ዝምተኛ ገዳዮች

በመላው ዓለም በየዓመቱ 41 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሕይወቱን እንደሚያጣ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል። በዚህ መልኩ ከሚመዘገበው ሞት ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባለባቸው ሀገራት እንደሆነ የድርጅቱ መረጃ ያሳያል።

ተላላፊ ያልሆኑ ነገር ግን በገዳይነታቸው ግንባር ቀደም ከሚባሉት በሽታዎች ውስጥ የካንሰር፣ የልብና የስኳር ሕመምን የመሳሰሉት እንደሚመደቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት በእነዚህ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ከሚያጡባቸው ሀገራት ተርታ እንደሚመደቡ «ክሊኒክ ኮምፔር» የተባለ በለንደን ከተማ የሚገኝ የጤና ተቋም፤ ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት፣ ከአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት እና ከዓለም አቀፍ የሳንባ ጤና ድርጅት ዋቢ በማድረግ ባወጣው ሪፖርቱ አስፍሯል።

ይህም የሚያሳየው በተለምዶ የሀብታም ሀገራትና ሰዎች ችግር ተደርገው ይወሰዱ የነበሩ እንደ ካንሰር፣ ስኳር፣ ልብ፣ ደም ግፊት፣ ኮሊስትሮል… ወዘተ የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፤ አሁን ላይ መካከለኛ ገቢ ያላቸውንና ድሃ የሚባሉት ሀገራትና ሰዎችን ጭምር በስፋት እያጠቁ መሆናቸውን ነው። ይሁን እንጂ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ዜጎቻቸውን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ለመታደግ፤ ችግሩንም ለመቆጣጠርና ለመከላከል የሚያደርጉት ጥረት የአሳሳቢነታቸውን ያህል እንዳልሆነ የዘርፉ ምሑራን ያስረዳሉ።

በሀገራችን ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ጤነኛ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ፣ በቂ አካላዊ እንቅስቃሴ ካለማድረግ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት፣ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ ከመጠጣት፣ አደንዛዥ እፅ ከመውሰድ ጋር ተያይዞ በሚመጡ እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር፣ ልብ፣ ካንሰር፣ ኩላሊት፣ ኮሊስትሮል በመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚታመሙና ሕይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ለአብነት፣ የስኳር ሕመም እንደ ኢትዮጵያ ብሎም እንደ ዓለም በአስደንጋጭ ሁኔታ ስርጭቱ እየጨመረ ነው። በዓለም አቀፉ የስኳር ማኅበር ሪፖርት መሠረት በ2019 በዓለም ላይ የስኳር ታካሚዎች ቁጥር 463 ሚሊዮን ያህል ነበር። ይህ ቁጥር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በ2021 ወደ 537 ሚሊዮን አሻቅቧል። ይህ መረጃ የሚያሳየው የበሽታው ስርጭት ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ ነው። ከዚህ በመነሳት የዓለም አቀፉ የስኳር ማኅበር፣ “በ2040 ላይ ወደ 700 ሚሊዮን የሚጠጉ የስኳር ታካሚዎች ይኖራሉ” በሚል ትንበያ አስቀምጧል።

እንደ ማኅበሩ ሪፖርት፣ አስደንጋጩ ነገር ደግሞ አብዛኛው ወይም 50 በመቶ የሚሆነው የስኳር ታማሚ፣ ምርመራ ስለማያደርግ የስኳር ሕመም እንዳለበት አያውቅም። ስለዚህም ያለ ሕክምና ከስኳር ሕመም ጋር እየኖረ ያለው ሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ ነው። ችግሩን የሚያጎላው ደግሞ በዓለም ላይ ከአምስት የስኳር ታካሚዎች አራቱ ወይም 80 በመቶ የሚሆኑት በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገሮች ውስጥ የሚገኙት ናቸው።

ከኢትዮጵያ አንጻር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም ባስጠናው ጥናት መሠረት ሦስት ነጥብ ሁለት በመቶ የሚሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በስኳር ሕመም ተጠቂ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ዘጠኝ ነጥብ አንድ በመቶ አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቅድመ ስኳር (ከመደበኛው የስኳር መጠን የበለጠ ሆኖም ወደ ስኳር በሽታ ያልተቀየረ) እንዳለባቸው ጥናቱ ያመላክታል።

ከጥናቱ አኅዛዊ መረጃ መገንዘብ የሚቻለውም በሽታው በኢትዮጵያ መስፋፋቱን ሲሆን፤ በዚህም ከጠቅላላው ሕዝብ አምስት በመቶ የሚጠጋው በስኳር ሕመም እንደተጠቃ እና 19 ነጥብ አንድ በመቶ የሚሆነው ደግሞ ቅድመ ስኳር እንዳለበት ይገመታል። 24 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ ወይ በስኳር ሕመም የተጠቃ ነው፤ አልያም ቅድመ ስኳር አለበት። ስለዚህ በሽታው እንደ ሀገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው።

ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከጠቅላላው ሕዝብ ቁጥሯ 1/4ኛው ወይም ሩቡ ገደማ የስኳር ተጠቂ እየሆነ ነው። በዚህም ሀገር በበሽታው በየዕለቱ ከምታጣቸው ዜጎች ባሻገር፤ ለስኳርና ከስኳር ጋር ተያይዘው ለሚመጡ በሽታዎች ሕክምና ለሚውሉ ግብዓቶችና መድኃኒቶች የምታወጣው ወጪ ኢኮኖሚዋ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው።

በተመሳሳይ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች የልብና የካንሰር ሕመም በዓለም ላይ በገዳይነታቸው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይይዛሉ። በሀገራችንም በነዚህ በሽታዎች የሚሰቃዩና ሕይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መረጃ እንደሚያሳየውም፣ በዓመት ውስጥ የካንሰር ሕመም እንዳለባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቁ ከስምንት ሺህ በላይ አዳዲስ ታካሚዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የተቋሙን በር ያንኳኳሉ። ነገር ግን የካንሰር ሕክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ከስምንት ሺህ አዳዲስ ታካሚዎች ውስጥ ከግማሽ የሚልቁት ሕይወታቸውን ያጣሉ።

ይሄ የሚሆነው ደግሞ በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው፣ በሀገሪቱ በአብዛኛው ጊዜ በበሽታው ከተጠቁ ታካሚዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ ጤና ተቋም የሚመጡት በጣም ከተጎዱ በኋላ ወይም ደግሞ ደረጃ 3 እና 4 ገብተው (ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ) ነው።

ሁለተኛው፣ በተለይ የጨረር ሕክምና የሚያስፈልጋቸው የካንሰር ሕመምተኞችን ለማከም እንደ ሆስፒታሉ ብሎም እንደሀገር ያሉ የጨረር ማሽኖች ውስን በመሆናቸው ሕመምተኞች ወደ ሕክምና ተቋም በሄዱበት ጊዜ ሕክምናውን ወዲያውኑ የማግኘት እድላቸው የጠበበ ነው። በነዚህ ምክንያቶች የካንሰር ሕክምናው ውጤታማ ባለመሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ “ካንሰር አይድንም” የሚል የተዛባ አመለካከት እንዲፈጠር ሆኗል።

የልብ ሕመምን በተመለከተም፣ በሆስፒታሉ ከስምንት ሺህ በላይ ዜጎች የልብ ቀዶ ሕክምና ለማግኘት ተመዝግበው ዓመታትን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የልብ ቀዶ ሕክምና ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ግብዓቶችን የሚጠይቅና የአላቂ እቃዎች እጥረት …ወዘተ በመኖሩ በወረፋ መርዘም አብዛኞቹ ታማሚዎች አገልግሎቱን ሳያገኙ ሕይወታቸው ያልፋል።

ስለዚህ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የችግሩን ጥልቀትና አሳሳቢነት በመረዳት ችግሩን ለማቃለል የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ መከላከል ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል። ማኅበረሰቡም በተለይ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ ከሚያደርጉ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤ መራቅ ይጠበቅበታል።

የጤና ባለሙያዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ላይ በስፋት ሊሳተፉና ኅብረተሰቡን በስፋት ሊያስተምሩ ይገባል። ኅብረተሰቡም የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተቀብሎ በመተግበር የበሽታዎቹን ስርጭት መግታት ይኖርበታል። ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት በመግታት በአህጉሪቱ ያላትን የመሪነት ሚና ልትወጣ ይገባል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You