ዓድዋ የአንድነታችን ምስጢር ነው !

ታሪኩ አካል ነስቶ፣ ነፍስ ዘርቶ ህያው ከመሆኑ አስቀድሞ ዓለም “ይደረጋል፣ ይፈጸማል፣ ይሆናል…” ብሎ ለቅጽበት እንኳን አስቦት አያውቅም። በዓለም ታሪክም ከዚያ ቀደምና በኋላም አልተፈጸመም። ለወደፊትም የሚፈፀም አይመስለኝም። ዛሬ ላይም ታሪኩ፣ ገድሉ፣ ሲታሰብና ሲወሳ የሆነው ነገር ሁሉ ለዓለም ሕዝብ “ህልም ነው” የሚመስለው። ነገር ግን በተባበረ ክንድና በነደደ የሀገር ፍቅር ፅኑ ተጋድሎ ታሪኩ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር፣ በዓድዋ ተራራ ግርጌ በ1888 ዓ.ም እውን ሆኗል።

አውሮፓውያን በፈረንጆቹ 1884 እና 1885 በጀርመን በርሊንግ ከተማ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ከፋፍለው በቅኝ ግዛት ለመቀራመት የአህጉሪቷን ካርታ ዘርግተው ዕጣ ሲጣጣሉ፤ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት እጣ የደረሳት ያልታደለችው ጣሊያን ነበረች። ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ሕልማቸው ሰምሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአፍሪካ ሀገራትን በቅኝ ግዛት ሥር አውለዋል። ኢትዮጵያን ለመውረር ቀይ ባሕርን አቋርጦ የመጣው የጣሊያን ወራሪ ጦር ግን ያልጠበቀው ዱብዕዳ ገጥሞታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአራቱም ማዕዘን ቀፎው እንደተነካ ንብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን (ከ1895 እስከ 1896 እ.ኤ.አ) ዓድዋ ላይ የጣሊያንን ጦር ገጥሞ ድል አደረገ። ይህ የዓለምን ሕዝብ በግርምት አፉን በእጅ ያስያዘ፤ “ጥቁር ሕዝብ፣ ነጭ ሕዝብን የሚመክትበት ወታደራዊ ሳይንስም ሆነ ጥበብ እንዲሁም ሞራል የለውም” የሚለውን የተዛባና መሠረተቢስ አመክንዮና እሳቤ ፉርሽ ያደረገ ነበር።

የዓድዋ ድል ነጭ በጥቁር እንደሚሸነፍ በተጨባጭ በአደባባይ የታየበት፤ ጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሚመካበትን አኩሪ ታሪክ አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው በማይሻር፣ በማይደበዝዝ፣ በማይፋቅ ደማቅ በወርቅ የብዕር ቀለም ዓድዋ ላይ ጽፈው በክብር ያለፉበት ታሪክ የተሠራበት ነው።

አባቶቻችን ያኔ በዓለም ዙሪያ ጥቁር ሕዝብ ሁሉ በባርነት ጥላ ሥር በድቅድቅ ጨለማ ተውጦ በነበረበት ወቅት የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ችቦን አቀጣጥለዋል። የሀገራቸውን ዳር ድንበር ሳያስደፍሩ ለመጪው ትውልድ ነፃ፣ የታፈረችና የተከበረች ሀገር አስረክበዋል። አባቶቻችን “የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውንና ከዚያ ቀደም ያልተፈጸመውንና ይፈጸማል” ተብሎ የማይታሰበውን ታሪክ ዓድዋ ላይ ሠርተው ያለፉበት ምስጢሩ በዋነኝነት አንድነታቸውና ለዓላማቸው በነበራቸው ፍጹም ፅናት ነበር።

ልክ እንደዛሬው ያኔም ልዩነቶች ነበሩ። ነገር ግን አባቶቻችን በመካከላቸው የነበሩ አለመግባቶችና ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፤ በሀገራቸው ጉዳይ የሚያለያያቸው የአንዲት ፀጉር ዘለላ ያክል እንኳን ክፍተት በመካከላቸው አልነበረም። የሀገራቸውንም ዳር ድንበር ለማስከበርና ቅጥሯን ላለማስደፈር የነበራቸው የዓላማ ፅናት እንደ አለት የጠነከረ ነበር።

“አንድነት ኃይል፤ ጽናት የማሸነፍ ሚስጢር” መሆኑን ዓለም ላይ ከዓድዋ የተሻለ አስተማሪ ምሳሌ ያለ አይመስለኝም። በዘመኑ ዓለም ላይ አለ የተባለውን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቆ ቅኝ ሊገዛ የመጣውን የጣሊያንን ጦር፤ በየትኛውም የጦር ሳይንስ መመዘኛ “በጣም ኋላ ቀር በሆነ የጦር መሣሪያ ያውም በጋሻና በጦር ይሸነፋል” የሚል ግምት አልነበረም። ዛሬም ድረስ ይህ እንዴት ይሆናል? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ነገር ግን እውነታው አባቶቻችን በጋሻና በጦር አንገት ለአንገት ተናንቀው ወራሪውን የጣሊያንን ጦር አንገቱን አስደፍተው ወደ መጣበት የመለሱበት ምስጢሩ በነበራቸው አንድነትና ፅናት ነው።

ነጮች እንደሬት እየመረራቸውም ቢሆን ሳይወዱ በግድ የተቀበሉትንና የተጎነጩትን የሽንፈት ጽዋ፤ እኛ የኢትዮጵያውያን ደግሞ በዓለም አደባባይ ቀና ብለን ሁሌም እንድንሄድ ያስቻለንን የጥቁር ሕዝብ ሁሉ የድል በዓል የሆነውን “የዓድዋ በዓልን” በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ እናከብራለን፤ እንዘክራለን። እነሆ ዘንድሮም 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል እያከበርን እንገኛለን።

አሁን ላይ በዓሉን የሚያወሱ ትልልቅ ባነሮችን አሠርቶ በየአደባባዩ በመለጠፍ፣ የጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ምስል ያለበት ቲሸርት አሠርቶ ለብሶ በየአደባባዩ ወጥቶ ከመጨፈር፣ … ወዘተ ባለፈ በዓሉን ስናከብር “እውነት አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ይቺ ሀገር ዛሬ እኛ ላይ እንድትደርስ የከፈሉትን መስዋዕትነት ተረድተናል? ጠላትን ያሸነፉበት ሚስጥሩ ወይም ድል የነሱበት ጥበቡ ገብቶናል?” ብለን ራሳችን ልንጠይቅ ይገባል።

አባቶቻችን የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት የሆነውን አኩሪ ገድል ዓድዋ ላይ የፈጸሙት “አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ” ተባብለው አንድነታቸውን በመጠበቃቸው ነው። ነገር ግን እኛ ልጆቻቸው ዛሬ ላይ ተከባብሮና ተባብሮ መኖር ተስኖን በግጭት አዙሪት ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን። ለሺህ ዘመናት ያሉን ልዩነቶች ሳይገድቡን በአንድነት የኖርን ሕዝብ፤ ዛሬ ላይ በሰላም አብሮ መኖር ተስኖን ታውከናል። ያሉ ልዩነቶችን ቁጭ ብሎ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ በሃሳብ ልዕልና መሸናነፍ ተስኖን ምድሪቱ የግጭት አውድማ ሆናለች።

በየዘመናቱ የተነሱብንን ጠላቶቻችን እንደሰም አቅልጠን፤ እንደብረት ቀጥቅጠን ያሸነፍንበት የኃይላችን ምስጢር አንድነታችንን ካላከበርን የእስራኤሉ መስፍን የሳምሶን እጣ ፈንታ እንደሚያጋጥመን እሙን ነው። የሳምሶን ታሪክ ከረዥሙ በአጭሩ እንዲህ ነው። እግዚያብሔር አምላክ ለሁሉም ሰው ጸጋን ሰጥቷል። ለሳምሶን ፈጣሪ የሰጠው ጸጋ ኃይልን ነው። የኃይሉ ምስጢር ደግሞ ያለው ጸጉሩ ላይ ነው ። ይህንን የተረዱት ጠላቶቹ ኃይሉን የሚያሳጡበት ወጥመድ አዘጋጁለት።

ጠላቶቹ ያለ ቦታው ተገኝቶ ባፈቀራት ገሊላ በኩል ጸጉሩን እንዲላጭ አደረጉት። ጉልበታሙ ሳምሶን የጠጉሩን ምስጢር እወቀ ጸጉሩን ለምላጭ አሳልፎ ሰጠ፤ በዚህም ኃይሉን አጣ ። በጠላቶቹ እጅ ወድቆ መጫወቻ ሆነ፤ ሁለት ዓይኑን አጥፍተው ተዘባበቱበት፣ ተፉበት፣ ተሳለቁበት፣ እንደ አሻንጉሊት ተጫወቱበት፣ አዋረዱት። ሳምሶን የተሰጠውን ጸጋ ተረድቶ በአግባቡ ሥራ ላይ ባለማዋሉ ክንዱ ዝሎ ለጠላቶቹ የጭካኔ ፈቃድ ተላልፎ ተሰጠ።

ልክ የእስራኤሉ መስፍን ሳምሶን ጉልበታሙ ፤ ጸጉሩን ሲላጭ ኃይሉን አጥቶ የጠላቶቹ መጫወቻ እንደሆነ ሁሉ፤ ውስጣዊና ውጫዊ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ደግሞ የኛ የኢትዮጵያውያን የኃይላችን ምስጢር የሆነውን አንድነታችን በመሸርሸር እንደ ቅርጫ ስጋ ከፋፍለው ተራ በተራ ሰልቅጠው ሊውጡን እንደ ጆፌ አሞራ ዙሪያ ዙሪያችን እየዞሩን ነው።

ከከፍታ ማማችን አውርደው በብሔርና በጎጥ ከፋፍለው ኃይላችን አሳጥተው አቅመ ቢስና ልፍስፍስ ሊያደርጉን እየታተሩ ነው። የኃይላችን ሚስጥር የሆነውን አንድነታችን ለማሳጣት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ይህ ደግሞ በገሃድ መሬት ላይ እየታየ ነው።

ስለዚህ የጥል ግድግዳውን ይቅር ለፈጣሪ ተባብሎ በመናድ፣ የተሰበረውን የፍቅር ድልድይ መልሶ በመገንባት፣ የተበደለውን በመካስ፣ በብሔርና በጎጥ ሳንከፋፈል፣ ከኢትዮጵያዊነት የከፍታ ማማችን ሳንወርድ ልክ እንደ ዓድዋው ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነት ቆመን ጠላቶቻችን የምናሳፍርበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

የተሰጠነን ፀጋ ተረድተንና በአግባቡ ጠብቀን ልክ እንደ አባቶቻችን የሀገራችን ዳር ድንበር አስከብረን ሳትሸራረፍ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የዛሬው ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው። ይህን ሳናደርግ ሀገር እንደቅርጫ ስጋ ከተከፋፈለች ነገ ላይ በልጆቻችን ዘንድ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆናችን ባለፈ አጽማችን በሰላም የምታርፍበት ምድር ወይም ሀገር እንዳማይኖረን ልንረዳው የሚገባ መራራ ሀቅ ነው።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን  የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You