ዛሬም እንደ ዓድዋ…

አውሮፓውያን አፍሪካን በመቀራመት ንድፋቸው (Scramble for Africa) በሚል ውጥን የአፍሪካ ሀገራትን ቅኝ ተገዢያቸው በማድረግ በብዙ እንደተሳካላቸው ታሪክ ምስክር ነው። ከዚህ በተቃራኒው ግን ኢትዮጵያ ለወረራ የመጣችባትን ጣሊያንን ድል በማድረግ ሉዓላዊነትና ክብሯን ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ ወራሪን አሳፍሮ የመመለስ ልዕልናን ሌሎች እንዲጎናጸፉ በማድረግ ለነጻነት እንዲታገሉ መንገድ አሳይታለች ።

የካቲት 23/1888 ዓ.ም ደግሞ ይሄ አኩሪ ገድል መከሰቻ በሆነው በዓድዋ ተራሮች የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ልዕልና እውን የሆነበት ነው። ወቅቱ በመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች በባርነትና በቅኝ ግዛት ላይ የነበሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም፤ የዓድዋ ድል ለወራሪዎች እፍረትን፣ ለቅኝ ተገዢዎች ደግሞ የአሸናፊነት መንፈስን የፈጠረ ነበር።

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ከ1847 እስከ 1983” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የታሪክ መጽሐፋቸው፤ “…ከሰፊው የፖለቲካና የታሪክ ትንታኔ አኳያ የዓድዋ ጦርነት ከአፍሪካ ምድር አዲስ ኃይል መነሳቱን የሚያበስር ይመስላል። የዚያች አህጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል ሊሆኑ እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል። እንዲያውም አሁን ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም ፣ ይህ ሁኔታ (ዓድዋ) ጨለማይቱ አህጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሰራፋችው በአውሮፓ ላይ የምታደርገው አመጽ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነውም ተብሏል፤” በማለት በዓድዋ ጦርነት ትረካው ለጣሊያን ግልጽ ወገናዊነት የሚሳይ የሚባለው ጆርጅ በርክሌን ዋቢ አድርገው አስፍረዋል።

ይሄ የሚያስረዳው፣ ታላቁ የዓድዋ ድል የቅኝ አገዛዝ ማዕበልን የመታ የጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑ ሲሆን፤ በዚህም ድሉ የሰው ልጅ ሁሉ በእኩልነት የሚታይበት እና የሚከበርበት አስተሳሰብ እንዲወለድም አድርጓል። ዓለማችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገርም አስገድዷል።

ለጥቁሮች መብትና ነፃነት በመታገል ደማቅ ታሪክ ፅፎ ያለፈው ማርክስ ጋርቬይ፤ “የዓድዋ ድል፣ የአውሮጳውያንን የአይበገሬነት ትርክት ያነኳኮተ፣ በመላው አፍሪካ ክፍለ ዓለምም ለነፃነት ለሚደረገው ትግል ተስፋን የፈነጠቀ ነው” በማለት የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የቀየረ ማርሽ ቀያሪ ድል መሆኑን መስክሯል።

ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦችን ለነጻነት ያነሳሳ፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲቀነቀን ያስቻለም ድል ነው። እንደ ማርክስ ጋርቬይ እነ ሴዳር ሴንጎርና የካረቢያን ወጣቶች ፓሪስ ላይ ቆመው ኔግሪቲዩድ በተሰኘ ተመሳሳይ ፖለቲካዊና ሥነጽሑፋዊ ንቅናቄ ጥቁርነትን በኩራት የማቀንቀን መነሳሳት የተፈጠረውም ከዚሁ ከዓድዋ መንፈስ ለመሆኑ እሙን ነው ።

እናም በዚህ ልክ ታላቅ የሆነ ድል ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ዓለም በታሪክ ብቻ ሳይሆን በተግባር እውቅና ሰጥቷል። አፍሪካዊያን የላቀ ክብር ቸረዋታል። እንደ ነጻነት ምልክት በመቁጠርም ከቅኝ ግዛት ማግስት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ለሰንደቅ ዓላማቸው ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን ወርሰዋል። ዛሬም ድረስ አፍሪካዊያን በአንድነት የሚሰባሰቡባት የኅብረታቸው መቀመጫ አድርገው ሰይመዋታል።

ዓለምም ለቅኝ ግዛት የተሰማሩ ምዕራባውያንን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ተገድደው እውቅናን ከመስጠት ባለፈ፤ ነጻነትና ሉዓላዊነቷን አክብረው ዲፕሎማሲን ለመከወን በማለም ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተዋል።

በቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓል። ዓድዋ ከድሉ ማግስት ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር መሆኗ እንዲረጋገጥ እና ድንበሯን እንድትካለልም አስችሏታል ።ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንድትታወቅ፣ ዝናዋ እንዲናኝና እንድትከበር ጭምር ምክንያት ሆኗል። ይህ ታዲያ የትናንቶቹ ትውልዶች የተግባር ፍሬ መሆኑን ልብ ይሏል።

እናም የትናንት ጀግኖች አያቶቻችን ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኩራት በዘመናት ብዛት የማይደበዝዝ ጀብዱ በደማቅ ቀለም እንደጻፉት ሁሉ፤ የአሁኑ ትውልድም የዓድዋን ከፍታ የሚመጥን ተግባር በልማት መድገም ይኖርበታል ። በመሆኑም አባቶች አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩአትን ሀገር አንድነቷን በማስቀጠል፤ ሁለተናዊ እድገትና ሰላሟን እውን በማድረግ ዳግም በድህነትና ሰላም እጦት ለሚቸገሩ ሕዝቦች አርአያ እንድትሆን ማድረግ ይጠበቅብናል።

በዚህ ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ጅምር ተግባራት አሉ። ለአብነት የሕዳሴ ግድብን መጥቀስ ይቻላል። የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የዘመናት ህልምና ቁጭት፤ የመሪዎች መሻት ነበር። አሁን ባለው ትውልድ ቁጭቱ በተግባር ተመንዝሮ፤ የሕዳሴ ግድብን በራስ አቅም እውን ማድረግ ተችሏል። ይሄም በብዙ መልኩ ዓድዋን የሚወክል፤ በተለይም የዚህ ዘመን ትውልድ የራሱን ዓድዋ በልማት መስኩ እንዴት መግለጥ እንዳለበት ተገንዝቦ የተገበረው ፕሮጀክት ነው።

ከህዳሴው ፕሮጀክት ባሻገር የግብርናው ዘርፍ በተለይ በስንዴ፣ ሩዝና ሌሎችም ምርቶች የተገኘውና እየተገኘ ያለው ውጤት የዘመኑ ትውልድ ምን ያህል የራሱን ኃላፊነት መወጣት የሚያስችለውን ሰብዕና እየተላበሰ ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ወጥታ ስንዴን ወደ ውጪ መላክ የቻለችበትን እድል ፈጥራለች።

ይህም እንደ ዓድዋው ሁሉ ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያስገኘ የኢትዮጵያን ስም በበጎ የቀየረ ግዙፍ ተግባር ነው። አፍሪካዊያንም በምግብ ራሳቸውን የመቻል እምቅ አቅም እንዳላቸው ያስመሰከረ በጎ ጅምር ሆኗል።

እነዚህና መሰል ጅምር ተግባራትና የልማት ውጤቶች ታዲያ ከልማትነታቸው ባሻገር እንደ ዓድዋ የአንድነት ውጤቶች፣ ተባብሮ በመሥራት የተገኙ ድሎች ናቸው። ይሁን እንጂ እነዚህ ድሎች ጅምር እንጂ ብዙ የምንኩራራባቸው አይደሉም ። ምክንያቱም ዓድዋ የግዛት ሙሉ ሉዓላዊነትና ነጻነትን ያጎናጸፈ ድል የመሆኑን ያህል፤ የዚህ ዘመን የልማት ድሎች ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን በማድረግ ውስጥ የሚመዘኑ መሆን አለባቸው ።

ለዚህ እውን መሆን ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀውን ትጋት፣ አንድነትና መደማመጥ መላበስ የግድ ይላል። በመሆኑም የዚህ ዘመን ፈተና የሆነውን ግለኝነት እና ጽንፈኝነት በመታገል በተባበረ ክንድ በልማት ኢትዮጵያን ከድህነት የማውጣት ኃላፊነት እንዳለብንም መረዳት ይጠይቃል። ከዓድዋ ድልም፣ በጦርነት ድል ማድረግን ብቻ ሳይሆን፤ በኢኮኖሚውም ፣ በፖለቲካውም፣ በማህበራዊ ዘርፍም ድል ማድረግ መቻልን ተምሮ በዛው ልክ መግለጥ ያስፈልጋል።

የዓድዋን ድል መንፈስ በተላበሰ መልኩ በአንድነት ተከባብረን መስራት ከቻልን፤ በጅምር ደረጃ ባለው በልማቱ መስክም አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ይቻላል። ለዚህም ነው እርስ በእርስ ከመጠላለፍ ተላቆ በተለያዩ መስክ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በአንድነትና በተባበረ መንፈስ ከዳር ማድረስም ያስፈልጋል። በጥቅሉም ኢትዮጵያን በማስቀደም ተቀናጅቶ መስራት ከቻለ ድህነት ዛሬ ያጠቆረው ሰማይ በብርሃን የፈካን ነገን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይቻላል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You