ከአምስቱ የዓለማችን ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የቶኪዮ ማራቶን ትናንት ሲካሄድ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሱቱሜ አሰፋ የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፋለች።
የርቀቱ የዓለም እና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኖች፣ የክብረወሰንና ፈጣን ሰዓት ባለቤቶች በሁለቱም ፆታ ጠንካራ ፉክክር ባደረጉበት የ2024 ቶኪዮ ማራቶን በርካታ ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ቀደም ሲል የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው በርካታ አትሌቶች የነበሩ ሲሆን ብዙም ትኩረት ያልተሰጣት የ29 ዓመቷ ሱቱሜ በድንቅ ብቃት ማሸነፍ ችላለች። የገባችበት 2:15:55 ሰዓትም የቶኪዮ ማራቶን የቦታው አዲስ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
ኬንያዊቷ የቀድሞ የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የነበረችው አትሌት ብሪግድ ኮስጌይ 2021 ላይ 2:16:02 በሆነ ሰዓት የቶኪዮ ማራቶን ባለክብረወሰን የነበረች ሲሆን፤ በትናንቱ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ሱቱሜ ክብረወሰኑን በእጇ ያስገባችበትን ውጤት አስመዝግባለች። በዚህም በጃፓን ምድር በሴቶች ማራቶን ከ 2:16:00 በታች በመግባት የመጀመሪያዋ አትሌት መሆን ችላለች። በተጨማሪም ያስመዘገበችው ሰዓት የርቀቱ የዓለም ስምንተኛው ፈጣን ሰዓት ሲሆን 2022 ላይ በሲዎል ማራቶን ካስመዘገበችው የራሷ ፈጣን ሰዓት ከሁለት ደቂቃ በላይ የተሻለ ነው።
በውድድሩ ሱቱሜን ተከትላ ኬንያዊቷ ሮዝማሪ ዋንጂሩ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ስታጠናቅቅ፤ የቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና የማራቶን ባለድሏ ኢትዮጵያዊት አትሌት አማኔ ቦሪሶ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን ጨርሳለች።
እንደ ርቀቱ የዓለም ሻምፒዮን አማኔ በሪሶ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷት የነበረችው የኔዘርላንዷ አትሌት ሲፋን ሐሰን 2:18:05 በመግባት አራተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን ፈፅማለች።
የመጀመሪያ የማራቶን ድሏን ያጣጣመችው ሱቱሜ ከውድድሩ በኋላ በስፍራው ለነበሩ ጋዜጠኞች በአስተርጓሚ በሰጠችው አስተያየት “እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፣ ደስታዬን ለመግለፅ ቃላት ያጥሩኛል፣ ይህ የመጀመሪያ ድሌ እንደመሆኑ ደስታዬ ወደር የለውም” በማለት ተናግራለች።
ጠንካራ ትንቅንቅ በታየበት የወንዶቹ ውድድር ኬንያውያን አትሌቶች ከ 1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ የበላይነት ይዘዋል። በውድድሩ ኬንያውያን በበላይነት ያጠናቁ እንጂ ለአሸናፊነት የተጠበቀው የቀድሞው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ኤሊድ ኪፕቾጌ 10ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ያልተጠበቀ ውጤት ሆኗል።
ቤንሰን ኪፕሩቶ የዘንድሮው የቶኪዮ ማራቶን
ባለድል ሲሆን በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ያልቻለው የሃገሩ ልጅ ኪፕቾጌ ይዞት የነበረውን የቦታውን ክብረወሰን በ24 ሰከንድ በማሻሻል 2:02:16 ሰዓት አሸናፊ መሆን ችሏል።
በ2021 እና 2022 የቦስተን እና ቺካጎ ማራቶኖችን ያሸነፈው ኪፕሩቶ፤ ቶኪዮ ላይ የገባበት ሰዓት 2:02:16 በማራቶን ታሪክ የምንግዜም 5ኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል።
ሌሎቹ ኬንያውያን ቲሞቲ ኪፕላጋት እና ቪንሰንት ንጌቲች 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን ጨርሰዋል። ኃይለማርያም ኪሮስ እና ጌታቸው ፀጋዬ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሆነዋል።
የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ የማራቶን ሻምፒዮኑ ኤሉድ ኪፕቾጌ በ2024 የመጀመሪያ ውድድሩ ከ20 ማራቶኖች በኋላ ዝቅተኛ የተባለውን 10ኛ ደረጃ 2:06:50 በሆነ ጊዜ አጠናቋል። በቅርቡ የማራቶን የዓለም ክብረወሰኑን በቅርቡ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ባለፈው ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ኬልቪን ኪፕቱም የተነጠቀው የ39 አመቱ ኪፕቾጌ ትናንት ያስመዘገበው ውጤት በስኬት የተሞላው የማራቶን ዘመኑ መጨረሻ እንደተቃረበ ማሳያ ነው ተብሏል።
በሦስት ተከታታይ ኦሊምፒኮች በማራቶን ወርቅ በማጥለቅ በታሪክ የመጀመሪያው አትሌት ለመሆን እየተዘጋጀ የሚገኘው ኪፕቾጌ ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ እየተሰናዳ በሚገኝበት ወቅት ቶኪዮ ላይ ያልጠበቀው ውጤት ነው የገጠመው። “የሆነው ነገር ሆኗል፣ ሁሌ ፋሲካ የለም” ሲል የምንጊዜም የርቀቱ ኮከብ አትሌት ኪፕቾጌ ከውድድሩ በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል።
“ለውድድሩ ብቁ ነበርኩ፣ አንዳንዴ በውድድር መሐል ላይ እንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል” ያለው ኪፕቾጌ ከስድስት ወራት በኋላ ስለሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ለመናገር ጊዜው ገና ቢሆንም ከትናንቱ ውድድር በኋላ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በቂ ዕረፍት ካደረገ በኋላ ወደ ልምምድ እንደሚመለስ ገልጿል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም