የአፍሪካ ኩራት የሆነው ዓድዋ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም

የጥቁሮች የነጻነት ተምሳሌት ተብሎ ዓለም የመሰከረለት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም የሚኮሩበት፣ ብዙ ቁም ነገር የሚማሩበትና ሁልጊዜም ቢሆን ትኩስ የድል ስሜት ሆኖ የሚቀጥል እያደር አዲስ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶችና እናቶች ምስጋና ይግባቸውና አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡበትን የነፃነት በዓል ሲያከብሩ፤ ኢትዮጵያ ግን የድል በዓሏን ስታከብር ዓለም ያውቃታል።

ከኢትዮጵያ አልፎ በቀኝ ግዛት እና በባርነት ውስጥ ለነበሩ አፍሪካ ሀገራት ነጻ መውጣትና ለፓን አፍሪካኒዝም መወለድ ምክንያት የሆነው የዓድዋ ድል እነሆ 128ኛ ዓመት ላይ ደርሷል፡፡ ዘንድሮ የሚከበረው ዝክረ ዓድዋም ካለፉት 127 ዓመታት ጋር ሲነጻጻር ልዩ የሚያደርገው አንድ ሁነት ከሰሞኑ በመዲናችን አዲስ አበባ መሀል ፒያሳ ላይ ተከውኗል፡፡ ይህ ክዋኔም ዓድዋን በልኩ ሊዘክርና ግዝፈቱን ሊያሳይ የተወከል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ነው፡፡

በግዙፉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የሚከበረው 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ለከተማው ነዋሪ ምን ስሜት ፈጥሯል፤ ሲል አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ስሜታቸውን እንደሚከተለው አጋርተዋል፡፡

ተማሪ ሃና ወንድምአገኝ የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ስካውት አባል ነች፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ሳትገዛ ነጻነቷን አስጠብቃ የቆየች በመሆኑ በየዓመቱ የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር የተለየ የደስታ ስሜት የሚፈጥርባት እንደሆነ ጠቅሳ፤ በባህላዊ መሣሪያ በመታገዝ ከሁሉም በላይ በሀገር ወኔ በአንድነት በቆሙ አባቶቻችን የተገኘው ድል ዛሬ ላይ ቀና ብለን ለመሄዳችን ምክንያት ነው ትላለች።

ለዚህ ታላቅ ድልም በቅርቡ ግንባታው ተጠናቅቆ ለጉብኝት ክፍት የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባቱ እጅግ የሚያስደስት መሆኑን ገልጻ፤ እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑ የሚያሳዝን ቢሆንም አሁን ላለውና ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ ጠቃሚ የሆነ ሙዚየም ነው ትላለች። ምክንያቱም ታሪካችንን በሚገባ በመሰነድ እና ለጎብኚዎችም በማሳየት ኢትዮጵያን የበለጠ ለማስተዋወቅ እና ከታሪካዊ የቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚገኝበት በመሆኑ ጠቀሜታው ከመታሰቢያም በላይ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ተናግራለች።

አቶ ፍቅረሰላም መኮንን የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ የዓድዋ ድል ከየትኛውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት እውቅና ያገኘው መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች፣ አባቶችና እናቶች በአንድነት ሆነው ያስመዘገቡትን የነጻነት ድል የዛሬው ትውልድም በጋራ ልማትና የሀገር ዕድገት ላይ ሊደግመው ይገባል ይላሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ትውልዱ የሀገሩን ታሪክ በጠራ መልኩ ማወቅ እና መረዳት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም ትኩረቱን ወደ ሥራ እና ልማት በማድረግ ጊዜው የሰጠውን ዕድል ሁሉ አሟጦ በመጠቀም የዓድዋ ድልን በኢኮኖሚው መስክ መድገም የሚጠበቅበት መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ አባቶቻችን የሀገር ነጻነትን ያስጠበቁበት የዓድዋ ድል ታሪክና ክብር በሚገባው ልክ የሚያውቅ ትውልድ መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህም አሁን እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ በቅርቡም የተገነባውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየሙ ያለፈውን ታሪክ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን በተጨባጭ ሊያውቅና ሊጠቀምበት የሚያስችለው ነው፡፡

ሙዚየሙ ስለ ዓድዋ እና ከዓድዋ ጋር ተያይዞ ስላለው የመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ታሪክ የሚያስረዳ በመሆኑ ትውልዱ ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው በተጨማሪ ትልቅ ዕውቀት የሚጨምርለት ነው፡፡ ትውልዱ የተከፈለትን መስዋዕትነት ይበልጥ እንዲያውቅ የሚያግዘው ይህ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በዚህ በአጭር ጊዜ መገንባቱም እጅግ አስደሳችና አኩሪ ታሪክ ነው ይላሉ፡፡ ትውልዱ የዓድዋን የድል ታሪክ በአግባቡ እንዲያውቅና እንዲረዳ ከማድረግ ባለፈ ሕዝቡን በአንድ ማስተሳሰር የሚችል መታሰቢያ ሙዚየም እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

አቶ ፍቅረሰላም፤ ባለፉት መቶ ዓመታት የተለዋወጡ መንግሥታት የዓድዋ ድል በዓል በዚህ ልክ እንዲታወስና ትውልዱ እንዲረዳው አላደረጉም፡፡ ይህ የሚያስቆጭ ነው፡፡ አሁን ግን የመላው ኢትዮጵያውያን ታሪክ የሆነው የዓድዋ ድል በሚመጥነው ከፍታ ከፍ ብሎ ታይቷል። ታሪካችንም መነበብ መታየት የሚችልበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም በዚህ መታሰቢያ ሙዚየም አማካኝነት ኢትዮጵያ ከፍ ብላለች ዓድዋም የሚመጥነውን ክብር አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ትውልዱ ከታሪኩ መማር ይኖርበታል ይላሉ፡፡

አንዳንድ ጸሐፍቶች እና የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉ የዓድዋን ታሪክ አዛብተው ሲፅፉ እንደነበር ያነሱት አቶ ፍቅረሰላም፤ የዓድዋ ድል ሊደበዝዝ የማይችል ተነግሮ የማያልቅ ደማቅ አኩሪ ታሪክ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትውልዱ ላይ በተፈጠሩ የተዛቡ ትርክቶች የጋራ አንድነትን እና ወንደማማችነትን ለመሸርሸር ተሠርቷል፡፡ ይሁንና ትውልዱ ታሪኩን መረዳት በሚችልበት የጋራ ትርክት ላይ በመሥራት አንድነትን እና ወንድማማችነትን ማጠናከር እንደሚገባ በማመላከት በቀጣይም ትውልዱ እንደ ጀግኖች አባቶቹ ሁሉ የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድነቱን አጠናክሮ በጋራ ሊቆም ይገባል በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

ሌላው የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወራቄ ዑመር በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ትውልዱ ታሪኩን በአግባቡ እንዳያውቅ ተደርጎ በተዛቡ ትርክቶች ውስጥ በመቆየቱ በትርክቶቹ ምክንያት ወደ አላስፈላጊ ግጭቶች ሲያመራ የነበረ መሆኑን አንስተው ሲያስረዱ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እነዚህን የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማረም እና ዓድዋንም በሚገባው የታሪክ ከፍታ ልክ ለመገለፅ ተሠርቷል፡፡ ከተሠሩ ሥራዎች መካከልም የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም አንዱ ነው፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከመታሰቢያነቱ ባለፈም የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡

በመሆኑም ትውልዱ ከዓድዋ ድል ብዙ ሊማር ይገባዋል፡፡ በተለይም፤ አንድነትን እና ለጋራ ጉዳይ በጋራ መቆምን ከዓድዋ አርበኞች በመማር ጀግኖች አባቶቹ ያቆዩለትን ሀገር በአንድነት ማስጠበቅ፣ ባህሉን እና እሴቶቹን መጠበቅ ይኖርበታል ይላሉ። ‹‹ጣልያን ተደራጅቶ እና ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ ለወረራ ሲመጣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶች ግን በባዶ እግራቸው ከሁሉም አቅጣጫ በወኔ ወጥተው ድል ተቀዳጅተዋል›› የሚሉት አቶ ወራቄ፤ የዓድዋ ድል ከኢትጵያውያን ባለፈ የአፍሪካውያን ድል ኩራት መሆኑን ጠቅሰው በወቅቱ በባርነት ቀንበር ስር ለነበሩ አፍሪካውያን በሙሉ ነጻ የወጡበት ፋና ወጊ የነጻነት ድል ነው ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ያለው ትውልድ አባቶቹ ያስረከቡትን ሉዓላዊት ሀገር በልማትና በቴከኖሎጂ ወደፊት ለማራመድ በቅድሚያ አንድነቱን ማጠናከር አለበት›› የሚሉት ደግሞ የሌተናንት አብዲሳ አጋ አምስተኛ ልጅ ወይዘሮ አኒሳ ወይም ኤልሳቤት አብዲሳ አጋ ናቸው። የሌተናንት አብዲሳ አጋ አምስተኛ ልጅ የሆኑት ወይዘሮዋ እንዳሉት አኒሳ አባታቸው ያወጡላቸው ስያሜ ሲሆን እናታቸው ደግሞ ኤልሳቤት ብለው ይጠሯቸው ነበር።

ወይዘሮ አኒሳ ወይም ኤልሳቤት እንደሚሉት፤ የኢትዮጰያውያን ማንነት የሚታወቀው በጀግንነት ነው፡፡ ጀግንነቱም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ታሪካዊ ከሆኑት ከጀግኖች እናቶች እና አባቶቹ የተወረሰ ነው። የዓድዋ ድልም የኢትዮጵያውያን ጀግኖች መታሰቢያ ድል ከመሆን ባለፈ የመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት በኢትጵያውያን ጀግኖች የተገኘ ድል ነው፡፡ ድሉ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል እንደመሆኑ አሁን ያለው ትውልድም የጀግኖች አባቶቹን ታሪክ በመድገም በልማት ዳግም ዓድዋን መፍጠር እንዳለበት አንስተዋል። በመሆኑም በሁሉም ዘርፍ ሀገሩን በጀግንነት መጠበቅ እና በጀግንነት የወረሰውን ነፃነት ማስቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።

ወይዘሮ አኒሳ ወይም ኤልሳቤት፤ ወላጅ እናታቸው ከሆለታ የጦር ትምህርት ቤት በመውጣት ከአብዲሳ አጋ ጋር ጣልያን ድረስ የዘመቱ መሆኑን አስታውሰው፤ ‹‹ሴቶችም ሆነ ወንዶች ከአባቶቻቸው የወረሱትን የሀገር አደራ በመጠበቅ እና በጀግንነት ለሀገራቸው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል›› በማለት የዛሬው ትውልድም ኢትዮጵያ ምን ላይ እንዳለች ዓይኑን ከፍቶ ማየት አለበት፡፡ ከአባቶቹም ሆነ ከታናናሾቹ መልካሙንና ለሀገር የሚጠቅመውን በጎ ሥራ የመሥራት ግዴታና ኃላፊነት አለበት በማለት አስገንዝበዋል፡፡

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You