይበልጥ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የሲሲኤፍ ተመራማሪዎች በሁለት ክልሎች መካከል ባሉት የአቦ ሸማኔ ግልገሎች ላይ ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል፣ እ.ኤ.አ በ2010 እና በ2019 መካከል 300 የሚደርሱ የአቦ ሸማኔ ግልገሎች ከአፍሪካ ቀንድ መልክዓ ምድር የሕገ ወጥ ዝውውር ሰለባ ሆነዋል፡፡ ግልገሎቹ የሕገ ወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑት በሰውና በዱር እንስሳት መካከል ባለው ግጭት እንዲሁም በቤት እንስሳት መልክ አላምዶ ቤት ውስጥ ለማኖር ፍላጎት ባላቸው ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ነው፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ አቦ ሸማኔዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መመናመን ጋር ተያይዞ አስቸኳይ የመፍትሔ ርምጃ ካልተወሰደ ዝርያቸው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአካባቢው እንደሚጠፋ የዱር እንስሳት ጥበቃ ተቆርቋሪዎች ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UN Environment Programme) የአፍሪካ ብዝሀ ሕይወት የተፈጥሮ ቱሪዝምን በማስፋፋት የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ይለውጣል ሲል ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጓል። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ብዙ መንግሥታት ለሌሎች አንገብጋቢ የሕዝብ ፍላጎቶች በጀቶቻቸውን ስለሚያውሉ ለብዝሀ ሕይወት ጥበቃ የሚመድቡት በጀት ውስን መሆኑን ይገልፃል። በዚህ ምክንያት በተፈጥሮ ላይ በተለይ በደኖች፣ በዱር እንስሳት እና መሰል የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ከሚያደርጉት ጥበቃ ወደኋላ እየተመለሱ መሆኑን በማሳሰብ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ በየጊዜው ያሳስባል።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም የዱር እንስሳቶችና እነርሱ የሚኖሩባቸው ቦታዎችን መጠበቅ ከምንጊዜውም በተለየ መንገድ አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባል። መንግሥታት የተጠበቁ የተፈጥሮ ቦታዎችንና በውስጣቸው የሚኖሩ የዱር እንስሳትና አጠቃላይ ብዝሀ ሕይወትን ቦታዎችን እንደ የአካባቢ ንብረት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያቸውን ጭምር የሚያሳድግ ግዙፍ ሀብት አድርገው ሊመለከቱ ይገባል በማለት ሪፖርት አውጥቷል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቱ 8 ሺህ 400 የተጠበቁ አካባቢዎች እና እጅግ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንስሳት አሉ። እዚህ እምቅ ሀብት ላይ ተመርኩዞ የየአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሙ በሠራው ጥናት 48 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የማስገኘት አቅም እንዳላቸውም ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

ዳግም ከበደ

 

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You