በክፉዎች ሃሳብ የማይደናቀፈው የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጉዞ

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ላይ ይዞታ የነበራትና ቀይ ባሕርንም ስታዝበት የኖረች ሀገር ነች። 1 ሺ800 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው የቀይ ባህር ይዞታ ለወጭና ገቢ እቃዎች ሁለት ወደቦች የምታስተዳድር ሀገር ነበረች። እናም ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ውጪ ቀይባሕርንም ከኢትዮጵያ ውጭ ማሰብ አይቻልም ነበር። ሆኖም በሴራ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራትን ሚና እንድታጣ ተደረገ።

በዚህም ኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተጋልጣለች። ለምሳሌ፣ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል። ለኪራይና ለመጓጓዣም ከፍተኛ ዶላር ስለምታፈስ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንርና የኑሮ ውድነትም እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል። በዲፕሎማሲ እና በተጽዕኖ ፈጣሪነት ረገድም ማጉደሉ አልቀረም።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወደብ አልባ ከሆኑት 16 ሀገራት አንዷ ብትሆንም፤ ወደብ አልባ የሆነችባቸው አመክንዮዎች ግን ታሪካዊም ሆነ ሕጋዊ መሠረት የሌላቸው ናቸው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ 126 ሚሊዮን ደርሷል። በዚህም በኢትዮጵያ የሚኖረው ሕዝብ የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት ሕዝብ 1/3ኛውን ይሆናል። ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ይዞ የባሕር በርና ወደብ የተነፈገ ሀገር የለም።

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በባሕር በር የተከበበች፣ ለቀይ ባሕርም የቀረበች ሀገር ነች። በሶስተኛ፣ ደረጃ በታሪክም በቀይ ባሕር ላይ ለዘመናት የበላይ ሆና ቆይታለች። ስለሆነም የኢትዮጵያ ወደ ቀይባህር አካባቢ መመለስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የዘመናት ጥያቄ ነው።

ከ33 ዓመታት በኋላ ግን ኢትዮጵያን የባሕር በር የሚያስገኝላትን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በቅርቡ ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራርማለች። ስምምነቱ ሲተገበርም አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣና ኢትዮጵያም በቀጣናው ላይ ለሚኖራት ተጠቃሚነት በር የሚከፍት ነው።

ሆኖም ይህንን ስምምነት ለማጣጣልና የግጭት መንስኤ ለማድረግ ቀን ከሌሊት የሚሠሩ ሀገራት ተፈጥረዋል። ጥያቄው ግን እነዚህ ሀገራት በዚህ መጠን መጮህ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? ለምንስ በዚህ መጠን ደነገጡ? የሚለው ነው።

እነዚህ ሀገራት ሁነቱን ለማጣጣልና ወደ ግጭት ለመምራት ሱማሌላንድ ዓለም አቀፍ የሆነ እወቅና የተሰጣት ሀገር አይደለችም፤ ስለዚህም ስምምነቱ ሕጋዊ አይደለም የሚል ሃሳብ ያነሳሉ። ነገር ግን ከ1991 ጀምሮ ረዘም ያለ ዓመታትን እራሷን ስታስተዳደር ቆይታለች። የተለያዩ ምርጫዎችን እያካሄደችም የራሷን የመንግሥት ሥርዓት መሥርታ ያለችም ናት። የራሷ የሆነ መገበያያ ገንዘብ ያላት፤ ዜጎቿ ከሀገር ሀገር የሚንቀሳቀሱበት የራሷ የሆነ ፓስፖርት ጭምር ያላት ናት።

በአንድ ወቅት በ2005 አካባቢ ሶማሊላንድ ከአንድ ያልተወከለው የብሔሮች እና ሕዝቦች ድርጅት (Un­represented Nations and Peoples Organization) ከሆነ ዓለም አቀፍ ተቋም (ተቋሙ ባልተወከሉ ሕዝቦች ዙሪያ የሚሠራ ነው) ወይም ደግሞ የሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀስ ድርጅን ተቀላቅላለች። ከዚህ የተነሳ አንድ ርምጃ ወደፊት የሄደች ሀገር ናት።

የኢትዮጵያና የሶማሊ ላንድ ስምምነት ያስደነገጣቸው ሀገራት ደጋግመው የሚያነሱት የእውቅና እና የህልውና ጉዳይ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ መሆኑ፤ ለምን? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል። ሶማሊላንድ ወደ ሀገር የተጠጋች ነች። ቀደም ብሎ የነበሩ ታሪኮችን ስናይ በቅኝ ግዛትም የተለያዩ ቦታ ላይ የነበሩ ሀገራት ናቸው። አንደኛዋ በጣሊያን ስር፣ ሱማሌላንድ ደግሞ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረች ሀገር ናት። አንድ ላይ ለመዋሃድ ሙከራዎች የነበሩትም ከነጻነት በኋላ ነው። ያም ቢሆን እስካሁን አልተሳካም።

በሣህል ቀጣና የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛና የአትላንቲክ ካውንስል የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም ሶማሊላንድን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ በፈረንጆቹ በ1960ዎቹ በርካታ ሀገራት ሶማሊላንድን በነጻና ሉዓላዊት ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋት ነበረ። ሆኖም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከሶማሊያ ግዛት ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል። ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መፈራረስ በኋላ ሶማሊላንድ የራሷ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች በማድረግ የራሷን አስተዳደር መሥርታ ከ30 ዓመታት በላይ መቆየቷንም አንስተዋል።

ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች ሀገራትም በሱማሌላንድ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሆነ ተናግረዋል። ለአብነትም የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ፖርትስ ኩባንያ ጋር በመሆን ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት በበርበራ ወደብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን በመጥቀስ፤ ቢዘገይም ቢፈጥንም፤ ቢፈለግም ባይፈለግም ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ እውቅና የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

ለምሳሌ፣ ሶማሊላንድ በተደጋጋሚ ጊዜ ምርጫ ባካሄደችባቸው ጊዜያት ሁሉ በርካታ ሀገራት ታዛቢዎቻቸውን ልከው የምርጫውን ፍትሃዊነት ሲገልጹ ኖረዋል። በዋናነት የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎችን ልከው ምርጫ ታዝበዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ትንፍሽ ያለ ሀገር አልነበረም። ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ለምን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራርያ በሰጡበት ወቅት ይህንኑ ጉዳይ አንስተው የሚከተለውን ብለው ነበር፡-

‹‹…ለምንድነው ዓለም እንደዚህ አድርጎ ይህችን ሀገር የሚጫናት የሚለው ጉዳይ ብዙ አልገባኝም። አንዳንድ ጊዜ እንደ ፖለቲከኛ ሆኜ ለማየት እሞክራለሁ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመንፈሳዊ ዓለም እንደሚባለው እውነትም የኪዳን ሀገር ሆና ይሆን እንዴ ብዬ እጠረጥራለሁ፤ አላውቅም። ግራ ያጋባኛል፤ እናንተም መርምሩ ፤ እኔም እመረምራለሁ።…

ነገር ግን ፍትሐዊ የሆነ ዳኝነት ያለበት ዓለም ግን አይደለም። ጉልበት ያለው የተደራጀ የተሰበሰበ የሚያሸንፍበት ዓለም እንጂ በፍትህ የሚታይበት ዓለም አይደለም አሁን ያለው። እኛ የጠየቅነው ግን በጣም በጣም ትንሿን ነው፤ ለ120 ሚሊዮን ሕዝብ ደህንነት የምትሆን ትንሿን ነገር ነው የጠየቅነው።›› ሲሉ የሁኔታውን እንቆቅልሽ ገልጸው ነበር።

እንደዚህ ጸሃፊ እምነት የኢትዮጵያን የዕለት ተዕለት እቅስቃሴ በአንክሮ የሚከታተሉ ሀገራት በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌት እና አፍሪካውያን ኩራት በመሆኗ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁሉ ሌሎች አፍሪካውያንም ይከተላሉ የሚል ስጋት አለ። ስለዚህም የኢትዮጵያን ተስፋ መገድል ማለት የአፍሪካን ተስፋ መግደል አድርገው ስለሚወስዱት ኢትዮጵያ ጎልታ እንዳትወጣ መኮርኮም የቅኝ ገዢዎችና የተላላኪዎቻቸው ፍላጎት ይመስለኛል።

ይሄ ግን ስለ ኢትዮጵያ መልካምን የማይሹ፣ ስለ አፍሪካ ብልጽግናን የማይመኙ ኃይሎች ህልም ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትናንት በዓድዋ ወራሪዎችን አሳፍራ የተጎናጸፈችው ድል ለብዙዎች የነጻነት ጮራን እንደፈነጠቀ ሁሉ፤ ዛሬም ለብልጽግናዋ በምትጓዘው ጎዳና ላይ የምታሳርፈው ዐሻራ ለብዙ ድሃ ሀገራት ከድህነት የመውጫ ደረጃን የሚሠራ መሆኑ አይቀሬ ነው።

ለዚህ ደግሞ በግብጽ የብቻ ተጠቃሚነት ስር በኖረው የዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የሕዳሴው ግድብ አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ከሶማሌ ላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተደረሰበት የባህር በር ጉዳይም ሌላ የመቻል አቅም ሆኖ መገለጡ አይቀሬ ነው። በመሆኑም እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ የሚነሱ የክፋት ሃሳቦች ቢኖሩም፤ እነዚህ ሃሳቦች ግን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዞን የሚያደናቅፉ አይሆኑም።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You