ለዓድዋ ድል የሚመጥን ሰብዕና ይኑረን!

መላውን ዓለም ያስገረመው፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገውና ኢትዮጵያ የጭቁኖች የነፃነት ምልክትና መሰረት ሆና እንድትታይ ያስቻለው ታላቁና አንጸባራቂው የዓድዋ ድል፣ ኢትዮጵያን የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ያደረገ ብቻ ሳይሆን፤ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ብዙ እድገቶችንና መሻሻሎችን እንድታስመዘግብ የሚያስችሉ በርካታ ትሩፋቶች ያሉት ታሪካዊ ክስተት ነው።

የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ዓለም ጭቁኖች የነፃነት ተስፋን የፈነጠቀና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገ አስደናቂ ገድል ነው። የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች ምልክት መሆን የቻለ ወሳኝ ታሪካዊ ክዋኔም ነው። በአፍሪካ፣ በካሪቢያንና በእስያ ለተካሄዱ የነፃነት ትግሎች መጀመርና ስኬታማ መሆን የዓድዋ ድል የጎላ ሚና ነበረው።

የፓን አፍሪካዊነት ንቅናቄ (Pan-African­ism) የተጠናከረውም በዓድዋ ድል ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) መመስረት የዓድዋ ድል ውጤት ነው። የድርጅቱን ምስረታ፣ ዋና መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ላይ የመሆኑንና የአፍሪካ አገራትም በዚህ የመስማማታቸውን እውነት ከዓድዋ ድል ውጭ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፤ አይቻልምም።

በድሉ ማግሥት ታላላቅ የአውሮፓ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት መስርተዋል። ከድሉ በፊት ‹‹ኢትዮጵያውያን ኋላ ቀሮች ናቸው›› ብለው ያስቡ የነበሩ አካላት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት መስርተው የምጣኔ ሀብትና ወታደራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት አሳይተዋል። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ዋና ከተማ (አዲስ አበባ) የብዙ አውሮፓውያን መንግሥታት ኤምባሲዎች መቀመጫ እንድትሆን እድል ፈጥሯል። ድሉ ለምጣኔ ሀብታዊ እድገት (ለከተማ እድገት መነቃቃት፣ ለመሰረተ ልማቶች መገንባትና ለሥራ እድል መፈጠር) ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል። ኢትዮጵያ ‹‹የዓለም መንግሥታት ማኅበር›› (League of Nations)ን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መስራች አባል እንድትሆን ድሉ ከፍተኛ ሚና ነበረው። በአጠቃላይ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ አስችሏታል።

ከላይ የተጠቀሱትን የዓድዋ ድል ያስገኛቸውን በጎ ውጤቶችን (መልካም አጋጣሚዎች) ይዘን ‹‹ድሉ ያስገኛቸውን ትሩፋቶች በሚገባ መንዝረን ተጠቅመንባቸዋል? በድሉ የተገኙትን ውጤቶች በማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች የበለፀገችና ጠንካራ የሆነች ሀገርን ለመገንባትስ ተጠቅመንባቸዋል?›› ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ አናገኝም!

የዓድዋ ድል ትሩፋቶችን እያሰብን የኢትዮጵያን ያለፉት።ን ዓመታት (በተለይ ያለፉትን 50 ዓመታት) ጉዞ ስንቃኝ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንና የዓድዋ ድል ይተዋወቃሉ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ሀገሪቱ በድህነት፣ በግጭት፣ በዘረኝነትና በጦርነት ጎዳናዎች ላይ ደጋግማ መመላለሷ የዓድዋ ድል ያስገኘላትን በረከቶች መዘንጋቷንና አለመጠቀሟን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ በዓድዋና በሌሎች ስፍራዎች ለማመን የሚከብዱ ከባድ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ አገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም ‹‹ተተኪው ትውልድ›› (በተለይ ልኂቃኑ) ግን ያን ታሪክ በሚገባ በማወቅና በመመንዘር ለሀገር ግንባታ ሊጠቀምበት አልቻለም። ይህ መራራ እውነት እጅግ ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም።

ኢትዮጵያ በዘር፣ በሃይማኖትና በአመለካከት ሳይከፋፈሉ ዓድዋ ላይ ጠላትን ድል ያደረጉ ልጆች እናት መሆኗን ማሰብና፣ ከዓድዋ ድል በኋላ ባፈራቻቸው ‹‹ልጆቿ›› ምክንያት በአስከፊ የዘር ፖለቲካ ስትታመስ መመልከት እጅግ አሳዛኝና አስገራሚ ተቃርኖ ነው። ይህ ውድቀት ደግሞ ‹‹በእውነቱ ይህ የታላቁን የዓድዋ በረከቶች የዘነጋ ትውልድ ድሉን የማክበር/የመዘከር ሞራል አለው?›› የሚል ጥያቄን ይጋብዛል።

የዓድዋ ድል ያስገኘልንን በረከቶች መንዝረን ተጠቅመንባቸው ቢሆን ኖሮ … ዛሬ በዓባይ ወንዛችን ላይ በምንገነባው ግድባችን ምክንያት ‹‹ጥቅሜ ተነካ›› የሚሉ አካላትና የእነርሱ ወዳጆች ጫና ሊያደርጉብን እንዲሁም ታሪካዊና ሕጋዊ መብታችንን በአደባባይ ሊነጥቁን አይሞክሩም ነበር። [በነገራችን ላይ የዓድዋ ድል በዓባይ ወንዛችን ላይ እየገነባነው እንዳለው ዓይነት ግዙፍ የልማት ስራዎችን እንድንሰራ ስንቅ የሚሆን ድል ነበር] … የዓድዋን በረከቶች ብናውቃቸውና ብንጠቀምባቸው ኖሮ በብሄርና በፖለቲካ የሚታመስ፣ ሚሊዮኖች በችጋር የሚሰቃዩባትና የሚፈናቀሉባት …. ሀገር አትኖረንም ነበር!

የዓድዋ ድል ሀገርን ከጠላት ወረራ ከመጠበቅ ያለፈ ዓላማና ትርጉም ነበረው። በእርግጥ ድሉ ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ የማቆየት አኩሪ ታሪክ እንደሆነ ባይካድም ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከወራሪው የኢጣሊያ ጦር ጋር የተፋለሙት ኢትዮጵያን ከወቅቱ ወራሪ ኃይል ለመጠበቅ (ዳር ድንበሯን ለማስከበር) ብቻ ሳይሆን ወራሪው ኃይል ውሎ አድሮ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት በመገንዘብ ያን ጥፋት በእንጭጩ ለመቅጨት ጭምር እንደሆነ መዘንጋት አይገባም።

ድሉ ያስገኘውን መልካም ፍሬ መንዝሮ ማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች በአጠቃላይ ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የድሉ ዘላቂ ዓላማና ትርፍ ሊሆን ይገባ ነበር። የዓድዋ ድል የትብብርና የአንድነት ውጤት መሆኑን ተገንዝበን ኢትዮጵያን በትብብርና በአንድነት ካለችበት ዘርፈ ብዙ መከራና ችግር ማላቀቅ ያልቻልነው ለምን ይሆን?

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ባስገኙት ድል መኩራትና ድሉን መዘከር ጥሩ ቢሆንም የድሉን ትሩፋቶች ሳይጠቀሙ፣ ድሀ የሆነች ሀገር ይዞ በድሉ ‹‹መኩራት›› ብቻ ግን ግራ የሚያጋባ ይመስለኛል። በዓድዋ ለመኩራት ዓድዋን ማወቅና መጠቀም ይገባል! ለመሆኑ ዓድዋን ማባከናችን የሚቆጨን መቼ ይሆን?

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንትና የዓድዋ ድል ለጥቁሮች፣ በተለይም ለአፍሪካውያን፣ የነፃነት ትግል ስለነበረው ፋይዳ ተናግረው የማይጠግቡት ታቦ ምቤኪ፣ ‹‹የዓድዋ ድል ለትናንት ድሎቻችን ብቻም ሳይሆን ልናሳካቸው ላሰብናቸው አፍሪካዊ እቅዶቻችን ስኬት ታላቅ ስንቅ የሚሆነን አኩሪ ድል ነው›› በማለት በተደጋጋሚ የሚናገሩት የድሉ መታሰቢያ መከበር ከድሉ መንፈስና ዓላማ ለመነጩት አፍሪካዊ እቅዶች ስኬት ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው በማመን ነው።

የዓድዋ ድል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ጠንካራና ኃያል የሆነች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ድል መሆኑን መረዳትና መቀበል ያስፈልጋል። የዓድዋን ድል ያስገኘልንን በረከቶች አውቆ እየመነዘሩ መጠቀምና ማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀችና ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር (መገንባት) የድሉን ትርጉም የማወቅ ንቃት ነው። ይህን በመተግበር ኢትዮጵያን ለታላቁ የዓድዋ ድል የምትመጥን ታላቅ ሀገር ማድረግ ይገባል!

ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You