ቡና የኢትዮጵያ ምድር ከሚበቅሉ የግብርና ምርቶች መካከል አንዱ ሲሆን ኢኮኖሚውን በመደገፍ ረገድም ቀዳሚውን ሥፍራ ይዟል። ከ35 እስከ 40 በመቶ ያህሉ የሀገሪቷ ገቢ ከቡና የሚገኝ ሲሆን፤ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ሕይወትም ቡናን መሠረት ያደረገ ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችው ቡና የሀገሪቱ አንጡራ ሀብት እንደመሆኑ ከልማቱ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ቡና ሰብሳቢዎች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ቡናው ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ትልቅ ድርሻ አላቸው።
ከእነዚህም መካከል የዕለቱ እንግዳችን በቡና ላኪነት ረዘም ያሉ ዓመታትን ያሳለፉና የቡና ንግድ ከአያታቸው ወደ አባታቸው ተላልፎ እርሳቸው ደግሞ ከወላጅ አባታቸው በመረከብ ሶስተኛ ትውልድ በመሆን እየሠሩት ያለ ሥራ ነው። እንግዳችን አቶ አብደላ አቡበከር የአብደላ ባገርሽ ወይም የኤስኤ ባገርሽ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ድርጅቱ የቡና ንግድን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ በቅብብሎሽ የመጣና ላለፉት 75 ዓመታት በቡና ንግድ ሥራ ቆይቷል።
ሶስተኛ ትውልድ ሆነው ድርጅቱን የሚመሩት አቶ አብደላ እንዳሉት፤ በቡና ንግድ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ‹‹አብደላ ባገርሽ›› ሲጀመር ጀምሮ ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ይሰራ ነበር። በአያታቸው የተጀመረው የቡና ንግድ በዋናነት ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ ሲሆን፤ ይህንኑ ሥራ የዛሬ 30 ዓመት አካባቢ እንደ አባታቸው ሁሉ እርሳቸውም ከወላጅ አባታቸው ተረክበዋል። ድርጅቱ ሥራውን ሲጀመር ጀምሮ ቡናን ኤክስፖርት በማድረግ የጀመረ ሲሆን፤ በሀገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ቡናውን ሰብስበው ከሚያቀርቡ አቅራቢ ድርጅቶች በመረከብ ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ።
አቶ አብደላ፤ ድርጅቱ ማንኛውም ቡና ላኪ እንደሚሰራው ሥራ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጣውን ቡና ከአቅራቢዎች ይረከባል። የተረከበውን ቡናም አዲስ አበባና ድሬዳዋ በሚገኙ የቡና ማበጠሪያ ፋብሪካዎች አበጥሮ ለውጭ ገበያ በሚመጥን መልኩ በማዘጋጀት ለዓለም ገበያ ሲልክ ቆይቷል። አሁንም እየላከ ይገኛል። የሀረር ቡና ከድሬዳዋ በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ የሚላክ በመሆኑ ድርጅቱ ድሬዳዋ ላይ በሚገኘው የቡና ማጠቢያ ቡናውን አዘጋጅቶ ኤክስፖርት ያደርጋል ይላሉ።
በተመሳሳይ ከሌሎች አካባቢዎች የሚረከበውን ቡና አዲስ አበባ በሚገኘው ማበጠሪያ ጣቢያ አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ ዝግጁ ያደርጋል፤ ይልካል። በቀጣይም መንግሥት የያዘው አቅጣጫ የኤክስፖርት ሥራ በተለያዩ ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎች መሰራት የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አብደላ፤ ይህም ለቡና ላኪው ጥሩ አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነ ነው ያስረዱት። በዋናነት ኤክስፖርተሩ በተለያዩ አካባቢዎች ቡና ማበጠሪያ ማሽን በፈለገው አካባቢ መትከል እንዲችል ያደርገዋል። ይህም የአንድ አካባቢን ቡና በልዩ ሁኔታ የማዘጋጀት ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ሲያስረዱ፤ ኤክስፖርተሩ በፈለገው አካባቢ ማበጠሪያ ጣቢያውን ተክሎ የፈለገውን አካባቢ ቡና አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል በማለት ነው።
ድርጅቱ ቡናን ከአቅራቢዎች ብቻ ሰብስቦ ከመላክ ባለፈ በአሁን ወቅት ቡና ወደ ማምረት ተሸጋግሯል የሚሉት አቶ አብደላ፤ ለዚህም ደቡብ ምዕራብ፣ ከፋ፣ ቤንች ማጂና ጉጂ አካባቢን ምርጫው በማድረግ የቡና እርሻዎቹን በማስፋት ቡና እያለማ ይገኛል። ቡናን ከአምራቹ ገዝቶና ከአቅራቢዎች ሰብስቦ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ አምርቶና አዘጋጅቶ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እጅግ አዋጭ መሆኑን ያነሱት አቶ አብደላ፤ ወደ ምርት የገቡበት ምክንያትም ቡናን በጥራት አምርቶ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ነው ይላሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ በተለያዩ አካባቢዎች ቡና እያለሙ ሲሆን፤ የቡና እርሻዎች ሰፋፊ አይደሉም። ያም ቢሆን ታዲያ የጥራት ደረጃቸው ከፍ ያለ ነው። አነስተኛ የሆነ የእርሻ ቦታ ስፔሻሊቲ ወይም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ለማምረት አመቺ ነው። በመሆኑም በመጠን ያነሰ ነገር ግን ከፍተኛ ገቢ ማምጣት የሚችል ጥራት ያለው ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ነው። ይህም ገዢ ሀገራት የሚጠይቁትን መስፈርት ለማሟላት አመቺ ሲሆን፤ ገዢ ሀገራት በተለይም ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር ለመፍጠር የቡናውን ዱካ ተከትለው መነሻና መድረሻውን አውቀው መግዛት ይፈልጋሉ።
በቅርቡም የአውሮፓ ኅብረት አዲስ ባወጣው መመሪያ መሠረት ዓለም አቀፍ ቡና ገዢዎች የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙት ከደን ጭፍጨፋ ነፃ በሆነ መንገድ የተመረተ ቡና ብቻ እንደሆነና ከዛ ውጭ የሆነ ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ እንደማይቻል ያነሱት አቶ አብደላ፤ ድርጅታቸውም ይህንኑ በመገንዘብ ዓለም አቀፍ ገዢዎች የሚጠይቁትን መስፈርት ማሟላት እንደሚችል ነው ያስረዱት። ድርጅቱ ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ በቡና ላኪነት የቆየ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ቡና ገዢ ሀገራት የሚፈልጉትን የጥራት መለኪያዎች የማወቅ ዕድል አግኝተዋል። ስለሆነም ዓለም አቀፍ ገዢዎች በሚፈልጉት መስፈርት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ነው ያሉት።
በአሁን ወቅትም የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን አዲስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የሚችል ሲሆን፤ ድርጅቱ በተለይም ቡና በሚያመርትበት አካባቢ ደን እንዳይጨፈጨፍ ይከላከላል። የአካባቢውን የአየር ንብረት ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነውን ዛፍ የመትከል ሥራም አጠናክሮ ይሠራል። በመሆኑም ከደን ጭፍጨፋ ነፃ በሆነ አካባቢ ያመረተውን የቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚችል እንደሆነና የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው አዲስ መመሪያ ለድርጅቱ ስጋት አለመሆኑን አመላክተዋል።
ድርጅቱ ጥሬ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ ከመላክ ባሻገር እሴት በመጨመርም እየሠራ መሆኑን ያነሱት አቶ አብደላ፤ በአሁን ወቅት የተቆላ ቡናም ለዓለም ገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹የአብደላ ባገርሽ›› እህት ኩባንያ በሆነው ‹‹ተራራ ኮፊ›› በተሰኘ የንግድ ስም የተቆላ ቡና ወደ ውጭ ገበያ እየላኩ እንደሆነ አጫውተውናል። በቡና ንግድ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ድርጅት እንደመሆኑ በቀጣይም በእሴት ጭምር ቀሪ ሥራዎችን በመሥራት ከምርት እስከ ሲኒ የማድረስ ዕቅድ ያላቸው መሆኑን አቶ አብደላ አስረድተዋል።
አቶ አብደላ እንዳሉት፤ የቡና ሥራ ከልማቱ ጀምሮ ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል የሚሳተፍበትና ረዥም ሰንሰለት ያለው ነው። በቡና ንግድ ሂደት ውስጥ ያለው ሰንሰለት ከቀደመው ጊዜ ይልቅ አሁን ላይ የተሻለ ነው። ከዚህ ቀደም ቡና ለውጭ ገበያ ይቀርብ የነበረው በምርት ገበያ አገበያይነት በጨረታ ነበር። ይህም የቡናውን ጥራት ከመጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ክፍተት የነበረበት ነው። ነገር ግን አሁን ላይ የተለያዩ የገበያ አምራቾችን በመምጣታቸው አዋጭ በሆነ መንገድ እንዲሁም አማራጭ ባለው የገበያ ሰንሰለት ግብይቱ ይፈጸማል። ከዚህም ባለፈ ቡና ላኪዎች በሀገሪቱ ከሚገኙ ቡና አቅራቢዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ እየቀረበ ይገኛል።
በተለይም ዓለም አቀፍ ገዢዎች የሚጠይቁትን መስፈርት ለማሟላት እርሻው ላይ የሚሠራው ሥራ ብቻ በቂ አለመሆኑን አንስተው፤ አቅራቢዎች የሚያቀርቡት ቡናም ዱካውን የተከተለና ጥራቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ነው ያመላከቱት። ለዚህም ድርጅታቸው በቡና ጥራት ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል። በተለይም በቡና ማጠቢያ እና ማበጠሪያ ጣቢያዎቻቸው ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ቡናን እንዴት በጥራት ማዘጋጀት እንዳለባቸው አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ ያደርጋል። የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻርም ከአንድ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
‹‹ሀገሪቷ ከቡና የምታገኘውን ጥቅም በሚገባት ልክ ማግኘት እንድትችል ጥራት ላይ መሥራት የግድ ነው›› በማለት ያስረዱት አቶ አብደላ፤ ድርጅታቸው ዘርፉ ላይ እንደመቆየቱ የቡናን ባህሪ አውቀውና ተረድተው በጥራት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል ነው ያሉት። በተለይም ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ስፔሻሊቲ ወይም ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ ሲሆን፤ እሴት በመጨመር ረገድም ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ በጥሬው ከሚልኩት ቡና በተጨማሪ ‹‹ተራራ ኮፊ›› የተባለውን ቡና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ቡናን በጥሬው ለውጭ ገበያ ከመላክ ይልቅ እሴት ተጨምሮበት ቢላክ የተሻለ ገቢ ማስገኘት የሚችልና ብዙ ሊሠራበት እንደሚገባ ያነሱት አቶ አብደላ፤ ቡና አምራች ሀገራት በሙሉ ቡናቸውን በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምረው መላክ ላይ ትኩረት የሚያደርጉትም በዚሁ ምክንያት እንደሆነና ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መሆኑንም ገልጸዋል። ድርጅታቸው ትኩረት አድርጎ እየሠራበት ሲሆን፤ በተለይም የተቆላ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተራራ ኮፊ ላለፉት አራት ዓመታት ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘ ነው የገለጹት።
የማምረት አቅምን በተመለከተም ድርጅቱ በቂ የማምረት አቅም እንዳለው የጠቀሱት አቶ አብደላ፤ ድርጅታቸው የሚያመርተውን የተቆላና ጥሬ ቡና በተለያዩ የዓለም ሀገራት ተደራሽ እያደረገ እንደሆነና በውጭ ምንዛሪ ግኝት የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁን ወቅት በቡና ሥራ ውስጥ እያለፉ ያሉ ተዋናዮች በርካታ ቁጥር ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ውድድሩ ከባድ መሆኑን ያነሱት አቶ አብደላ፤ ያም ቢሆን ታዲያ ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል ከዘርፉ ተዋናዮች ብዙ ይጠበቃል ባይ ናቸው። ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ትልቅ ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ እንደመሆኑ መንግሥት ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ከእርሻ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ያሉትን የቡና ችግሮች በመለየት በኃላፊነት ይዘው መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
‹‹በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ ተዋንያኖች ትልቁ ሥራችን መሆን ያለበት ተወዳድረን ቡናውን ለዓለም ገበያ ማቅረብና የተሻለ ዋጋ ማግኘት ነው›› ያሉት አቶ አብደላ፤ በዘርፉ ያሉት ተዋናዮች የሚያገኙት ድምር ውጤት በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ በጎ ዐሻራውን የሚያሳርፍ እንደሆነ ጽኑ እምነት አላቸው።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ድርጅቱ በተለይም ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል የሚሉት አቶ አብደላ፤ ‹‹አርሶ አደር ጋር መሄድ እንግዳ መሆን ነው›› በማለት አርሶ አደሩ ጋር በእንግድነት ሄደው ምርት ማምረት ሲችሉና ጥቅም ሲያገኙ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጥቅም መጠበቅ ግዴታ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ ኃላፊነትም ብዙ መገለጫዎች ሲኖሩት፤ ለአብነትም ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ፣ ትምህርት ቤትና መንገድ በመገንባት እና ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም ይገለጻል። ከዚህ ባለፈም በአካባቢው የሚገኙ ቡና አምራቾችን ቡና በጥሩ ዋጋ በመረከብ አርሶ አደሩ ጥሩ ገቢ እንዲያገኝ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች በየጊዜው የሚታዩ ናቸው ብለዋል።
‹‹አሁን ላይ ትላልቅ ቢዝነሶች የቢዝነስ ሥራቸውን የሚያስተዋውቁት ማህበራዊ ኃላፊነት ላይ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ነው›› የሚሉት አቶ አብደላ፤ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሰው ቢዝነስ በትክክል ተሠራ የሚባለው ማህበራዊ ኃላፊነት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ነው ይላሉ። ይህም ለጊዜው ወጪ የሚያስወጣ ቢመስልም የሚያስገኘው ጥቅም ከወጪው በላይ መሆኑን አስረድተዋል። ማህበራዊ ኃላፊነቶችን በአግባቡ መወጣት የቡና ገዢ ሀገራትን ጥያቄ ለመመለስ ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን በመግለጽ፤ ማንኛውም ቢዝነስ ማህበራዊ ኃላፊነትን ማዕከል አድርጎ መሰራት እንዳለበትና መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ እንደሆነም አመላክተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም