ታላቁ ዓድዋ ከከያኒዋ አንደበት

የዓድዋን ጦርነትና ድል በጥሞና ስቃኝ፣ የእንባ ጤዛና የድል ዜማ ማዶ ለማዶ ሆነው በአእምሮዬ ጓዳ ድቅን ይሉብኛል። በተለይም የዓድዋን መዝሙር በእጅጋየሁ ሽባባው ሙዚቃ ውስጥ ሳደምጥ ልክ እንደ ሙዚቃው፤ በኩራት፣ በክብር፣ በደስታ፣ በፍቅር፣ ደግሞም በኀዘን እኖራለሁ።

ይህ ድብልቅልቅ ስሜት፣ ረቂቅ ትውስታ ሁለት ገጽታ ያለው የሁሌ ትዝታ፣ መዝሙርና ሙሾ በአንድ ሰዓት በአንድ ሀሳብ በውስጤ ይመላለሳሉ። በጦርነቱ ዕለት፤ ከዚያ አስደናቂ ድል በኋላ በዐፄ ምኒሊክ፣ በራስ መኮንንና ሌሎችም ጀግኖች ፊትና ልብ ላይ የሚንቀዋለል ስሜት ዛሬ ላይ የሆነ ያህል እንዲታየን ሆኗል።

ከዚህ አንፀባራቂ ድል በኋላ የወደቁት እነ ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራውን) የመሳሰሉ ጀግኖች ሞት ለጓዶቻቸው ሕመም ነበር። ሰው ከፍሎ፣ ውድን ሰጥቶ ሌላ ውድ ነገር መቀበል ቀላል ያልነበረ መሆኑንም በእንባና ሳቅ ድብልቅ ስሜት እንድናይ ሆነናል።

ጀግኖቻችን የዓለም ዕብሪተኛ በስላቅ ምላሱን አውጥቶ እንዳያላግጥብን፣ የተሳለልንን ቢላዋ ነጥቀው፣ ቀንበሩን ከጫንቃችን የሰበሩት በራሳቸው ደም ነው፤ የድል ዜና ያሰሙን፣ ገድሉን የፈጸሙትና በታሪካችን ላይ ዘውድ የደፉት ከጠላት ጋር ተናንቀው ደምና ላብ ከፍለው ነው። ዛሬ ሲታሰቡን የማያረጁና በታሪካችን ገጾች የማይደበዝዙ ዝርግፍ ጌጦቻችን ሆነው ነው፤ ለዚህም ነው ከልብ የማይጠፋ ክብር ነፍስያችን ውስጥ ያኖሩት።

የድል ቦታዋ ዓድዋ ሰንሰለታማ ሰፈር አይደለችም፤ በትንሽ መንደርም አትመሰልም፤ ትልቁን የአፍሪካን ድል ምድሯ ላይ በደማቅ ቀለም የፃፈች ናት፤ ሙሉ ታሪኩ ሲነሳ መንደርነቱ ተረስቶ የሀገር፤ የአህጉር፤ የጥቁር ሕዝቦች ድል … ነው።

እምቢ ለሀገሬ፤ ለነፃነቴ በሚል በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜት ከመድፍ ጋር በጎራዴ የተፋለሙበት፤ ለጓጉለት ነፃነታቸው በባዶ እግራቸው በተራራና በጢሻ እየሮጡ ሕልማቸው ላደረጉት ድል ሁለንተናቸውን መስዋዕት አድርገው የከፈሉበት ነው። የዓድዋ መዝሙር ባለቤቷ፣ የሙዚቃዋ ንግሥት እጅጋየሁ የተዋደቁት ለነፃነትና ለፍትሕ ልዕልና፣ ሰው ለመሆን ለክብር ነው ትለናለች፣ “ሰው” የሚለው ቃል ሁለንታዊ መሆኑን ልታጠይቅ።

“ሰው ክቡር” ስትል ደግሞ የሰው ክብሩ ከነፃነቱ ይጀምራል ልትለን ስለወደደች ነው? በነፃነት መኖር ሰዋዊና ሕሊናዊ ነው። እምቢኝ ያሉት አባቶች ገድል የተፃፈበት የሰው መሆን ክቡርነት የተገለፀበት የእንቢታ ማሳያና ውጤት ነው- ዓድዋ ።

ለሰው መሆን ክብር ዓድዋ ላይ “ሰው”ን ሰው ለማድረግ ሰው ሞቷል፤ ለመንፈስ ልዕልና ሕይወቱን በጦር ሜዳ ገብሯል፤ ደሙን ሜዳ ላይ አፍስሷል። ወርቅ የሆነ ሰው በእሳት አልፎ፣ አፈር ሆኗል፤ ይህ ሁሉ ግን ሌሎችን ወርቅ አድርጎ ለማኖር የቻለበት ድል ሆኖ ዘወትር ይዘከራል።

‹‹የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነፃነት፣ ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት›› ትላለች! ያንን የደም ዋጋ፣ ያንን ታላቅ ተጋድሎ፣ ያንን በደማቁ ታሪክን የፃፈ ደም በእጅጋየሁ ሽባባው እንዲህ ስትገልፀው።

‹‹በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፤ በክብር ይሄዳል፤ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ›› … ዓድዋ የመስዋዕትነት ታሪክ ነው ነፍስን ለሌሎች ነፍስ የመስጠት መስዋዕትነት። ይህንን የሚያደርግ ደግሞ የጀግና ልብ ነው፤ ሩቅ ተመልካች ዓይን። የከበረች ምድሩን አሳልፎ የማይሰጥ ክንድ፤ የነፃነቱ ምልክት የባንዲራው ቀለም በልቡ የታተመ፤ ስለዚህ ሕልሙ ሀገሩ፤ ክብሩም ነፃነቱ የሆነ።

ሲጠቀለል የዓድዋ ጦርነት መነሻ ምንጩ “አትንኩን!” ነው። “አትንኩን” ባይሆንማ ቤቱ ተቀምጦ ባልተነካ!…”አትንኩን!” ያለው ግን ትግራይ ያለው ወገኑ ሲነካ ስላመመው ነው፤ ሰሜኑ፣ ደቡቡ፣ ምሥራቁ፣ ምዕራቡ ሲነካ “አትንኩን!” ብሎ በቁጣ ቤቱን ጥሎ ወጥቷል። ይህ ውለታ ያልጠፋት ከያኒ እንዲህ ታቀነቅናለች።

በዛሬው የነፃነት ዜማ፣ በሀገር አደባባዮች ላይ ለመቆም ትናንት የተከፈለ ውድ ዋጋ አለ፤ ሰው የተባለ ውድ ዋጋ። ዛሬ ላይ ጥሩ የነፃነት መዓዛን ለመተንፈስ ያስቻለ ትናንት የከሰለ የወገን አፅም ነበር። በዚያ የውጊያ ሜዳ ላይ የብዙ ጀግኖች አጥንት እንደ ችቦ ነዷል፤ ያ የብርሃን ወጋገን ግን ዛሬ በጸና ሥነልቡናዊ ማንነትና ክብር ሁላችንንም አቁሞናል።

እጅጋየሁ ሽባባው ለዚህ ምስክሯ የዓይን እማኝ ብላ የጠራቻት ዓድዋ ናት እያለችን ነው።… ዓድዋ ተራራው -ዓድዋ – ሰማዩ ፣ ሰማዩን የሳመው የተራራው ከንፈር … ከውስጡ የሚመነጨው የትዝታ ገሞራ – ፊታውራሪ ገበየሁ – ገብቶ ሲነድድ – መዓዛው ለዛሬ ጣፋጭ- የነፃነት ዜማ … የባርነት ስርየት ነው። የመትረየስ እሳት ምላስ ያነደደው ተራራ፣ አፈሩን የዛቀው መድፍ ግራና ቀኙን የተጎሰመው ነጋሪት ድምፅ ያሸበረው ቁጥቋጦ የተሳከረውን ድብልቅልቅ ዋጋ፣ ስሌቱን የታሪክ ድርሳናት ብቻ ሳይሆኑ ዓድዋ ራሱ ይተርከው ብላለች።

ከያኒዋ ‹‹ትናገር … ትናገር!›› ያለችው ያኔ የነበረችው፣ ዛሬም በጉያዋ ስር ያንን ተዓምር ያቀፈችው እርሷ ናት!… የነደደ ፊቷ … የከሰለ ልቧ … ያንን ጠባሳ በእንባ እያጠቀሰ ሳይሆን በሳቅ እየፈካ ይናገረዋል!… እንባችንን አባቶቻችን አልቅሰው በሳቅ መንዝረው ሰጥተውናል! አፈር ሆነው ወርቅ አውርሰውናል!

እጅጋየሁ ሽባባው ዓድዋን እንዲህ ታሞካሻታለች፤

‹‹ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትናንት፣

መቼ ተረሱና የወዳደቁት፡፡

ምስጋና ለእነሱ የዓድዋ ጀግኖች፣

ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ጀግኖች፡፡

የጥቁር ድል አምባ ዓድዋ አፍሪካ እምዬ ኢትዮጵያ

ተናገሪ የድል ታሪክ አውሪ …. ዓድዋ ››

በዜማ አቀንቅና አላበቃችም፤ ስለ ዋነኞቹ ጀግኖች አውስታለች፤”ምስጋና!” ብላ የክብር ዘውድ ደፍታላቸዋለች፤ አበባ ጉንጉን አጥልቃላቸዋለች፤ ሻማ ለኩሳለች።

የስንኟ ጅማሬ ከሰው ልጅ ጥቅም ተነስቶ ወደ ጥቁር ሕዝቦች ከዚያም ወደ አፍሪካ አፍንጫ ደርሷል፤ የድሉን አበባ እያሸተተች፣ ጀግኖች በነሰነሱት የነፃነት ጉዝጓዝ በክብር አዚማለች። ኢትዮጵያ የአፍሪካ-የጥቁር ሕዝቦች ከፍታ ችቦ ለኳሽ!… ታዲያ ይህን ታላቅ የአንድነት ዋጋን ዛሬ ላይ ጠብቆ የማቆየትን ቅኔ ሊቀኝ የሚሻ ሌላ ከያኒ እናጣ ይሆን? ልብ ያለው ልብ ይበልና ያቺን የጥቁር ፈርጥ አትዮጵያን ዳግም ወደ ከፍታ መንበሯ ለመመለስ የዘመን አርበኛ እንሁን እላለሁ።

ለብሥራት

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You