ዓድዋ – የነፃነትና የፍትሕ ትግሎች መሰረት

ታላቁ የዓድዋ ድል መላውን ዓለም ያስገረመ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገና ኢትዮጵያና ድሏ የጭቁኖች የነፃነት ምልክትና መሰረት ሆነው እንዲታዩ ያስቻለ ደማቅ ታሪክ ነው፡፡ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር በወራሪው የኢጣሊያ መንግሥት ጦር ላይ ያስመዘገበው ድል በዓይነቱ የተለየ ስለነበር መላውን ዓለም ያስገረመ፣ ያስደነቀና ያስደነገጠ ክስተት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።ይህ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ዓለም ጭቁኖች የነፃነት ተስፋን የፈነጠቀና ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደረገ፤ በአንፃሩ ለወራሪው ጦር ደግሞ ሁለገብ ውድመትንና ውርደትን ያስከተለ ድል ነው፡፡

የዓድዋ ድል የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች ምልክት መሆን የቻለ ወሳኝ ታሪካዊ ክዋኔ ነው። ጦርነቱና ድሉ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው ዓለምን ያስደነቀ ገድል መፈፀማቸውን ለመላው ዓለም ያሳዩበት በመሆኑ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው በጋራ ሆነው መታገል እንደሚገባቸው ትምህርት የሰጠ ታላቅ ክስተት ነው፡፡ የድሉ ትሩፋቶች ለጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ትግል ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆነዋል፤ የነፃነት ትግሎቹም ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ የስኬት መንገድን ጠርገዋል፡፡

ድሉ በአፍሪካ፣ በካሪቢያንና በእስያ ለተካሄዱ የነፃነት ትግሎች መጀመርና ስኬታማ መሆን የጎላ ሚና ነበረው፡፡ የዓድዋ ድል በመላው ዓለም የሚገኙ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳ፣ ትግላቸውን ያጠነከረና ለስኬት እንዲበቁ ያደረገ የአሸናፊነት ምንጭ ስለመሆኑ የበርካታ አገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ በጥናቶቻቸውም አረጋግጠዋል፡፡ ከአሕመድ ሴኮ ቱሬ እስከ ኔልሰን ማንዴላ፣ ከክዋሜ ንክሩማህ እስከ ታቦ ምቤኪ፣ ከዊልያም ኤድዋርድ ዱ ቦይስ እስከ ማርክስ ጋርቬይ፣ ከስቬን ሩቤንሰን እስከ ማሞ ሙጬ፣ ከሬይሞንድ ጆናስ እስከ አየለ በከሪ፣ ከቨርጂኒያ ሊ ጃኮብስ እስከ ሮበርት ኔስታ ማርሌይ (ቦብ) … በርካታ የአገራት መሪዎች፣ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች ስለዓድዋ ድል አንፀባራቂነትና በዓድዋ ስለደመቁት ኢትዮጵያውያን ጀግንነት ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፤ አዚመዋል!

ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ አገራቸውና ቤታቸው ቆጥረዋል፡፡ የአፍሪካ የነፃነት መሪዎች (ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮበርት ሙጋቤ እና ሌሎችም) የነፃነት ትግላቸውን ባደረጉባቸው ጊዜያትም ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው የተለያዩ ድጋፎችን አግኝተዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ እንደነፃነት ምልክት መቆጠሯ በወሬና በንድፈ ሃሳብ የተገለፀ ብቻ ሳይሆን በተግባር የታዬና የተረጋገጠ መሆኑን ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ የዓድዋ ድል ነው፡፡ የአብዛኞቹ የዓለም የጭቁኖች የነፃነት ትግሎች መነሻና የስኬት ምንጭ የዓድዋ ድል እንደሆነ አይካድም፡፡

የዓድዋ ድል በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ለተደረጉ የነፃነት ትግሎች መነቃቂያ ከመሆን ባሻገር አገራት ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ በጭቁኖች ለተቋቋሙ ተቋማት መመስረትም ሚናው የጎላ ነው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization of African Unity – OAU) የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት (African Union – AU) ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (Organization of African Unity) መመስረት የዓድዋ ድል ውጤት ነው፡፡ የድርጅቱን ምስረታ፣ ዋና መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ላይ የመሆኑንና የአፍሪካ አገራትም በዚህ የመስማማታቸውን ነገር ከዓድዋ ድል ውጭ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፤ አይቻልምም፡፡

ለድርጅቱ መመስረት ምክንያት የሆነው የፓን አፍሪካ ንቅናቄ (Pan-Africanism) የተጠናከረውም በዓድዋ ድል ነው፡፡ ምንም እንኳ የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከዓድዋ ጦርነት ቀድሞ የተጀመረ ቢሆንም በዓድዋ የተገኘው ድል ግን የፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴን ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጎታል፡ ፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዓድዋ ድል ውጤት መሆኑ የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የነፃነት ትግሎችና ከትግሎቹ መጠናቀቅ በኋላ የተመሰረቱ ተቋማት የዓድዋ ድል ደማቅ አሻራ እንዳረፈባቸው ጠቋሚ ምስክር ነው፡፡

የዓድዋ ድል የትብብርንና የአንድነትን ውጤታማነት እንዲሁም ለነፃነት መስዋዕትነት መክፈል ታላቅ ክብር እንደሆነ ያሳየ፤ የነጮች የበላይነት ማክተም እንደሚችልም የጠቆመና መንገድ የከፈተ አንፀባራቂ ክስተትም ነው፡፡ ይህን ክብርና መንገድ በጀግንነትና በመስዋዕትነት በታጀበ ተግባር ያሳዩትና የመሩት ኢትዮጵያውያን ደግሞ የጭቁኖች መመኪያ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድን ለመታገል በተደረገው ጥረት ኢትዮጵያ እንደነፃነትና ክብር ምልክት ተደርጋ ትወከል ነበር፡፡ ከ1896 እስከ 1897 ዓ.ም ድረስ ሩስያና ጃፓን ያደረጉትና በጃፓን አሸናፊነት የተጠናቀቀው ጦርነት (Russo-Japanese War) ከዓድዋ ድል ጋር ተያያዥነት እንዳለውም በታሪክ ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ዓድዋ ለመላው ዓለም ጭቁኖች የነፃነት ምልክትና የሞራል ምንጭ ሆኗቸዋል፡፡ በተለይ የአፍሪካ አገራት ነፃነታቸውን እንዲጎናጸፉ ትልቅ መሰረት የሆነ ድል ነው፡፡ የአፍሪካ አገራት ነፃ ከወጡ በኋላም የሰንደቅ ዓላማዎቻቸውን ቀለማት የወሰዱት ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት (አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ) ነው፡፡

የዓድዋ ድል በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው ለነበሩ የአፍሪካ ሕዝቦች የነፃነት ትግል ትልቅ ፋይዳ እንደነበረው የነፃነት ትግሎቹ መሪዎች የነበሩና በኋላም አገሮቻቸውን በመሪነት ያገለገሉ አፍሪካውያን የትግል መሪዎች መስክረዋል፡፡ የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚደንት ክዋሜ ንኩርማህ ‹‹ኢትዮጵያ ነፃ ከሆነች ሁላችንም አፍሪካውያን አንድ ቀን ነፃ እንደምንሆን አምናለሁ›› በማለት ነበር የዓድዋ ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ትግል መጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረውና በአትዮጵያም ያላቸውን ሙሉ ተስፋ የተናገሩት፡፡

የመጀመሪያው የጊኒ ፕሬዚደንት አሕመድ ሴኮ ቱሬ ደግሞ ‹‹ … ኢትዮጵያውያን ታላቅ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ጀግና አፍሪካውያን ናቸው፡፡ በጀግንነት ተዋግተው ነፃነታቸውን አስከብረዋል፤ ለመላው አፍሪካውያንም የነፃነትን መንገድ አሳይተዋል›› በማለት ለኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ለዓድዋ ድል አበርክቶዎች እውቅና ሰጥተዋል፡፡

የፀረ-አፓርታይድ መሪውና የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪ በነበሩበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና እንደወሰዱ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ምንጊዜም በውስጤ ልዩ ቦታ አላት፡፡ ወደ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ከመሄድ ይልቅ ወደ ኢትዮጵያ መጓዝ የበለጠ ልዩ ስሜት ይሰጠኛል፤ አፍሪካዊ ወዳደረገኝ የማንነቴ ምንጭ እንደሄድኩ ይሰማኛል›› በማለት የተናገሩላት የዓድዋ ድል ባለቤቷ ኢትዮጵያ ለትግላቸው ያደረገችላቸው ድጋፍ ትርጉሙ ብዙ ነው። ምስክርነታቸውም ከዓድዋ ድል ታሪክ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡

የማንዴላ ተተኪ ታቦ ምቤኪም የዓድዋ ድል ለጥቁሮች፣ በተለይም ለአፍሪካውያን፣ የነፃነት ትግል ስለነበረው ፋይዳ ተናግረው አይጠግቡም፡፡ ‹‹የዓድዋ ድል ለትናንት ድሎቻችን ብቻም ሳይሆን ልናሳካቸው ላሰብናቸው አፍሪካዊ እቅዶቻችን ስኬት ታላቅ ስንቅ የሚሆነን አኩሪ ድል ነው›› በማለት በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

በዓድዋ ጦርነት ላይ ብዙ ጥናቶችን ያደረጉትና የምርምር ጽሑፎችን ያሳተሙት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሪ፣ የዓድዋ ድል፣ ነፃነትን አጥብቆ የሚሻ አዲስ የአፍሪካዊነት ስሜት እንዲጎለብት ማድረግ የቻለ ታሪካዊ ድል እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ እሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው አንፀባራቂ ድል የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች ምልክት መሆን የቻለ ወሳኝ ታሪካዊ ክስተት ነው። ጦርነቱና ድሉ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው ዓለምን ያስደነቀ ገድል መፈፀማቸውን ለመላው ዓለም ያሳዩበት በመሆኑ ጭቁን ሕዝቦች ለነፃነታቸው በጋራ ሆነው መታገል እንደሚገባቸው ትምህርት ሰጥቷል፡፡

ፕሮፌሰር አየለ ‹‹The Victory of Adwa ፡ An Exemplary Triumph For The Rest of Af­rica›› በሚለው ጽሑፋቸው የደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴን (ዶ/ር) ሃሳብ ይጠቅሳሉ፡፡ አምባሳደሩ ስለጦርነቱና ድሉ በገለፁበት ማብራሪያቸው፣ ‹‹የዓድዋ ድል የአውሮፓን ሰማዮች የሀዘንና የድንጋጤ ደመና ያለበሰ፤ በአንፃሩ በቅኝ ገዢዎች እየተበዘበዙ ለነበሩ ጭቁን የአፍሪካና የእስያ ሕዝቦች ደግሞ የነፃነት ተስፋን የፈነጠቀና የጀግንነት ወኔን ያላበሰ ደማቅ ድል ነው›› በማለት ይገልፁታል፡፡

ከዚህ የደጃዝማች ዘውዴ ገለፃ መረዳት የሚቻለው የዓድዋ ድል ንዝረቱ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው ዓለም እንደተሰማ እንዲሁም የድሉ ትሩፋቶች ለጭቁን ሕዝቦች የነፃነት ትግል ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሆኑና ትግሎቹም ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ የስኬት መንገድን የጠረጉ ታሪካዊ አጋጣሚዎች እንደነበሩ ነው፡፡

የታሪክ መምህርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገላውዴዎስ አርዓያ፣ በ1988 ዓ.ም፣ በዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ፣ ‹‹The Ethiopian Victory at Adwa ፡ Meanings For Africans and People of African Descent in The Diaspora›› በሚል ርዕስ በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ባቀረቡት ገለፃ፣ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የድሉን ዜና ለመላው ዓለም ማስተጋባታቸውን ጠቁመው፣ የድሉ ብስራት በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአሜሪካና በካሪቢያን አካባቢዎች ከፍተኛ መነቃቃትን እንደፈጠረ አስረድተዋል፡፡ ቅኝ ገዢ ኃይሎችም የዓድዋ ድል ታላቅ ድንጋጤና ፍርሃት እንዳሳደረባቸውም ፕሮፌሰር ገላውዴዎስ ተናግረዋል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ እንዳልሆነ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ገላውዴዎስ፣ ድሉ በመላው ዓለም በሚገኙ የአፍሪካ ዝርያ ባላቸው ጥቁር ሕዝቦች መካከል የወንድማማችነትና የትብብር መንፈስ እንዲፈጠረም አብራርተዋል፡፡ ‹‹የዓድዋ ድል የአፍሪካ የነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካዊ ስልጣኔ ኅዳሴ ምልክት ጭምር ነው›› ብለዋል፡፡

ስመጥሩ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ዊሊያም ኤድዋርድ ዱ ቦይስ ‹‹በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የወደቁ ሕዝቦች ከዓድዋ ድል በመማር የነፃነት ትግሎቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። በርትተው ለመታገል ቁርጠኛ በመሆን በነፃነት መኖርን ለድርድር እንደማያቀርቡት ለመላው ዓለም ማሳወቅ አለባቸው፤ ከኢትዮጵያ መማር ያለባቸውም ይህን እውነት ነው›› በማለት የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ትግል መነሻና ስንቅ እንደሆነ ለጭቁኖች መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡

የ‹‹Roots of Rastafari›› መጽሐፍ ጸሐፊዋ ቨርጂኒያ ሊ ጃኮብስ፣ የዓድዋን ድል ‹‹ኢትዮጵያ ዘረኛና ከፋፋይ የሆነውን የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ተግባርን በመቃወምና ድል በማድረግ የማይነቃነቅ ግዙፍ የክብር ማማ እንድትገነባና በድል የታጀበ ተጋድሎዋ ለሌሎች አፍሪካውያን የነፃነት ትግል አርዓያ እንድትሆን ያስቻላት ተምሳሌታዊ ድል›› በማለት ገልጸውታል፡፡

ሮበርት ኔስታ ማርሌይ (ቦብ ማርሌይ)ን ጨምሮ ስመጥር የኪነ-ጥበብ ሰዎች በልብሶቻቸውና በሙዚቃ መሳሪያዎቻቸው ላይ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ቀለማትን መጠቀማቸውና ከ30 በላይ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን አገራት ለሰንደቅ ዓላማዎቻቸው እነዚህኑ ቀለማት መምረጣቸው የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ኢትዮጵያና በዓድዋ ያስመዘገበችው ደማቅ ድሏ የጭቁኖች መመኪያ በመሆናቸው ነው፡፡

ጥቁሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የዓድዋ ድል ትዝታና ስሜት ነበር፡፡ ጭቁኖች ኢትዮጵያን የነፃነት ምልክትና የጥቁሮች ሁለተኛ ቤት አድርገው ነው የሚመለከቷት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት›› ብለው ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት እንቅስቃሴ ሲያደርጉም ነበር፡፡ በተለይ ጃማይካዊው የፖለቲካ አክቲቪስትና የመብት ተሟጋች ማርክስ ጋርቬይ በንግግሮቹና በጽሑፎቹ ላይ ‹‹በባርነት ተይዛችሁ በዘር አድልኦ በሽታ በተጠናወተው ኅብረተሰብ ውስጥ የምትኖሩ ጥቁር አፍሪካውያን በሙሉ ወደ አገራችሁ ወደ አፍሪካ፣ የነፃነት አገር ወደ ሆነችው ሀገራችሁ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ፊታችሁን ወደ ኢትዮጵያ መልሱ፤ ወደ ጥንት ርስታችሁ ወደ አፍሪካ ተመለሱ፤ ዘውዱን የደፋውን ጥቁር ንጉሥ ተመልከቱ፤ እርሱ አዳኛችን ነው›› እያለ ደጋግሞ መጥቀሱ ኢትዮጵያ የጭቁኖች ተስፋና መመኪያ ተደርጋ መቆጠሯን የሚጠቁም ነው።

በአጠቃላይ የዓድዋ ድል ለጭቁን ሕዝቦች፣ በተለይም ለአፍሪካውያን፣ የነፃነት እንቅስቃሴዎች ሂደትና ስኬት ደማቅ አበርክቶ እንደነበረው ከአገራት መሪዎች፣ ከምሁራንና ከታዋቂ ሰዎች የተሰጡ ምስክርነቶች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ስለዓድዋ ድል አስደማሚነትና ዘመን አይሽሬ አበርክቶዎች የተሰጡ ምስክርነቶች ኢትዮጵያ በዓለም የነፃነት ትግልና የጀግንነት ታሪክ የማይነቀነቅ ታላቅ የከፍታ ስፍራ እንዳላት የሚያረጋግጡ ዘመን ተሻጋሪ ማስረጃዎች ናቸው፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You