አሜሪካ ከ28 ዓመታት በኋላ በሶማሊያ የነበረውን ኤምባሲዋን በድጋሚ ከፍታለች፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ፣ የሶማሊያ ሰላምና ፀጥታ በየጊዜው እያሳየው ያለው መሻሻል ለውሳኔው ምክንያት እንደሆነ አስታውቋል፡፡ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ ኤምባሲውን እንደሚመሩትም ታውቋል፡፡
የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ሂዘር ኖሬት፣ አሜሪካ እ.አ.አ በ2013 ለሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት እውቅና መስጠቷን አስታውሰው፣ ኤምባሲውን ለመክፈት የተወሰነው ውሳኔ አሜሪካ በሶማሊያ የምታደርጋቸውን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች መደበኛና ተቋማዊ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ውሳኔው አሜሪካ የሁለቱም አገራት ፍላጎት የሆኑትን ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈንና ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ለማምጣት ያላትን ቁርጠኝነት ያመለክታል፡፡ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶና ቡድናቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በትጋት ይሰራሉ›› ብለዋል፡፡
እ.አ.አ በ1991 የሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲጀመር አሜሪካ በሶማሊያ ኤምባሲዋ የነበሩ ሰራተኞችን አስወጥታ ኤምባሲውን መዝጋቷ ይታወሳል፡፡ በቅርብ ዓመታትም የሶማሊያ ጉዳዮችን የሚከታተለው የአሜሪካ የዲፕሎማሲ ቡድን ናይሮቢ ውስጥ ከሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ ጋር በትብብር ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ራሱን የአልሸባብ የምስራቅ አፍሪካ ክንፍ አድርጎ የሚቆጥረውና አል-ሸባብ የተባለው አሸባሪ ቡድን እ.አ.አ በ2011 ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ቢባረርም አሁንም በሌሎች አካባቢዎች ይዞታዎች አሉት፡፡ ሞቃዲሾን ጨምሮ በሌሎች ጥቂት አካባቢዎች አንፃራዊ መረጋጋት መታየቱን ተከትሎ በውጭ የሚገኙ ሶማሊያውያን በአገራቸው የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ የዓለም ባንክ በበኩሉ ባለፈው መስከረም ከ30 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ ነው የተባለ የ80 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ጦር ሰሞኑን በአልሸባብ ላይ በወሰደው እርምጃ፣ ዘጠኝ የቡድኑን ታጣቂዎች መግደሉን ገልጿል፡፡ ታጣቂዎቹ የተገደሉት በአየር ጥቃት እንደሆነና በዘመቻው ንፁሃን እንዳልተጎዱ የጦሩ የአፍሪካ ተልዕኮ ቅርንጫፍ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ከተሾሙ ወዲህ የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ የሚወስደው ወታደራዊ እርምጃ ጨምሯል፡፡ ፕሬዝደንት ትራምፕ የአሜሪካ ጦር በአልሸባብ ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንደሚያጠናክሩ ከሹመታቸው ጥቂት ቀናት በኋላ ተናግረው ነበር፡፡
አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ 500 ወታደሮችና ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ያሏት ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የተሰጠውን የሶማሊያ ፌደራላዊ መንግሥት በመደገፍ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን እየፈፀመች ትገኛለች፡፡ እየተገባደደ ባለው 2018 ብቻ ከ37 በላይ የአየር ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች፡፡
አሜሪካ በሶማሊያ የነበረውን ኤምባሲዋን በድጋሚ መክፈቷና በአልሸባብ ቡድን ላይ የምትፈፅመውን የአየር ላይ ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏ ለቀጣናው ሰላም መሻሻል አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡ የመረጃው ምንጮች ፡ ‹‹አልጀዚራ›› እና ‹‹ቢቢሲ›› ናቸው፡፡