አዲስ አበባ:– ባለፉት ሃያ ዓመታት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የበጀትና የመሠረተ ልማት ተደራሽነት እንዳልነበረ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክርቤቱ 5ኛ የፓርላማ ዘመን 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሳባ ትናንት በተደረገበት ወቅት፤ የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ ባለፉት 20 ዓመታት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በክልሎች መካከል እንዳልነበረ አመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርትን አቅርበዋል። እርሳቸው እንዳሉት ሪፖርቱ ወደኋላ የ20 ዓመታትን የፌዴራል የመሠረተ ልማት ስርጭት አፈጻጸምን ተመልሶ ገምግሟል። ለአብነትም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ባለፉት 20 ዓመታት ያከናወናቸውን ሥራዎች በጥልቀት ተመልክቷል።
ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናውን በዋናነት ታሳቢ የሚያደርገው ከመንገዶች ባህሪና አጠቃላይ ፋይዳዎች አኳያ በመሆኑ፤ ለየክልሎቹ ሊያዳርሳቸው የሚገባውን የመንገድ አውታር መጠንና ዓይነት በኮታ መልክ ወይም በቀመር አስቀድሞ በመወሰን እንዳልነበር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የውጭ ፋይዳቸው ከፍ ያለ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ቅድሚያ በመስጠት ሲያከናውን እንደነበር ተናግረዋል።
ነገርግን አገሪቱ ይሄነው ተብሎ የምትመራበት የመንገድ ሕግ እንደሌላት የጠቆሙት ኢንጂነሩ፤ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የሚመራበት እና የሚተዳደርበት እራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት ሥልጣን እና ኃላፊነቱ ተለይቶ ባለመታወቁ፤ ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማከናወንና ለክልሎች እኩል ተደራሽ ለማድረግ ሲቸገር እንደነበር ገልጸዋል።
ሪፖርቱን ካዳመጡት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዳንዶቹ እንዳሉት፣ ሪፖርቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አልተጠናም፣ ታማኝነቱ አጠያያቂ ነው፣ በገለልተኛ አካል ሊጠና ይገባል፣ በአጠቃላይ ግልጽ የሆነ መስፈርት ወጥቶለት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍሉ ባለፉት ዓመታት ነበረ አልነበረም የሚለው ሊታይ ይገባል ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች የቋሚ ኮሚቴው አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሰጡት ምላሽ ኅብረተሰቡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄን ለዘመናት ሲያነሳ እንደነበር ተናግረዋል።
ተቋማት ባለፉት 20 ዓመታት ያከናወኗቸው መሠረተ ልማቶች ግልጽ የልማት ፍኖተ ካርታና መስፈርት ሳይኖራቸው እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህም በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሳይፈጠር ቆይቷል። ስለዚህ ከአሁን በኋላ የሚሰሩ መሠረተ ልማቶች መስፈርት ወጥቶላቸው እና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው እኩል ተጠቃሚነትን በክልሎች መካከል በማስፈን ሕዝብን የሚጠቅሙ እንጂ በሕዝቦች መካከል ቅራኔን የሚፈጥሩ መሆን የለባቸውም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የ2011 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለምክርቤቱ አባላት አቅርቦ፤ የምክርቤቱ አባላት ከተወያዩበትና ከተከራከሩበት በኋላ በስድስት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ታዕቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ሶሎሞን በየነ