
በአመጋገብ ሥርዓት ዙሪያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ባጠናው ጥናት በኢትዮጵያ አንድ በመቶ የማይሞላ ሰው ብቻ ጤነኛ የአመጋገብ ሥርዓትን እንደሚከተል አመላክቷል፡፡ ይህ ደግሞ ከአካላዊ ጤና ጀምሮ እስከ አዕምሯዊ ጤና ቀውስ የሚያስከትል ችግር መሆኑን ሳይንስ ያስረዳናል፡፡ ለመሆኑ ሥርነቀል ለውጥ የሚሻው የአመጋገብ ሥርዓታችን እንዴት ሊታረም ይገባል?
በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ አማካሪ አቶ ቢራራ መለሰ፤ በሀገሪቱ አብዛኛው ማህበረሰብ የአመጋገብ ሥርዓት የተስተካከለ አይደለም ይላሉ፡፡ ይህ የምግብ አለመመጣጠን ችግር ሕፃናት፣ እናቶችና ወጣቶች ላይ በስፋት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡
የተመጣጠነ አመጋገብ ሥርዓት በንጥረ ነገር የበለጸጉ የምግብ ምድቦች መመጣጠን መሆኑን ገልጸው፤ እንደየዕድሜ ክልሉ ተከፋፍሎ የሚታይ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ የእነዚህም መብዛትና ማነስ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ነው የሚያብራሩት፡፡
አብዛኛው ማህበረሰብ በቀን መመገብ ስላለበት የምግብ አይነትና መጠን ዙሪያ የግንዛቤ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይስተዋላል የሚሉት ቢራራ፤ ይህም እንደስጋ እና መሰል ውድ ዋጋ ያላቸው ምግቦችን በብዛት መጠቀም የተመጣጠነ ምግብ ነው የሚልን የተሳሳተ ሃሳብ እንደሚጨምር ነው የጠቀሱት፡፡
አቶ ቢራራ እንደሚሉት፤ ዕድሜው ከሁለት ዓመት በላይ የሆነ ሰው የተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት ተከትሏል የሚባለው በቀን በሚመገበው ምግብ ውስጥ 6 የምግብ ምድቦችን መመገብ ሲችል ነው፡፡ በተመሳሳይ ከስድስት ወር ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ያሉ ሕፃናት ጡትን ጨምሮ በቀን አምስት የምግብ ምድቦችን መመገብ ይገባቸዋል፡፡ እንዲሁም የሚያጠቡ እናቶች በቀን አምስት የምግብ ምድቦችን ካገኙ የተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት እየተከተሉ ነው፡፡
ታዲያ ሰውነታችን የሚያገኘው ምግብና ንጥረ ነገር በሚፈለገው ልክ ሳይመጣጠን ሲቀር ከልክ ላለፈ ውፍረትና መቀንጨር ይዳርጋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡
አቶ ቢራራ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ኢንስቲትዩት ያጠናውን ጥናት ጠቅሰው እንዳብራሩትም፤ 20 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት በማህጸን እያሉ በእናቶች አመጋገብ አለመስተካከልና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ይቀነጭራሉ፡፡ ይህ ደግሞ አዕምሯዊ እና አካላዊ እክል ይፈጥራል፡፡ ከዚህም ባለፈ ሲወለዱ አካላቸው ያልተስተካከለ ሊሆን ይችላል፡፡
እንዲሁም በተስተካከለ ምግብ እጥረት ምክንያት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት 39 በመቶ የመቀንጨር፣ 22 በመቶ ክብደታቸው ከሚጠበቀው በታች መሆን እና 11 በመቶ ሕፃናት በአጭር ጊዜ የምግብ እጥረት ምክንያት ይቀጭጫሉ፡፡ በተጨማሪም 22 በመቶ እናቶችም ክብደታቸው ከሚጠበቀው በታች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተቃራኒው የምግብ ንጥረ ነገር ከሚፈለገው በላይ ሲሆን ከልክ ላለፈ ውፍረት ይዳርጋል ያሉት አቶ ቢራራ፤ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ስምንት በመቶ የሚሆኑ ሕፃናት ተጠቂ ሲሆኑ፤ ችግሩ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣል ሲሉ የጉዳዩን አስጊነት አብራርተዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴርም በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የምግብ አለመመጣጠን፣ የምግብ ደህንነትና ጥራት ችግሮችን የለየ መሆኑን አስታውቀው፤ በቂ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና ቀጣይነት ያለው ተደራሽነትን በማረጋገጥ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ሥርዓትና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ በማዘጋጀት የ10 ዓመት ስትራቴጂ ከመንደፍ ጀምሮ በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና የትምህርት ክፍል ዲን የሥነምግብ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አበራ ላምቤቦ በበኩላቸው፤ አንድ ሰው የተስተካከለ አመጋገብ እየተመገበ ነው ለማለት የሚመገብበት ሰሀን መልከ ብዙ ወይም ህብረቀለም መሆን አለበት ይላሉ፡፡
ይህም ማለት የተለያየ ምግብ ይዘትን ያካተቱ ምግቦችን አሰባጥሮ መመገብ ሲሆን፤ እንደ ቃሪያ፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ስኳር ድንች የመሳሰሉት አትክልት ምርቶች መጠቀም ከፍተኛ ንጥረ ምግብ እና ቫይታሚን የበለጸጉ ከመሆኑም በላይ የሆድ ድርቀትን የሚከላከልና የምግብ ውህደትን ለማፋጠን የሚረዱ ናቸው ብለዋል፡፡
እንዲሁም ከፍራፍሬ እንደ ሎሚ፣ አቩካዶ፣ ብርቱካን፣ ሙዝ የመሳሰሉትንና ከጥራጥሬ እንደስብዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ጤፍ በመጠቀም የተስተካከለ በስነምግብ ዘዬ መከተል አስፈላጊ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
መከተል ያለብን የአመጋገብ ሥርዓት በየዕድሜ ክልሉ እንደሚለያይ የተናገሩት ዶክተር አበራ፤ በግንዛቤ እጥረት ምክንያት አሰባጥሮ መመገብን እንደቅንጦት ይታያል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምግቦች በተመጣጣኝ ዋጋ ብሎም በጓሮ የሚገኙ ምርቶች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ የሚስተዋለውን የገበያ አለመረጋጋት ለመከላከል የራስን ምርታማነትን በመጨመርና የምግብ ጤንነትን በመጠበቅ ለሰውነት ዕድገት፣ የበሽታ መከላከል አቅምን ማሳደግና ጤናን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
በሀገሪቱ ለሚስተዋለው የግንዛቤ እጥረትም በስነምግብ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ማነስ አንዱ ምክንያት ነው ያሉት ዶክተር አበራ፤ ባለሙያ በበዛ ልክም ወደማህበረሰቡ የመድረስ ዕድል ስለሚጨምር ብቁ የስነምግብ ባለሙያዎችን በብዛት መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ይህ የስነምግብ ችግር መከላከል የሚቻል ነገር ግን ትልቅ ሀገራዊ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም