ትውልድን የሚያነቃ ትርክት ለመገንባት

እኤአ የካቲት 1926 በአገረ አምሪካ በጥቁሮች ሕይወትና ታሪክ ጥናት ማኅበር አማካኝነት የካቲት የጥቁሮች ወር (Black History Month) ተብሎ እንዲጠራ ተወሰነ፡፡ ይህ ውሳኔ በአሜሪካና በካናዳ መንግስት ወዲያው እውቅና ተቸረው። በቅርቡ ደግሞ በአየርላንድና በዩናይትድ ኪንግደም ተቀባይነት አገኘ። አሜሪካና ካናዳ በየካቲት ወር ሲያከብሩት ቀሪዎቹ ሁለቱ አገራት ደግሞ በሕዳር ወር አስበውት ያልፋሉ።

በዋናነት አፍሪካ አሜሪካውያንና ጥቁር ዳያስፖራዎች የካቲት ወርን ምርጫቸው አድርገዋል። ወሩ ለዚህ ክብር የተመረጠበት ምክንያት የጥቁሮች ነፃነት መሰረት የነበሩት 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት አብርሃም ሊንክንና አፍሪካ አሜሪካዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የነፃነት አርበኛ ፍሬድሪክ ዳግላስ የተወለዱበት በመሆኑ ነው፡፡ ቀኑ ላለፉት 50 ዓመታት በአፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ይነገራል፡፡

ወርሃ የካቲት ከዚህም ሌላ ታላቅ ቁምነገርም ይዟል። ኢትዮጵያውያን በታላቅ የድል ስሜት የሚያስቡት ነው። በጥቁር ላይ ይደርስ የነበረው የባርነት ቀንበር የተሰበረበት የነፃነት ጮራ የፈነጠቀበት፣ እና የትግል አድማሱ እንዲሰፋ አርዓያ የሆነው የዓድዋ ድል በኢትዮጵያውያን አርበኞች የተመዘገበበት ነው፡፡

የዓድዋ ድል የነፃነት ጎህ ፈንጣቂ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ድል በዚሁ ወር የካቲት 23 ቀን ነው የተገኘው። በዓድዋ ተራሮች በደምና በአጥንት የሰውን አስተሳሰብ እጥፋት የቀየሩ አያቶቻችን የተጋድሎ ታሪክ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ችቦ የሆነበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ዓድዋና የፓን-አፍሪካኒዝም ላይነጣጠሉ የተጋመዱት፡፡

የዓድዋ ጀግኖች ቀኝ ገዢዎች ላይ የተቀናጁት ድልም ከአትላንቲክ ማዶ ድረስ የነዘረ የነጭና ጥቁር ይሉት የቆዳ ቀለም ድልድልን የሰበረ፣ በሰው ልጆች ታሪክ ፍትህና እኩልነትን ያነበረ፤ ሁሌም መቼም የምንኮራበት የጋራ የታሪክ ገፃችን ነው፡፡

ዶክተር ዊሊየም ኤድዋርድ ከፓን አፍሪካ ንቅናቄ ፋና ወጊ መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የዓድዋን ድል ሲገልጹት ‹‹ዓድዋ በቀኝ ገዢዎች ትግል አይበገሬ መንፈስ ላላቸው እንዲሁም ለነፃነታቸው ፋና ወጊ ለሆኑ አፍሪካዊያን ሕዝቦች ምስክርነት የቆመ ድል ነው›› በማለት ነበር፡፡ እነ ማርክስ ጋርቬ ፣ ዶክተር ክዋሚ ኒክሩማ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ፓትሪክ ሉሙምባ ስለ ዓድዋ ድል የነፃነት ቀንዲልነት ደጋግመው መስክረዋል።

የጥቁሮች ወር ተብሎ የሚታወቀው ወርሃ የካቲት የነፃነት ቀንዲል ከሆነው የዓድዋ ድል ጋር የታሪክ ግጥምጥሞሽ ፈጥሯል፡፡ ጥቁሮች ለነፃነታቸው ያደርጉት የነበረውና አንድ ጊዜ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ይል የነበረው ሂደቱ የተቀጣጠለው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወራሪውን የጣሊያን ሰራዊት ድል በመምታት ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ችቦ ለኩሰዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ አፍሪካውያን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በወሰደው የነጻነት የተጋድሏቸው በኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ ገዢዎቻቸውን አንበርክከዋል፡፡ የሰንደቋን ቀለማትም የአሸናፊነት መገለጫ አድርገው ወስደዋል፡፡

በአፍሪካ ምድር የምትገኝ ኢትዮጵያ የተሰኘች ሀገር በዘመኑ የሰለጠነና እስካፍንጫው የታጠቀ ወራሪ በጦርና ጋሻ ድባቅ መምታት ችላለች። ድሉ የሰው ልጆች ከቀለም ልዩነት ውጪ የሚለያቸውና አንዱን የበታች አንዱን የበላይ የሚያደርግ ምንም አይነት ኃይል እንደሌለ ማስረዳት ችሏል። የሰው ልጆችን እኩልነት አስርጿል። የጥቁር ሕዝቦችን ስነልቦና እንዲነቃቃ እርሾ ነበር፡፡

አዲስ አበባም ዓድዋን በግዙፍ አሻራ ሀገሪቱ እምብርት ላይ አኑራ፣ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ጠንካራዋን አህጉር ለመፍጠር የሚታትሩ መሪዎቿ በመዲናቸው ተሰባስበው መምከሪያ ሆናለች፡፡ ይህ ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ አንድም ለጉዳዩ የሰጠነው ክብር የሚያሳይ ሁለትም የነፃነት ቀንዲል የተከፈለበት ዋጋን ግልፅ የሚያደርግ ነው፡፡

የአፍሪካ መዲናነቱ እንዲሁ ባጋጣሚ የተገኘ በረከት ሳይሆን ከወሳኝ የታሪክ ውለታዎች ጋር የሚተሳሰር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለመላው አፍሪካውያን የጭቆናን ቀንበር አሽቀንጥረው ይጥሉ ዘንድም የብርታት ትጥቃቸው፣ የአሸናፊነት መንፈስ መገኛ ማዕከል በመሆናችን ምክንያት የተገኘ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡

ወርሃ የካቲት የዓድዋ ድልና የፓን አፍሪካኒዝም በአንድነት በሕብረ ቀለማት የደመቁበት እንደመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ለሆነውና ልዩነታችንን ለማስፋት ለሚነዙ የሀሰት ትርክቶች ማረቂያና በጋራ ለመሰባሰብም ጥላ እንዲሆነን ልንሰራበት ይገባል፡፡ ወሩ በዓለም ጥግ ያሉ ጥቁሮች ሁሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው ለመብታቸው የሚከራከሩበት የታሪክ እጥፋት የተፈፀመበት ወቅት ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ የታሪክ የከፍታ ቦታ ላይ ባለቤት ሆኖ ለመዝለቅ ደግሞ ታሪክን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታዋቂው እንግሊዛዊው ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ‹‹ታሪክ በዘመን ጀግኖች የሚሰራ አሻራው ግን ትውልዶችን ተሻግሮ የሚዘከር ገድል ነው›› ብሏል፡፡ ይህ ተግባር ደግሞ በዘመን ጅረት ውስጥ ትውልድ የሚጋደልበት ወይም የመሰባሰቢያ ጥላ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የታሪክ ባለሙያዎች ታሪክና ትርክትን የሁለቱ ሚዛን አድርገው ይመለከቱታል፡፡

የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በተለይ በኛ ሀገር ታሪክና ፖለቲካ ሚናቸው ተደበላልቋል፡፡ እናም ፖለቲከኛው እንደዜጋ የሀገሩ ታሪክ ጉዳዩ ቢሆንም የፖለቲካው መታገያው አድርጎ እውነትን መሻሩ የሂደቱ ፈተና ሆኗል፡፡ በባለሙያዎችና በፖለቲከኞች ሀሳብ ምክንያት የሚነገሩ ትርክቶች ማኅበረሰቡም ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ ባለሙያዎች የሚገባቸውን ያክል ወደፊት ገፍተው እውነትን ለመናገር ስለእውነት ቆመው ለእውነት ለማለፍ ዝግጁ ሲሆኑ አይታዩም፡፡

ባለሙያዎች ባገኙት አጋጣሚ የተለያዩ ምርምሮችን በመስራት ታሪክ ለዴሞክራሲያዊ ሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ታሪክ ለብሔራዊ ውይይትና ለሀገራዊ ሰላም ያለውን አስተዋፅኦ ሙያዊ በሆነ መልክ የምርምር ስራዎችን ወደ አደባባይ በማቅረብ ሕዝብን ማስተማር ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለጥቁር ሕዝቦች ያበረከቱት የነፃነት ተጋድሎ እየተዘከረ ያልፋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ታሪክ የተነገረበት መንገድ የልዩነት ሆኖ ወንድም ከወንድሙ ተጣልቷል፤ ተጋድሏል፡፡ ትርክት ለዘመናት የቆየውን አብሮነት አናግቷል፣ አሻክሯል ለዘመናት ተገንብቶ የቆየውን ሰላም አደፍርሷል፡፡ የልዩነት ትርክት ራሳቸውን ከሀገር አብልጠው ለሚወዱ፣ አንድነትን ለማይፈልጉ በአብሮነት ውስጥ ሳይሆን በልዩነት ለሚያተርፉ ጠቅሟል፡፡

አሁን እየታየ ያለው የኢትዮጵያውያን የልዩነት መንገድ ያለንን እንዳናውቅ አድርጎ ሰፊውን የጋራ መንገድ በከበባ አጥረን በቀጭኗ መንገድ እንድንጋፋ አድርጎናል፡፡ በሀይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋ ተጋመድን የተፈጠርንና ለበርካታ ሺህ ዓመታት አብረን እየኖርን በመሆናችን እንጂ የተሄደበት ትርክት ሊያቀራርብ አብሮ ሊያኖር የሚያስችል አልነበረም፡፡

ባለፉት ዓመታት ጥላሸት ተቀብቶ የትውልዱ መጋደያ የሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ቅድመ አያቶቻችን የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ በመፍታት የጋራ ጠላት ሲመጣ ደግሞ በጋራ በመነሳት ዘመናዊ ኢትዮጵያን ዓድዋ ላይ አስረክበውናል፡፡ በኋላ የመጣው ትውልድ ግን በሆነው ባልሆነው እየተሻኮተ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ስናረክስ ይታያል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አሕመድ ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ‹‹በትላንት ጉዳይ እየተባላን ነገ እያመለጠን ነው›› ያሉ ሲሆን ነገን ለመያዝ ደግሞ ዛሬ ብቸኛ የመቆጣጠሪያ መሳሪያችን ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ሰው ከትላንት ተምሮ ዛሬ ሰርቶ ነገን ማነፅ ሲገባው ዛሬ ላይ ሆኖ ትላንትናን እየተፋጀ ነገን እያጣን ነው፡፡ የተዘጋጁ ብቻ የሚወርሱ ስለሆነ በደምብ ካልተዘጋጀን ጥፋት ሊያመጣብን ይችላል፡፡ ለዚህም የሚያሰባስብ ትርክት ያስፈልጋል፡፡ ልክ እንደ ዓድዋ›› በማለት መፍትሄውን አስቀምጠዋል፡፡

ታሪክ ትላንት የተፈፀመ ቢሆንም አሻራው ግን እስከ ነገ ይሻገራል፡፡ እናም ከዚህ ተምሮ ጠንክሮ መቆምን ታሪካቸውና መስፈንጠሪያቸው ካደረጉቱ አገራት እንማር ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳስባሉ፡፡ በሕንድ ሀገር እርስበርስ ሊደማመጡ የማይችሉ ከመቶ ሃያ በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡ ይሄ ልዩነት ለዘመናት ቢያስቸግራቸውም በመመካከርና በጥበብ አልፈውት አሁን ሰልጥነው አድገው በዓለም ላይ 5ኛውን ኢኮኖሚ መገንባት ችለዋል፡፡ መሰል ልዩነቶችን ሌሎች መባያ አድርገውታል፡፡ ተሞክሮውን ወስደን የሚያለያየንን ነገር ይዘን ለጋራ ሀገር ልንተጋ ይገባል እንጂ ልንባላ አይገባም፡፡

ከታሪክ ብዙ ልንማር እንጂ የመለያየት ሽንቁር ልንፈጥር አይገባም። እኛ ልንማርባቸው የምንችላቸው በርካታ ታሪኮች ደግሞ አሉን። አንድነታችንን ለማጠንከር የሚረዱ ታሪኮችን ሌሎች አገሮች ጋር ሄደን ሳይሆን እዚሁ ደጃችን ላይ ማግኘት እንችላለን። ብዙ ዶሴም ማገላበጥ አይጠበቅብንም። የየካቲት ወርን ብቻ ብንመዝ አስደናቂ ታሪኮችና ግጥምጥሞሽን ያመላክተናል።

በእብሪት ተወጥሮ ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ የሀገራችንን ድንበር ዘልቆ የገባው ዚያድባሬ በ66ቱ አብዮት የተከፋፈለውን ሰራዊት መዳከም ተገን አድርጎ ነበር፡፡ የየካቲቱ አብዮት የፈጠረው መከፋፈልና የሽብር አዙሪት ሀገርን ቢያዳክምም ለሀገሩ ምንጊዜም ሟች ለሆነው ኢትዮጵያዊ ከያለበት ተጠራርቶ በዚች የካቲት ወር የካራማራን ድል አስመዝግቦ የምስራቁን ድንበር ለዘለቄታው አስከብሯል፡፡ ይህ ታሪክ በሉአላዊነታችን የማንደራደር፣ በአንድነታችን የማንቆምር መሆናችንን የሚያሳይ አጋጣሚ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም።

የየካቲት ገድል ብዙ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ድልና ሽንፈት ተምረን መወጣጫ ካላደረግነው ግን በየዓመቱ የአበባ ጉንጉን ከማስቀመጥ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ከድሎቻችን ጀርባ ሁሉ ሕብረታችንና መደማመጣችን ሲኖር ከሽንፈታችን ጀርባ ደግሞ ልዩነታችንና ክፍፍሎቻችን አሉ፡፡ ዛሬም ዓድዋና ካራማራ ልንደግምባቸው የሚገቡን ፀረ ድህነት ትግሎች አሉብንና እንደ ዓድዋውና እንደካራማራው ሁሉ በሕብረትና በአንድነት ልዘምትባቸው ይገባል፡፡

ዛሬም የልዩነት ሽንቁራችንን ለማስፋት የሚጥሩ ኃይሎች መኖራቸውን አንዘንጋ። ድክመታችንን ተገን አድርገው አጀንዳቸውን ለማሳካት በሚጣጣሩ ታሪካዊ ጠላቶች መከበባችንን አንዘንጋ። በድህነትና በስልጣኔ እጦት ተይዘዋል ብሎ የመጣውን ጣሊያንን አሳፍረው ከመለሱት አባት አርበኞች ልንማር ይገባል። በአንድነታችን እንደማንደራደር ሉአላዊነታችንን አሳልፈን እንደማንሰጥ የሚያሳየው የካራማራ ድል ማንቂያችን ይሁን።

ዛሬ ሌላ ዓድዋን የሚያክል ችግር ከፊት ለፊታችን አለ። ድህነትን ማሸነፍ የትውልዱ ሌላ ዓድዋ ነው። ለመልማት ወደብ ያስፈልገናል። ለማደግ አባይን ገንብተን ማጠናቀቅ እና ጥቅም ላይ ማዋል ያሻናል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ጠላቶቻችን ሽንቁሮቻችንን ተጠቅመው ሊያዳክሙን ይሻሉ።

የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ምንም ያህል ጤናማና ሕጋዊ ቢሆንም ዓለምን ሲያንጫጫ ተመልክተናል፡፡ ትንሿን የልማት እርምጃችንን በማጣጣል ሁሌም የተረጂነት ስሜት እንዲኖረን ሊሰሩብን የሚፈልጉ በርካቶች ናቸው፡፡ ይሄ የሚያሳየው የፖለቲካ ነፃነታችን ብቻውን ትርጉም እንደሌለውና የኢኮኖሚም ነፃነት ሊኖረን እንደሚገባ ነው፡፡ በመሆኑም ልዩነቶቻችንን በምክክር፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል። መላው የጥቁር ሕዝብን ያስተሳሰረው የዓድዋ ድል የአንድነታችን መሰረት እንጂ ልዩነታችንን የሚያሰፋ ሽብልቅ አለመሆኑን እንገንዘብ። ለዚህ ነው እሩቅ ሳንሄድ የየካቲት ወር ታሪካዊ በረከቶቻችንን የሚጠበቅብን።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You