አሁን ላይ የአገር ባሕል አልባሳቶች ዘመኑን በሚፈልገው ልክ በተለያየ ዲዛይን ውብ በሆነ መልኩ ተሰርተው በተለያዩ አማራጮች እየቀረቡ ነው። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችም የአገር ባሕል አልባሳቶቹ በማንኛውም ሥፍራ ዘወትር መለበስ እንዲችሉ ቀላልና ምቹ በማድረግ እየተጠበቡበት ይገኛሉ።
እነዚሁ ልብሶች ታዲያ በአዘቦት ቀናት እና በበዓላት ወቅት በስፋት የሚስተዋሉ ሲሆን፤ አልባሳቱ በገበያ ላይም እንዲሁ ለሽያጭ ቀርበው እንመለከታለን። ይህም በብዙዎቻችን ዘንድ አግራሞትን የሚጭር በመሆኑ ‹‹እንደዚህ ውብ የሰውን ቀልብ የሚስቡ የኛው የአገር ልብሶች ናቸው እንዴ!›› በማለት ራሳችንን እንድንጠይቅ ያስገድዱናል።
እነዚህን የሀገር ኩራት የሆኑ ውብና ማራኪ የሀበሻ ልብሶች በዓለም ላይ እንዲተዋወቁና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት አግኝተው በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መስራት ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቀው ሥራ ነው። ለዚህ በዘርፉ የተሰማሩ ዲዛይነሮች የኢትዮጵያን ልብሶች ባሕላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ በተለያዩ አማራጮች በማዘጋጀት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳድረው ተመራጭ ሆኖ እንዲታዩ ለማስቻል ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
ከአልባሳቱ ባለፈም በአገሪቱ የሚገኙ የሀበሻ ልብስ ዲዛይነሮችም እንዲሁ ጎልተው እየወጡ ይገኛሉ። ከእነዚህ ዲዛይነሮች መካካል ‹የአብ ጥበብ› የተሰኘ ድርጅት መስራች ዲዛይነር የኔነሽ አቦነህ አንዱ ናት።
ዲዛይነር የኔነሽ፤ ወደዚህ ሙያ ከገባች 14 ዓመታት ገደማ ተቆጥሯል። በቀለም የተነከረ የሀበሻ ልብስ በመስራት ይበልጥ ትታወቃለች። የምትሰራቸውን የሀበሻ ልብሶች በቀለም በመንከር በተለያየ አማራጭ እየሰራች ለገበያ ታቀርባለች። ከዚህም በተጨማሪ የሀበሻ ቀሚሶችን፣ ቶፖችን እንዲሁም ለሴት እና ለወንድ የሚሆኑ ልብሶችን ትሰራለች። እንዲሁም ለሕጻናት የሚሆኑ የሀበሻ ልብሶችን በተለያየ ዲዛይንና አይነት ትስራለች። አሁን ላይ ደግሞ ተደራሽነትዋን በማስፋት የአልጋ ልብስ፣ የጠረጴዛ ልብሶች እና እንደ ሶፍት የሚያገለግሉ ልብሶች በተለያየ ዲዛይን በመስራት ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች።
ዲዛይነር የኔነሽ የዲዛይኒንግ ሙያ ገና ተማሪ ሳለች ጀምሮ ውስጧ ተዳፍኖ የኖረ መሆኑን ትናገራለች። ወደ ሙያ ለመግባት መጀመሪያ የስፌት ሙያ ተምራ እንደነበረ በማስታወስ፤ ቀጥላም ያላትን እውቀት በመጠቀም የዲዛይኒንግ ሙያ በመማር ሙያዋን እያሳደገች መጥታለች።
‹‹በተለይ ለቀለማት ጥምረት ትኩረት ሰጥቼ በተመስጦ መስራት በመቻሌ የቀለማቱ ጥምረትና የምሰራቸው ዲዛይኖች በብዙዎች ሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ የሀበሻ ልብሶች ዕለት ተዕለት እንደ ዘወትር ልብስ እንዲለበሱ በማሰብ ቀለል አድርጋ እንደምትሰራ ትናገራለች።
በተለይ በተለያዩ ቀለማት በመንከር የምታቀርባቸው ንክር የሀበሻ ልብሶች ተመራጭና ተፈላጊ ናቸው። ንክር ልብሶቹ ቀለል ያሉና በጣም የሚመቹ እንደሆኑም ነው የምትገልጸው። ለባሾችም ‹‹ነጭ የሆነው የሀበሻ ልብስ ያወፍረናል›› ብለው ስለሚያስቡ በቀለም የተነከረው በአማረ ዲዛይን የተሰራውን ልብስ መልበስ የሚመርጡ መሆኑን ዲዛይነሯ አንስታለች››።
በቀለም የተነከሩ የሀበሻ ልብሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣ ሲሆን፤ በተለይ በበዓላት፣ በሰርግ እና በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ለየት ብለው ደምቀው ለመታየት የሚፈልጉ ሰዎች ምርጫዎች ነው። በአዘቦትም ቀንም እንዲሁም እየተለመዱና በተለያዩ ቦታዎች እንደማንኛውም ልብስ ይለበሳሉ። ልብሶቹ በአገር ውስጥ ገበያም ሆነ በተለያየ መልኩ ውጭ አገር ድረስ የሚሄዱ ሲሆን በተለይ ከውጭ አገር የሚመጡና ገዝተው የሚሄዱ ሰዎች በክረምት ለመልበስ እንደሚመርጧቸው ዲዛይነር የኔነሽ ትገልጻለች።
ለምትሰራቸው ንክር ልብሶች የምትጠቀመው ከለር ለልብሱ የሚስማማው አይነት ስለሆነ የማይለቁ እና እንደነበሩ የሚቆዩ ናቸው የምትለው ዲዛይነሯ፤ ‹‹ንክር ልብስ ሲባል እኔ የምሰራው ንክር ልብስ የሚለቅ አይደለም ለዚህም፤ ስምንት እና ዘጠኝ ዓመታት ያህል የለበስኳቸው ልብሶች እንደ አዲስ መታየታቸው ምስክር ነው›› በማለት ትገልጻለች። ለምትሰራቸው ልብስ የሚስማማ ቀለም የምትጠቀም በመሆኑንም ንክር ልብስ የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች እሷን ምርጫ አድርገው እንደሚጎበኟት ትናገራለች።
የልብሱን ባሕላዊ ይዘታ ሳይለቁ በተለያየ መልክና ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ዲዛይን ካደረገች በኋላ ወደ ቀለም መንከር ሥራ እንደምትገባ የምትናገረው ዲዛይነሯ፤ ቀለሙ መንከር የምትፈልገው ልብስ በምትፈልገው የቀለም አይነት በመንከር ውብና ማራኪ ሆኖ በለባሾች ዘንድ የሚወደድ እንዲሆን ጥረት እንደምታደርግ ትገልጻለች።
ዲዛይነር የኔነሽ፤ ምርቶቿ ለማስተዋወቅ የተለያዩ ድረገጾችና የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች (እንደ ፌስ ቡክ፣ ኢንስትግራም እና ቲክቶክ) በመሳሳሉ በማስተዋወቅ ለገበያ እያቀረበች ትገኛለች። አልፎ አልፎም ቢሆን በመጽሔቶች (ኢትዮጵያን ሪቪዩ እና ሪፖርት የተሰኙ መጽሔቶች) ሥራዎቿ ማስተዋወቋን ትገልጻለች፡፡ ሥራዎቿ ማስተዋወቋን ትገልጻለች።
የምትሰራቸው ልብሶች ጥራታቸውን የጠበቁና በኤክስፖርት ደረጃ ያሉ ሲሆን፤ ወደ ውጭ ለመላክ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጻ፤ ምርቶቿ ዓለም አቀፍ ገበያን እንዲቀላቀሉ ጥረት ማድረጓን ነው ያመላከተችው።
‹‹የባሕላዊ አልባሳት ያለንን ቱባ ባሕል በአልባሳቶቻችን በመግለጽ ለዓለም የምናስተዋወቅበት አንዱ መንገድ በመሆኑ በደንብ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ ከዚህ ባሻገር ዘርፉ ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ማምጣትና ለብዙ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የሚችል በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ናት።
አሁን ላይ እነዚህን ምርቶች ለማምረት ለአሥራ አንድ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል የፈጠረች ሲሆን፤ የሸማኔዎችና የጥልፍ ሥራ ለሚሰሩ ለብዙ ባለሙያዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠሯንም ገልጻለች።
ባሕላዊ አልባሳት ዋጋ በአንድ ቦታ የሚቀመጥ አይደለም፤ እንደጊዜው የጥሬ እቃ አቅርቦት ሁኔታ መሠረት በየጊዜው እየጨመረ የሚመጣ ነው የምትለው ዲዛይነሯ፤ ሆኖም ግን የምትሰራቸውን ልብሶች ኀብረተሰቡ በየደረጃ ሸምቶ ሊለብሰው በሚችል መልኩ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እያቀረበች መሆኑን ነው የገለጸችው።
የአገር ባህል አልባሳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ በባለሙያው ሆነ በሚመለከታቸው አካላት መስራት ያለበት ብዙ የቤት ሥራዎች እንዳሉ የምትናገረው ዲዛይነሯ፤ ባለሙያው ሙያ የሚጠይቀውን ሥነምግባር ከግምት ውስጥ በማስገባት በትክክል ጥራታቸውን የጠበቁ የሀገሩን ባሕል ሊገልጹ የሚችሉ ልብሶቹን ሰርቶ ለገበያ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት ትገልጻለች። የሚመለከታቸው አካላት እንዲሁ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት በመስጠት በዘርፉ የሚነሱ ችግሮች የሚቀረፉበት መንገድ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል። ይህ ከሆነና በዚህ መንገድ መጓዝ ከቻልን በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልቶ የሚታዩ ሥራዎች ይዞ መምጣት ይቻላል ስትል ምክረ ሀሳብ ትለግሳለች፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም