ዋ ! ዓድዋ …

የዓድዋ ድል ጀግኖች ሀገራቸው በቅኝ ገዥ እንዳትያዝ ለማድረግ ከጣልያን ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው የተዋደቁበትና የነጭን ወራሪ ድል ያደረጉበት ነው፡፡ በዚህም ጦርነት እናቶቻችን እና አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው በደማቅ ቀለም የኢትዮጵያን ታሪክ ለዓለም በሚያንፀባርቅ መልኩ ጽፈዋል፡፡

ከዓድዋ ጦርነት በፊት ግን ጣልያኖች በዶጋሊ፣ ሰገነይቲ፣ ሰንአፌ፣ አምባላጌ፣ መቀሌና ኰአቲት ከኢትዮጵያ ጋር ተዋግተው ተሸንፈው ነበር። የሰንአፌና ኰአቲት ጦርነት ድል የተመዘገበው በምኒሊክ ዘመን በራስ መንገሻ ዮሐንስና በራስ አሉላ ጦር ነው፡፡

ድሉ 128 ዓመት አስቆጥሯል፡፡ የዘንድሮው በዓል ልዩ የሚያደርገው ደግሞ እንደ ድሉ ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአዲስ አበባ መገንባቱና ባለፈው የካቲት 3 ቀን መመረቁ ነው። ይህን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የተሳተፉ መሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ጎብኝተውታል፡፡ በሙዚየሙ መደመማቸውንም ለመገናኛ ብዙኃን ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡

በግሌም መሪዎቹና ሚኒስትሮቹ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ጎራ ማለታቸውን ስሰማ ጉራ ቢጤ ተሰምቶኛል፡፡ ደስም ብሎኛል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ዋ! ያቺ …. ዓድዋ በሚል ከ52 ዓመት በፊት የተቀኘባትን ግጥም እንዳስታውስ አድርጎኛል።

‹‹ ዋ! ….

ዓድዋ ሩቅዋ

የዓለት ምሶሶ አድማስ ጥግዋ

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

ዓድዋ ….

ባንቺ ሕልውና

በትዝታሽ ብፅዕና

በመስዋዕት ክንድሽ ዜና

አበው ታደሙ እንደገና …. ››

በነገራችን ላይ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ነው፡፡ 128ኛው ዓድዋ በሚከበርበት ዘመን ይህን ዘመን ተሻጋሪ አስደማሚ ሙዚየም መሠራቱ ዓድዋ የበለጠ የሚያጎላ፣ ዜጎችን የሚያኮራ፣ ቱሪስቶችንና ጎብኚዎችን የሚጠራ ነው፡፡ እያጎጠጎጠ ያለው ጎጥ (ጎጠኝነት) የጥላቻና ሽኩቻ ትርክቶች አስወግደን ባንድነት እንድንቆም ግድ ይለናል፡፡ በመደመር እንጂ በመደናበር ጠላት ድህነትን ማስወገድ አይቻልም። እርስ በርስ መቃቃርና መናቆር ፋይዳ ሳይሆን ፍዳ እንዳያመጣብን ተገንዝበን ዓድዋን አስበን ከግጭት መራቁና እርቅ መፍጠሩ ይበጀናል፡፡

የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት፤ ጣልያን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ማንዣበብ የጀመረችው በዐፄ ዮሐንስ ዘመን ነው፡፡ የጣልያን ወታደሮች በእንግሊዝ አይዞህ ባይነት ግብፆችን ተክተው ምፅዋ የገቡት ጥር 28 ቀን 1878 ነበር፡፡

ወታደሮች በወቅቱ ጠረፍ እየወረሩ ስለነበር የመረብ ምላሽ ገዥ ራስ አሉላ ለኢጣልያው አዛዥ ለጄኔራል ካርሎ ዠኔ የያዘውን የኢትዮጵያን ምድር ለቆ እንዲሄድ ላኩበት፡፡ አለቅም ብሎ ገለፀላቸው፡፡ በኋላም በሰሐጢ መሽጎ ይጠባበቅ ከነበረው ማጀር በረቲ ውጊያ ገጥመው ድል አደረጉት፡፡ ቀጥሎም ሌተናል ኰሎኔል ክርስቶፎረስ ሦስት ክፍል የጦር ሠራዊት ይዞ 1879 በጥር 20ዎቹ መግቢያ ከምፅዋ 500 ገደማ ሠራዊት የተላከለት የኢጣልያ ጦር ዶጋሊ ላይ ገጥሞ፤ የአሉላ ጦር ከቦ ሁሉንም ዶጋመድ አደረገው፡፡

በጦርነቱ ጣልያን 23 የጦር መኮንኖችን ስታጣ 407 ደረጃ ያላቸው ወታደሮች ደግሞ እንደተገደሉባት ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በዚህም ጣልያን ሰዓቲን አስረክባ ወደ ቀይ ባሕር ጠረፍ ሸሸች፡፡ የዶጋሊ ድል በጣልያን ሲሰማ ከፍተኛ ደንጋጤና ሀዘን ፈጠረ፡፡ ወዲያው ሽንፈቱን እንዲመልሱ ታስቦ 20ሺ የጣልያን ወታደሮች ምጽዋ እንዲሰበሰቡ ተደረገ፡፡

የጣልያን ወዳጅና የዐፄ ዮሐንስ የአጎት ልጅ የነበረው ፊታውራሪ ደበበ ከጣልያን ተጣልቶ ሰገነይቲ ሸፍቶ መሽጎ አስጨንቋቸው ነበረ፡፡ በነሐሴ 2 ቀን 1880 ዓ.ም ሰገነይቲ አምርተው ድንገተኛ ጥቃት ለመፈጸም በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ ደበበ ከሁለት ቀን በፊት መምጣታቸውን ሰምቶ እንቅስቃሴያቸው ይከታተል ነበር፡፡ ለዚህም ሴት፣ ሽማግሌ ልጅ ከመንደሩ አስወጥቶ ጠበቃቸው፡፡ ተኩስ ከፍቶ ጦርነት ተካሄደ፡፡

በዚህም 5 የጣልያን የጦር መኰንኖችና 250 ወታደሮቻቸው ተገደሉ፡፡ ያልቆሰሉ ሸሽተው ምፅዋ ገቡ፡፡ ደበበ 470 ጠብመንጃ የታጠቁና 400 ጐራዴና ሳንጃ የታጠቁ ተዋጊዎች ነበሩት፡፡ ሰገነይቲ ከዶጋሊ ቀጥሎ ጣልያኖች የሽንፈትን ጽዋ የተጐነጩበት ነው፡፡

ጣልያኖች መረብን ተሻግረው ትግራይ አካባቢን የወረሩት በመስከረም1888 ነበር፡፡ንጉሡ ችግሩን ለመፍታት በዲፕሎማሲ ጥረት ሞክረው ጣልያኖች አሻፈረኝ ስላሉ፤ ከ100 ሺ ጦር ላይ ይዘው ከእቴጌይቱ ጋር ወደ ሰሜን ዘመቱ፡፡ በወቅቱ ሀገሪቱ መደበኛ ጦር አልነበራትም፤ በሰላም ጊዜ አርሶ አደርና አርብቶ አደር በግጭት ጊዜ ደግሞ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ሕዝብ ነበር፡፡

ዓድዋ ከአዲስ አበባ 1ሺ66 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ለጦርነቱ ዋና መነሻ የውጫሌ ውል ነበር፡፡ የውጫሌ ውል የተፈፀመው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘዋ ከአምባሰል ተራራ ግርጌ በውጫሌ ነበር፡፡

የውጫሌ ውል መፍረሱን ተከትሎ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን መውርር በጀመሩ ጊዜ ምኒሊክ ክተት አወጁ፡፡ “ወረኢሉ እንገናኝ” ሲሉ አስነገሩ፡፡

የዓድዋ ውጊያ መጀመሪያ በኅዳር 29 ቀን አምባላጌ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ራስ መኮንን ጣልያኖቹ ያሉበትን ቦታ በሰላም ለቀው እንዲወጡ በመደራደር ላይ ሳለ ፊታውራሪ ገበየሁ ሠራዊቱን የአምባላጌን አቀበት እየተዋጋ ወጥቶ ጣልያንን ድል አደረገ፡፡

በወቅቱ የጣሊያን ጦር አዛዥ ቶዚሊ ከሞቱት መካከል ሲሆን የቀረው የጣልያን ጦር ተበተነ፡፡ በወቅቱ ገበየሁ ድል በማድረጋቸው አዝማሪ እንዲህ ገጠመላቸው ፦

የንጉሥ ፊታውራሪ የጐራው ገበየሁ፣

አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው፣

ለምሳም አልበቁት ቁርስ አደረጋቸው፡፡

በጥር ወር ከጣልያኖች ጋር የነበሩት የሐማሴኖቹ ራስ ስብሐትና ደጃች ሀጎስ ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር ሆነን ሀገራችንን አንወጋም ብለው ከነባንዳቸው መጥተው ከንጉሡ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ምኒሊክ ጦሩን መርተው ዓድዋ ሲደርሱ፤ ጣልያኖች ከአዲግራትና እንጢቾ ምሽጋቸው ወጥተው ጦርነት የሚገጥሙበትን መጠባበቅ ጀመሩ፡፡

የካቲት 23 ቀን በማለዳ የጣልያን ጦር አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ድንገተኛ አደጋ ለመጣል ጦሩን አንቀሳቀሰ፡፡ በሦስት መስመር ያጠቃ የነበረው የጣልያን ጦር እርምጃዎች ማቀናጀት ተሳነው፡፡ በአልቤርቶኒ የሚመራ ብርጌድ በተሳሳተ ካርታ ንባብ ከሁለቱ ብርጌዶች ተነጥሎ ለተባበረው የኢትዮጵያ ጦር ጥቃት ተዳረገ፡፡ አልቤርቶኒን ለማዳን የገሰገሰው የዳቦርሜዳ ጦርም መንገድ ስቶ በባዶ ሜዳ ቀረ፡፡

በሀገር ፍቅር ስሜት ይዋጋ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር በስልትና በቅንጅት ከጠላት ልቆ በመገኘቱ ብዙ ሰው ቢያልቅም እኩለ ቀን ላይ ጦርነቱ አከተመ፡፡ 10 ሺ የሚደርስ የጣልያንን ጦር ጨምሮ ጄነራል አርሞንዲና ዳቦር ሜዳ ተገደሉ፡፡ የጣልያን ቅኝ አገዛዝ ህልም ዓድዋ ላይ እልም አለ፡፡

በዓድዋ ጦርነቱ ከሞቱት መካከል ልዑል ዳምጠው፣ ደጃዝማች መሸሻ፣ ደጃች ሜጫ፣ ደጃች ገነሜ ይጠቀሳሉ፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፊታውራው ገበየሁ ከመሞታቸው በፊት

‹‹የዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው›› ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡

በጦርነቱ ሲሞቱ ደግሞ እንዲህ ተገጠመላቸው፦

‹‹ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፣

አሻግሮ ገዳይ፥ ዲብ አንተርሶ

የዳኛው አሽከር፥ ባልቻ አባ ነፍሶ። ››

በዚህ ጦርነት ሊቀ መኳስ አባተ በያዙት መድፍ አነጣጥረው የጣልያኖችን መድፍ ባፉ አግብተው ሰባብረውት ስለነበር እንዲህ ተገጠመ‹‹

አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው

ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው።

በሻ ጉድ አለ ጣልያን ወተወተ

ዐይነ ጥሩ ተኳሽ በዋለው (ቧ ያለው) አባተ፡፡

በዚህም በዐድዋ የነጭን ወራሪ ድል ያደረገችዋ ኢትዮጵያ ዝናዋ በዓለም ተሰማ፡፡ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ ጥቁሮች ሁሉ እኛም ማሸነፍ እንችላለን የሚል ተስፋ ፈነጠቀላቸው፡፡ ይህም ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መነሻ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ስም በዓለም ላይ ናኘ። በአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በሚገኙ ጥቁሮችና ነፃነት ናፋቂዎች ዘንድ፡፡ ቅኝ ገዥዎቹ ነጮች ለኢትዮጵያ ክብርና ዕውቅና ሰጡ፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያ ኤምባሲዎቻቸውንም በአዲስ አበባ ከፈቱ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ ሲከፈትም በዚህ አንፀባራቂ ድል ምክንያት መሆኑ እሙን ነው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም በዐፄ ኃይለሥላሴ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተማ ይፍሩ ሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖችና ዲፕሎማቶች ጥረት መቀመጫው አዲስ አበባ ተደረገ፡፡ ይህም አዲስ አበባን ከኒውየርክና ጄኔቫ ቀጥላ ሦስተኛ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማ ለመሆን አስችሏታል፡፡

ዓድዋ ከአዲስ አበባ ያለውን ርቀት አስበን ከደቡብ እና ከምሥራቅ የመጡ ጦሮች ስናሰላ እስከ 2ሺህ ኪሎ ሜትር የተጓዘ ጦር እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚያው በእግርና በፈረስ አቀበቱን ቁልቀለቱን ጋራ ሸንተረሩን ዓድዋ የሄዱ ዜጎች ነበሩ፡፡ መደበኛ ጦር ያልነበራት ኢትዮጵያ በዓድዋ ተዋድቀው ታሪክ ያፃፉላት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ነበሩ፡፡ በችግር ጊዜ ተጠርተው ከግብርናቸው ተነስተው የዘመቱ ዜጎች ዘመናዊ መሣሪያ ያልነበራቸው፤ ቢኖራቸውም አጠቃቀሙን የማያውቁ ነበሩ፡፡ እናም አብዛኛው ተዋጊ ጦርና ጎራዴ የታጠቀ ጋሻ የያዘ ከፊሉ እግረኛና ገሚስ ፈረሰኛ ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚል መጽሐፋቸው የዓድዋ ድልን የቅኝ ግዛት ማዕበልን የገታ፣ የቅኝ ገዥዎችን ቅስም የሰበረ ይሉታል፡፡ በዓድዋ ጦርነት ትረካው ለጣልያን ግልፅ ወገናዊነት የሚያሳየው ጆርጅ በርክሌ እንኳን ‹‹ ከሰፊው የፖለቲካና ታሪክ ትንታኔ አኳያ የዓድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድር አዲስ ኃይል መነሳቱን የሚያበስር ይመስላል፡፡ የዚያች አህጉር ተወላጆች የማይናቅ ወታደራዊ ኃይል ሊሆኑ እንደሚችሉ ልናሰላስል ተገደናል፡፡ እንዲያውም አሁን ነገሩ አስቂኝ ቢመስልም፤ ይህ ሁኔታ (ማለትም ዐድዋ) ጨለማይቱ አህጉር በላይዋ ላይ ሥልጣኗን ባንሰራፋችው በአውሮጳ የምታደርገው አመፅ የመጀመሪያ ምዕራፍ ነውም ተብሏል ›› ሲሉ ጠቅሰዋል።

በዘመኑ የነበሩ ዜጎች የእምነትና የብሔር ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ‹‹መጀመሪያ መቀመጫዬን›› እንዳለችው ዝንጀሮ መጀመሪያ ሀገሬን ብለው በአንድነት ተዋግተዋል፡፡ ተሽከርካሪም ሆነ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በሌለበት በዚያን ወቅት በእግራቸው ዳገት ቁልቁለቱን እየሄዱ ዓድዋ ደርሰው ከጣልያን ወራሪ ጋር ተዋግተው ሀገራቸውን ከወራሪ ማዳን ችለዋል፡፡

የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል መማር ያለበት የአንድነትን ጥቅም ነው፡፡ ስለሆነም ትውልዱ ከመገፋፋት እና ከማይጠቅም መጠላላፍ ወጥቶ አንድ በመሆን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉትን ጠንካራ የሀገረ መንግስት የመገንባት ሂደት ውስጥ የራሱን አሻራ ሊያሳርፍ ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ኃይለማርያም ወንድሙ

አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You