“የጋራ ጥረታችን ለዲጂታል ኢትዮጵያችን !”

በ2015 በተደረገው አንድ ጥናት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት ብቻውን 296 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጥቅም ያስገኘ ሲሆን ይህም በአማካይ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሥራዎችን በየዓመቱ ከመፍጠር ጋር በእኩል እንደሚታይ ተመልክቷል። የክሬዲት ካርድ፣ ዴቢት ካርድ፣ ኢ-ዋሌት፣ የባንክ የማስተላለፍ ዘዴና የካሽ ክፍያ ዘዴ የሚባሉት ደግሞ የዚህ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት ዘዴዎች ሲሆኑ ሀገራችን በዚህ ዘርፍ ይቀራታል።

ዓለማችን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርት 79 ትሪሊየን አጠቃላይ ዓመታዊ ሀብት የምታመነጭ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ስድስት ትሪሊዬን ዶላር የሚመነጨው በቴክኖሎጂ ብቻ ነው ። ይህም በየዓመቱ 18 ትሪሊዮን ከምታመነጨው አሜሪካና 11 ትሪሊዮን ከምታመነጨው ቻይና ቀጥሎ ሶስተኛው ግዙፍ የኢኮኖሚ ሀገረ ያደርገዋል። ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መካከል ያለው ትልቁ የኢኮኖሚ እድገት ልዩነት ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀምና ባለመጠቀም መካከል ያለ ልዩነት ብቻ ስለሆነ ቴክኖሎጂ ለእድገት ዋልታ አድርጎ መጠቀም ግድ ይላል ።

በአሁኑ ጊዜ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዓለምን እየተቆጣጠረ ይገኛል። በኢትዮጵያም መንግሥት የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢኮኖሚውን ለማሳደግና የማኅበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንትን አስመልክቶ ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎታቸውን በቀላልና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተደራሽ እያደረጉ ናቸው።

ኢትዮጵያም በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ከተቀመጡት አንኳር ጉዳዮች መካከል የዲጂታል መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ማስፋት፤ የዳታ ማዕከላትን መገንባት እንደሚገኙበት፤ እንዲሁም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የዲጂታል መታወቂያ ማዘጋጀትና የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ፣ የኢ-ኮሜርስና የመንግሥትን አገልግሎት ዲጂታል በሆነ መንገድ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በዘርፉ አስቻይ ምህዳር ለመፍጠር በክህሎት በፋይናንስና በሕግ ማዕቀፍ ረገድ ዝግጁ በማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር)ገልጸዋል።

የዲጂታል ሳምንት ዝግጅትም ለማኅበረሰቡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ለማስተዋወቅ፤ ብሎም ኅብረተሰቡ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤን በመፍጠር የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የሚጠቅም መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው፤ መንግሥት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለልማት እና ለዕድገት በማዋል የማኅበረሰቡን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ እያከናወናቸው ስላሉ ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴዎች የሚቀርቡበት ይሆናል።

በተጨማሪ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ገጽታዎችን የሚያጎሉ የተለያዩ አሳታፊ ተግባራትና ትምህርታዊ ዝግጅቶች የሚካሄዱበት ሲሆን፤ ማኅበረሰቡ በዚህ ረገድ የተሠሩ ሥራዎችን በመከታተል ሊገለገል እንደሚገባ አሳስበዋል። የመጀመሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ “የጋራ ጥረታችን ለዲጂታል ኢትዮጵያችን” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከየካቲት 18 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ መርሀ ግብሮች የሚከበር ሲሆን፤ ከሁሉም ክልል የሚመለከታቸው አካላትና የፌዴራል ተቋማት የሚታደሙበት መሆኑም በ”አዲስ ዘመን”ዘገባ ተመልክቷል።

ቀደም ባለ መጣጥፌ እንዳስነበብሁት፤ ዓለማችን ሶስተኛውን የኢንዱስትሪ አብዮት አገባዳ ወደ አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ማማተር ከጀመረች ሰነባበተች። ሶስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ከ20ኛው መክዘ አጋማሽ ዛሬ ድረስ የቀጠለው ሲሆን ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በይነ መረብ ወይም ኢንተርኔት፣ አውቶሜሽን፣ ሮቦቲክስና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች የተስፋፉበትና በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉበት ነው። ብዙ ሊቃውንት አሁን የምንገኝበትን ጊዜ የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት የተጀመረበት፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቀናጀበት፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ወደ ሥራ የገባበት፣ በይነ መረብ እያንዳንዱን የሕይወት ቅንጣትና የኢኮኖሚ ዘርፍ ማዳረስ የጀመረበት ከመሆኑ ባሻገር በአኗኗራችንና በግንኙነታችን ላይ ዕለት ዕለት እየተገለጠ ያለ ነው።

እጃችን የገባን ቴክኖሎጂ ተለማምደነውና ተዋውቀነው ሳናበቃ እጃችን ላይ የሚያረጅበትና በፍጥነት የሚለዋወጥበት ዘመን ነው። ዓለማችን ዲጂታል እየሆነች ነው። በዲጂታል ቴክኖሎጂና በኮሙኒኬሽን ኔትወርክ እየተሳሰረች በአኗኗራችን፣ በሥራችንና በዕለት ተዕለት ግንኙነት ላይ ለውጥ እየመጣ ነው። ከዚህ ጋር የተያያዙ ዲጂታል መሣሪያዎች፣ የሶፍትዌር መተግበሪያዎች፣ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ መድረኮች፣ በመረጃ ወይም በዳታ ላይ የተመሠረቱ እንደ መረጃ የማፈላለግና ኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እየተስፋፉ ነው። ፍጥነት፣ ተለዋዋጭነት፣ የማያቋርጥ መሻሻል፣ ወዘተረፈ የዲጂታል ዓለሙ መለያ ነው።

ለፈጠራና ለንግድ አዳዲስ ዕድሎችን ይዞ እንደመጣው ሁሉ የዜጎችን ግለ ሕይወት ወይም ፕራይቬሲ፣ ደህንነትና ግንኙነት አደጋ ላይ እየጣለ ነው። የተሳሳተና ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ እንደ እንጉዳይ እየፈላ፤ በይነ መረብ፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ የሞባይል ስልኮች፣ ክላውድ፣ ቢግ ዳታ አናሌቲክስ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትና ብሎክቼይን የዲጂታል ዓለሙን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገሩት ይገኛል። እነዚህ የቴክኖሎጂ እምርታዎች መረጃን በቀላሉ እንድናጋራና እንድንለዋወጥ፣ ከሌሎች ጋር እንድንተባበር፣ ሂደቶችን አውቶሜት እንድናደርግ፣ የዲጂታል ምርቶችንና አገልግሎቶችን እንድናስፋፋ በመጋዝ አኗኗራችንና አሠራራችን አቅልለውልናል።

ወደ አህጉራችን አፍሪካ ስንመጣም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ እናገኘዋለን። ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች በፍጥነት እያደጉ ነው። የተንቀሳቃሽ ስልክና የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች መበራከት ለአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚ ማበብ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ዲጂታል አፍሪካ ሰፋ ያለ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ማለትም የሞባይል ስልኮችን፣ ማህበራዊ ሚዲያን፣ ኢ-ኮሜርስን፣ የዲጂታል ክፍያን፣ ፊንቴክን፣ ኢ-ጤናን፣ ኢ-ትምህርትን እና ኢ-ግብርናን የሚያካትት ነው።

በአህጉሩ ለዲጂታል ፈጠራ መስፋፋትና መጎልበት የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተ ያለው ደግሞ የሞባይል ስልክ ሲሆን ለበይነ መረብ ተደራሽነትና ለዲጂታል አገልግሎት መስፋፋትም የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ሞባይል መኒ በአፍሪካ እያደገ ለመጣው የፋይናንስ አካታችነት እንዲሁ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታት የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጽዕኖ በአፍሪካ አሁን ከሚገኝበት ይልቅ እያደገና እንደ ዋርካ እየሰፋ እንደሚሄድ ሀገራችን ጥሩ ማሳያ ናት። የዲጂታል መሠረተ ልማት መስፋፋት ለዲጂታል ኢኮኖሚው ጥሩ መደላድል እየፈጠረ ነው። ሆኖም ተግዳሮቶች የሉበትም ማለት አይደለም። የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነት በእኩል ደረጃ አለመገኘት ወይም ዲጂታል ዲቫይድ ቀዳሚው ችግር ነው። ዜጋው ስማርት ስልኮችን፣ ታብሌቶችን፣ ላፕቶፖችንና በይነ መረብን በቀላሉ አለማግኘቱ የመረጃ ተደራሽነቱን ኢፍትሐዊ አድርጎታል። የዲጂታል ክህሎት እጥረትና የዲጂታል ኢንቨስትመንቱ ውስን መሆን ሌላው የዘርፉ ማነቆ ነው። ለመሆኑ በሀገራችንስ ዲጂታል ኢኮኖሚው በምን ሁኔታ ነው የሚገኘው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በአንድ መድረክ እንደገለጹት ከሞላ ጎደል የዲጂታል ኢትዮጵያን ምስል ቅንብብ አድርጎ ያሳያል ብዬ አስባለሁ። የመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ድርሻን ለማሳደግና ቀልጣፋ ለማድረግ እስካሁን የ159 ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴ እንዲተገብሩ መደረጉን ያስታወቁት ሚንስትሩ፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራት 79.2 ቢሊዮን ብር ክፍያ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መከፈሉን፤ ኢትዮ ቴሌኮም የመንግሥት የኤክትሮኒክስ ክፍያ ድርሻ ለመወጣት እንዲያስችለው የሪፎርም ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

ለአብነትም የታክስ ክፍያ አሰባሰብ ሥርዓቱ በቴሌ ብር እንዲከፈል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን፤ በባንኮች በኩል ተከፋይ የሚሆነውን የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በቀጣይ በቴሌ ብር እንደሚሆን መገለጹን ተከትሎ ኩባንያው የሚጠብቀው ቅድመ ዝግጅትና ያለው አቅም ምን ይመስላል? በሚለው ዙሪያ የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ኮሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት ለሪፖርተር እንዳስረዱት ፣ በመንግሥት የተያዙት ጉዳዮች ወቅቱን ጠብቀው ቢገለጹ እንደሚሻል ተናግረው፣ ነገር ግን ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማቅረብ የሚያስችል በቂ ዝግጅትና አቅም እንዳለው አስታውቀዋል።

ተቋሙ በሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎቱ እስካሁን ከ32 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አገልግሎት እየሰጠ እንደመገኘቱ መጠን የዘረጋው ሲስተም አገልግሎቱን በቀላሉ ለመስጠት ያስችለዋል። የትኛውም ውሳኔ ከሚመለከተው አካል ከመጣ መሥራት እንደሚቻል፤ ደመወዝ በቴሌ ብር መከፈሉ የተቋማትን ቅልጥፍና በመጨመር የሚያደርገውን አስተዋጽኦ በመግለጽ፤ በዕረፍትና በበዓላት ወቅት የሚውል የደመወዝ ክፍያ ቀንና ተዛማጅ ጉዳዮች ለደመወዝ ከፋዩም ሆነ ተከፋዩ በሚያመች ለመክፈል እንደሚያስችል አቶ መሳይ ይናገራሉ። እስካሁን ባለው አገልግሎቱ እንደ ደመወዝ ዓይነት የጅምላ ክፍያ በሚከፈልበት ወቅት ሠራተኞች የደመወዛቸውን እስከ 35 በመቶ ያለምንም ዋስትና መበደር እንደሚችሉ፤ ኩባንያው በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ አማራጮች እንደሚያቀርብና እስካሁን ድረስ ግን ከሚመለከተው አካል የመጣ አቅጣጫ አለመኖሩን አቶ መሳይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ ዝውውርን ይፋ ካደረገበት ግንቦት 3/2013 ዓ.ም ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት 2015 ዓ.ም ድረስ 32.2 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳፈራ፤ በአገልግሎቱም እስካሁን ከ375.2 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ግብይቶች (ትራንዛክሽንስ) እንደተፈጸመ አስታውቋል። እንዲሁም የነዳጅ ክፍያ በአስገዳጅነት በቴሌ ብር እንዲፈጸም ከተደረገበት ከሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ 2.7 ቢሊዮን ብር ግብይት መፈጸሙ ታውቋል። ስለ ዲጂታል ክፍያ ወቅታዊ ሁኔታ ካነሳሳሁ ላይቀር፤ የዲጂታል ኢትዮጵያን ታሪካዊ ዳራ መለስ ብለን እንቃኝ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል በኢትዮጵያ መንግሥት የሚመራ ተነሳሽነት ነው። ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ እና የ10 ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ ሀገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጀንሲ ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሠረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነትን በመለየት የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉ አራት ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎችን ለይቷል። ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ቱሪዝም ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች ናቸው።

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምንድነው?

ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን÷ በአካል ከሚደረጉ ግንኙነቶች ወጥቶ የዲጂታል አሠራሮችን በመተግበር ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመድረስ ባለ ሂደት ውስጥ ያለ “ጉዞ” ነው። የዲጂታል የሽግግር ጉዞ በመንግሥት፣ በንግድ ድርጅቶች እና በማኅበረሰቡ መካከል ግንኙነት በአካል ይካሄድ ከነበረበት አናሎግ ኅብረተሰብ ወጥቶ ግንኙነትና ልውውጦች በበይነ መረብ በጣም ፈጣን፣ ርካሽ፣ እና ደህንነቱ አስተማማኝ የሆነን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወደሚካሄዱበት የተቀናጀና አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚደረግ ጉዞ ነው።

ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያመለክተው የተሻሻለ የኔትወርክ ግንኙነቶችን እና እርስ በርስ ተያያዥነት ያላቸውን የዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም የሚደረግ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ነው።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከአናሎግ ኢኮኖሚ ይጀምራል። በአናሎግ ኢኮኖሚ ውስጥ በዜጎች በመንግሥትና በንግድ ድርጅቶች መካከል ያለው ግንኙነት የዲጂታል ቴክኖሎጂን የማይጠቀም እና በአካል የሚደረግ ነው። ከአናሎግ ኢኮኖሚ ቀጥሎ የሚገኘው ደግሞ ዝቅተኛ የዲጂታል ተደራሽነት ነው። በዚህ ውስጥ ውስን የዲጂታል መሠረተ ልማት ይኖራል፤ የተወሰኑ የዲጂታል ማሳያዎች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞው ይቀጥልና አናሎግ ግን የዲጂታል አሠራር እያደገ ይሄዳል። በዚህ ውስጥ አብዛኞቹ አገልግሎቶች አናሎግ የሆኑበት፣ ግልፅ የሆነ የዲጂታል ራዕይ ካልተቀናጁ አገልግሎቶች ጋር ያሉበት እና የሚተገበርበት ነው። ይህ አናሎግ እና ያልተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት ደግሞ የተቀናጀ የዲጂታል ሥርዓትን ይወልዳል። በዚህ ውስጥ የላቀ፣ የተቀናጀ የዲጂታላይዜሽን አገልግሎትና ጠንካራ አስቻይ ሥነ ምህዳሮች ይኖራሉ። የዲጂታል ኢኮኖሚም ይገነባል። የዲጂታል ኢኮኖሚ የተሟላ የዲጂታል ኢኮኖሚ የተተገበረበት፣ ከመንግሥትና የንግድ ተቋማት ጋር ለመገናኘት የዲጂታል አገልግሎትን የሚጠቀም ነው። የንግድ ተቋማት ፈጠራ የታከለበት አገልግሎት ያቀርባሉ። የመንግሥት ሥራዎችና አገልግሎቶች ዲጂታል ይሆናሉ።

አብዛኞቹ የንግድ መነሻዎች ዲጂታል ይሆናሉ።

ጎረቤት ሀገር ኬንያ ከ14 ዓመታት በፊት የጀመረችው ‘ኤምፔሳ’ የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ ሥርዓት አሁን ላይ 72 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ነዋሪ እየተጠቀመው ይገኛል ይላል ቮክስ ከተባል ድህረ ገጽ የተገኘ መረጃ። በሰባት ሀገራት የሚሰራው ኤምፔሳ 42 ሚሊዮን ንቁ ደንበኞችና 400 ሺህ ወኪሎች አሉት። 50 በመቶ የሚሆነው የኬንያ ዓመታዊ ጥቅል ምርት/GDP/በዚሁ ሥርዓት በኩል ይንቀሳቀሳል። በኡጋንዳ ከጠቅላላ ሕዝቡ የባንክ አካውንት ያለው 11 በመቶ ሲሆን ኤምፔሳን የሚጠቀመው ሰው ግን 42 በመቶ ተሸጋግሯል። እናም እነዚህ ሀገራት ከግብይት በኋላ ቁጥር ህ/ሽን ንገረኝ ማለት የተለመደ ነው ይለናል ቢቢሲ።

ሻሎም ! አሜን።

 

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You