የዓድዋ ሙዚየም – ጀግኖቻችንን እና አንጸባራቂ ድላቸውን የሚመጥን

ጥቁር እና ነጭ እኩል መሆኑን ማረጋገጫ የሰጠ፤ የዓለምን የፖለቲካ አሰላለፍ የቀየረ፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የኩራት ምንጭ የሆነው የዓድዋ ድል ሊታወስ እንደሚገባ አያከራክርም፡፡ በእርግጥ ለ127 ዓመታት ሲወሳ ኖሯል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን እያከበርን እንገኛለን። ነገር ግን ድሉን ያስመዘገቡ ጀግኖች በልካቸው በእርግጥ በአግባቡ አውስተናቸዋል? የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ ያጠያይቃል፡፡

የውጪውን ዓለም ያዩ የታሪክ ምሑራንም ሆኑ ሌሎች የተለያዩ ዜጎች የዓድዋ ድል በግዝፈቱ ልክ ማስታወሻ እንዳልተቀመጠለት እና እየታወሰ አለመሆኑን ደጋግመው ሲያነሱ ቆይተዋል፡፡ መነሻቸው በዓለም የሀገራቸውን ጀግኖች ለመዘከር የተለያየ ታሪካዊ ሙዚየሞችን የገነቡ ሀገሮችን በመጎብኘታቸው ነው፡፡ በትልቅነታቸው፣ የታመቀ ታሪክን ቀርፆ በመያዝ፣ በጎብኚዎች ብዛት እና በሌሎችም መመዘኛዎች ታዋቂነትን ያተረፉ ሙዚየሞችን ከገነቡ ሀገራት መካከል አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ አየር ላንድ፣ ግሪክ፣ ጃፓን እና አሜሪካን ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህ ሀገራት ጀግኖቻቸውን የሚያወሱ እና ስለጀግኖቻቸው ታሪክ በሰፊው ሊያስረዱ የሚችሉ ሙዚየሞችን ሲገነቡ፤ እነርሱ የፈፀሙት ጀብድ ከኢትዮጵያ ጀግኖች ጋር የሚነፃፀር አይደለም።ሕድላቸውም በዓለም ደረጃ የዘር ልዩነትን ጥቁር እና ነጭ የሚል ክፍፍልን ወይም ነጭ ብቻ አቅም እንዳለው የሚገልፀውን ድሉ ከአገራቸው አልፎ በኢትዮጵያ የዓድዋ ድል ልክ ለሌሎች መሻገር የሚችል ሆኖ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ የሰውን ልጅ እኩልነት ማረጋገጥ እስከ ቻሉ ድረስ ሳይሆን ለሀገራቸው ነፃነት ታግለዋል በሚል ብቻ ነው፡፡

ነገር ግን ከሙዚየም በተጨማሪ የተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮችም ሆኑ አሜሪካን እና ሌሎችም ሀገሮች ከተሞቻቸውን ያደመቁት በክብር ለሀገራቸው የተሰዉ ጀግኖቻቸውን በሚያውሱ ሐውልቶች ነው፡፡ መናፈሻ በመሥራትም መታሰቢያነቱን ለጀግኖቻቸው ይሰጣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን እዚህ ላይ ሰፊ ክፍተት እናስተውላለን፡፡ በእርግጥ ዓድዋ ሰፈር አይደለም-ዓድዋ መንደር አይደለም፤ ሀገር ነው፤ ከነታሪኩ-አህጉር ነው፣ ሰ……ፊ ዓለም ነው እያልን ግጥም ገጥመናል፡፡ ዓድዋ ዛሬ ናት ዓድዋ ትናንት መቼ ተረሱ እና የወዳደቁት ብለን ከመዝፈን ውጪ ጀግኖቻችንን በቅጡ በትውልድ አዕምሮ ውስጥ ተቀርፀው ሊቀሩ በሚችሉበት መልኩ አውስተናቸዋል ምስላቸውን ቀርፀን አስቀምጠናል ለማለት ያዳግታል፡፡

የጀግኖችን ምስል ለይቶ በማስቀመጥ በኩል በተለይ ከአሁኑ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በፊት እኛ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ክፍተት ነበረብን፡፡ ከሰፊው የዓድዋ ድል ታሪክ ውስጥ ጥቂቱን በማሳየት ለዓድዋው ድል ጀግኖች ተገቢው ማስታወሻ ሳናስቀምጥ መቆየታችን ደግሞ ያስቆጫል።ዓመት ጠብቆ በማክበር ቀኑን ለመዘከር ከሚደረግ ጥረት ባለፈ የዓድዋ ድልን ታላቅነት የሚመጥን የታሪክ ማስታወሻ በማኖር በኩል ብዙ አለመሠራቱ ብዙዎችን በእጅጉ ሲያነጋግር ቆይቷል።

ጦርነቱን ከመሩት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክን ከሚያሳይ ቅርፅ በጊዮርጊስ አደባባይ ከማስፈር ውጪ የነበሩት ማስታወሻዎች እጅግ ውስን ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል በዓድዋ ጀግኖች ስም የተሰየሙ ትምህርት ቤቶች እና የዓድዋ ድልድይ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእርግጥ ከ100 ሺህ በላይ ገበሬዎች ማረሳቸውን፣ መዝራት እና ማጨዳቸውን ትተው ወደ ቀረበላቸው ሀገርን በነፃነት የማቆየት ጥሪ ምላሽ የሰጡትን በሙሉ አካቶ ምስላቸውን በመላው ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ እንዲከተብ ማስቻል እና ለማስታወሻነት ማስቀመጥ ያዳግታል፡፡ ነገር ግን ራስን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑትን በተለያየ መልኩ በስዕል በማስቀመጥ፤ ጦርነቱ በተካሔደበት ወቅት ጦር በመምራት በጀግንነታቸው የታወቁ ስለውለታቸው ምስላቸው ተቀርፆ እንዲጎበኝ አለመደረጉ እስከ አሁን ለምን ይህ ሆነ ያስብላል። በሌላ መልኩ ዛሬ ይህንን ማድረግ መቻሉ ብዙዎችን አስደስቷል፡፡

ከሰሞኑ በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ድሉን ላጎናፀፉን ጀግኖች ምስላቸው ተቀርፆ እና በስዕል መልክ ተሰቅሎ ማየታችን ብዙዎቻችንን አስደስቷናል፡፡ ስንል መነሻችን በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጥቁር ሕዝቦች መጎብኘት እንዲችል እና ታሪካችን ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ስለሚያግዝ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁንም ከጦር መሪነት ባሻገር በተለያየ መልኩ ለድሉ መገኘት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ጀግኖች ሊኖሩ ቢችሉም፤ በዋናነት መታወቅ ያለባቸው ለትውልድ ታሪካቸው ሊነገርላቸው የሚገቡትን በዚህ መልኩ ቀርፆ ማስቀመጡ በብዙዎች ድጋፍ ያስገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ከየአቅጣጫው የመጣውን ሕዝብ እየተዋጉ እያዋጉ ከፊት ሆነው የመሩ፤ ለሀገራቸው ራሳቸውን የሰጡ ብቻ ሳይሆኑ እህል ይዘው የተጓዙ፣ ፈጭተው አብኩተው እና ጋግረው ሠራዊቱን ሲመግቡ የነበሩትም ለዓይን በሚማርክ መልኩ በስዕሎች በሙዚየሙ ተጠቃልለው ተገልፀው መታየታቸው የበለጠ የተሟላ አድርጎታል፡፡

የዓድዋ ጀግና የነበሩት ከንጉሥ አፄ ምኒሊክ እና ከጀግናዋ እና ከብልኋ እቴጌ ጣይቱ ብጡል በተጨማሪ ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ፣ ንጉሥ ተክለኃይማኖት ተሰማ ጎሹ፣ ንጉሥ ሚካኤል አሊ ልበን፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮባ፣ ራስ ወሌ ብጡል ኃይለማርያም፣ ፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሁንዱል፣ ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አባተ ቧያለው፣ ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም፣ ፊት አውራሪ ገበያው ገቦን የመሳሰሉ በግምባር ቀደምትነት የሚነሱ 12 የጦር መሪዎች ከለኮሱት የድል ችቦ ጋር በመሐል የኢትዮጵያ እምብርት አዲስ አበባ በፒያሳ አካባቢ ስማቸው እና ምስላቸው ተቀርፆ መቀመጡ የሀገር ባለውለታ አባቶች ገድል ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ በኩል የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡

የጀግንነት ስማቸውን ጨምሮ አባ ጎራው፣ አባ ቃኘው፣ አባ ጠና ፤ አባ ሻንቆ፣ አባ መላ ፣ አባ ነጋ፣ አባ ግጠም እያሉ ክብር በተሞላው መልኩ ሙሉ ማስታወሻቸውን በማቆሙ ትውልዱ ታሪኩን የበለጠ ለማወቅ እንዲነሳሳ የሚግዝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በዓድዋ ከዘመቱት ኢትዮጵያውያን መካከል 45ሺህ አካባቢዎቹ ፈረሰኞች ሲሆኑ፤ እነርሱንም የሚወክል ቅርፅ በሙዚየሙ መቀመጡ በምን መልኩ ጦርነቱ ሲካሔድ እንደነበር የሚመላክቱ ናቸው፡፡ ይህ እና ሌሎችም የጦርነቱን ዓይነት የሚያመላክቱ ሌሎችም የአሸዋ ገበታን የመሳሰሉ ቅርፆች በሙዚየሙ መገኘታቸው ይህንን ታላቅ ዐሻራ ላስቀመጡ ምስጋና ይገባል እንድንል ያስገድደናል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You