የዓድዋ ድል ሥጋ ለብሶ የታየበት የዘመኑ ትውልድ ስኬት

ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያን ኩራት በመሆን ዘመናትን የተሻገረው የዓድዋ ድል ዛሬም ሕያው ነው፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ ለበርካታ ዓመታት ሲዘከር መኖሩም ከታሪኩ ግዝፈትና ጥልቀት የተነሳ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በደም የተጻፈው ይህ የ128 ዓመት ታሪክ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ቢኖረውም ሁነቱን የሚዘክር መታሰቢያ ሳይኖረው ክፍለ ዘመን ተሻግሯል፡፡ ዛሬ ግን ጥበቃው አብቅቶ ግዙፉን የዓድዋ ድል የሚያህል መታሰቢያ ሙዚየም በመሐል ፒያሳ ተገንብቷል፡፡

ሙዚየም የተገነባበት ቦታ ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸው ሲሉ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ወደ ጦርነት ለመትመም በአንድነት በተሰባሰቡበት መሐል አዲስ አበባ ፒያሳ ላይ መሆኑም ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡ የ128 ዓመት ታሪክ ሥጋ ለብሶ መታየት የቻለበት ይህ ሙዚየም የታሪኩን ግዝፈት በልኩ ማሳየት የቻለ የዘመኑ ትውልድ ሌላኛው ዓድዋ ነው ቢባል ከዕውነት የራቀ አይሆንም። ዓድዋ ሁሌም አዲስና ረቂቅ እንደመሆኑ አሁን ያለው ትውልድ ‹‹የእኔ ዘመን ስኬት ነው›› በሚል ሊጠብቀው፤ ሊንከባከበውና ለመጪው ትውልድ ሊያሻግረው እንደሚገባ ይታመናል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በየትኛውም ዘመን ያልታየ የዘመኑ ስኬት ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የዓድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን ድል እንደመሆኑ መታሰቢያ ሙዚየሙም እንዲሁ የመላው ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፎ ለጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የድል ታሪካቸውን የሚዘክሩበትና ለትውልድ የሚያስተላልፉበት ብሎም ለዓለም የሚያስተዋውቁበት የጋራ ቤታቸው ነው፡፡

የዓድዋ ድል እጅግ ግዙፍና ረቂቅ እንደመሆኑ የታሪኩን ግዝፈት ከፍ ማድረግ የሚችል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባቱ የዘመኑ ድል ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የዓድዋ ድል ግዙፍነት እንዲሁም ረቂቅ ሚስጥር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ደምቆ የተጻፈ ቢሆንም እስከዛሬ ድሉን ማጣጣምና ዕውነታውን ፍንትው አድርጎ ማሳየት የሚችል ሥፍራ አልነበረውም። ይሁንና አሁን ላይ ይህ ታላቅ ድል ገዝፎ መታየት የሚችልበት መታሰቢያ ሙዚየም መገንባት መቻሉ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ሙዚየሙ ከዓድዋ ድል ታሪክ ባለፈም የኢትዮጵያን የታሪክ ከፍታ ማሳየት የሚችልና በወቅቱ የተከፈለውን መስዋዕትነት ፍንትው አድርገው የሚገልጡ የተለያዩ ቅርሶች በውስጡ የያዘ በመሆኑ ትውልዱ ሥጋ የለበሰውን ይህን ታሪክ የማወቅ፣ የመረዳትና ለሌሎች የማስተላለፍ ወርቃማ ዕድል ገጥሞታል፡፡

በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ እንደ ጀግኖች አባቶቹ ሁሉ የጋራ አንድነቱን በማጠናከር ሠላሙን ማጽናት ይጠበቅበታል የሚሉት የታሪክ ምሑራን በተለይም አሁን ያለው ትውልድ ከ128 ዓመታት በኋላ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የነፃነት፣ የሉዓላዊነትና የአርበኝነትን ልክ ማሳያ መሆኑን በመረዳት ለመጪው ትውልድ የማሻገርና የማስተማር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

የሁሉም የጥቁር ሕዝቦች የትግል መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው የዓድዋ ድል ታላቅ ድል መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው እንዳሉት የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የዓለም ሕዝብ ኩራቴ፣ ተምሳሌቴ፣ ፋናዬ ነው የሚለው ትልቅ ድል ነው፡፡ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ግን እስካሁን ድረስ ይህን ታላቅ ድል የሚመጥን መታሰቢያ ማቆም አልቻልንም ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህን ቁጭት የሚቀይር ፕሮጀክት መገንባቱ እጅግ የሚያኮራ ነው›› ይላሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በወቅቱ የነበረውን ሁነት ቁልጭ አድርጎ ማሳየት የሚችል ነው፡፡ በዓድዋ ዘመቻው በጦርነቱ ወቅት ተሳታፊ የነበሩ ጀግኖቻችን፣ ሴቶቻችን፣ ገበሬዎቻችን ይዘው የነበሩትን ቅርሶች በሙሉ አሰባስቦ የያዘ ታላቅ ሙዚየም ነው። ከጦር መሣሪያ ጀምሮ እስከ የዕለት ተዕለት ምግብ መመገቢያ ያሉትን የዓድዋ ዘማች አርበኞች መገልገያ ቁሳቁሶች አሟልቶ ይዟል፡፡ እነዚህን ቁሳቁሶችን በአንድ ቦታ አሰባስቦ ማሳየት ማለት ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ትልቅ ዕውቀት ማስገንዘብ ማለት ነው፡፡

ሌላው ዓድዋን በልኩ ለማስረዳትና ለመግለጽ ሥነ- ጥበብን በመጠቀም ማስረዳት አለብን የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ሥነ-ጥበብ ላይ የተለያዩ ቅርጾች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ እንዲሁ የተካተቱት በርካታ ቅርጾች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ጦርነቱ ምን ይመስል እንደነበር የሚያሳዩ በርካታ ቁሳቁሶች በሙዚየሙ ይገኛል፡፡ ጦርነቱም በምናብ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በወቅቱ ከነበሩ ስዕሎች፣ ስኬቾችና ከየተለያዩ ቁሳቁሶች የተነሳና ያካተተ እንደሆነም አስረድተዋል። ዓድዋ ከቅርሶቹ ባሻገር ለትውልድና ለቀሪው ዓለም ማሳየት ይቻላል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ለዚህ ሥነ ጥበብ አንዱ መንገድ ነው ይላሉ። በዓድዋ መታሰቢያ ውስጥ የተገነቡ ቅርፆች (የጀግኖች መሪዎችና የጦር ጀነራሎች ሐውልቶች) መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የሠላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና በታሪክና ባሕል ላይ ጥናትና ምርምር ደረጉት ዶክተር ኬይረዲን ተዘራ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የታሪክ ባዶነት እንዳይሰማን ያደረገ፤ ሁሉ ነገራችን ገዝፎና የልኬታችን ልክ ሆኖ መገንባቱን አንስተዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከዓድዋ አስቀድሞም በተለያዩ ግንባሮች ላይ ሀገራቸውን ነፃ ለማውጣት የታገሉና ድል ያደረጉ ቢሆንም ትግላቸው በአንድ አካባቢ ወይም ነጠላ በሚባለው መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን መላው ኢትዮጵያውያንን በአንድ አሰባስቦ ድል ማድረግ የተቻለው በዓድዋ በመሆኑ የዓድዋ ድል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድል ነው ይላሉ፡፡

‹‹የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሰባሰበና መነበብ የሚችል መታሰቢያ ሙዚየም መሆኑን ሲያስረዱ፤ ኢትዮጵያን በአግባቡ ለተረዳና በቀና ልብ ለሚመለከተው ማንም ሰው የለውም የሚልበትን ዕድል በሙሉ የዘጋና የሚነበብ ነው›› ይላሉ። እሳቸው እንደሚሉት በሀገሪቱ በርካታ ፕሮጀክቶች የተገነቡ ቢሆንም የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ግን ቀደም ሲል መገንባት የነበረበት ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ሙዚየሙ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳስብና ሊያሰባስብ የሚችል መሆኑን ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ይላሉ፡፡

በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ ያልተካተተ ኢትዮጵያዊ የለም የሚሉት ዶክተር ኬይረዲን ከብሔር፣ ከፆታና ከጀግኖች የቀረ አለመኖሩን አንስተው ሙዚየሙ ኢትዮጵያን ለማቆም የተከፈለ መስዋዕትነትን ለማሰብ የቆመ እንደመሆኑ ከመታሰቢያነቱ ባሻገር ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርግ፣ ሊያሰባስበንና አናሳ የሆኑ ትርክቶች ቦታ እንዳይኖራቸው በማድረግ ኢትዮጵያውያን ገዝፈን እንድንታይ ያደረገ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጿል፡፡

ዶክተር አየነው ማሞ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ የዓድዋ ድል መላው ኢትዮጵያዊ ከጫፍ እስከ ጫፍ መስዋዕትነት የከፈለበትና ለነፃነቱ የታገለበት ታላቅ ድል ነው፡፡ በመሆኑም ለጥቁር ሕዝቦች ጭምር መመኪያና ኩራት ሆኗል ይላሉ፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ድሉ አቻ የማይገኝለት የአፍሪካውያን ድል ነው፡፡ ከዛም አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል በመሆኑ ከፍ ያለና ትልቅ ምስጢር ያለው ነው።

‹‹ነፃነቱን አጥቶና ለጠላት ተገዢ ሆኖ መኖር ለኢትዮጵያውያን ጀግኖች የማይዋጥ የጉሮሮ አጥንት ነበር›› የሚሉት ዶክተር አየነው፤ የድሉ ባለቤት መሆን የቻሉት ኢትዮጵያውያን በወቅቱ አንድነታቸውን ማጠናከር በመቻላቸው መሆኑን ያስረዳሉ፤ በዓድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን በሠለጠነ ወታደርና በዘመናዊ መሣሪያ የተቃጣባቸውን ወረራ በአልበገር ባይነት በሀገር ፍቅር ስሜት፣ በጋራ በመቆም የድል ባለቤት መሆን ችለዋል። አሁንም ያለው ትውልድ ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ቆሞ የጋራ ታሪኩን ማጣጣምና ለመጪው ትውልድ ብሎም ለዓለም ማስተዋወቅ አለበት፡፡

ለዓድዋ ድል ስኬት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ያለምንም ልዩነት በአንድነት ሆነው የሰጡት ፈጣን ምላሽ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አየነው፤ ይህም እጅግ የሚያስገርም ድንቅ ዕውነታ እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡ ‹‹ሕዝቡ በተለይም የንጉሠ ነገሥቱን የክተት አዋጅ ተቀብሎ በፍጹም ቆራጥነት፣ በልበሙሉነትና በድፍረት ጦርነቱን መቀላቀሉ ለድል አብቅቶታል፡፡ አንድነት ትልቅ ጉልበት በመሆኑ የጋራ ጠላትን በጋራ ለመመከት አስችሎታል›› በማለት አሁን ያለው ትውልድም ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች አንድ መሆን እንዳለበትና ዳግማዊ ዓድዋን መፍጠር እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡

የዓድዋ ድል አከባበርን አስመልክቶም እሳቸው እንደሚሉት፤ ዓድዋ ግዙፍ እንደመሆኑ የገዘፈ አከባበር፣ የገዘፈ መታሰቢያና ማስታወሻ ያስፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም ይላሉ፤ ምክንያቱም የዓድዋ ድል ሩቅ መንገድ የመጓዝና ብዙ ትውልድን የማስተማር አቅም ያለው ነው፡፡ ስለዚህ በታላቅ ክብርና ድምቀት መከበር ያለበት በዓል ነው፡፡ ለዚህም ሙዚየሙ አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ሲሆን፤ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያ ብቻ መከበር የለበትም ባይ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ድሉ ለአፍሪካውያን ነፃ መውጣት አርዓያ እንደመሆኑ የዓድዋ ድል በዓል በመላው አፍሪካ መከበር ያለበት የድል በዓል ነው በማለት ሲያስረዱ፤

የዓድዋ ድል ሲከበር ለሀገር ፍቅር ተዋድቀው ለዚህ ታልቅ ድል ያበቁንን አባቶቻችንን ከመዘከር ጎን ለጎን የድሉ ተጠቃሚ ለሆነው ለዘመኑ ትውልድ ታሪኩን የጋራ በማድረግ ማስተላለፍ ተገቢ እንደሆነ በመጥቀስ ጭምር ነው፡፡ በተለይም የዓድዋ ድል ለወጣቱ ትውልድ ያለውን አንድምታ በማሳየት ትውልዱ የመላው ኢትዮጵያዊ ድል መሆኑን አምኖ በመቀበል ሊኮራበትና ሊሠራበት እንደሚገባ አንስተው፤ የዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያውያን አንድነት ጎልቶ የታየበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የነፃነትና የአንድነትን ትርጉም ማወቅ፣ መረዳትና በተግባር ማዋል ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ጦርነቱ የኢትዮጵያን ነፃነት ከማስከበር ባሻገር ብሔራዊ ስሜት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብትና ስር እንዲሰድ አድርጓል ይላሉ፡፡

‹‹ከዚህ እውነታ የምንማረው የትኛውንም አይነት የሀሳብ ልዩነት ቢኖር በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አመለካከትና ግንዛቤ መያዝ አስፈላጊና አዋጭ ነው›› የሚሉት ዶክተር አየነው፤ በዚህ ረገድ የዓድዋ ድል አሁን ላለው ትውልድ ነፃነቱን በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚኖረው አበርክቶ ጉልህ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ለዚህም ትውልዱ በራስ የመተማመን ባሕል ማዳበርና ታሪክን ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ታሪክን ለማወቅ ደግሞ የታሪክ ትምህርት መማር አንዱ መንገድ ነው። ታሪክን ከመማርና ከመዘከር ባለፈም ትውልዱ እንደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሁሉ የገዘፈ ታሪክ በዘመኑ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

ሙዚየሙን ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲሁም አፍሪካውያን ማየት አለባቸው ያሉት ዶክተር አየነው፤ ሙዚየሙ ግዙፉን የዓድዋ ድል ታሪክ የሚያሳይ በመሆኑ ኢትዮጵያውያኑም ሆኑ የአፍሪካ መሪዎች ዳግማዊ ዓድዋ፤ የክፍለ ዘመኑ ትልቅ ድል አድርገው መውሰድ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በተለይም ሙዚየሙ የያዘውን ዕውነታ ለትውልድ የማስተማር፣ የመጠበቅ፣ የማስተላለፍና የማስተዋወቅ ኃላፊነት ጭምር ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል። ምክንያቱም ‹‹ነጮች በጥቁሮች አይሸነፉም›› የሚለውን ለዘመናት የቆየ ትርክት መቀየር የቻለና የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ የያዘ ትልቅ ሙዚየም በመሆኑ ነው፡፡

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም የሚኮሩበት፣ ብዙ ቁም ነገር የሚማሩበትና ሁልጊዜም ቢሆን ትኩስ የድል ስሜትን የሚፈጥር ታሪክ እንደመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ከዚህ ታሪክ ብዙ መማርና ታሪኩን ማወቅ መረዳት እንደሚገባው ያነሱት ዶክተር አየነው፤ ድሉ በታሪኩ ግዝፈት ልክ መከበርና መዘከር እንዳለበትም ያነሳሉ፡፡ በቀጣይም በደመቀ መልኩ መከበር እንዲችል ትውልዱ በሁሉም ዘርፍ ዘመኑ የሚጠይቀውን ሥራ ጠንክሮ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የቀደሙ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የፈጸሙትን አኩሪ ታሪክ ትውልዱ በልኩና በክበሩ በመዘከር፤ በማስታወስ፤ ከሚከፋፍል ጉዳይ ወጥቶ በጋራ ልማትና የአገር ዕድገት ላይ ትኩረት በማድረግ፤ መተባበርን እና አንድነትን ከዓድዋ ድል መማር ከሁሉም ይጠበቃል በማለት አበቃን!

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You