ዓድዋ! በኢትዮጵያ ድል የደመቀ የአፍሪካ ኩራት

‹‹ያገሬ ሰው ከአሁን በፊት የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ፣ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ እንደሁ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ማርያምን! አልተውህም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው አስከጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ››

ይህ ታላቅ የክተት አዋጅ ከኢትዮጵያው ንጉሽ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አንደበት በተሰማ ጊዜ መላው ኢትዮጵያዊ ከያለበት ተመመ፡፡ በወቅቱ ማቄን ጨርቄን፣ ቤቴን ፣ ትዳሬን፣ ያለ አልነበረም፡፡ ጥሪው የንጉሥ፣ ነገሩ የህልውና ጉዳይ ነውና ሁሉም ስለሀገሩ መኖር፣ ስለ ወገኑ መቆም ራሱን ሊሰጥ ዓላማው በአንድ ሆነ፡፡

የኢትዮጵያ ድንቅ ተፈጥሮ እንደ ልዩ መዓዛ ከሩቅ የሚስባቸው ባዕዳን ዝናዋን ሰምተው ብቻ አልተቀመጡም፡፡ ጣዕሟን ሊመጡ፣ ክብሯን ሊያዋርዱ ድንበር ጥሰው፣ ባህር አቋርጠው ተመላልሰዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ሊያጣጥሟት የሻቷትን ሀገር ደርሰው እጇን አልጨበጡም፡፡ እንደ እሳት የሚፋጀው የጀግኖች ልጆቿ ሀያልነት የውርደት ሸማን አከናንቦ መልሷቸዋል፡፡

ይህ እውነት የኢትዮጵያ ሀገራችን ተደጋጋሚ ታሪክ ነው፡፡ ለዘመናት ማንነቷን ሊፈትኑ ከደጇ የደርሱ ጠላቶቿ መጨረሻቸው በሽንፈት መንበርከክ ሆኗል፡፡ ሀገራችን በዘመኗ ባህር አቋርጣ ድንበር ጥሳ የሌሎችን ሀብት የተመኘችበት ጊዜ የለም፡፡ በእሷ ታሪክ ግን ይህ አይነቱ ሀቅ ተገላቢጦሽ ሆኖ ታላቅነቷን ሲያስመሰክር ፣ስሟን በዝና ሲያስጠራ ኖሯል፡፡

የዓመታት ታሪክ ወደ ኋላ ሲቃኝ አውሮፓውያን መላ አፍሪካን በቅኝ ለመግዛት ፣ መሬቷን ለመቀራመት የተንቀሳቀሱበት ዘመን ላይ ያደርሰናል፡፡ የዚህ ጊዜ ሌላው መልክ በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መንግሥት መካከል የውጫሌ ውል ስምምነት የተካሄደበት ጊዜ ነበር፡፡

ኢጣሊያኖች ምጽዋን በእንግሊዞች ርዳታ ከግብጽ ከወሰዱ በኋላ ዓላማው ለነጋዴዎች ማረፊያ በሚል ምክንያት አስመራንና ዙሪያውን በቁጥጥር ስር አደረጉት፡፡ ቀስ በቀስም ሰራዬ የተባለውን ስፍራ ጨምሮ እስከ ሀማሴን ምድር ዘለቁ፡፡ ውሎ አድሮ አጼ ምኒልክ ጣሊያኖቹ በያዟቸው ድንበሮች ላይ ወሰን ለመለየት የሚስላቸውን የውጫሌ ውል ለመፈራረም ከስምምነት ደረሱ፡፡

እነሆ ! ሁለቱ ወገኖች በአንድ ሊቀመጡ ቀኑ ደረሰ ፡፡ የተጻፈው ሃሳብ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው፡፡ ስምምነቱ ከመፈረሙ አስቀድሞ ጉዳዩን በወጉ ማጤን ይገባል ፡፡ ውሎቹ ገፅ በገፅ እየተገለጡ፣ ቃል በቃል እየተነበቡ አንድ በአንድ ተፈተሹ፡፡

ምርመራው ሲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ላይ የሰፈረው አንቀጽ ከሌሎች ሁሉ የሚለይ መሆኑ ታወቀ ፡፡ በኢጣሊያ ቋንቋ የሰፈረው ይህ ውል ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን በሀገረ ኢጣሊያ በኩል ብቻ እንድታካሂድ የሚያስገደደድ ስለመሆኑ በግልጽ ሰፍሯል፡፡፡

ንጉሥ አጼ ምኒልክ ይህን ውል አይተው ለመፈረም ልባቸው አልፈቀደም፡፡ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ስለሚሰጠው አስገዳጅ ውል ከባለሟሎቻቸውና ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር መከሩበት፡፡ ባገኙት ምላሽ መሠረትም ውሉን ላለመፈረም በአቋማቸው ጸኑ፡፡ ይህ ውሳኔያቸውንም ለኢጣሊያ መንግሥት በግልጽ አሳወቁ፡፡

ከዚህ በኋላ ኢጣሊያ የልቡ ሃሳብ አለመሙላቱን ተረዳ፡፡ ውሎ ሳያድርም ግዛቱን ከመረብ አሻግሮ ኢትዮጵያን ለመውረር ጦሩን አደራጀ ፡፡ አሁን ወራሪው የኢጣሊያ ጦር ያነሰ ግምት ለሰጣት ኢትዮጵያ የበዛ ጦሩን አስታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብቷል፡፡

ዕቅዱ ግን እንደታሰበው አልሆነም፡፡ በአምባላጌና መቀሌ የተላኩት የኢጣሊያ ወታደሮች በአፍታ ቆይታ በኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ ድል ሆኑ፡፡ ይህ ሽንፈት ባህር አቋርጦ ለመጣው የጠላት ጦር ከውርደት በላይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ሰፊውን ጦር በዘመናዊ የመሣሪያ ሃይል ያደራጀው የኢጣሊያ ሠራዊት መላ ኢትዮጵያን አንበርክኮ የቋመጠባትን ድንቅ ሀገር በእጁ ሊያደርግ ተጣደፈ፡፡

የጦርነቱ አይቀሬነት የገባቸው ንጉሥ ምኒልክ ‹‹አለኝ›› የሚሉትን ዘመናዊ መሣሪያ ከልበ ሙሉው ጦራቸው ጋር አዘጋጁ፡፡ አምስት ጎራሹ የወጨፎ ጠመንጃ ተወልውሎ ከጀግኖቹ እጅ ዋለ፡፡ ከውጭ ሀገራት በግዢ የተገኙት በሚሊዮን የሚገመቱ ጥይቶች ተቆጠሩ፡፡ ከፈረንሳይ መድፎች ተገዙ፡፡ ብልሁ ንጉሥ ይህ ብቻ አልበቃቸውም፡፡

በወቅቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሀገር ውስጥ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት ሞከሩ፡፡ ያኮረፉ፣ የከዱና የሸፈቱ አገረ ገዢዎችን በምህረትና ይቅርታ እየመለሱ ከጎናቸው አደረጉ፡፡ እንዲህ መሆኑ የሀገር አንድነትን አበረታ፡፡ ሁሉም ለአንድ ዓላማና ግብ ተጣምሮ ወራሪውን ጠላት ሊመክት በሙሉ ልብ ተዘጋጀ፡፡

ምኒልክ የሆነባቸውን ሁሉ ለመላው ዓለም ለማሳወቅ አጠገባቸው ባሉ የፈረንሳይና የሩሲያ ዜጎች አንደበት ተጠቀሙ፡፡ እውነታው በታወቀ ጊዜም የዓለም ዓይንና ጆሮ ወደ ኢትዮጵያ ምድር አዘነበለ፡፡

ዓድዋ ላይ የምኒልክ ጦር በጀግንነት ተሰልፏል፡፡ በእጁ ያለው መሳሪያ ከጠላቱ ጋር ሲተያይ እዚህ ግባ ይሉት አይደለም፡፡በባዶ እግር፣ በአጭር ሱሪ በኋለ ቀር ጠመንጃ ጠላቱን ሊዋጋ በሙሉ ወኔ ዘብ ቆሟል፡፡ ፉከራና ቀረርቶው ልብ እያሞቀ ወንድ ሴቱን እያነሳሳ ነው፡፡

የኢጣሊያው ጦር አዛዥ ጄኔራል ባላቶሊ ይህን ባወቀ ጊዜ ሃያ ሺህ የሚሆነውን በዘመናዊ መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀ ጦሩን በሶስት ግንባር አሰልፎ ወደፊት ተጠጋ፡፡ ጦርነቱ አይቀሬ ሊሆን ደቂቃዎች ተቆጠሩ፡፡ የአጼ ምኒልክ ጦር በሶስት ግንባር ተሰልፎ የተጋፈጣቸውን የጠላት ጦር ለመመከት የጀግንነት ሥልቱን ተጠቀመ፡፡

ሃያልነቱን ተመክቶ ንቀቱን ሊያሳይ ጉዞ የጀመረው ጠላት በትንታጎቹ ኢትዮጵያውያን እጅ ሲገባ በድንጋጤ ግራ ተጋባ ፡፡ ከፊት የሚያጠቃው ሃይል ከኋላው በሚገኝ የደጀን ጦር እየታገዘ ጠላትን ያስጨንቅ ያራውጠው ያዘ፡፡

ጦርነቱ ተፋፋመ፡፡ በጥይት አረር መፋጀቱ፣ በሳንጃ ስለት መሞሻለቁ ቀጠለ፡፡ ከየአቅጣጫው የሚወድቅ፣ የሚቆስለው በረከተ፡፡ በዓድዋ ምድር ደም እንደውሃ ጎረፈ፡፡ ሁለት የኢጣልያ ጄኔራሎች በሽንፈት እጅ ሲሰጡ አንደኛው ከፊታቸው ወድቆ የሞት ጽዋን ተጎነጨ ፡፡

ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ ጦር ምርኮ የሆነበት ጠላት እንደአገባቡ ሁሉ ሜዳው አልቀለለውም። መውጫው ጠፍቶት ከወዲያ ወዲህ ተራወጠ፡፡ በዓድዋው ጦርነት ከአስር ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መስዋዕት ሆነዋል፡፡

ይህ መሰዋዕትነት ያቀለመው ታላቅነት ነጮች በአሸናፊነት የመዝለቃቸውን እውነት የሚያከሽፍ ሆኗል፡፡ በዘመኑ በቅኝ ግዛት ስር ለሚማቅቁ ሀገራትም የማንቂያ ደወል ነበር ፡፡ ውሎ ያላደረው ብርቱ ትግል በአንድ ቀን ተጋድሎ ፣ ድሉን ለኢትዮጵያውያኑ አደረገው፡፡

እነሆ! የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ፡፡ ኢትዮጵያውያን ‹‹እምቢኝ ለሀገሬ ሲሉ በደማቸው ታሪክ የጻፉበት፣ ነጻነታቸውን ያዋጁበት ድንቅ ቀን፡፡ አንድነታቸውን በሕይወት መስዋዕትነት ያሳዩበት አስደናቂ ውሎ፡፡ ይህ ዕለት ታሪካዊነቱ ለምድረ አበሻ ብቻ አልሆነም፡፡ በማንም ዘንድ ያልተሞከረው ሃያል ተጋድሎ አሸናፊነቱ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ሆኖ ድሉን በመላው ዓለም አስተጋባ፡፡

በቅኝ ቀንበር የታገቱት ሕዝቦች ትግልን ይጀምሩት ዘንድ ሃይልና ጉልበት የሆነው የዓድዋው ድል የወንዶች ተሳትፎ ብቻ አልነበረም፡፡ እቴጌ ጣይቱን የመሰሉ ብልህ የጦር መሪና አማካሪ ድንቅ ጀግንነት ታክሎበታል፡፡

በጣይቱ መሪነት በተካሄደው ጦርነት በመላው ሀገሪቱ የነበሩ ሴቶች ተጋድሎ የበዛ ነበር፡፡ ከስንቅ ዝግጅት ደጀን እስከመሆን፣ ቁስለኞችን አክሞ ጦር መርቶ እስከመዋጋት የደረሰው የሴት አርበኞቹ ትግል ለዓድዋው ድል መሠረት ለአፍሪካውያን ህብረት ክንድ ነበር፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You