ዴሞክራሲን በተግባር

የሰው ልጅ በባህሪው ክብርና ነፃነቱን የመጎናጸፍ፤ ልዕልናና ብልጽግናውን የማረጋገጥ፤ በጥቅሉ ራሱን ሆኖ፣ ራሱን ችሎ፣ በራሱ የመቆምም፣ በራሱ የመወሰንም ከፍ ያለ ፍላጎት አለው። ይሄን ነፃነቱን በማንም ሊነጠቅ፤ በማንም ሊነፈግ አይሻም። ይሄ ፍላጎቱ ደግሞ በማህበራዊውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣… መስኮች ከፍ ብሎ ይገለጻል።

ይሄ ግለሰባዊ መገለጫ ታዲያ፣ እንደ ቡድን፣ እንደ ማህበረሰብ፣ እንደ ሕዝብ ብሎም እንደ ሀገር የሚንጸባረቅ እውነት ነው። ለዚህም ነው የየዘርፉ ልሂቃን በተለይም የፖለቲካው ዘርፍ ዘዋሪዎች ይሄንን የሰው ልጆች ከፍ ያለ የነፃነት መሻት ማርካት እንኳን ባይቻል ማስታገስ የሚያስችሉ መስመሮችን ለማግኘት ያለመታከት ሲታትሩ የሚታየው።

በዚህ ረገድ በተለይ መንግሥታት እንደ ሀገር የሚታዩ የሕዝቦች ፍላጎትና መሻቶችን መመለስ የሚያስችሉ የነፃነት አጽኚ እሳቤዎችን ማማተር የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ እንደየመንግሥታቱ ባህሪ የዜጎቻቸውን (የሕዝቦችን) ጥያቄና ፍላጎት ለማሳካት የሚጓዙበት መንገድ የተለያየ ነው።

ለምሳሌ፣ አንዳንዱ ዜጎችን በኢኮኖሚ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ማድረስን ታላሚ ያደርግና ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸውን ቸል ይልባቸዋል። አንዳንዱ ደግሞ ለማህበራዊ እሴቶቻቸውና ፖለቲካዊ ነፃነታቸው ቦታ ይሰጥና በኢኮኖሚው ረገድ ያለውን መሻት ይገታዋል። አንዳንዱም ሁሉንም እኩል ለማሳካት ሲታትር፤ አንዳንዱም ደግሞ ሁሉንም ዘግቶ ሕዝቡን ሲያስጨንቅ ይስተዋላል።

እነዚህ እንደየመንግሥታት ባህሪ የሚገለጹ እሳቤና መንገዶች ታዲያ ለአንዳንዶቹ ሰምረዋል፤ ለአንዳንዶቹ መራር ሆነዋል። አንዳንዶቹ ጋ መንግሥታቱን ያስመሰገኑና ምሳሌም የሆኑ መልካም ሕዝባዊ ይሁንታዎችን ሲያስገኙ፤ በአንዳንዶቹ ዘንድ ደግሞ እንዳሰቡት ሳይሆን የሕዝብን ብሶትና እምቢታ ቀስቅሶ ለራሳቸውም እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።

በኢትዮጵያም በሺህ ዘመናት የሥርዓተ መንግሥት ጉዞ ውስጥ የመንግሥት አስተዳደርና የሕዝብ ፍላጎቶች ጉድኝት ከእነዚህ ሁነቶች የፀዱ አልነበሩም። በሆነ ዘመን የኢኮኖሚው፣ በሆነ ዘመን የማህበራዊ ልዕልናው፣ በሆነ ዘመን ደግሞ የፖለቲካው መስክ ጭላንጭል ብልጭ ድርግም እያሉ ኖረዋል። በዚሁ ልክ ሕዝቦች ስለማይደራደሩበት ነፃነትና ክብር ሲሉ አመጽ ቀስቅሰው፤ ነፍጥ አንስተው ሥርዓቶችን ለዋውጠዋል።

ለምሳሌ፣ የ66ቱ አብዮት ዜጎች በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ፍትሃዊ ያልሆነ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የፈጠረው ከፍ ያለ ብሶት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በተመሳሳይ የ83ቱ የሥርዓት ለውጥ የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ምላሽ ናፍቆ መቆየቱን ያመላክታል።

የ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ደግሞ ዜጎች በ66ቱም፣ በ83ቱም አብዮቶች ያነሷቸው ጥያቄዎች በሙላት መመለስ ባለመቻላቸው ምክንያት፤ በሙላት እንዲፈጸሙ መሻታቸውን ያረጋገጠ ነበር። የእነዚህ ድምር ውጤት መገለጫው ደግሞ በኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ውስጥ የነበረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከሕዝቦች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፤ ብሎም እንደ ዜጋ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን ነፃነት ያለበትን ደረጃ ያሳያል።

ስለ ዴሞክራሲ ሲነሳ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ፣ የሥነ-ምግባርና ሥነ-ዜጋ መምህራኖቻችን ስለ ዴሞክራሲ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚሉት ሁሌ በአዕምሮዬ ይመላለሳል። በተለይ ስለ ዴሞክራሲ ሲነሳ፤ የቃሉ መነሻ፣ የቃሉ ትርጓሜ እና የቃሉ ተግባሪ ሀገራት አብረው መነሳታቸው አይቀሬ ነበር። ለምሳሌ፣ ዴሞክራሲ የሚለው ቃል መነሻው ግሪክ ስለመሆኑ፤ የቃሉ ትርጓሜ ደግሞ የሕዝብ አስተዳደር ማለት ስለመሆኑ፤ ይሄንን እሳቤ ከሚተገብሩ ሀገራት መካከል ደግሞ አሜሪካ ቀዳሚዋ እንደሆነች፤… በዝርዝር ሲያስረዱን ትዝ ይለኛል።

ርግጥ ነው፣ በዴሞክራሲ እሳቤ መሠረት የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው። ምክንያቱም በዴሞክራሲ እሳቤ መንግሥት የሥልጣን ባለቤት የሚሆነው በሕዝብ ሲመረጥ ብቻ ነው። ነገር ግን ሕዝብ መንግሥትን በካርድ በመምረጡ ብቻ የሥልጣን ባለቤት ሆኗል ለማለት አያስችልም። ምክንያቱም በካርዱ መርጦ የሰየመው መንግሥት ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ ለሕዝብ ምን ሠራ፤ ከሕዝብ ጋርስ እንዴት ሠራ፤… የሚሉ ጉዳዮች ተያይዘው መታየት ይኖርባቸዋል።

በተለይ ሕዝብ መርጦ መንግሥት ያደረገው አካል ምን ያህል ሕዝብን ማዕከል አድርጎና አሳትፎ ሠራ፤ ምንስ አስገኘ፤ የሚሉት ጉዳዮች በወጉ መታየት ያለባቸው ናቸው። ለምን ቢባል፣ በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ ያለምርጫም ሆነ በምርጫ ሥልጣን ላይ የኖሩ ሥርዓቶች አንድም ሕዝብን ያገለለ አካሄዳቸው፤ ሁለተኛም ሕዝብን ባይተዋር ያደረገ የውሳኔም የተጠቃሚነትም መስመራቸው የገፉት ሕዝብ እንዲገፋቸው፤ ያራቁት ሕዝብ እንዲያርቃቸው አድርጓል።

የ2010ሩም ለውጥ የዚህ አንዱ መገለጫ መሆኑ እሙን ነው። በዚህ መነሻነትም ነው፣ ከለውጡ ማግስት የተወሰዱና እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችም ይሄንኑ ጉዳይ ተገንዝቦ ለሕዝብ መብትና ጥቅም ምላሽ መስጠት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው። በተለይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እውን ከማድረግ፣ እንዲሁም የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ተቃኝተው እየተፈጸሙ ያሉ ናቸው።

እነዚህ ደግሞ ያለ ምክንያት የተፈጸሙ አይደሉም። ይልቁንም አሁን ሀገር እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ፣ በፓርቲው ፕሮግራም ላይ፣ “ፓርቲያችን ለትብብርና መግባባት ትኩረት የሚሰጥ የሥልጣን ክፍፍልና ውክልና፣ እራስን በራስ የማስተዳደር ያልተማከለ ፌዴራላዊ ሥርዓት እና ታላቅ ቅንጅትን መሠረት ያደረገ የጋራ አስተዳደር፤ እንዲሁም ትንሽ ቁጥር ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች መብት በልዩ ሁኔታ የሚያስከብር አካታችና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ በማድረግ በሂደት በሃሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ይታገላል።” ሲል ባሰፈረው እና በምርጫው ዋዜማ በገባው ቃል መሠረት፤ ሕዝብም ይሄንኑ ተማምኖ የመረጠው መሆኑን ታላሚ በማድረግ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በማህበራዊውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውና ሌሎችም መስኮች በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም፤ ከበዙት ተግባራት ውስጥ የተወሰኑትን ለማሳያነት ለመጥቀስ ወደድሁ፡፡ የመጀመሪያው ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዳይጠቀሙ ሲያደርጉ የቆዩ አሳሪ ሕጎችን የማረም፣ የመቀየርና አዳዲስ ዴሞክራሲን የሚያጎለብቱ ሕጎችን የማውጣት ርምጃ ነው፡፡

በዚህ መልኩ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ እንዲከለስ/እንዲሻሻል እና የሚዲያ ፖሊሲ እንዲወጣ ተደርጓል። የሲቪል ማህበራትን የሚመለከተው አዋጅ፣ የፀረ ሽብር አዋጅ እና ሌሎችም ዴሞክራሲን በሚያጎለብት መልኩ ተቃኝተው ተሻሽለዋል፡፡ አዳዲስ ሕጎች፣ አዋጅና ፖሊሲዎችም ወጥተው ወደ ትግበራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ እነዚህን ሕጎች በሙላት ለማስፈጸም አቅም ያላቸው ተቋማት እንዲፈጠሩ ያደረገ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፤ በተለይም የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማት ላይ የተወሰደው የሪፎርም ርምጃ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው መሬት መርገጥ መጀመሩን ያስመሰከሩ ነበሩ፡፡ በዚህም መጠናከር የሚገባቸው እንዲጠናከሩ፤ መዋሃድ የሚገባቸው እንዲዋሃዱ፤ በአዲስ መልኩ እንዲደራጁ ያለባቸውም እንደ አዲስ እንዲፈጠሩ ተደርጓል፡፡

ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በዕንባ ጠባቂ ተቋም ላይ የተከናወነው የሪፎርምና ማሻሻያ ተቋማቱ ከፓርቲ መጠቀሚያነት ወደ ሕዝብ ድምጽነት እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ ላይ የተሠራው ሥራም፣ ቦርዱ ትክክለኛ የዴሞክራሲ አውድ ማጽኛ ሆኖ እንዲገለጽ ያደረጉትን በርካታ ተግባራት እንዲፈጽም አስችሎታል፡፡ እንደ ተቋምም ተዓማኒነትን እንዲያተርፍ፤ ሙገሳንም እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

በዚህ መልኩ አሳሪ ሕጎች ከታረሙ እና የዴሞክራሲ ተቋማት በተልዕኳቸው ገጽ እንዲገለጡ ከተደረገ በኋላ፤ በእነዚህ ሕጎችና ተቋማት ታግዞ የሕዝቦች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለስ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውም እንዲተገበሩ ወደማድረግ ተሸጋገረ። በዚህም በአንድ በኩል ዜጎች በነፃነት የመምረጥና የመመረጥ መብቶቻቸውን በተግባር ማሳየት የቻሉበትን ነፃ ምርጫ ማካሄድ ተችሏል፤ በሌላም በኩል ራስን በራስ የማስተዳደርና የመልማት የዘመናት መሻትና ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በተለይ የዜጎች የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን አምቆ የያዘው እና ለዘመናት ታፍኖ የኖረው ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ከለውጡ ማግስት በትኩረት የተሠራበት ነበር፡፡ ይሄ በመሆኑም ነው ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ የፌዴራል አወቃቀር በዘጠኝ ክልል ተወስኖ የቆየበትን ታሪክ ሰብሮ ወደ 12 ክልል ከፍ እንዲል ያስቻለ ተግባር መከወን የተቻለው፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ሊነሳ የሚገባው እና የለውጡ ማግሥት አንኳር ርምጃ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የኖሩበትን የአጋርና አውራ የፖለቲካ መዋቅር መስበር መቻሉ ነው፡፡ ምክንያቱም የአጋር እና አውራ ፓርቲ እሳቤ፣ ዜጎች በሀገራቸውም ሆነ በራሳቸው ጉዳይ መወሰን የማይችሉበትን፤ ይልቁንም የእነሱን ጉዳይ እነሱ ሳይሆኑ ሌሎች አቡክተውና ጋግረው የሚያቀርቡላቸውን አካሄድ አንግሶ የኖረ ነበር፡፡

በመሆኑም ከለውጡ ማግስት የተወሰደው የአጋርና አውራ የፓርቲ መስመርን ሰብሮ፤ ሁሉም በራሱና በሀገሩ ጉዳይ ከዳር ተመልካችነት ወደ ባለድርሻነት እንዲሸጋገር ያደረገ ሆኗል፡፡ አጋር ሆነው የመወሰንም፣ የሥልጣን ባለቤትነትንም መብት ተነፍገው የኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፤ ወደ መሃል መጥተው የሥልጣን ባለቤትም፤ ውሳኔ ሰጪም የሆኑበትን አውድ ፈጥሯል፡፡

ከኢህአዲጋዊ የዳር እና የመሃል ፖለቲካ እሳቤ፤ ወደ ብልጽግናው ሁሉን አቀፍና አካታች ሀገራዊ ፓርቲ እሳቤ ሽግግር መደረጉ፤ ሕዝቦች በቁጥር አንሶ መገኘት፣ አርብቶ አደርነት፣ ወይም ሌላ ምክንያት ሳይገድባቸው በሚገባቸው ልክ እንዲወከሉ፤ በሚገባቸው ቦታ እንዲቀመጡ፤ በሚገባቸው ልክ እንዲጠቀሙ (ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ)፤… የማህበራዊውንም፣ የኢኮኖሚውንም፣ የፖለቲካው ንም ምህዳር አደላድሎላቸዋል፡፡

ከእነዚህና መሰል አንኳር ተግባራት ባሻገር እንደ ሀገርም አዲስ ልምምድ፣ እንደ አህጉርም መልካም አርዓያነት ያለው እና ዴሞክራሲ ከብያኔ ባሻገር በተግባር መግለጥ መሆኑን ያሳየ፤ የፓርቲን ሳይሆን የሕዝብና ሀገርን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገው የአካታችነት ፖለቲካ መሥመር ተጀምሯል፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ የፖለቲካ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ይከተላል ቢባልም፤ ለዘመናት ግን የዴሞክራሲ ልምምዱ ስላልነበር ቃልና ተግባር ተራርቀው መኖራቸውን ልብ ይሏል፡፡

ከ2010ሩ ለውጥ ማግስት ግን መንግሥት ይሄንን አካሄድ መቀየር እና የፖለቲካ አካታችነትን በተግባር ለመግለጥ የሄደበት ርቀት ሕዝባዊነቱን ያሳየበት እና ዴሞክራሲን ለማጽናት ያለውን ቁርጠኝነት ያስመሰከረበት ብቻ ሳይሆን፤ ይሄ አካሄድና ተግባሩ በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው። ምክንያቱም፣ ተግባሩ የፖለቲካ ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሥርዓቱንም ከዳር ተመልካችነት ወደ መሃል ያመጣ፤ ከአናሳነት እሳቤና መገፋት ወደ እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መርህ መለወጥ አስችሏል፡፡

በመሠረቱ የዴሞክራሲ እሳቤ፣ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ ነው ይበል እንጂ፡፡ በዓለም የዴሞክራሲ ታሪክ ውስጥ ሕዝብ በራሱ ብዙኃን እና አናሳ በሚል የተፈረጀበት ነው፡፡ በዚህም የዴሞክራሲ እሳቤ፣ ብዙኃኑን ወደ መሪነት በማምጣት የአናሳዎችን መብት አክብረውና አስከብረው እንዲያስተዳደሩ የሚፈቅድ ነው፡፡ ለዚህም ነው በተለያየ ሁኔታና አግባብ የብዙኃኑ ሃሳብ ገዢ ሆኖ፣ የአናሳዎች ሃሳብ ለብዙኃኑ ሃሳብ ተገዢ እንዲሆን፣ ግን መብቶቻቸው እንዳይጨፈለቁ ጥበቃ ይደረግላቸዋል ሲባል የሚደመጠው፡፡

በኢትዮጵያም ሲሆን የኖረው ይኸው ነበር። አቅም ያለው ሲገዛ፤ ጊዜያዊ ድምጽ ያገኘ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ለብቻው ሲዘውር፤ የተቀረው አናሳ ተብሎ የዳር ተመልካች የሆኑት፤ ሌላው ቀርቶ ውክልና አለኝ የሚለው ሕዝብ ሳይቀር መብትና ጥቅሞቹ፤ ፍላጎትና መሻቶቹ የማይጨበጡ ሆነውበት ቆይተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሕግ የታገዘ አሠራር የተዘረጋለት ሲሆን፤ በተለይ በምርጫ አብላጫ ድምጽ ያለው ፓርቲ መንግሥት የመመስረት መብት መጎናጸፍ መቻሉ ለዚህ እንደ ትልቅ እድል ሆኖ ቆይቷል፡፡

የለውጡ ማግሥት መንገድ ታዲያ ይሄንን በሕግ እና የፖለቲካ ፍልስፍና ጭምር እውቅና የተሰጠውን የዴሞክራሲ ሥርዓትን አቀጫጭ አካሄድ ከመሰረቱ ተረድቶ እየለወጠ ያለ ነው።፡ ለምሳሌ፣ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ በማግኘት መንግሥት መመስረት የሚችልበትን ሙሉ ዕድል አግኝቷል፡፡ ይሄንንም ሕገ መንግሥታዊ መብት ተጠቅሞ መንግሥት መሥርቶና ካቢኔውንም አዋቅሮ ሀገር እየመራ ነው፡፡

ፓርቲውም ዴሞክራሲ ማለት የሕዝብ አስተዳደር ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ሕዝቦች ያለ ልዩነት በመንግሥት ውስጥ ተካትተው ለሀገርና ሕዝብ በአቅማቸው ልክ መሥራት እንዳለባቸው ማረጋገጥ መቻልን የግድ እንደሚል ቀድሞ ተገንዝቦ በዛው ልክ እየሠራ ይገኛል፡፡ የዚህ ዐብይ ማሳያው ደግሞ፣ ፓርቲው በመንግሥት ምሥረታው ሂደት በምርጫ ያሸነፋቸውን የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጭምር በሚኒስትርነት (በካቢኔ አባላነት) ማካተቱ ነው፡፡

ይሄን መሰል አካሄድ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እንግዳ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የትኛውም ገዢ ፓርቲ ከፓርቲው አባላት ውጭ ያለን ሰው የመንግሥት አስፈጻሚነት ቦታ ላይ ማስቀመጥ አልተለመደም፡፡ ብልጽግና ግን እንደ መንግሥት ቦታውን ሲይዝ ከአንድም ሦስት የአስፈጻሚነት(ሚኒስትርነት) ቦታዎች በተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እንዲያዝ አድርጓል፡፡

ይኸው በፌዴራል መንግሥቱ የታየው የአካታችነት ተግባር ታዲያ በክልል መንግሥታት መዋቅር ውስጥም ተደግሟል፡፡ በዚህም አንድ ፓርቲ ምንም እንኳን በምርጫ ቢሸነፍም፣ ያ ፓርቲ የወከለው አካል፤ ቁጥሩ ያነሰ ቢሆንም የመረጠው ሕዝብ በመኖሩ፤ ያ ፓርቲ የወከለውም ሆነ ፓርቲውን የመረጠው ሕዝብ ዋጋ ሊያጣ አይገባውም። ብልጽግናም እንደ መንግሥት ይሄንኑ ታሳቢ በማድረግ እና በምርጫ ወቅት የገባውን ዴሞክራሲን የማስረጽ ቃል በተግባር ለመግለጥ ያስቻለውን ተግባር ፈፅሟል ለማለት ይቻላል፡፡

ይሄ ደግሞ የፓርቲ አመራሮቹ በካቢኔ ስብሰባ ላይ ጭምር ያላቸውን ሃሳብና አስተያየት ከመሰንዘር ባለፈ፤ አጋጣሚውን ተጠቅመው ያላቸውን እውቀትና አቅም ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም የሚያውሉበትን ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ከሰሞኑም የአስፈጻሚ አካላት ሹመት ላይ የታየውም ከለውጡ ማግስት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች፣ ከፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት ባሻገር ያለውን የሕዝብ እና የሀገር ጥቅም የማስቀደም ከፍ ያለ ልዕልና ነው፡፡

በተለይ በሰሞኑ ሹመት የታየው ተጨባጭ እውነት፣ ብልጽግና ፓርቲ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ብቻ ሳይሆን፤ አቅም እና ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ማናቸውም ግለሰቦች ቀዳሚ አጀንዳቸው ሀገርና ሕዝብ እስከሆነ ድረስ በየትኛውም የሥልጣን ቦታ ላይ መጥተው መሥራት እንዲችሉ ዕድል የተፈጠረ መሆኑን ነው፡፡

ምክንያቱም፣ በተለይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እና በጤና ሚኒስትርነት የተሾሙት ሁለቱ ሚኒስትሮች፤ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደሉም፡፡ ይልቁንም በየተመደቡበት የሥራ መስክ የካበተ ልምድ (በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር) ያላቸው እና ተገቢው የትምህርት ዝግጅትም ያላቸው ናቸው፡፡

ይሄ ደግሞ እውቀትና ልምዳቸውን ተጠቅመው ለሀገር የሚበጅ፣ ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራን ለመሥራት የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ብልጽግና ፓርቲም እንደ መንግሥት ይሄንን ማድረጉ ከፓርቲው ጥቅምና ፍላጎት ባሻገር ለሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት መቆሙን በተግባር የገለጠበት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለሕዝብ የመቆምን፣ ለሀገር የሚጠቅም ነገር እንዲከወን መሻትን ብቻ ሳይሆን፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ማበብ፤ ለሕዝቦች ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እውን መሆን ከፍ ያለ አበርክቶ አለው፡፡

በርግጥም፣ “ፓርቲያችን የሀገረ መንግሥት ግንባታችን ኅብረ ሀገራዊ ማንነትን የተላበሰና ብዝሀነትን የሚያንጸባርቅ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፡፡”፣ ሲል በፕሮግራሙ ላይ ያሰፈረው ብልጽግና ፓርቲ፤ ከፓርቲው ውጭ ያሉ አምስት የካቢኔ አባላትን (ሚኒስትሮችን) በማካተት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በብዝሀነት ደምቀው እንዲዘልቁ የሚያስችለውን መንግሥታዊ ኃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑ አሳይቷል።ቃሉን በተግባር እየገለጠ መሆኑንም ከዚህ አካሄዱ መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህም በላይ ዴሞክራሲ ለአንድ ሀገር ጠንካራ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳርን ለመፍጠር ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ፤ በተለይ ለሚፈለገው ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን ብዝሀ ሃሳብ በእጅጉ አስፈላጊ እንደመሆኑ፤ በጅምር ደረጃ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ብዝሀነትን ማስተናገድ የሚችል መሠረት እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ ብልጽግናም ከፓርቲ ባሻገር ያለውን ሀገርና ሕዝብ ተመልክቶ በዚህ መልኩ ሁሉን አቀፍ ብዝሀነትን በዴሞክራሲ አውድ ውስጥ ለመግለጥ እያደረገ ያለው ሥራ ለሀገራችን ኩራት፤ ለአህጉራችንም አርአያነት ያለው ተግባር በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል!

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You