
ዜና ሐተታ
ድርጊቱ ለነዋሪው የደኅንነት ስጋትና ፈተና ሆኗል፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ግለሰቦች ለማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ አካላዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይወድቃሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጠራራ ፀሐይ ንብረቴን ተቀማሁ እያለ የሚጮኸው ተበራክቷል፡፡ በከተማው የሚፈጸመው ይህ እኩይ ተግባር ለነዋሪዎቹ ቀውስና ፈተናን እየደቀነ ቀጥሏል፡፡
ወጣት ገነት ግርማ (ስሟ የተቀየረ) የዚህ ወንጀል ገፈት ቀማሽ ነች። ከመገናኛ ወደ ሃያ ሁለት ለመሄድ ነው ከቤቷ የወጣችው። ከዚያም መደበኛ ሥራውን እየሠራ ወደሚመስለው ታክሲ ገባች፡፡ ጉዞ ከጀመረች በኋላ ግን ነገሩ መቀየሩን ተረዳች፡፡
ወደ ታክሲው ስገባ ዝምታና ከፍተኛ የሲጋራ ሽታ ነበር የምትለው ወጣት ገነት፤ ከመገናኛ ጎላጎል እንደደረሱም የዘረፋ ተግባራቸውን እንደጀመሩ ትናገራለች፡፡ የታክሲው ሾፌር በአካባቢው ሰው መኖሩን አለመኖሩን ካጣራ በኋላ ለእኩይ ተግባር አጋሮቹ ምልክት ይሰጣል፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር ከኋላዋ ተቀምጦ የነበረው ተባባሪ አንገቷን በማነቅ በስለትና በመድኃኒት አስፈራርቶ ሞባይል ስልክ፣ 10 ግራም የአንገት ሐብል እንዲሁም 200 ብር የነጠቋት፡፡
ወጣት ገነት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በታክሲዎች ለመንቀሳቀስ የድሮው አይነት በራስ መተማመን እንደሌላት ትናገራለች፡፡ ከድርጊቱ በኋላ ለተለያየ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጫናም ተጋልጣለች፡፡ የመኪናውን ሰሌዳ ቁጥር በመያዝ አቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ጥቆማ ብታቀርብም ያለብን ጉዳይ ብዙነው በሚል ምላሽ መፍትሔ ሳይሰጣት እንደቀረች ትጠቁማለች፡፡
ከንብረቱ መጥፋት በላይ በፖሊስ በኩል የተሰጠኝ ምላሽ የበለጠ የደኅንነት ስጋት እንዲሰማኝ አስገድዶኛል ባይ ናት፡፡ ፖሊስ መርምሮ ወንጀለኛውን ለማቅረብ ሰዎች መሞት አይጠበቅባቸውም የምትለው ወጣት ገነት፤ ሕዝቡ በፀጥታ አካላት ላይ እምነት እንዲኖረውና ይህንን እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ከሥራቸው እንዲታቀቡ ለወንጀሉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መሥራት እንዳሚያስፈልግ ትመክራለች፡፡
ከአጎና ሳሪስ እየተጓዝኩ ትራፊክ ሊቀጣኝ ነው ውረጂ በሚል ማዋከብ የሞባይል ስልኬን ቀሙኝ ያለችው ደግሞ ወጣት የምሥራች ደስታ ናት (ስሟ የተቀየረ)፡፡ የወንጀል ድርጊቱ የግለሰቦችን ሕይወት ያመሰቃቅላል የምትለው ወጣት የምሥራች፤ ወቅቱ ሥራ ፈላጊ የነበርኩበት ጊዜ በመሆኑ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና አጋልጦኛል ትላለች፡፡
የሥራ እድል ፈጠራ ውስንነት፣ የፀጥታ አካላት ከኅብረተሰቡ ለሚቀርበው ጥቆማ ተገቢውን ምላሽ የማይሰጡ በመሆኑ፣ የፖሊሶች ስምሪት ውስንነትና ማኅበረሰቡ ድርጊቱን በጋራ አለማውገዝ ለጉዳዩ መባባስ ምክንያት ሆኗል ትላለች፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በተለምዶ ሿሿ እየተባለ የሚጠራው የወንጀል ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር እያዋለ ይገኛል ይላሉ፡፡ ፖሊስ ግንባር ቀደም ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ ወንጀል መከላከል ነው የሚሉት ምክትል ኮማንደሩ፤ በተለይ ተሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረቡ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይናገራሉ፡፡
ድርጊቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ተጨማሪ ሥራዎች ይጠይቃልም ነው የሚሉት፡፡ ኅብረተሰቡ በየጊዜው ለሚደረገው የወንጀል መከላከል ተግባር ለፖሊስ ተባባሪ መሆን እንዳለበትም ምክትል ኮማንደሩ ይገልጻሉ፡፡
የፖሊስ አካላት በአግባቡ ጥቆማችንን አልተቀበሉንም በሚል ለተነሳው ቅሬታም፤ ፖሊስ ጣቢያዎችም ሆኑ የፖሊስ አባላት ጥቆማዎችን ተቀብለው ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ይህንን በማያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 / 2016 ዓ.ም