በቅርቡ የተቋቋመው ሸገር ከተማ በስፖርቱ ዘርፍ የተለያዩ ክለቦችን በማቋቋም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪ ከመሆን ባለፈ ወደ ቻምፒዮንነት እየተሸጋገረ ይገኛል። ይህንንም ከየካቲት 16/2016 ጀምሮ ለተከታታይ አስራ አንድ ቀናት በባቱ ከተማ በተካሄደው የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ በማጠናቀቅ አስመስክሯል።
ለስድስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ውድድር ለዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ሲካሄድ ከመላው ኦሮሚያ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ትምህርት ቤቶች በበርካታ የስፖርት አይነቶች ተፎካክረዋል።
የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በክልሉ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ ቆይቷል። ዘንድሮ ግን በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እንዲሁም በኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አማካኝነት በአዲስ መልክ ዳግም ሊጀመር ችሏል።
ውድድሩ በትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና የትምህርት ቤቶችን ስፖርት ለማሳደግ የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህም ክልሉን በሀገር አቀፍ ውድድሮች ከመወከል ባለፈ ሀገርን በታላላቅ የስፖርት መድረኮች የሚያስጠሩ ጠንካራ ስፖርተኞች ማፍራትን ዓላማው እንዳደረገ ተጠቁሟል።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ሰቦቃ፣ ሀገራችን የበርካታ ወጣቶች ሀገር መሆኗን ጠቁመው ትምህርት ቤቶች ወጣቶች እውቀት ብቻ የሚሸምቱባቸው ሳይሆኑ ጠንካራ ስፖርተኞች የሚፈሩባቸው ጭምር መሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም በትምህርት ቤቶች ስፖርት ተጠናክሮ መቀጠሉ ለጤናማ አካልና ለብሩህ አእምሮ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ ወጣቶች በትምህርታቸው ጠንክረው እንዲወጡ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።
የውድድሩ ዓላማ በዋናነት ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስፖርት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማነቃቃት ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር የክልሉን ስፖርት ለማሳደግና ለማጠናከር እንደሚረዳም ገልፀዋል።
ከክልሉ ባሻገር ወደፊት ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም መድረኮች የሚያስጠሩ ጠንካራ ስፖርተኞች መፍለቂያቸው ትምህርት ቤቶች እንደሆኑ በማመን የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ስፖርት በስተቀር በሌሎች ስፖርቶች እንደ አፍሪካም እንደ ዓለምም ተፎካካሪ መሆን እየቻለች አይደለም። ይህን ለመለወጥ የሀገሪቱ ስፖርት ተስፋ ያለው በትምህርት ቤቶች ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።
እንደ አቶ ማቲዎስ ገለፃ፣ ስፖርትን ለማሳደግና ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ለማድረግ ትምህርት ቤቶች ላይ ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ በዚህም መሠረት የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በቀደሙት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ አትሌቶች ሀገር ማስጠራት የቻሉት መነሻቸውን ከትምህርት ቤቶች ስፖርት በማድረግ ነው፡፡
አሁንም ሀገርን የሚያስጠሩ ኮከብ ስፖርተኞችን በብዛት ማፍራት ከተፈለገ የትምህርት ቤቶች ስፖርት ላይ ትኩተር አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የክልሉ የስፖርት ቢሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት የተለያዩ ስምምነቶችን ፈፅሟል፡፡ ይህም የክልሉን ስፖርት ከማጠናከር ባለፈ እንደ ሀገር ጠንካራ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
‹‹ትምህርት ቤቶች የእውቀት ብቻ ሳይሆን የጠንካራ ስፖርተኞችም ምንጭ ናቸው›› ያሉት አቶ ማቲዎስ፣ ስለዚህም ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በተለያዩ ስፖርቶች ብቃት ያላቸው ታዳጊዎች አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩ ሲሆን ወደ ፊትም በትምህርት ቤቶች ስፖርት ላይ ሰፋፊ ስራዎችን ለመሥራት ቁርጠኝነቱ እንዳለ አክለዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም