ብሌን ኪነጥበባዊ ምሽት ነገ ይካሄዳል
በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር እየተዘጋጀ በየወሩ የሚቀርበው ብሌን የኪነጥበብ ምሽት ስድስተኛው መርሃ ግብር ነገ ሰኔ 3 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን ከ11፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡
ገጣሚና ጋዜጠኛ ሰለሞን ደሬሳ ይታወስበታል፤ ይዘከርበታል በተባለው በዚህ ምሽት በርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ፣ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፣ የፍልስፍና መምህር ዮናስ ዘውዴ እንዲሁም ከገጣሚያን ፍሬዘር አድማሱ፣ ትዕግስት ማሞ፣ ባዩልኝ አያሌው፣ ኤልስ ሽታሁን፣ እንድርያስ ተፈራ እንዲሁም የፊልም ባለሙያው ሄኖክ አየለ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ በዝግጅቱ ላይ መታደም ለሚፈልጉ ሁሉ ማኅበሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
‹ጥበብን ፍለጋ› የሥዕል አውደ ርዕይ ለእይታ ክፍት ሆኗል
‹ጥበብን ፍለጋ/In Search of Wisdom/› የሚል ስያሜ የተሰጠውና የሰዓሊ ዮናስ ኃይሉ ሥራዎች የሚቀርብበት የሥዕል አውደ ርዕይ ካሳለፍነው ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2011ዓ.ም ጀምሮ ለእይታ ክፍት ሆኗል፡፡
በጣሊያን የባህል ማዕከል ተከፍቶ ለእይታ የቀረበው አውደ ርዕዩ እስከ ሰኔ 9 ቀን 2011ዓ.ም ክፍት ሆኖ ይቆያል የተባለ ሲሆን፤ ከሰኞ እስከ አርብ በሥራ ሰዓት ተመልካቾች ወደስፍራው በማቅናት እንዲመለከቱት አዘጋጆቹ ጋብዘዋል፡፡
ዳጉ ሚድያ ወርሃዊ ፌስቲቫል ማክሰኞ ይከናወናል
ወርሃዊው ዳጉ ሚድያ ፌስቲቫልና ዓመታዊ ሽልማት የሰኔ ወር መርሃ ግብር «ምርጫና ሚድያ በኢትዮጵያ» በሚል መሪ ሃሳብ ከነገ በስቲያ ሰኔ 4 ቀን 2011ዓ.ም ማምሻውን ከ11፡00 ጀምሮ በቦሌ ዳይመንድ ሆቴል ይከናወናል፡፡
ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን እንደሚያካትት በተገለጸው በዚህ ክዋኔ በፖለቲካ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን ተሳትፎ የሚያደርጉ እንግዶች ተጋብዘውበታል፡፡ ሙያዊ ወግ ይቀርባል፤ ከመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ባለሙያዎችም የሚመካከሩበት መድረክ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዕለቱ አንጋፋው ድምጻዊ አሸናፊ ከበደ ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረኩ እንደሚገኝ የክዋኔው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ማናዬ እውነቱ ገልጸዋል፡፡ መታደም ለሚፈልጉም ሁሉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ነብይ መኮንን «ነብይ» የሆነበት መድረክ ተካሄደ
ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ነብይ መኮንንን ያከበረ መድረክ ከትናት በስቲያ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ተከናውኗል። ይህ ዝግጅት በሥነጽሑፍ ሕይወታቸው ላበረከቱት ድንቅ ተግባር ውለታ የሚታወስበት ሲሆን፤ በዚህኛው መድረክም ነብይ መኮንን ተታውሶበታል።
በቦታው ከገጣምያን ጌትነት እንየው፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ተስፋሁን ጸጋዬ፣ አበባው መላኩ፣ ደምሰው መርሻ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ምልዕተ ኪሮስ፣ ምሥራቅ ተረፈና ረድኤት ተረፈ ተገኝተውበታል። ወግ አቅራቢዎቹ ደግሞ ተፈሪ አለሙና በሃይሉ ገብረመድህን ነበሩ።
በሙዚቃው ያጀበው መሶብ የባህል ቡድን ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎችም ተገኝተውበታል። ለገጣሚ፣ ደራሲ፣ ተርጓሚና ጋዜጠኛ ነብይ መኮንንም የቤት ሥጦታ ተበርክቶለታል።
«ትውልድ አይደናገር፣እኛም እንናገር» የተሰኘው መጽሐፍ ለገበያ ቀረበ
«ትውልድ አይደናገር፣እኛም እንናገር» የተሰኘው በፖለቲከኛው አንዳርጋቸው ጽጌ የተጻፈው መጽሐፍ ለአንባብያን የቀረበ ሲሆን፤ በፖለቲካው ዘርፍ አዲስ አበባ፣አንድ ቤተስብ፣ አብዮቱ እና ኢህአፓ ምን እንደሚመስሉ የተዳሰሰበት ነው ተብሏል።
664 ገጽ ያለው ይህ መጽሐፍ ለገበያ የቀረበው በ379 ብር ሲሆን፤ 19 ምዕራፎችም እንዳሉት ከበፍቃዱ አባይ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አምስተኛው አገር አቀፍ የግዕዝ ጉባዔ «ግዕዝና ስነ ፈውስ» በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ በባህልናቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጽሐፍት ኤጀንሲ እና በትግራይ ክልል ባህልናቱሪዝም ቢሮ አስተናጋጅነት የሚከበረው ይህ ጉባኤ የግዕዝን በርካታ ጥበቦችና ምስጢራት ለማወቅ አቅም የሚፈጥር እንደሚሆን ተገልጿል። ቋንቋውን ለመጠቀምና ለማሳደግም ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነም ተጠቁሟል። የዘንድሮው ጉባዔ ግዕዝ ከስነ ፈውስ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት የሚዳሰስበት መሆኑም ከቀደሙት አራት ጉባኤዎች ለየት ያደርገዋል ተብሏል።
በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የኃይማኖት አባቶችና የዘርፉ ባለሙያዎች እንደተገኙበትም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011