ዓድዋና ኒኮላይ እስቴፓኖቪች ሌዎንቴቭ

አሜሪካዊው ፀሐፊ ማርክ ትዌይን፤ «ታሪክ ራሱን አይደግምም፤ የእገሌ ዘመን፣ የምንትሴ ዘመን ከሚለው መመሳሰል ውጪ ነው» ይላል። እርግጥ ነው ፀረ ቅኝ አገዛዝ ጦርነት በተለያዩ አካባቢዎችና ሀገራት ተደርጓል። በእስያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በአፍሪካ ለነፃነታቸው ለረጅም ዘመናት የታገሉና ድልም የተቀዳጁ አሉ፤ የአድዋው ጦርነት ግን በተደረገበት የታሪክ የዘመን ነቁጥና ሥፍራ ሲታይ እጅግ አንፀባራቂና ቀዳሚ ቦታ ያለው ነው። የዛሬው ጽሑፉ ማጠንጠኛም ከዚሁ የዓድዋ ገድል ጋር በቅርብ የተገናኘ አንድ ሩሲያዊን ማስታወስ የፈለገ ነው፡፡

ኒኮላይ እስቴፓኖቪች ሊዎንቴቭ ይባላል፤ ይህ ሰው የዓድዋ ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ጊዜያት በፊት ከአፄ ምኒልክ ጋር በቅርብ የተዋወቀ ነው፤ ሰውየው የሩሲያ የሚሊታሪ መኮንን የነበረ ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የተጓዘ ሀገር አሳሽና የጂኦግራፊ ሚሲዮን አባልም ሆኖ ሀገሩን ሩሲያን አገልግሏል።

በ1887 ዓ.ም ከጥቂት ረዳቶቹና ከበጎ ፈቃድ ተጓዦች ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፤ አመጣጡም በኦፊሴላዊ መንገድ የሩሲያ መንግሥትን ተልዕኮ በመያዝ በጊዜው ለነበሩት ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ለማድረስ ነበር፡፡አፄ ምኒልክ ከዚህ ሰው ጋር ጥሩ ወዳጅነትና መቀራረብ እንደፈጠሩና አንዳንድ ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ጉዳዮች እንደፈፀሙ በታሪክ ተፅፎ ይገኛል፤ ወቅቱ በአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛት እሽቅድድም ወደኋላ የዘገየችው ኢጣሊያም ኢትዮጵያን ለመያዝ ዝግጅቷን ሁሉ ጨርሳ ትንኮሳዎችን እምታደርግበት ሰዓት መሆኑም ይታወሳል፡፡

ሊዎንቴቭ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የነበረውን ቆይታ ጨርሶ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ምኒልክ 30ሺ ጠመንጃ፣ ከ5 ሚሊዮን በላይ አረርና ጥይት፣ 42 ያህል የተራራ ላይ መድፎች እንዲያመጣላቸው ከአደራ ጋር ለመስኮብ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ኒኮላ የተጻፈ ደብዳቤ አስይዘው እንደ ላኩት፤ አፄ ምኒልክ ተልዕኮውን ከፈፀመ በኋላም ለዚህ የችግር ቀን ወዳጃቸው ለሆነ ሰው የማዕረግ ሽልማትም እንደሰጡት በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።ይህም ሆኖ ግን የተጠበቀው ወታደራዊ እርዳታ መድረስ የቻለው የዓድዋ ውጊያ ከተፈፀመ ከሦስት ወራት በኋላ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡

አፄ ምኒልክ የላኩት ደብዳቤ ሙሉ ቃል ይህን ይመስል ነበር ፦

“ይድረስ ከክቡር ወልዑል ቄሣር ከመስኮብ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ኒኮላ… ሰላምና ጤና ለርስዎ ይሁን ። ከርስዎ ዘንድ የተላኩ መነኩሴና መኳንንቶች በደህና ደረሱ። እኛም በክብርና በደስታ ተቀበልናቸው፡፡ የክቡር አባትዎን ሞት ሰምተን እጅግ አዝነን ነበር። እርስዎ በእግዚአብሔር ፈቃድ በሕዝብዎ መውደድ ባባትዎ ዙፋን መቀመጥዎን ሰምተን በጣም ደስ ብሎናል።

“ግዛትዎና ዕውቀትዎ እየበዛ እየተረፈ እንዲሔድ እጅግ ተስፋ አለን። ያባትዎን የጥንት ፍቅርና ወዳጅነት አለመርሳታችንን ለማስታወቅ ኃዘንዎና ኃዘናችን አንድ ዘንድ እንዲተባበር ብለን ከንጉሠ ነገሥት (እስክንድር) መቃብር ላይ የሚደረግ የኢትዮጵያ ዘውድ ሰደናል። ከዘውዱም ጋራ የታመኑ ሰዎቻችንን ሰደናል፡፡

“ዳግመኛም የክርስቲያን ሃይማኖት ኦርቶዶክሳዊት ወንድሞቻችሁ መሆናችንን የሚያስረዳ ፍቅራችንንም የሚያሳይዎ ወንጌልና የወርቅ መስቀል ልክናል። እርስዎም በክቡር (አክብረው) እንዲቀበሉን ተስፋ አለን። ክቡር አባትዎ ዊክቶር (ቪከቶር) ማሽኮፍን ወደኛ የላኩ ጊዜ የጻፉልኝን የፍቅር ደብዳቤያቸውን ቃል እርስዎም እንዳይረሱ እናውቃለን።

“ዕድሜዎን እንዲያራዝም መንግሥትዎን የእርቅ የሰላም አድርጎ እንዲያሰነብትዎ መልካም አሳብዎን ሁሉ እንዲፈጽምልዎ ይልቁንም ክርስቲያን በመርዳትዎ እንዲጠብቅዎ ልዑል እግዚአብሔርን እለምናለሁ። በሚያዝያ በ22 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ በ1887 ዓ.ም ተጻፈ”

ንጉሰ ነገሥቱ ደብዳቤያቸው እንደሚያመለክተው፤ የጣሊያኖች ትንኮሳ ወደ ለየለት ጦርነት መግባቱ እንደማቀር፣ ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ፣ በሊዎንቴቭ በኩል በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው ግንኙነት ይህንኑ ፍላጎታቸውን ተጨባጭ ለማድረግ እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ እንደተጠቀሙበት የሚጠቁም ጭምር ነው።

ሁኔታው ንጉሰ ነገሥቱ እንዳሰቡት ባይሆንም፤ ኢትዮጵያውን ለነጻነታቸውና ለፍትህ ካላቸው ቀናኢነት የተነሳ ወራሪውን የጣሊያን ጦር በዓድዋ ድል አድርገዋል። ይህ ለአንድ ዓላማ በአንድነት የመቆም ፣ ሀገርን ያለማስደፈር የተጋድሎ ታሪክ ዛሬ የመላው አፍሪካ (ፓን- አፍሪካዊነት) ምልክት ሆኗል፤ የአይበገሬነትና የአንድነት ትግል ተምሳሌት በመሆንም ይቀጥላል፤ ኢትዮጵያ በዓደዋ ድል ማድረጓን ተከትሎ ዙሪያዋን የከበቧት ኢምፔሪያሊስቶችና ቅኝ ገዢዎች አደብ እንዲገዙ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት ብዙ ታሪካዊ አጋጣሚዎችን የሚጠቅስና መልከ ብዙ ቢሆንም በሊዎንቴቭ የተጀመረው ወዳጅነት ግን እንደ ዓድዋው ድል ሁሉ ዘመን ተሻጋሪ ሆኗል፤ የኋላ ኋላ ተጠናክሮ በርከት ላሉና በሁለቱ ሀገራት በተግባር ለተተረጎሙ ክንዋኔዎች ምክንያትም ሆኗል።

ከጊዜ በኋላ ተጠናክሮ ለተከፈተው የደጃች ባልቻ ሆስፒታል ይህኛው አጋጣሚ እርሾ ሆኖ እንዳገለገለ አይካድም፤ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥቅምት 16 ቀን 1950 ዓ.ም የደጃች ባልቻ ሆስፒታል ምሥረታ 10ኛ ዓመት በዓል ላይ ሲናገሩ፤ የሩሲያ መንግሥት ለዜጎቻቸው ጤንነትና ደህንነት የሚያግዙ ተግባራትን በመፈፀሙ እጅጉን መደሰታቸውን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሩሲያ ከዚያም በኋላ በተለያዩ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ ኢትዮጵያውያን በፈተናዎች ውስጥ በሆኑባቸው ወቅቶች የክፉ ቀን ወዳጅነቷን በተጨባጭ አስመስክራለች። በየዓለም አቀፉ መድረክ ሳይቀር ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት በተጨባጭ አሳይታለች፡፡

ይህ በኒሎላይ እስቴፓኖቪች ሊዎንቴቭ የተጀመረው ምንም ዓይነት ቅኝ ግዛታዊና ኢምፔሪያሊስታዊ ፍላጎትና ዓላማ ያልነበረው የኢትዮጵያና የሩሲያ ግንኙነት በሌሎችም መስኮች በተደረጉ ትብብሮች ተደግሟል፤ ሩሲያኖች (ሞስኮቦች) በባህርዳር የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ ድጋፍና ትብብር አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ በተወረረችም ጊዜ በወታደራዊ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ አስችሏል፡፡

በኦጋዴንም በምሥራቅና ምዕራብ ጋሻሞ፣ በካሉብና ጎዴ የነዳጅና ጋዝ ፍለጋና ቁፋሮ ሥራዎች፤ በባሕልና በትምህርት መስክ በተደረጉ ስምምነቶች ብዙ ኢትዮጵያዊያኖች ወደ ሩሲያ ተልከው ተምረው መመለሳቸው ለጤናማ ግንኙነታቸው ተጨማሪ ማሳያ ናቸው። እነዚህ በሩሲያ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ባለፈ ለዓለምም የተረፉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡

ይህ በተለያዩ መንግሥታት የዘለቀው የሀገራቱ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሠረተ ለመሆኑ እምብዛም ማስረጃ የሚጠይቅ አይደለም፡፡በታላቅ ሀገርና በትንሽ ሀገር፣ በሀብታምና በድሃ መካከል የሚታይ ሳይሆን ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ በእኩልነትና በፍትህ አደባባይ በእኩልነት ይታያሉ የሚለውን መርህ በተጨባጭ ተግባራዊ ያደረገ ነው፡፡

ዛሬ ስለ ዓድዋና ሊዎንቴቭን ስናስታውስ፤ ጠላት የፈለገውን ያህል መሣሪያ ታጥቆና ተደራጅቶ ቢመጣም ለነጻነት ካለን ቀናኢነት እና ለሀገር ካለን ፍቅር እንደማይበልጥ ነው። ለዚህ ደግሞ የዓድዋ ድል ሕያው ምስክራችን ነው።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You