የቱሪስት አስጎብኚዎች ታሪካዊ ቦታዎቻችን፣ መዳረሻዎቻችን እና የቱሪዝም መስህቦች በማስጎብኘት አምባሳደሮች በመሆን ያገለግላሉ። የጎብኚዎችን ልምድ በማሳደግ እና ዘላቂ ቱሪዝምን በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። አስጎብኚነትም (Tour Guiding) ለዓለም የቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያበረክት ሙያ ውስጥ ይመደባል። የመስህብ ሥፍራዎችን በቱሪስቶች እይታ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግም ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስዱት እነዚሁ ባለሙያዎች ናቸው።
የቱሪስት አስጎብኚዎች፤ አረንጓዴ ቱሪዝምን በማስተዋወቅ፣ ቅርሶች እንዲጠበቁ፣ አዳዲስ መዳረሻዎች እንዲፈጠሩ በማበረታታት እና በመሞገት ለለውጥ የሚታገሉም ጭምር ናቸው። ስለ ተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አካባቢዎች ግንዛቤ ለመፍጠር የቱሪስት አስጎብኚዎች በልዩ ሁኔታ ተመራጭ ናቸው። ከቱሪስቶች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ለአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፍ አድገት ምሰሶ ሲሆን ይታያል። የአንድ ሀገር መንግሥት የቱሪዝም ሀብቶቹን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኙ ከሰራ ቅድሚያ ሊያሳድጋቸውና ሊደግፋቸው ከሚገቡ ሙያዎች ውስጥ አስጎብኚ (Tour Guide) አንዱ ሊሆን እንደሚገባ ምሁራን ሲመክሩ ይደመጣል።
ኢትዮጵያ ካለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት መስጠቷ ይታወቃል። ቱሪዝም ከዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ በማድረግም የፖሊሲ ማሻሻያ አድርጋለች። ያንን ተከትሎ ሰፋፊ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች፣ የገበያና የፕሮሞሽን እቅዶች በማውጣት ዘርፉ ውጤት እንዲያመጣ እየተሠራ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይሰማል። በዚህ ውስጥ በዘርፉ አስጎብኚዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎችን ለማፍራትም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ህብረት ፈጥረው ቱሪዝም ላይ የድርሻቸውን ለማበርከት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ባሳለፍነው ሳምንት ዓለም አቀፍ የአስጎብኚዎች ቀን በመላው ዓለም ተከብሮ ነበር። የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎችም በመሠረቱት ማህበር አማካኝነት ይህንን ቀን ሙያዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር፣ ሊሻሻሉ፣ ሊጎለብቱ ይገባል ያሏቸውን ሃሳቦች ከባለድርሻ አካላት ጋር ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ በመምከር አክብረውታል።
አቶ እንደኛነው አሰፋ የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት በአህጉር ደረጃ ደግሞ የሰሜንና የምስራቅ አፍሪካ ጀነራል ማናጀር በመሆንም ይሠራል። እንደ እርሱ እምነት በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ቱሪዝምን የጀመረው እና እየመራ ያለው አስጎብኚው (Tour Guide) ነው። ከዚህ መነሻ በባለድርሻ አካላት ሙያው ላይ ያለውን አመለካከት ለማሳደግ እየሠሩ እንደሚገኙ ይገልፃል። የቱሪዝም ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስጎብኚዎችን እየደገፈ መሆኑን አንስቶ ይህም በማያቋርጥ የሙያ ላይ አቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ ያስተላልፋል።
ማህበራቸው አስጎብኚዎች በመስክ ላይ ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ከመደበኛው ሰዓት ውጪ የማስጎብኘት አገልግሎት ይሰጣሉ የሚለው ፕሬዚዳንቱ፤ ያንን ታሳቢ ያደረገ ፍትሀዊ ክፍያ በቱር ኦፕሬተሮች ሊመደብለት እንደሚገባም ይገልፃል። በተለይ አስጎብኚው እንግዶችን ወደ መስህብ ስፍራ ይዞ በሚንቀሳቀስበት ወቅት በርካታ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል በማንሳት ለዚህም ዓለም አቀፍን ተሞክሮ በመውሰድ የጤና ኢንሹራንስ መግባትና ዋስትናውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ይገልፃል። የመገናኛ ብዙሃኑም በሙያው ላይ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በመቀየር ረገድ የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ያሳስባል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፤ አስጎብኚዎች በቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ባለሙያዎች መሆናቸውን ይናገራሉ። የማህበረሰብን ባህል፣ ታሪክና ተፈጥሮ ለጎብኚው በሚገባ ከማስጎብኘት ባሻገር ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ይናገራሉ።
አንድ አስጎብኚ ቱሪስቱን ወደ መስህብ ሥፍራዎች በሚወስድበትና በሚያስጎበኝበት ወቅት፤ በቸልተኝነት ቱሪስቱ ፓርኩ፣ አሊያም የዱር እንስሳት የሚኖሩበት የተፈጥሮ ስፍራ ላይ የማይገቡ ተግባራት ሊፈፅም ይችላል የሚሉት አቶ ስለሺ፤ ይህንን መሰል ተግባር እንዳይፈጠር የአስጎብኚው ሚና ትልቅ እንደሆነ ይገልፃሉ። ቱሪስቶች የመጡበት ማህበረሰብ እና አመለካከት በሚጎበኙበት ማህበረሰብ ላይ ተፅእና እንዳይፈጥር፣ የአካባቢውን ባህል እንዳይበርዙ፣ ሃይማኖቱን እንዲያከብሩ ጥንቃቄ ለማድረግም ከፍተኛ ድርሻ የሚጫወት መሆኑን ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎችም ይህንን መርህ ተከትለው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ያነሳሉ። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም አስጎብኚዎች ተገቢውን ሙያዊ ድጋፍና ክብር እንዲያገኙ ከባለሙያዎቹና ከማህበሩ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ይገልፃሉ።
አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ዩኒት አስተባባሪ ናቸው። ዓለም አቀፉ የአስጎብኚዎች ቀን ክብረ በዓል ላይ በተካሄደው ውይይት ላይ የአስጎብኚነትን ሙያ በተመለከተ ሙያዊ ሃሳባቸውን አጋርተው ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ለአስጎብኚነት የነበረው አመለካከት የተዛባ እንደነበር ይገልፃሉ። ቋንቋ የቻለና መንገድ የሚያውቅ ሁሉ አስጎብኚ ተደርጎ የሚቆጠርበትና የተሳሳተ እይታ የነበረበት ወቅት መኖሩንም አንስተው፤ ሙያው እንደ አንድ የትምህርት መስክ መሰጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተሻሻሉ ነገሮች ያሉ ቢሆንም አመለካከቱ ግን አሁንም ድረስ በሚፈለገው ልክ እንዳልተስተካከለ ይገልፃሉ።
በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ አስጎብኚዎች ወሳኝ ሥፍራ ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ የኢትዮጵያ የዘርፉ ፖሊሲም ይህንን ያቀፈ መሆኑን ይናገራሉ። አስጎብኚዎች ጎብኚውን ከማህበረሰቡ፣ ከእሴቶቹ፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ እጅግ ወሳኝ ሚና ያለው እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል ይላሉ።
‹‹የአስጎብኚነት ወሳኝ ሚና አንዱ መገለጫ የኢትዮጵያን ገፅታን በመገንባት ረገድ የሚወስደው ድርሻ ነው›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ የሀገር ገፅታ በሰው የሚገለፅ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም አንድ አስጎብኚ በመልካም ሥነምግባር፣ በበቂ እውቀትና እንግዳ ተቀባይነትን በተላበሰ የአገልጋይነት ስሜት ጎብኚዎችን ተቀብሎ፣ ደህንነታቸውን መጠበቁን አረጋግጦ የሚፈልጉትን የመስህብ ሥፍራ እንዲጎበኙ የሚያስችል መሆኑን ያነሳሉ። ይህም የኢትዮጵያን ገፅታ የሚገነባው በመልካም ስም ለቀሪው ዓለም ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ሲችል እንደሆነ ይገልፃሉ። ጎብኚው አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከጋይዱ ጋር መሆኑን በመግለፅም ከዚህ አንፃር ሀገርን ለማስተዋወቅ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ይናገራሉ። ከዚህ አኳያ አስጎብኚዎች ኃላፊነትን የሚወስዱና በእሴት ሰንሰለቱ ላይ ወሳኙን ሚና የሚጫወቱ መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ ቴዎድሮስ የአስጎብኚው ሚናን የሚያጎላው ሁለተኛው ጉዳይ መረጃ መስጠት እንደሆነ ይናገራሉ። አንድ መረጃ ብቻውን ሕይወት አይኖረውም በማለትም ያንን በሚገባ ተርጉሞና ሕይወት ሰጥቶ ለጎብኚው የሚያቀርበው አስጎብኚው መሆኑን ይገልፃሉ። ይህም ሙያው ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻውና ቱሪስቱ የኢትዮጵያን ቅርሶች፣ ተፈጥሮ ቦታዎች፣ ታሪኮች ጠንቅቆ እንዲያውቅ ለማስቻል ሙያውን በሚገባ ማክበርና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። በዚህ ምክንያት አስጎብኚነት ካለው የሥራ ባህሪ የሚመነጭ እጅግ ወሳኝ የሆነ የቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ቁልፍ ሚና ያለው ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ሙያው ውስጥ ማንም ሰው ለመሥራት ስለፈለገ ብቻ የሚገባበት መሆን የለበትም›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፤ መርህ ያለው፣ ሙያዊ መመሪያና ሥነምግባር ደንብ የያዘ በመሆኑ አንድ በሙያው ላይ መሰማራት የፈለገ ግለሰብ በትምህርት፣ በልምድና በልዩ ልዩ መንገድ ባካበተው እውቀት መሆን እንዳለበተ ነው የሚገልጹት። ለዚህም ባለሙያዎቹም ሆኑ የሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት ሙያውንና ሙያተኛውን ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው ይገልፃሉ።
አቶ አሸናፊ ካሳ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ለ18 ዓመታት በአስጎብኚነት የሰራ የዘርፉ ባለሙያ ነው። እርሱ ደግሞ በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሙያው ላይ የሚደርሱ እክሎችን ባለሙያው ተሻግሮ ስኬታማ ለመሆን ከልምዱ ተነስቶ መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ምክረ ሃሳብ ይሰጣል።
የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ መስህቦች፣ ቅርሶች ሌሎችም የቱሪዝም እሴቶችን ቱሪስቱ በሚገባ የሚያውቀው ከአስጎብኚው መሆኑን የሚናገረው አቶ አሸናፊ ካሳ፤ ይህ ማለት አስጎብኚው ሥነ አእምሯዊ ጉዳይ የያዘና ኢትዮጵያን ለቀሪው ዓለም የማስተዋወቅ አቅም ያለው አምባሳደር መሆኑን ይናገራል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጥሮ (ድርቅና መሰል አደጋ) እንዲሁም ሰው ሠራሽ በሆነ ጦርነትና ግጭት ገፅታን የሚያበላሹ አጋጣሚዎች በየገዜው እንደሚከሰትና የቱሪዝም እድገት ላይ ተፅእኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ ይናገራል።
‹‹አስጎብኚው ይህንን ችግር ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ገፅታ እንዳይበላሽ ሙያውን እንደ ምቹ አጋጣሚ ሊጠቀምበት ይገባል›› የሚለው፤ አቶ አሸናፊ፤ ባለሙያ እራሱን በትምህርት በልምድ እንዲሁም ብቁ አድርጎ በማዘጋጀት የሀገሪቱ የውስጥ አምባሳደር መሆን እንደሚጠበቅበት ይናገራል። ቅርሶችን፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በቀዳሚነት መንከባከብና የሀብቶቹ ጠባቂ መሆን ያለበትም ባለሙያው እንደሆነ ይናገራል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የኮቪድ ወረርሽኝና ጦርነት ባጋጠመ ወቅት ቀጥተኛ ተጎጂ የነበረው አስጎብኚው ነበር በማለትም መሰል ችግሮችን ተቋቁሞ የኢትዮጵያን የቱሪዝም እድገት ላይ የጎላ ድርሻ ለመጫወት መትጋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል።
እንደ መውጫ
ልምድ ያላቸው አስጎብኚዎች ጉዞዎችን አስደሳች እና አስተማሪ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ምክንያት ይሆናሉ። የቱሪዝም መስህብ ቦታዎችን በተመለከተ ሰፊ እውቀት፣ የታሪክ እውነታዎች አላቸው። በሙያው ውስጥ ለብዙ ዓመታት በመቆየታቸው ምክንያት ቱሪስቶች ቆይታቸው አዝናኝ፣ አስተማሪና በትዝታ የተሞላ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ። በጠቅላላው የእግር ጉዞ ወይም የጉዞ ጉብኝት ልምድ ባለው አስጎብኚ ሲታገዝ ስኬታማ ይሆናል። ለዚህ ነው አስጎብኚዎች በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ ቁልፍ ድርሻ አላቸው የሚባለው።
በዘመናዊው ዓለም አብዛኛዎቹ ሰዎች መጎብኘት ይወዳሉ። እንስሳትን፣ እፅዋትን፣ ሸለቆዎችን፣ ወንዞችን፣ ታሪካዊ ቦታዎችን እና ሌሎች የውሃ አካላትን እንዲሁም ኮረብቶችን እና ተራሮችን የሚያካትት ተፈጥሮን ለማየት የቱሪዝም ቦታዎችን መጎብኘት ከምርጥ ተሞክሮዎች አንዱ ነው። ነገር ግን፣ ይህ ልምድ ያለ አስጎብኚዎች እገዛ የተሟላ አይሆንም። በጠቅላላው የቱሪዝም ቦታዎችን በሥርዓት በማስጎብኘት ደንበኛውን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይወስዳሉ። ከእንስሳት ጋር እንዴት እንደሚገናኙ እና የፓርኮች አጠቃላይ ገጽታ ላይ ሰፊ እውቀት እንዴት ማግኘት እንደሚቻል አስጎብኚዎች ጠንቅቀው ያውቃሉ። ይህንን መሠረት አድርገው የቱሪስቱን ፍላጎት ያሟላሉ።
አንድ ቱሪስት ስለሚጎበኘው ቦታ ባህላዊ ቅርስ እና የማይረሳ ጉዞ እንዴት እንደሚያሳልፉ የተሟላ መረጃ ያለው አስጎብኚው (Tour Guide) ነው። ለዚህ ነው የአንድ ሀገር የቱሪዝም ፖሊሲ አስጎብኚዎች ሙያዊ ብቃታቸውን ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ላይ ዘላቂ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ማእቀፍ ሊኖረው ይገባል የሚባለው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም