“የዓድዋን ዕሴቶች በሚገባ በመጠቀም እንደ ዓድዋ ተራሮች የጸናች ኢትዮጵያን መገንባት ይቀረናል”  – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!

እናቶቻችንና አባቶቻችን ታላቁን የዓድዋ ድል ከሰጡን 128 ዓመታት አስቆጥረናል። የዓድዋ ድል የሰጠንን ዕሴቶች ግን በሚገባ የተጠቀምንባቸው አይመስለኝም። ቢያንስ አራቱን ታላላቅ የዓድዋ ድል ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ ልንጠቀምባቸው የግድ ይለናል።

የመጀመሪያው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው። ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያ ዋናው መልኳ መሆኑን ከዓድዋ ዘመቻ በተሻለ ለማሳየት የቻለ ክስተት በዘመናዊ ታሪካችን አናገኝም። የዓድዋ ዘመቻ ሁለት ጊዜ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አሳይቷል። የመጀመሪያው በጦርነቱ ዘመቻና ድል ጊዜ ነው።

ዛሬ በምናውቃት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል ወደ ዓድዋ ያልዘመተ ወገን የለም ብሎ መናገር እውነትን መናገር ነው። ሁለተኛው ክስተት ደግሞ የዓድዋ ድል በተገኘ በሰባት ዓመቱ የዓድዋ በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ሲከበር ትርዒቱን ያቀረቡት ከተለያዩ የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች የመጡ የኢትዮጵያ ጦር አባላት ነበሩ። በዚህ ትርዒት ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊት ሀገር መሆንዋን በአደባባይ ሰልፈኛው አሳይቶ ነበር።ይሄ በዓድዋ ዘመቻና በዓል የተንጸባረቀ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አጽንተን ልንይዘው ይገባል።

ኢትዮጵያ ማለት ኅብረ ብሔራዊ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ናት። ኅብረ ብሔራዊነታቸው ከፈጣሪ ሲያገኙት ነው። አንድነታቸውን ደግሞ እነርሱ ራሳቸው በዘመናት ትስስርና መስዋዕትነት ገንብተውታል። ኢትዮጵያ እነዚህ ሁለቱን ነገር፣ ግን አንዱ ከሌላው ጋር ሳይነጣጠል የሚኖሩትን መገለጫዎቿን ትታ ኢትዮጵያ አትሆንም። በእያንዳንዱ ጉዞዋ ይሄንን እያረጋገጠች መጓዝ አለባት።

ሁለተኛው ዕሴት ለታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ሲባል ንኡስ ፍላጎቶችን መሰዋት ነው። ወደ ዓድዋ የዘመቱ ሁሉ በወቅቱ በነበረው ሥርዓተ መንግሥት የሚስማሙና የተደሰቱ አልነበሩም። አንዳንዶቹ እንዲያውም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ግጭትም ቅራኔም ነበራቸው። አንዳንዶቹም በነበረው ሀገራዊ ሁኔታ ቅር ተሰኝተው ከጠላት ጋር የሚሠሩ ነበሩ። ነገሩ የሀገር ጉዳይ ሲሆንባቸው ግን ሁሉም ንኡስ ፍላጎቶቻቸውን ትተው፣ ለታላቁ ፍላጎት ለሀገር ህልውና መስዋዕት ለመሆን መጡ። ማንኛውም ፍላጎት ከሀገር ፍላጎት በታች መሆኑንም አሳዩን።

እንኳን ዛሬ ብዙ ዓይነት መረጃ፣ ዕውቀትና የሃሳብ መንገዶች ባሉበት ዘመን ቀርቶ ከመቶ ዓመት በፊትም ሰዎች ልዩ ልዩ ፍላጎቶች ነበሯቸው። በፍላጎቶቻቸው የተነሳም ቅራኔዎችና ግጭቶች ነበሩ። ሁሉንም ለአንድ ዓላማ የምታስተሳስር ሀገር የምትባለው ናት። ዛሬም ንኡስ ፍላጎቶቻችን ከኢትዮጵያ አይበልጡም።

ኢትዮጵያን የሚያዳክም፣ የሚያሳንስና የሚያሳጣ መንገድ ከትልቁ ዓላማ የሚጋጭ መንገድ ነው። ጦርነት የትልቁ ዓላማ የኢትዮጵያ ህልውና ማስከበሪያ እንጂ የንኡስ አካባቢያዊና ግላዊ ዓላማዎች ማስፈጸሚያ ሊሆን አይገባም። ጦርነት ለትንሽ ነገር የሚወጣ ወጪ አይደለም።

ዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉት ሁሉ ብዙ የመፍትሔ አማራጮችም አሉት። መከራከር፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ በሕግ መዳኘት፣ አንዱ ሌላውን መሸከም፣ የትየለሌ አትራፊ መንገዶች አሉት። ትልቁ ዓላማ ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ስንል ንኡስ ዓላማዎቻችንን እያመሙን እንኳን ቢሆን መሰዋት አለብን።

ሦስተኛው ዕሴት የጦርነትን ምርቅና ፍትፍት ማወቅ ነው። ጦርነት ምንም ያህል በአሸናፊነት ቢጠናቀቅ የሚያስከፍለው ዋጋ አለው። የዓድዋ ዘማቾች ሀገር ሆኖባቸው፤ ሉዓላዊነት ሆኖባቸው፤ የታላቅ ዓላማ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ ጦርነት የመጀመሪያ አማራጫቸው አልነበረም። ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ነገሩ በሰላም እንዲቋጭ ደጋግመው ጽፈዋል፤ ለምነዋል፤ አልሆነም። የዓድዋ ዘመቻ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

የኢትዮጵያ ዘማቾች ግን ከድል የተመለሱት በደስታ ብቻ አይደለም። ከፊታውራሪ ገበየሁ ጀምሮ አያሌ ጀግኖች ለትልቁ ዓላማ ለኢትዮጵያ ህልውና ሲሉ ተሠዉተዋል። የሄዱት ሁሉ አልተመለሱም። የኢትዮጵያ ሠራዊት በድልና በኀዘን ነው የተመለሰው። ብዙዎችም በየአካባቢያቸው በፌሽታ አልነበረም ድሉን ያከበሩት። እንኳን በራሳቸው ወገኖች፣ በጣልያኖች መሞት ኢትዮጵያውያን አዝነዋል።

ጦርነት ተገድደን ብቻ ለትልቁ ዓላማ ስንል የምንገባበት የመጨረሻ አማራጭ እንጂ ከደረት ኪሳችን ቶሎ የምንመዘው አይደለም። እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በጠመንጃ ለመፍታት መነሣት የዓድዋ ዘማቾችን ኀዘን አለመጋራት ነው። የዓድዋ ዘማቾች ድልን ብቻ ሳይሆን ጦርነት የሚያስከትለውን መከራም ጭምር አስተምረውን አልፈዋል።

አራተኛው ትዕግስት፣ ዝግጅት እንጂ ፍርሐት አለመሆኑን ነው። ጣልያኖች ከሦስት ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን ሲገፏት ነበር። በሀገሪቱ የደረሰውን የእንስሳትና የሰዎች ማለቅ ምክንያት አድርገው ትንኮሳውን አባብሰው ነበር።

ኢትዮጵያ እየተገፋች እንኳን ቢሆን ታግሳለች። ትዕግስቷ ግን ከዐቅመ ደካማነቷ የመጣ አይደለም። ለባሰው ነገር እየተዘጋጀች ስለነበር እንጂ። እህል እስኪደርስ፣ ሰው እስኪያገግም፤ የተገዛው መሣሪያ እስኪደርስ፣ የደረሰው መሣሪያ ከጦሩ ጋር እስኪላመድ ታግሳለች። በመጨረሻ ግን የትዕግስቷን ውጤት በዓድዋ ተራሮች ላይ አሳይታለች።

ኢትዮጵያ ዛሬም ትታገሳለች። እየተገፋችም እንኳን ቢሆን ትታገሳለች። የምትታገሰው ስለሚያቅታት አይደለም። ለባሰው ነገር ስለምትዘጋጅ ነው። ያ የባሰው ነገር ሲመጣ የዓድዋውን ድል በብዙ እጥፍ ትደግመዋለች። እነዚህን ዕሴቶች ዘወትር ማሰብ፣ አስበን መተግበር እንድንችል የሚያስታውሰን ነገር ያስፈልግ ነበር። ዓድዋን የሚመጥን ታሪኩንም ዕሴቱንም የምናስብበት መታሰቢያ ዘመቻው በተጀመረበት ሥፍራ ባስገነባን ማግሥት ነው በዓሉን የምናከብረው። ይሄም ለዘንድሮው በዓል ሞገስና ክብር ጨምሮለታል።

ዛሬ መታሰቢያውን በከበረ ሁኔታ አከናውነናል። ነገ ግን የዓድዋን ዕሴቶች በሚገባ በመጠቀም እንደ ዓድዋ ተራሮች የጸናች ኢትዮጵያን መገንባት ይቀረናል። ያ ደግሞ የሁላችንንም ስክነት፣ ብስለትና ጥምረት ይፈልጋል።

በድጋሚ መልካም የዓድዋ ድል በዓል ይሁን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

የካቲት 22/2016 ዓ.ም

አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም

Recommended For You