«ከሕገወጥ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በሦስት ዓመት ውስጥ በበርካታ ሰዎች ላይ ርምጃዎችን ወስደናል» – አቶ አዳነ ቆጭቶ

በአረንጓዴ ደኖች የተሸፈነው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፤ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት፣ የሕዝቦች ጥያቄዎች ተደምጠው ምላሽ ማግኘት መጀመራቸውን ተከትሎ 11ኛ ክልል ሆኖ የተመሠረተ ነው፡፡ የክልሉ በደን መሸፈን ተፈጥሯዊ «ኦርጋኒክ» የሆኑ ማር ፣ ቅቤና ሌሎች ምግብ ነክ ምርቶችን ለማምረት ምቹ ያደርገዋል፡፡

ይሁን እንጂ የወገኖቻቸውን ጤና እና ሕይወት ግድ የማይሰጣቸው፤ በአቋራጭም ለመክበር የፈለጉ ሕገወጦች ይሄንን ተፈጥሯዊ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል ለገበያ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ ተግባሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ከመሄዱ ጋር ተያይዞም፤ ጉዳዩ በሕዝብ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር በክልሉ ይስተዋላል፡፡

የዛሬው የተጠየቅ ዓምዳችንም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚስተዋሉ እነዚህን እና መሰል ከምግብና መድኃኒት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ምንነትና ሁኔታ፤ ችግሩን ተገንዝቦ ለማረም ብሎም ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብና መድኃኒት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ምን እየተሰራ እንደሆነ በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን የምግብ መድኃኒት ተቆጣጣሪ ኃላፊና ባለሙያ አቶ አዳነ ቆጭቶ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ባለፉት ወራት በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ሥራዎች ላይ ምን ተሰራ?

አቶ አዳነ፡– በክልሉ ሕገ ወጥ መድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ሥራው ሲታይ ምግብን ከባዕድ ጋር መቀላቀል “አዳልትሬሽን” ይታያል፡፡ ይህም በርበሬን ከቀይ አፈር ጋር፤ ጤፍን ከእብቅ፤ ቅቤን ከባዕድ ነገር እና ማርን ከሞላሰስ ጋር ቀይጦ ለገበያ ማቅረብ በክልሉ አልፎ አልፎ ይስተዋላል። ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ለሥራው በሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ቁጥጥር እየተካሄደ ነው። በዚህም ከኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒት ባለሥልጣን፤ ከክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ጊዚያት በምግብና መድኃኒት ከአራት ዙር በላይ ቁጥጥር ተደርጓል፡፡

ክትትልና ቁጥጥሩም በአብዛኛው በምግብ ላይ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም ከደረጃ በታች የሆኑ፣ ገላጭ ጽሑፍ የሌላቸው፣ ሀገር ውስጥ የተመረቱ ሆነው የሕግ ማዕቀፍ ያልተቀመጠላቸው እና የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ያላጸደቀላቸው እንደ ዘይት፤ የሕፃናት ምግብ፣ የሕፃናት ወተት፣ የታሸጉ ለስላሳና መሰል ምግብ ነክ ቁሳቁሶችን ተገኝተዋል፡፡ በዚህም ወደ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር ግምት የሚያወጡ ምግቦችን በመሰብሰብ እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡

በምግብ መከለስ ላይ በአብዛኛው ቅቤን ከባዕድ ነገር ጋር መቀላቀል ይስተዋላል። በርበሬ ለማስፈጨት በሚቀርብበት ጊዜ በወፍጮ ቤቶችና በእህል መጋዝን ቤቶች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 522 ሺህ 343 ብር ግምት የሚያወጣ ምርት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። በዞኖች የተገኙ ግኝቶችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንዲወገዱ የማድረግ ሥራ ተከናውኗዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሕገ ወጥ መድኃኒት ላይ ያለው የቁጥጥር ሥራ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አዳነ፡- በመድኃኒት ላይ ያለው ቁጥጥር ሲታይ ሰፊ ሥራን የሚጠይቅ ነው። እንደ ሀገር የወባ በሽታ መድኃኒት የለውም እየተባለ የሚነገርበት ደረጃ ላይ እየደረስን ነው፡፡ ይህም መድኃኒቶች፤ ደረጃቸውን፣ ጥራታቸውንና የአገልግሎት ጊዚያቸውን ሳይጠብቁ በሕገ ወጦች ስለሚዘዋወሩ ነው ችግሮች እንዲከሰቱ እየደረጉ ያለው፡፡ በዚህም ሕገወጥ ተግባር ምክንያት በመድኃኒቶች ላይ ያለው የፈዋሽነት ጥርጣሬ ደግሞ፣ እንደገና መድኃኒቶቹ በሕገ ወጥ መንገድ እንዲዘዋወሩ ያደረገ ነው፡፡

ይሄን የመድኃኒት ሕገወጥ ዝውውር ከመከላከልና መቆጣጠር አኳያም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ለአብነትም፣ ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ያልተመዘገቡ፤ ከውጭ ሀገር በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚገመት የወባ መድኃኒት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ክትትል እና ቁጥጥር ለሕዝቡ ሳይሰራጭ በፊት መያዝ ተችሏል፡፡

ይሄ ውጤታማ ሥራም በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የጅማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፤ የክልሉ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣ ዞኖችና ወረዳዎች በጥምረት በመሥራት የተገኘ ሲሆን፤ ቁጥጥር ከተደረገና ከተያዘ በኋላ መድኃኒቱ እንዲወረስና እንዲወገድ ተደርጓል። በተጨማሪም የሕግ ወጥ ነጋዴዎቹ ምርቱን የሚያገኙበት ምንጩ ከየት እንደሆነ ተጣርቶ በሕግ አግባብ የታየ ሲሆን፤ በአብዛኛው ከውጭ የሚገባው ከኬንያ ጋር በሚዋሰነው ምዕራብ ኦሞ ዞን መሆኑ ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ መልኩ፣ ሀገር ውስጥ ያልተመረተ ‹‹ክሎሮኪን›› የተባለ በባለሥልጣኑ ያልተመዘገበ መድኃኒት አብዛኛው በጋምቤላ በኩል በማስገባት በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ተገኝቷል፡፡ መድኃኒቱ በጉራፈርዳ አድርጎ በሚዛን ከተማ የሚገባ ሲሆን፤ በተደረገ ቁጥጥር በ19 የመድኃኒት ችርቻሮ መደብሮች ምርቱን ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በእነዚህም ላይ ርምጃ ተወስዷል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ትንባሆ አንዱ የሕዝብ ጤና ጠንቅ እየሆነ መጥቷል፡፡ በዚህ ላይ ያለው የቁጥጥር ሥራ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አዳነ፡- ከትንባሆ ቁጥጥር ጋር በተያየዘ ኢትዮጵያ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር የተፈራረመችው ስምምነት አለ፡፡ ይሄንኑ ስታንዳርድ አድርጋ እየሰራች ሲሆን፤ በክልሉም ስድስት የሚሆኑ ከተሞች ላይ ከፍተኛ ሥራዎች እየሰተራ ነው፡፡ ለእነዚህ ከተሞች የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ከምግብ መድኃኒት ቁጥጥር ባሥልጣን ጋር ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዚህም ከአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ፕላን የሚቀዳ የአንድ ዓመት እቅድ በማቀድ እየተሠራ ሲሆን፤ ከተሞችን ከትንባሆ ጭስ ጽዱ ለማድረግ በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራ ነው። በዚህም የክልሉ ዋና ከተማ ቦንጋን ከትንባሆ ጭስ ለማጽዳት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ይህም ሲሆን የፍትህ አካላትና የሕግ ባለሙያዎች የፖለቲካ አመራሮችና ሌሎች አካላት በተገኙበት ማህበረሰቡን የማስተማር ሥራ ተሰርቷል። አሁንም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የጤና ማስጠንቀቂያ ጽሑፍ የሌላቸው ሲጋራዎች ተሰብሰበው እንዲወገዱ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ምርቶቹ ከተሰበሰቡ በኋላ ከመወገዳቸው በፊት መረጃውን ለማህበረሰቡ ለማስገንዘብ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀም እንዲሰራጭ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል። ትንባሆ በጤና ላይ የሚያስከትለውን የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ለማህበረሰቡ በማስገንዘብ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ በመሥራት ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራ እንዲሰሩ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ምግብን ከባዕድጋር ቀላቅለው የሚሸጡ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን በሕግ እንዲጠየቁ ተደርገዋል?

አቶ አዳነ፡- ከምግብ ‹‹አዳልትሬሽ›› ጋር ተያይዞ የሚነሱ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በተለይም በምግብ መከለስ በቅቤ ላይ ሶስት መዝገቦች ናቸው ውሳኔ ያልተሰጠባቸው፤ በክልሉ ጨው ዳግም የማሸግ ፈቃድ ሳይወስድ ያመረተ አንድ ግለሰብ ምርቱ እንዲወገድና ቤቱም እንዲታሸግ በማድረግ በሕግ እንዲጠየቅ ተደርጓል። ይህ ሥራ የሚሰራው ምርቱ በላብራቶሪ ተመርምሮ ከደረጃ በታች መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሕገወጥ የመድኃኒት እና ምግብ አዘዋዋሪዎች ላይ ርምጃ ወሰዳችሁ?

አቶ አዳነ፡– ከሕገወጥ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በተለይም በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ በበርካታ ሰዎች ላይ ርምጃዎችን ወስደናል። በሕግ አግባብ የተቀጡ ሰዎችን ስናይ በ2014 ዓ.ም በምግብ ጋር በተያያዘ 16 ጉዳዮች ይዞ በ16ቱም ላይ እልባት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመት ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ 11 ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ርምጃም ተወስዶባቸዋል፡፡ ይህን ርምጃ በምንወስድበት ጊዜ በተለይም በክልሉ በሚገኝ አንድ ዞን ላይ ከፍተኛ ሕገ ወጥ ሥራ ይሰራ ነበር። ይህን ተከትሎ በዞኑ እስከ ጎጥ ድረስ ክትትል በማድረግ ሕገ ወጦችን ለሕግ ማቅረብ ተችሏል፡፡ በሕገ ወጦች ላይ ክስ በመመስረት በእስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረግ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይ ሕገ ወጥ መድኃኒት ዝውውር ጋር በተያያዘ ዳውሮ ዞን በአራት ሰዎች ላይ ክስ መስርቶ የአምስት ዓመት እስራት እንዲፈረድባቸው አድርጓል። በ2015 ዓ.ም በደቡብ ሼኮ ዞን ቤንች ወረዳ ላይ እንዲሁ በእስራት የተቀጡ አሉ። በዚህ ዓመትም በቤንች ላይ እንዲሁ በሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውር በአምስት ዓመት እስራት የተቀጡ ሰዎች አሉ፡፡ በቅርቡ ክስ የተመሰረተባቸው እና እልባት ያላገኙ በክትትል ውስጥ ያሉ መዝገቦችም አሉ። በሕግ ማስፈጸሙ ላይ የክልሉ መንግሥት ጠንክሮ እየሰራ ነው ፡፡ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ርምጃ እንዲወሰን እየተደረገ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ክልሉ በቅርብ ጊዜ የተመሠረተ እንደመሆኑ መጠን የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን ለመስራት ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችለው አደረጃጀት ፈጥሯል ብለው ያስባሉ?

አቶ አዳነ፡– የሰው ኃይል አደረጃጀት በተመለከተ በቀጥታ የጤና ሚኒስቴር አደረጃጀትን በመጠቀም እየተሠራ ነው፡፡ አደረጃጀቱም የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ራሱን አስችሎ በፌዴራል ደረጃ አለ። በተጨማሪም በጤና ሚኒስቴርም የጤናና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር ተብሎ ራሱን ችሎ በዴስክ የሚመራ መዋቅር አለ። በክልሉም እነኚህን አደረጃጀቶች በቀጥታ በመጠቀም በሁለት ዳይሬክቶሬቶች እንዲመራ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- ባላችሁ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ውጤታማ የቁጥጥር ሥራ መሥራት ያስችላል ብለው ያስባሉ?

አቶ አዳነ፡– ውጤታማ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የክልሉ አመራር ቀና አስተሳሰብና ለሥራው ተነሳሽነት ስላለው ክልሉ የበጀት እጥረት ቢኖርበትም የቁጥጥር ሥራውን ለመስራት ብዙም ጫና አልፈጠረበትም። የክልሉ ተቆጣጣሪ፣ ዞን ላይ ያለውን የቁጥጥር እና ፈቃድ መስጠት ሥራዎች በትብብር እንዲሰሩ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ሠራተኞች የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሙያዎች ስላሉ የክልሉና የፌዴራል የቁጥጥር ባለሥልጣን በጋራ በመሆን ውጤታማ ሥራ እንዲሰራ ቅንጅት ተፈጥሯል፡፡ ሆኖም በክልሉ ያለው የበጀት እጥረት በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለሚስተዋለው የሰው ኃይል እጥረት አብይ ምክንያት ነው፡፡

በክልሉ ከዚህ በፊት ሁለት ባለሙያዎች ብቻ የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከሁለት ወደ ሶስት ከፍ ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በቂ የሰው ኃይል የለም ተብሎ የተስተጓጎለ ሥራ የለም፡፡ ስለዚህ ማን ከማን ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ በመግባባት ላይ የተመሠረተ ሥራ ስለሚሠራ ውጤታማ እየሆነ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቂ ባለሙያ በሌለ ቁጥር ከሥራው ጫና አንጻር ለብልሹ አሠራር የሚዳረጉበት አግባብ አይፈጠረም? እስካሁንስ ምን ያህል ቁጥጥር ይደረግ ባቸዋል?

አቶ አዳነ፡– ባለሙያዎች ለሙስናና ብልሹ አሠራሮች እንዳይጋለጡ የኢንተለጀንስ ሥራዎችን በተለያየ መልኩ ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም ተቆጣጣሪዎች ባነሱ ቁጥር ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚጋለጡበት ሁኔታ ስላለ ከላይ እስከ ወረዳ ያለው አመራር በቅንጅትና በመደጋገፍ እየሠራ ነው፡፡ በዚህም የቁጥጥር ባለሥልጣኑ ሥራውን በተሻለ ደረጃ እንዲያከናውን አስችሎታል። ነገር ግን በተቋሙ ሊኖር የሚችለው የሰው ኃይል ቁጥር በባለሙያ ብቻ 17 ነው፡፡ ይህ በቀጣይ የሚሟላ ይሆናል፡፡

በዚህ ረገድ ተቋሙ በክልሉ ከተቋቋመ ሶስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የራሱ የሆነ አዋጅ፤ ደንብና መመሪያም አለው፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የጸደቀ ደንብ አዋጅ 4/2014 ላይ በመመስረት የራሱ የሆነ አደረጃጀትና አሠራር ፈጥሮ እየሠራ ነው፡፡ በደንቦች ከተቀመጠው መካከል የቁጥጥር ሥነ-ምግባር መመሪያ አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም ተቆጣጣሪ በጥቅማ ጥቅም ከትንሹ ሻይ እስከ ትልቁ ገንዘብ ድረስ ሊታለል ይችላል፡፡ ሆኖም በሥነ ምግባር ደንቡና መመሪያው መሠረት ደንቡን ተላልፎ ቢገኝ ሊከተል የሚችለው ቅጣት በግልጽ ተቀምጧል።

ለምሳሌ፣ በአንዳንድ ዞኖች ላይ የምርት ፈቃድ አሰጣጥ ስህተቶች ነበሩ፡፡ ለስህተቶቹ የእርምት ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ፈቃድ ሲሰጥ ተቋሙን ማየት፤ ምርት አቅራቢው ያለው የሙያ ፈቃድ እና ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ መስፈርቶች ሊሟሉ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ በቤንች ሸኮ ዞን ሥራቸውን በአግባቡ ባልተወጡ ሁለት ባለሙያዎች ከሥራ ታግደው ተጠያቂነት እንዲኖር እየተደረገ ነው። እነዚህ የዲሲፕሊን ግድፈት የተገኘባቸው ሠራተኞች አሁን ላይ የዲስፕሊን ጉዳያቸው እየታየ ነው፡፡ የዲስፕሊን ውሳኔው ሲያልቅ ወደ ሥራ የሚመለሱበት ወይም ወደ ሌላ መደብ የሚሄዱበት አለበለዚያም ቀጥታ ከሥራ የሚሰናበቱበት ሁኔታዎች ይኖራል፡፡

ይሁን እንጂ እያንዳንዱን ባለሙያ ከላይ እስከታች እንዲታሰር እና እንዲቀጣ ለማድረግ በተለይ ደግሞ ታች ላይ ስትሄድ በአብዛኛው በመረጃ እና በማስረጃ አይደገፍም፡፡ መረጃ እና ማስረጃ ባልተደራጀበት አግባብ ሰዎችን በሥነ ምግባር ጥሰት ተጠያቂ ማድረግ መመሪያው አይፈቅድም፡፡ የክልሉ መንግሥት ከሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም አበረታች ለውጥ ተገኝቷል።

አዲስ ዘመን ፡- አጠቃላይ በክልሉ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር እና ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቱ ላይ ያጋጠሙ፤ በሥራችሁ ላይም ጫና የፈጠሩ ችግሮች ምንድን ናቸው?

አቶ አዳነ፡– በክልላችን በሕገ ወጥ ምግብ እና መድኃኒት አዘዋዋሪዎች ላይ በሚደረገው ቁጥጥር እና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የተለያዩ ችግሮች ቢስተዋሉም፤ የፍትህ አካላት የሚፈጥሩት ችግር ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ሲባል የፍትህ አካላት ሕገ ወጦችን ያግዛሉ ወይም ለሕገ ወጦች ሽፋን ይሰጣሉ ለማለት አይደለም፡፡ አንድ ግለሰብ በሕገ ወጥ መንገድ መድኃኒት እና ምግብ ሲያዘዋውር ተይዞ ፍርድ ቤት በሚቀርብበት ጊዜ ለተፈጠረው ችግር ፍርድ ቤቱ ፈጣን ውሳኔ ሲበይን አይታይም፡፡

ጥራት የጎደላቸው ምግብ እና መድኃኒቶች በሰዎች ጤና እና ሕይወት ላይ የሚፈጥሩት ችግር እየታወቀ የፍትህ አካላት አፋጣኝ ውሳኔ የማይወስኑ ከሆነ በሰዎች ጤና እና ሕይወት ላይ አደገኛ ችግር መፍጠራቸው የማይቀር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የፍትህ አካላት ፍትህን በማጓተት የሚፈጥሩት ችግር እንደ ክልል አደገኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህን ለማስተካከል ለፍትህ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እየሰጠን እንገኛለን፡፡

የፍትህ አካላት ለችግሩ ቶሎ እልባት አለመስጠታቸው የህብረተሰቡን ጤና እና ሕይወት ከማወኩም ባለፈ ፤ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች የሥራ ሞራላቸው ላይ አሉታዊ ጥላ እንዲያጠላ እና ቁርጠኝነታቸው እንዲቀንስ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከፍርድ አሰጣጥ ሂደቱ መዘግየት ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ ተብለው የተያዙ ምርቶች ውሳኔ እስከሚሰጥባቸው ድረስ ለህብረተሰቡ የሚሸጡበት አግባብ አለ?

አቶ አዳነ፡– አንድን ሕገ ወጥ ምርት የሚያመርት እና የሚያከፋፍል ሰው ባገኘህ ጊዜ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር እንዲሆን ይደረጋል። ቀጥሎም ሂደቱን ጠብቆ ክስ ይመሰረትበታል፡፡ ክሱን መስርተህ ምስክር ከቀረበ በኋላ ለፍርድ ቤት ዋቢ እንዲሆን የሙያ ትንተና ይያይዛል። ከዚህ በተጨማሪ የምግብ እና መድኃኒቱን የጥራት ጉድለት በላብራቶሪ ተመርምሮ እንዲመጣ ይደረጋል። ነገር ግን በዚያ ላይ ውሳኔ ከመስጠት አንጻር ፍርድ ቤቶች ሲዘገዩ ይስተዋላል፡፡

ፍርድ ቤት ዘገየ ማለት ግን ጥራት የሌለው ምርት ይሰራጫል ማለት አይደለም። ምክንያቱም እንደ ክልል አንድ የሚሠራበት አሠራር አለ፡፡ ይህም ስለምርቱ የተጣራ መረጃ ከተገኘ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ጉባኤ ተካሄዶ በቃለ ጉባኤ ምርቱ እንዲወገድ ይደረጋል። ስለሆነም የተጣራ ማስረጃ ባገኘን ጊዜ ፍርድ ቤቶችን ሳንጠብቅ በቃለ ጉባኤ ጥራታቸው ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን እናስወግዳለን፡፡ ይህ ሲደረግ በአዋጅ ቁጥር 11/12 ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ መሠረት ተደርጎ እንጂ እንዲሁ የሚወሰድ ርምጃ አይደለም፡፡ በአዋጁ መሠረት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እንዲወገድ ይደረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁን የጸደቀው ደንብ ከመጽደቁ በፊት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምን ምን ችግሮች ያጋጥሙት ነበር? አሁንስ ደንቡ ምን ምን ችግሮችን ይቀርፋል?

አቶ አዳነ፡– ይህ ደንብ ከመጽደቁ በፊት ቀጥታ የምንጠቀመው የፌዴራሉን አዋጅ 11/12 ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ግን የመድኃኒት መጋዝኖች እና ከመድኃኒት ቤቶች ጋር በተያያዘ ዝርዝር መመሪያ የለም፡፡ ከዚህ በፊት 2006 ዓ.ም ላይ የወጣ የፌዴራል የምግብ እና መድኃኒት ችርቻሮ ሕግ ነበር፡፡ እዚያ ላይም የሙያ ደረጃን በተመለከተ ወጥነት አልነበረውም፡፡

ስለሆነም አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሌላ ደንብ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ክልሉም ከዚህ ደንብ ጋር የተገናኘ የራሱን ደንብ አውጥቷል። ይህን ደንብ እንደ ሕግ ለማካተት የሙያ ማህበራት በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚህም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ የተለያዩ ችግሮችን መቅረፍ ያስችላል የሚል እምነት ተጥሎበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከምግብ ጋር ባዕድ ነገር ቢጨመር በቀላሉ የምትለዩበት አሰራር በክልል ደረጃ አለ?

አቶ አዳነ፡- የምግቦች ተፈጥሮ የተለያየ በመሆኑ በቀላሉ ባዕድ ነገር የተጨመረባቸውን ምግቦች መለየት ይከብዳል፡፡ ይህ ሲባል በቀላሉ የሚለዩ የለም ለማለት አይደለም። በቀላሉ የሚለዩ እንዳሉ ሁሉ በቀላሉ የማይለዩ እና የላብራቶሪ እገዛ የሚፈልጉ አሉ። ለምሳሌ ከበርበሬ ጋር ባዕድ ነገር ቢቀላቀል በቀላሉ መለየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ቅቤ ፣ ማርን ላይ ባዕድ ነገሮች ቢጨመሩ በቀላሉ መለየት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ዓይነት ምግቦችን ጥራት ለማወቅ የግዴታ ላብራቶሪን እንጠቀማለን፡፡

ለዚህም የሚያጠራጥር ምግብ ሲኖር እና ጥቆማ ሲደርሰን የተባለውን ምግብ በሌሎች ሰዎች አስገዝተን ወደ ላብራቶሪ እንልካለን። ጉድለት ከተገኘበት በምርቱ ላይ ቅኝት ሥራዎች እንዲሰሩ ይደረጋል። ቅኝት የሚሰራው ያችን ቦታ ለማጠር ነው፡፡ ምርቱ ችግር ካለበት ምርቱን የሚያከፋፍሉት ሰዎች እና ምርቱ በፖሊስ እንዲያዙ ይደረጋል፡፡ ቀጥሎም ጉዳዩ ለመርማሪ ፖሊስ ይሰጣል። ከዚያም ምርቱ እንደገና ወደ ላብራቶሪ ይላክና የውጤቱ እውነታነት ይረጋገጣል። በዚህ መልኩ ሕገ ወጦች እንዲያዙ ይደረጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን

አቶ አዳነ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም

Recommended For You