“የምክክሩ ዓላማ በመደማመጥና በውይይት ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበትን አውድ መፍጠር ነው”ብሌን ገብረ መድህን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

የዛሬ የዘመን እንግዳ ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን ይባላሉ። ትውልድና እድገታቸው በአዲስ አበባ መርካቶ መሳለሚያ አካባቢ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በናዝሬት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ክፍል አግኝተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ሕግና በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ተከታትለዋል። የሰብዓዊ መብትና የጦርነት ጊዜ መብቶች ላይም ተጨማሪ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሀዋሳና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሕግ መምህር በመሆን አገልገለዋል። በተጨማሪም በአፍሪካ ህብረት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ድርጅት ተወካይ በመሆንና በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብት ዙሪያ ሰርተዋል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውስጥ ኮሚሽነር በመሆን ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ኮሚሽነር ብሌን በማንኛውም ቦታና ጊዜ ጠንክሮ መሥራት የሕይወታቸው መርህ ነው። በተሰማሩበት የሥራ መስክ ሁሉ ጥንካሬን ማስቀደም ከተቻለ የማይሳካና የማይለወጥ ነገር የለም ይላሉ። በሕይወት ውስጥ ፈተናዎችና ችግሮች የሚያጋጥሙ ቢሆንም አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለአንድና ሁለት ጊዜ ነው። ቁርጠኝነት፣ ጥንካሬና ፍላጎት ካለ የትኛውንም ችግር ለመሻገር አያዳግትም ይላሉ።

ቤት ውስጥ የምትውል ልጅ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያላትና ጎበዝ ተደርጋ ሰለምትታሰብ በልጅነታቸው ከወንዶች እኩል የመጫወት፣ ድምጻቸውን የማሰማት፣ ከሰዎች ጋር የማውራትና ሌሎች ሥራዎችን የመሥራት ዕድል አለማግኘታቸውን ይናገራሉ። ባሳለፉት የሕይወት ተሞክሯቸው ሴት በመሆናቸው ብቻ ማድረግ የሚፈልጉትን እንዳይሰሩ በማኅበረሰቡ ግፊት ቢያድርባቸውም እርሳቸው ግን ቁርጠኝነት፣ ጥንካሬና ፍላጎት በማስቀደማቸው ከአላማቸው ዝንፍ አላሉም።

ሴት በመሆናቸው ብቻ ነገሮችን እንዳይሰሩ ቢከለከሉም እሳቸው ግን ክልከላውን ተቀብለው አያውቁም። የኮሚሽነር ብሌን መልስ ሰርቶ በማሳየት ለሌሎች ሰዎችም ትምህርት መሆን ነው።

ኮሚሽነር ብሌን ብዙ ውጣ ወረዶችን አልፈው አሁን ላይ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ በታመነበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ ኮሚሽነር ሆነው እያገለገሉ ነው። በሀገራዊ ምክክሩ በኮሚሽነርነት መመረጣቸው ሴቶች በትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችና በየትኛውም የኃላፊነት ቦታ ላይ ቢቀመጡ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ማሳያ ነው ይላሉ። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን ሲለዩም ምሳሌ መሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ሂደትን በተመለከተ ከኮሚሽነር ብሌን ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል። መልካም ንባብ።

ዲስ ዘመን፡- ቆይታችንን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ዓላማውና መዳረሻ ግቡ ምንድነው ከሚለው እንጀምር?

ኮሚሽነር ብሌን፡- የኮሚሽኑ መቋቋም ዋና ዓላማው በሀገራችን ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ የማያግባቡ ጉዳዮች ማለትም ኅብረተሰብ ከመንግሥትን እና ኅብረተሰብን ከኅብረተሰብ እንዲጋጭና መተማማን እንዲጠፋ ያደረጉ በርካታ ችግሮች አሉ። ይህም ለጋራ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት፣ ብልጽግና፣ አንድነት፣ ሰላምና ልማት እንዳንሰራ ምክንያት ሆኗል። አለመተማመንን የሚፈታ የተቀመጠ ሕግ ባለመኖሩ እነዚህና መሰል ችግሮች ሲፈጠሩ በተለመደው የሕግና ሥርዓት አግባብ ለመፍታት ያስቸግራል።

ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ኅብረተሰቡ፣ የተለያዩ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ አካታች የሆነ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ተግባር ከገባ ወደ ሁለት ዓመት እየተጠጋው ነው።

የምክክሩ ዋና ዓላማ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመምረጥ ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት ነው። በተጨማሪም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ምክክር ማድረግ፤ መግባባትን ለመገንባት፣ በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ ማኅበራዊ እሴቶችን ለማደስ የሚረዳ ነው።

መዳረሻ ግቡ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ጠንካራና ቅቡልት ያለው ሀገረ መንግሥት መገንባት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማስፈን፣ በመንግሥትና በማኅበረሰቡ መካከል ያሉትን አለመግባባቶች፣ አለመተማመንና ልዩነትን ሊፈታ የሚችል የመፍትሔ ሃሳብ በማስቀመጥ የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ምን ምን ሥራዎችን ሠራ? በተሰሩት ሥራዎችስ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች ምንድን ናቸው?

ኮሚሽነር ብሌን፡- በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ጠቅለል ለማድረግ ግን ኃላፊነት ወስዶ የሚሰራና በሰዎች ዘንድ ሊታመን የሚችል ኮሚሽን ማቋቋም የመጀመሪያው ተግባር ነው። ሀገራዊ ምክክር ያስፈልጋል የሚሉ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም በተጨባጭ ግን ኮሚሽኑ እንደ ኮሚሽን በአንድ ጊዜ ቅቡልነት አላገኘም። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሁሉም ማኅበረሰብ ተቀባይነትን አግኝቶ ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአጋርነት እንዲሰሩ የግንዛቤ ሥራ በስፋት ተከናውኗል። ይህም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ አለው።

አዋጁ ላይ በተቀመጠው መሠረት ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን ለይቶ አጀንዳ በማሰባሰብ ያወያያል ይላል። በዚህም ተሳታፊዎች በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚለዩና አጀንዳ እንዴት እንደሚሰበሰብ አዋጁ ላይ ባለመቀመጡ ተሳታፊዎችን ለመለየትና አጀንዳ ለማሰባሰብ የሚረዱ ግብዓቶችን በየክልሉ ከሚገኙ ከየማኅበረሰብ ክፍሎች በመቀበል ዝርዝር ስራዎችን አዘጋጅተናል። የተሰሩት ስራዎችም የሀገራዊ ምክክር ሥነ-ዘዴ አካታች፣ አሳታፊና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ እንዲሆን አስችሎታል።

በዚህም መሠረት በተለያዩ ክልሎች በወረዳ ደረጃ ለሀገራዊ ምክክሩ በአጀንዳ መረጣ የሚሳተፉ ከሰባት የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እንደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከአርሶ አደሮች፣ ከነጋዴዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎች እና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው። እስካሁን በተሠራው ሥራ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በሀረሪ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በአፋር ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች በአጀንዳ የሚሳተፉ አካላት ተካሂዷል። በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሊ እና በኦሮሚያ ክልሎች ላይ በወረዳ ደረጃ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወክለው የሚሳተፉ አካላትን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው።

በክልል ደረጃ ባለው የአጀንዳ መረጣ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማህበራት፣ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በደብዳቤ ጠይቀን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን እየላኩልን ይገኛሉ።

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵውያንም ለምክክሩ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት ሁኔታ ተመቻችቶ አጀንዳቸውን እያቀረቡ ነው። በዚህ መሠረት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በሁሉም አካባቢዎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች ሲጠናቀቅ በቀጥታ ወደ ምክክር ሂደቱ እንገባለን።

አዲስ ዘመን፡- በአማራና ትግራይ ክልሎች የተባባሪ አካላት ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እስካሁን ለምን አልተጀመረም? በነዚህ ክልሎች ላይ  አስፈላጊውን ሥራ ለማከናወን ኮሚሽኑ ምን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ቢያብራሩልን?

ኮሚሽነር ብሌን፡- በአማራና ትግራይ ክልሎች በነበረው የጸጥታ ሁኔታ የምክክር ሂደቱን ከሌሎች አካባቢዎች ጋር እኩል ማስኬድ አልተቻለም። ይሁን እንጂ በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታን ለመጀመር ከኮሚሽኑ ጋር በትብብር ለሚሰሩ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ስልጠና ተሰጥቷል። ስለሀገራዊ ምክክሩ ዓለማ፣ የተባባሪ አካላትና የተሳታፊ ልየታን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከክልሉ ነዋሪዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረግን እንገኛለን።

ትግራይ ክልልን በተመለከተ ስለሀገራዊ ምክክር ሂደትና ስለአስፈላጊነቱ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በተደረገው ውይይት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። ከሕዝቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ዶክመንቶችን ወደትግርኛ የማስተርጎም ሥራ እየሠራን ነው። በሁለቱም ክልሎች የሚገኙት የማኅበረሰብ ክፍሎች ሀገራዊ ምክክሩን አምነውበት እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው።

አዲስ ዘመን፡- በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች በምን ዓይነት ሁኔታ ይሳተፋሉ? ሚናቸውስ እስከምን ድረስ ነው?

ኮሚሽነር ብሌን፡- በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎ ሰፊ ድርሻ አለው። ምክክሩን በሥራ አስፈጻሚነትና ኮሚሽነርነት ከመምራት ጀምሮ በማወያየት፣ አጀንዳ በማሰባሰብ፣ አጀንዳ በመቅረጽ፣ ተሳታፊና ተባባሪ አካላትን በመለየት፣ በምክክር ሂደቱና በሌሎች ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።

ሴቶች በተለያየ ጊዜና ቦታ በሚፈጠሩ ችግሮች ቀዳሚ ተጎጂዎች ናቸው። በሀገሪቱ ካለው የሕዝብ ብዛት ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ተብሎ ይገመታል። ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሳተፉ በማድረግ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

ሀገራዊ ችግሮችን እንደሚፈታ ታምኖበት ወደሥራ በገባው የሀገራዊ ምክክር ላይ ሴቶች ከኮሚሽነርነት ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉ ዘላቂ ሰላምና እኩልነት የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ከማስቻሉም በላይ፤ ሴቶች በማንኛውም የኃላፊነት ቦታ ላይ ቢቀመጡ የሚያስመዘግቡት ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል።

ሴቶች በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በቤታቸው፣ በመሥሪያ ቤታቸውና በተለያዩ መድረኮች ይጸልያሉ፤መልካሙን ይመኛሉ። በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮችን ባከተተው የምክክር ሂደት ላይ መሳተፋቸው ደግሞ በውጭ ሆነው ስለሚያወሩለት ሰላም ዘላቂ የመፍትሔ ሃሳቦችን በተግባር ለማቅረብ ዕድል ይፈጥርላቸዋል። በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች እንደ አንድ የሕብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ከመምህራን ማህበር፣ ከዕድሮች፣ ከወረዳ አስተዳደር፣ ከአርሶ አደር፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥም ሴቶች ስላሉ በሁሉም ተሳታፊ መሆን ይችላሉ።

ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በመፍታት ሀገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም ማስፈን መዳረሻ ግብ ያደረገው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት አለባቸው።

ሴቶችን በአመራርነትና በሌሎች ሥራዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ኮታ ሳይሆን ችሎታ ነው:: ለሀገር አንድነት፣ እድገት፣ ብልጽግና እና ሌሎች ሥራዎች ላይ እቅድ ሲወጣ፣ ውሳኔ ሲወሰን፣ ሰነድ ሲዘጋጅና ተግባራዊ ሲደረግ የሁለቱንም ፆታ ያማከለ መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን፡- ለምክክሩ ስኬታማነት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መውሰድ ተችሏል? ተሞክሮውስ ምን ያሳያል?

ኮሚሽነር ብሌን፡- ስኬታማ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ከዚህ በፊት ምክክር ያደረጉ ሀገሮችን ተሞክሮና በሀገራዊ ምክክሮች ላይ የተጠኑ ጥናቶችን ለመመልከት ተሞክሯል። በዚህም መሠረት ሀገራዊ ምክክሩ የሕዝብ ባለቤትን ያረጋገጠ መሆን እንዳለበት መገንዘብ ችለናል። በተጨማሪም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት፣ ሃሳብ የሚያቀርቡበትና የሚደመጡበት ሊሆን እንደሚገባው እንዲሁም አካታች፣ ግልጽ፣ አሳታፊና ገለልተኛ መሆን እንዳለበት የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል። ሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የልሂቃን ብቻ ሳይሆን የሕዝብ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል።

ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ሁለተኛው ተዓማኒነት ነው። የምክክር ሂደቱን ለማስፈጸም በኮሚሽነርነት የሚመረጡት በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያላቸው፣ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የሌላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ያሳያል።

ለምክክሩ ስኬታማነት የውይይት አጀንዳው ወሳኝ ነው። ለዚህም ላለመግባባት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ሁሉ ለውይይት አቅርቦ እንዲፈቱ ማድረግ ይገባል። በሀገራዊ ምክክሩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ሲቪክ ማሕበራት፣ ዳኛዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች የሃይማኖት ተቋማት ሊካተቱ እንደሚገባ ተሞክሮ መውሰድ ችለናል።

በተጨማሪም ለምክክሩ የሚሰጠው ጊዜና ቦታ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። የምክክሩ ቦታ ሁሉንም አካባቢ ማካተት እንዳለበት እና የጊዜ ገደቡ መካከለኛ ሊሆን መሆን እንዳለበት ተምረናል። ለምሳሌ ያህል ግብጽ በአንድ ሳምንት ምክክር ለማድረግ ሞክራ ምንም ውጤት ሳይገኝበት መጠናቀቁን መረጃዎች ያሳያሉ። ጊዜው በጣም ከረዘመም ጉዳዩ ይረሳና የታለመለትን አላማ ማሳካት አይችልም።

አዲስ ዘመን፡- በሀገሪቱ ያሉት ችግሮች ስር ከመስደዳቸውና ምክክሩ ከመዘግየቱ የተነሳ ስኬታማ ላይሆን ይችላል ይባላል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

ኮሚሽነር ብሌን፡- በዚህ ቀን ቢጀመር ዘግይቷል፤ በዚህ ቀን ቢጀመር አልዘገየም ለማለት ከባድ ነው። ግን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቀስን ያደረግነው ጥናት የሚያሳየው ለምክክሩ በቂ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ነው። በሀገሪቱ ለዘመናት የቆዩ ውስብስብ ችግሮች አሉ። ይህንን ችግር በመፍታት ሀገራዊ መግባባት ማምጣት የሚቻለው በምክክር ብቻ ነው። በምክክሩ የሚሳተፉት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ እንዲሆኑ ለማድረግና የሚቀርበው ችግር ፍቺ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራው ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ሁለቱን ጉዳዮች መስመር ማስያዝ ከተቻለ ግን የምክክር ሂደቱ ፈጣን ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኮሚሽኑ የመንግሥት አጀንዳ አስፈፃሚ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ አላቸው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ኮሚሽነር ብሌን፡- ይህ ኮሚሽን ያስፈለገው ሕዝቡ መንግሥትን ስለማያምን እና መንግሥትም ኅብረተሰቡ ላይ ያለው በራስ መተማመን ስለቀነሰ ነው። ሰዎችም ኮሚሽኑን ሊያምኑት የማይችሉት በዚህ መንፈስ ውስጥ ስለሚሆኑ ነው። ሰዎች ኮሚሽኑ የመንግሥት አጀንዳ አስፈፃሚ ነው ብለው ቢያስቡ ይህ የሚሆነው ካለው ያለመተማመን ነው። ሆኖም በሀገራዊ ምክክሩ መንግሥትን የተመለከተ ነገር አይነሳ አንልም።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችም አካላት በራሳቸው ቅንጅት ሕዝቡን እንዲመርጡ የምንጠብቅባቸው እና በጋራ የሚሠሩ ናቸው። ስለዚህም በማሃላ ሳይሆን በተግባር ገለልተኝነታችንን እያረጋገጥን እየሄድን ነው።

ሆኖም መረጃ በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እየሆነ አይደለም። ይህን መረጃ ያገኙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለኮሚሽኑ ያላቸው አመለካከት ይቀየርና ገልልተኛነቱን በአግባቡ የተረዱ ይሆናሉ። ብዙ ሰዎችም ስለኮሚሽናችን ገልልተኝነት በአግባቡ ካስረዳናቸውና ከተግባርም ከመረመሩ በኋላ ጥርጣሬያቸውን አስወግደዋል። ከመንግሥት ጋር በሕግ ማዕቀፍም ሆነ በአሠራር አለመገናኘታችንን አድንቀው ያወሩልኛል። ይህን የሚያውቅ ሰው እየበዛ በመጣ ቁጥር በኮሚሽኑ ላይ ያለው መተማመን እየጨመረ ይመጣል።

በሀገራዊ ምክክር ውስጥ መንግሥት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ቁጭ ብሎ የሚወያይቸው ጉዳዮች ይኖራሉ። የመንግሥት ተሳትፎም በዚያ ልክ የተወሰነ ነው የሚሆነው።

አዲስ ዘመን፡- የዚህ ሀገራዊ ምክክር ዓላማ የሚሆነው ጠንካራ እና ሀገራዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መገንባት ነው። ከዚህ አንፃር እስካሁን የተሄደበት ርቀት እና አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ኮሚሽነር ብሌን፡– ጠንካራ እና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሀገራዊ ምክክር የመጨረሻ ውጤቱ ነው። ሰዎች ተመካክረው ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ያስፈልገናል ለዚህ ደግሞ ይህንን ማሻሻል አለብን ብለው የተግባቡት ነጥብ ሲፈፀም የምንደርስበት ቦታ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ ጠንካራ ሥራ እየሠራን ያለነው ተወካዮችን መለየት ላይ ነው።

እዚህ ጉባኤ ላይ ቁጭ ብለው የሚነጋገሩት እና ቁጭ ብለው ተወያይተው መፍትሔ የሚያመጡት ሰዎች ማኅበረሰቡ የሚያምናቸው፣ የሚቀበላቸው፣ በትክክል የሚወክሏቸው መሆን አለባቸው።

በበርካታ ክልሎች ላይ እየሠራነው ያለውም ሥራ ይሄው ነው። በክልሎች ሰው የሚያምናቸው እና የሚቀበላቸው፤ ነገ እንደዚህ ወስነዋል ቢባል አይ እኔ አልተሳተፍኩም ፤ የኔ ሃሳብ አልተነሳም የማይላቸው ዓይነት ሰዎችን እያስወከልን ነው ያለነው።

የሚመካከሩት ሰዎች ቅቡልነት፣ አመለካከት እና ዕውቀት ለውጤቱ ተዓማኒነት እና ባለቤትነት በጣም አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በዚህ ረገድ እየሠራን ያለነው ሥራ መቶ በመቶ ባይሆን እንኳን ብዙውን ሰው የሚያስማማ ነው። አብዛኛው ሂደትም የአብዛኛውን ሰው ተቀባይነት ባገኘ መልኩ የተከናወነ ነው።

አሁንም አጀንዳ እየሰበሰብን ነው የምንገኘው። ውይይት ደግሞ ቀጥሎ ይካሄዳል። ነገር ግን ከውይይት አስቀድሞ በደብዳቤ፣ በፖስታ፣ በአካል፣ በኢሜል የሚላክልንን እየሰበሰብን እና ብዙ ሰው ለማዳመጥ እየሞከርን ነው። ከዲያስፖራው ጋርም ውይይት አድርገናል።

ቅድም እንዳልኩሽ ዋናው የምክክሩ መሠረት የሆነውን ተመካካሪዎችን እየለየን ነው ያለነው። ይህ በመሆኑ የተነሳ ለካ ተቋማት እኛ ድረስ ይመጣሉ ብለው ሥርዓት መኖሩን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባሉ። ተደማጭነትም ይሰማቸዋል። ይህ በአንድ ጊዜ የሚገነባ ባይሆንም እየተሻሻለ የሚመጣ ነው ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የሕገ መንግሥት እና የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ሃሳቦች ቢመጡ የምታስተናግዱበት አግባብ ምን ይመስላል?

ኮሚሽነር ብሌን፡– ስለዚህ ጉዳይ አሁን በዚህ ጊዜ ላይ የምልሽ ነገር አይኖርም። ምክንያቱም አዋጁ የተቀመጠው እጅግ መሠረታዊ ሀገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ በሙሉ ተወያይቶ መፍትሔ ያስቀምጣሉ ይላል። ይህን እና ያን በሚል የተለየ ነገር የለም። ግን ደግሞ አሁን ላይ ሁሉንም አጀንዳ ሰብስበን ስላልጨረስን የመጡና የቀሩ አጀንዳዎችን ልዘረዝር አልችልም።

በሌላ በኩል ለሀገራዊ ምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን የሚያፈልቁት ኮሚሽነሮች አይደሉም። አጀንዳ የሚሰበሰበው በውይይት፣ በጥናት አልያም በተለያየ መንገድ ነው። ኮሚሽነሮች ሆነን ይህ ሊመጣ ይችላል፤ ያ ሊመጣ አይችልም አንልም። ነገር ግን ሀገራዊ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ የሚነሱ ሃሳቦች ለውይይት ይቀርባሉ።

አቅጣጫ የምናስቀምጠውም እኛ ኮሚሽነሮች አይደለንም። ክልሎችን፣ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መንግሥትን እና ሌሎችንም ወክለው የሚቀመጡ ሰዎች አሉ። የተነሱ ችግሮች ላይ የተነሱ ሃሳቦችን መዝነው ለዚህ ችግር ይኸኛው መፍትሔ ይሻለናል ያሉትን በምክረ ሃሳብ መልኩ ነው የሚቀርበው።

አዲስ ዘመን፡- በሀገራዊ ምክክሩ የኮሚሽነሮች ኃላፊነት ምንድነው?

ኮሚሽነር ብሌን፡– በዚህ ውስጥ የኮሚሽነሮች ኃላፊነት ሁሉም ሰው ሃሳቡን እንዲገልጽ ማድረግ ነው። ሰላማዊ የሆነ፣ አካታች እና ሁሉን ሰው የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ እንዲኖር ማስቻል ነው። አንድ ጮክ ብሎ የሚናገር ሰው ሂደቱን እንዲቆጣጠረው ማድረግ ሳይሆን የሁሉም ሃሳብ እንዲንሸራሸር ማስቻል ነው። ውሳኔ አሰጣጥ ላይም ሁሉም ሃሳብ በአግባቡ እንዲመዘን ማድረግ ነው። ሰዎች ከመከራከርና ከመጨቃጨቅ ይልቅ በምቹ ሁኔታ እና በመግባባት ወደ ውሳኔ እንዲመጡ ማድረግ ነው። በሂደቱ ነጥብ ማስጣል፤ ነጥብ ማስቆጠር አይደለም ዋናው ዓላማ። መደማመጥ እና በውይይት ሁሉም አካል አሸናፊ የሚሆንበት አውድ መፍጠር ነው።

በርግጥ ማወያየት በጣም ከባድ ነገር ነው። ፍሰቱ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚነሳ ስላልሆነ መጓተቶች፣ መበሻሸቆች፣ መቋሰሎች ይኖራሉ። እዚህ ላይ የኮሚሽኑ ሥራ እነዚህን ሁሉ በማስቀረት በተቻለ መጠን ሰዎች ሊፈፀም የሚችል፤ ሊያግባባ የሚችል መፍትሔ እንዲያመጡ ሃሳብን ሳይጫን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ማስቻል ነው። ስምምነት ላይ ሲደረስ ደግሞ ኮሚሽኑ ሪከርድ ያደርጋል። ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ፖሊሲ ከቀረጸና ዝርዝር እቅድ ካዘጋጀ በኋላ የክትትል ሥራን ይጀምራል። የተሰማማንበት የመፍትሔ ሃሳብ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ የማድረግ ሥራን ይሰራል እንጂ እኛ ወደምንፈልገው አቅጣጫ መምራት አይደለም።

በነገራችን ላይ በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ አካላት የኛም ተወካይ ናቸው። ለምሳሌ በእኔ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ የምትገኝ ሴት በሀገራዊ ምክክሩ ተሳትፋ የመፍትሔ ሃሳብ ስታገኝ እኛም እናገኛለን። በዚህ አግባብ ሰዎች ከመበሻሸቅ፣ ከግጭት፣ ካለመግባባት እንዲወጡ ማስቻል ነው። በዚህ ሥራ ላይ ግን የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እገዛ ያደርጋሉ።

አዲስ ዘመን፡- በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮች አሉ? ምን መፍትሄስ ተወሰደ?

ኮሚሽነር ብሌን፡- ዋናው ችግር በሀገሪቱ ያሉት ግጭቶች ምክክሩን በሚፈለገው ደረጃ ማስኬድ እንዳይቻል አድርገውታል። ለዚህ እንደመፍትሔ የወስድነው ግጭቱ በረድ በሚልባቸው አካባቢዎች ከአጃቢ ጋር መሄድና ጊዜን ጠብቆ ሥራዎችን ለመሥራት ተሞክሯል። ከበፊቱ የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም በምዕራብ ወለጋና በአማራ ክልል የቀጠሉት ግጭቶች ሥራዎችን እንዳንሠራ እየፈተኑን ነው።

ሌላው የሎጅስቲክስ እና የሰው ኃይል ችግር ነው። በኮሚሽኑ ያሉትን የሰው ኃይሎች ወደክልሎች በማሰማራት ሥራዎች እየተሰሩ ነው። በኢትዮጵያ በሚገኙት ከአንድ ሺህ 300 በላይ ወረዳዎችን ለማድረስ ሎጀስቲክስ ወሳኝ በመሆኑ መኪናና ሹፌሮችን ከተቋማት በመዋስ እየተሠራ ነው። ወደክልል ስንሄድ ደግሞ የቋንቋ ክፍተቶችን ለመሙላትና የተለያዩ ሥራዎችን ለማስፈጸም የዩኒቨርሲቲ መምህራንና በጎ ፈቃደኞች እንዲያግዙን እያደረግን እንገኛለን።

ሶስተኛው ችግራችን በግጭት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ አካላትን ወደሰላም ማምጣት አለመቻሉ ነው። ወደጫካ ከመግባት ይልቅ ሃሳባቸውን ለምክክር እንዲያቀርቡት የማድረግ ሥራ አለመሠራቱ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ሶስት ዓመት ነው። ሁለት ዓመቱን አጠናቋል ቀሪው አንድ ዓመት ነው። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ቀሪ ሥራዎችን ማጠናቀቅ ይቻላል?

ኮሚሽነር ብሌን፡– ይቻላልም፤ አይቻልምም። ዋናው ከባዱ ነገር ስትራክቸር መሥራቱ ነው። ኢትዮጵያን የሚመስል፣ የሚያካትት ብዙ ሰው የሚስማማበት ስትራክቸር ሰርተን እያጠናቀቅን ስለሆነ ከዚህ በኋላ የጊዜ ጉዳይ ነው የሚሆነው። እኛ ማፍጠን የምንችለው የተሳታፊና የአጀንዳ ልየታውን ነው። እኛ የምንቆጣጠረው የምናደርገው ተወካይና አጀንዳው ተለይቶ ሀገራዊ ጉባኤው እስኪካሄድ ድረስ ነው። ሥራዎችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማስኬድ የበዓላት መደራረብ፣ ግጭቶችና ሌሎች ችግሮች ፈትነውናል። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል የተባባሪ አካላትን ልየታ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በግጭቱ ምክንያት ማሳካት አልተቻለም። በነዚህና መሰል ችግሮች ባሰብነው ጊዜ እንዳይሄድ ሆኗል።

አጀንዳ የማሰባሰብ የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች ደግሞ የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች በሚፈታና ለውይይት በሚመች መልኩ አጀንዳ መቅረጽ ቀጣይ ሥራዎች ናቸው። አጀንዳ ሲቀረጽ ኮሚሽኑ አዲስ ነገር ሳይሆን የሚፈጥረው ከተለያዩ አካላት የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች መልክ ማስያዝ ነው። አጀንዳው ከተቀረጸ በኋላ ጠቅላላ ጉበዔውን በማዘጋጀት ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይሆናል።

በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉት ልሂቃንና ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሰው የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል በማለት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል። ሀገራዊ ምክክሩ የኮሚሽኑ ሳይሆን የሀገር መሆኑንም መረዳት ይገባል። ለዚህ ምክክር ስኬታማነትም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚያስቡ አካላት ካሉም ከነሱም መጠበቅ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን::

ኮሚሽነር ብሌን፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You