አሳሳቢው የአበረታች መድኃኒቶች  ተጠቃሚነት ጉዳይ

የስፖርቱን ዓለም ከሚያደፈርሱና ንጹህ የውድድር መድረኮችን ከሚያራክሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ጉዳይ ነው። የማይገባ ዝና ለማግኘት በሚደረግ አቋራጭ መንገድ በጥረታቸው ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑ ስፖርተኞችን ዕድል ከመዝጋት ባለፈ የስፖርት ተአማኒነትንም ገደል ይከታል።

የትኛውም ስፖርተኛና ባለሙያ አውቆም ይሁን ሳያውቅ አበረታች ቅመም ተጠቅሞ ሲገኝ፣ እንዲጠቀም ሲያደርግ ወይም መሰል ተግባር ላይ መሳተፉ ከተረጋገጠ ያገኛቸው ስኬቶችና ክብሮችን ተነጥቆ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ከዚያም ለሕይወት ዘመን ከስፖርት ዓለም እንዲሰረዝ ይደረጋል፡፡

ብርቱ ጥረትና ጽናትን በሚጠይቀው የስፖርተኝነት ሕይወት በአቋራጭ ለመጠቀም የተለየ ብቃት የሚጨምርላቸውን ዘዴዎችን መጠቀም ከጥንት አንስቶ ሲተገበር የቆየ ተግባር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ግሪካውያን፣ ግብጾች፣ የእንግሊዝና መሰል ሀገራት በኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶቻቸውን ለማበርታት የተለያዩ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር።

ይህ ሁኔታ ከዘመኑ ጋር እየዘመነና እየረቀቀ መጥቶ ሰው ሠራሽ የሆኑ ቅመሞችንና ፈሳሾችን በተለያዩ መንገዶች ወደ ሰውነት በማስገባት በተፈጥሮ የተቸሩትን ብቃትና በዘመናዊ ሥልጠና ያገኙትን ሁለንተናዊ አቅም በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ውጤታማ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል።

የስፖርት አበረታች ቅመሞቹ በእንክብል፣ በመርፌ፣ በምግብ፣ በሰውነት ውስጥ በሚቀበር እንዲሁም በግሉኮስ በደም ስር የሚሰጡ ሲሆን፤ ሳይንሳዊ ሂደትን ተከትለው የሚካሄዱና በጥንቃቄ ተግባር ላይ የሚውሉ መሆናቸውን ተከትሎም በምርመራ መረዳት አዳጋች የሚሆንበት ወቅት ይኖራል።

ይህ የንጹህ ስፖርት እና ሃቀኛ ስፖርተኞች ጸር የሆነ ጉዳይ ከግለሰብ እስከ ሀገር የሚከወን መሆኑ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። ከየትኛውም ዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድር የታገደችው ሩሲያ ለዚህ ዋነኛ ምሳሌ ስትሆን፤ በስፖርቱ ዓለም ታላላቅ ክብሮችን መቀዳጀት የቻሉ ምርጥ አትሌቶች፣ ዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት አስተዳዳሪዎች እና አሰልጣኞች ቀድሞ የነበሩበት የስኬትና የክብር ማማ ከመሠረቱ ተናግቷል።

በግለሰቦች ምክንያትም ሀገራት ስማቸው በአሉታዊ መንገድ መነሳቱ እጅግ የሚያስቆጭ መሆኑ አያጠያይቅም። ተጠቃሚነቱ እግር ኳስን ጨምሮ በሌሎች ስፖርቶች ላይ ስለመኖሩ አመላካች ፍንጮች ይኑሩ እንጂ፤ በከፍተኛ ሁኔታ ስር የሰደደው ግን በአትሌቲክስ ስፖርቶች መሆኑ ከስፖርት ቤተሰቡ የተደበቀ አይደለም።

በአትሌቲክስ ስፖርት በበጎ ስሟን የገነባችው ኢትዮጵያም ከዚህ አደገኛ ጉዳይ ጋር ስሟ መነሳት ከጀመረ ዓመታትን ተሻግሯል። ተፈጥሮ ባደላት መልከዓ ምድር እና የአየር ሁኔታ ንጹህ ላባቸውን በሚያፈሱ አትሌቶቿ ስሟ ለዘመናት በድል ሲነሳ ኖሯል፡፡

ከ2010 ዓ.ም አንስቶ ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ የአትሌቶች አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት ምልክቶች በመኖራቸው የዓለም አቀፉ የጸረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ ትኩረት ከሚያደርግባቸው ሀገራት መካከል ልትመዘገብ ችላለች። ይህም በጥቂት አትሌቶች ተጠቃሚነት በተግባር ሊረጋገጥ በመቻሉ ሀገር አቀፍ የጸረ አበረታች ቅመሞች ንቅናቄ ተፈጥሮ ነበር። ከ2011ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ደግሞ ሦስት ሦስት አትሌቶች ተጠቃሚ መሆናቸው መረጋገጡን ተከትሎ፤ ቁጥሩ እንደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቢሆንም ከሌላው ዓለም አንጻር ከስጋት ቀጣና ሊወጣ ችሎ ነበር።

ነገር ግን ካለፈው ዓመት አንስቶ በአትሌቶች ዘንድ ያለው የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት በድጋሚ እያንሰራራ በመምጣት አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ሊባል ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ነገሩን ይበልጥ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ በወጣትና ተተኪ አትሌቶች ዘንድ በስፋት መስተዋሉ ነው።

በ2015 ዓ.ም ከተያዙ የቅመሙ ተጠቃሚ አትሌቶች መካከል 11 የሚሆኑት ፌዴሬሽኑ በሚያዘጋጃቸው ቻምፒዮናዎች ላይ የተሳተፉ ሲሆኑ፤ ይህም ተተኪ አትሌቶች ላይ የተደቀነውን አደጋ በግልጽ የሚያመላክት ነው። በተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው የሚደረግላቸውን ምርመራ ማለፍ የማይችሉ ታዋቂ አትሌቶች ቁጥርም በተመሳሳይ እያሻቀበ ይገኛል።

በዚህም ኢትዮጵያ በድጋሚ እንደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን በዓለም አቀፉ ተቋም በዓይነ ቁራኛ ከመታየት እንዳትላቀቅ አድርጓታል። ይህም እጅግ ጠንካራ ሥራ በማከናወን የተመሰከረለትንና ለሌሎች ሀገራትም ተምሳሌት የነበረው የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣንን ተግባር ጥያቄ ውስጥ የሚከትና ፌዴሬሽኑንም ስጋት ላይ የሚጥል ሆኗል።

በመሆኑም ተቋማቱ የአደጋ ጊዜ ደውሉን በመጫን ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ መሆኑንና መንግሥትም እጁን እንዲያስገባ ጠይቀዋል። ከግለሰብ አንስቶ እስከ መንግሥት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በመሆኑ ከምንጩ አጣርቶ የማያዳግም መፍትሔ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም። የአትሌቶች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ቁጥጥሩን አዳጋች ሲያደርገው የግንዛቤ ማነስ ዋነኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይጠቀሳል።

ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገርን እስከመወከል የደረሱ አትሌቶች ስማቸው ከዚሁ ጋር መያያዙ ግን እውነታውን አንጻራዊ ያደርገዋል። በማናጀሮች መሰልጠን መስፋፋት፣ የውጭ ሀገራት ሰልጣኞችን (የሌላ ሀገራት ዜጎች) ጨምሮ ማንነታቸው የማይታወቁ አትሌቶች እንቅስቃሴ፣ በአትሌቶች ዘንድ እያደገ የመጣው የተለያዩ ቫይታሚኖችን የመጠቀም ዝንባሌ፣ መድኃኒት መደብሮች የተከለከሉ አበረታች ንጥረ ነገሮችን በውስጣቸው የያዙ መድኃኒቶችን ያለማዘዣ በቀላሉ መሸጣቸው፣ በሀገር ውስጥ ምርመራውን ማድረግ የሚችል ቤተሙከራ ባለመኖሩ በሚፈለገው ልክ የአትሌቶችን ናሙና መውሰድ አለመቻል፣ ተጠቃሚነታቸው የተደረሰበት አትሌቶች የላላ የቅጣት ሥርዓት፣… የመሳሰሉ ጉዳዮች ሁኔታው እንዲስፋፋ ምክንያቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ ሰኔ 30/1999 ዓ.ም በልዩ ስብሰባ በአዋጅ ቁጥር 554/1999 በዩኔስኮ የጸደቀውን የጸረ አበረታች ቅመሞች ኮንቬንሽን ተቀብላ አጽድቃለች። ኮንቬንሽኑ 7 ክፍሎችና 43 አንቀጾችን የሚያጠቃልል ነው። በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 526 ላይም አበረታች መድኃኒትን የተመለከተ ሕግ ተቀምጧል። በዚህም መሠረት አበረታች መድኃኒቱን ያመረተ፣ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ የሸጠ፣ በባለሙያነት ያዘዘ፣ ያከፋፈለ እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ የተጠቀመና ሌላ ሰው እንዲጠቀም ያደረገ በቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ ከባድ ጉዳት ካስከተለ ደግሞ በ5ዓመት ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል ይላል። ይሁንና ከሀገር ክህደት የማይተናነሰው ይህ ተግባር በስፖርት ማኅበራቱ በሚጣል የዓመታት እገዳ ከመታለፍ ባለፈ በወንጀለኝነት ተጠይቀው እርምጃ የመውሰዱ ሁኔታ አለመለመዱ ስፖርተኞቹ ራሳቸውን እንዳያቅቡ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ይታመናል።

ሻምበል አበበ ቢቂላ ከቀዶ ጥገና መልስ በመሮጥ፣ ዋሚ ቢራቱ ውስጥ እግራቸው እየደማ በመወዳደር፣ ቀነኒሳ በቀለ እና ጎተይቶም ገብረሥላሴ በቅጡ ከኀዘናቸው ሳያገግሙ በዓለም አደባባይ በመወከል፣ ጥሩነሽ ዲባባ ሕመሟን ተቋቁማ በማሸነፍ፣ ጉዳፍ ጸጋይ እና ያለምዘርፍ የኋላው በጽናት በመዋደቅ፣ ሙክታር እድሪስ ከሕክምና መልስ ለአሯሯጭነት ገብቶ የወርቅ ባለቤት በማድረግ፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ስለሺ ስህን፣ ወርቅነሽ ኪዳኔ… የወርቅ ሜዳሊያ ሳያሳሳቸው አሳልፈው በመስጠት፣ … መስዋዕትነትን የከፈሉት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ክብር ነው።

ለሀገር ላብ ብቻ ሳይሆን ደምም እንደሚፈስላት ያስተማሩን አንጋፎች በተወሰኑ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች አሳፋሪ ተግባር ፈጽሞ ገድላቸው ሊጎድፍ አይገባምና አትሌቲክስን የሕይወት መንገዳቸው ያደረጉ ሁሉ ወርቃማውን ታሪካችንን ሊያበላሹ አይገባም፡፡

የስፖርት ተቋማትና ባለሙያዎች ኃላፊነት ብቻም አይደለምና የሚመለከታቸው ሁሉ እጃቸውን ከደሙ ሊያነፁ ይገባል። ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንስቶ የጤና ሚኒስትር፣ ትምህርት ሚኒስትር፣ የፍትህ አካላት፣ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ … የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ጉዳያቸው አድርገው ስለ ኢትዮጵያ ክብር የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ትልቅ መሆኑን ተረድተው በዚያ ልክ ሊሠሩ ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You