አስም ሳንባችን እና የትንፋሽ ቧምቧችንን ለረጅም ጊዜ አጥቅቶ የሚቆይ የበሽታ ዓይነት ሲሆን ከ100 ሰው አምስቱ በበሽታው ይያዛል።
ምልክቶች
የአስም ምልክቶች ትንፋሽ ማጠር፣ የደረት መጥበቅ፣ ሲተነፍሱ ማፏጨት እና ሳል ናቸው። እነዚህ ስሜቶች የሚመነጩት የመተንፈሻ ቧንቧችን ሲጠብ ወይም ሲቃጠል ነው። በአንዳንድ ሰዎች ላይ እነዚህ ስሜቶች በቋሚነት ሲከሰቱ ሌሎች ላይ ግን ህመሙ በሚነሳበት ወቅት ብቻ ያጋጥማሉ።
አስም እንዴት ነው የሚይዘን?
አስም በየትኛውም ዕድሜ ሊይዘን ይችላል። ለምን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ተከስቶ ሌሎች ላይ እንደማይከሰት እስካሁን አይታወቅም። አስም ያለባቸው ሰዎች የትንፋሽ ቧንቧቸው ለህመሞች ተጋላጭ ነው።
- ቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው አስም ካለው ሌሎች ላይ የመኖሩ ዕድል ከፍ ይላል፡፡
- የአስም ህመም በቀዝቃዛ አየር፣ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ እና በጭንቀት ሊነሳ ይችላል፡፡
- አለርጅን ተብለው የተጠቃለሉ በአካባቢያችን የሚገኙ ኬሚካል ይዘት ያላቸው ንጥረ ነገሮች ህመሙ እንዲነሳብን ያደርጋሉ፡፡
- የአበባ ዱቄት፣ የእንስሳ ጸጉር፣ አቧራ፣ አንዳንድ ምግቦች፣ ሽቶ፣ ሲጋራ ጭስ እና የመሳሰሉት ንጥረ ነገሮች አለርጅን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
- እነዚህ አለርጅኖች የትንፋሽ ቧንቧችን እንዲያብጥ እና የቃጠሎ ስሜት እንዲሰማው ያደርጋሉ። የበለጠ አክታ እንድናመነጭ እና የትንፋሽ ቧንቧ ጡንቻዎች እንዲጠብ ምክንያት ይሆናል። አየር በቀላሉ ማስገባት እና ማስወጣት አንችልም፡፡
- የደረት ኢንፌክሽን ያለባቸው ላይ ህመሙ ይጠናል፡፡
አስም ምን ያህል ሊያሳስበን ይገባል?
አስም በብዙ ጤና ባለሙያዎች እንደ ከባድ ህመም አይታይም። የህመሙ ስሜት ከባድ አለመሆን እና ህመሙን በቀላሉ መቆጣጠር የሚያስችሉ ህክምናዎች መብዛት ከባድ ህመም ተብሎ እንዳይፈረጅ ምክንያት ሆኗል። ቢሆንም ግን አስም በቂውን ክትትል ካላገኘ ኑሮአችንን ያውካል። አብዛኛው ሰው የአስም በሽታን ተቆጣጥሮ መኖር ይችላል። ነገር ግን በጥቂት ሰዎች ላይ በሽታው ለሕይወት የሚያሰጋ ሆኖ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ህመሙ ሲነሳ ወዲያው ክትትል ካላገኘ ከመክበዱ የተነሳ ሞት ሊከተል ይችላል።
አስም ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?
የአስም ህመም እየመጣ የሚሄድ ዓይነት ህመም ነው። የሚሰሙን ህመሞች ከጊዜ ጊዜ ይለያያሉ። ብዙ ሰዎች ዘንድ ህመሙ አልፎ አልፎ የሚመጣ ነገር ሲሆን አንዳንድ ሰዎች ግን በየቀኑ ይታመማሉ። የምናደርገው ህክምና የህመሙን ስሜት በማስታገስ አንድ የህመም ዙር ለተወሰኑ ሰዓታት ወይም ደቂቃዎች ብቻ እንዲቆይ ማድረግ ይችላሉ። ያለህክምና ህመሙ ለቀናት የሚቆይበት ሁኔታ አለ። አንዳንድ ልጆች ዕድሜአቸው ሲጨምር ህመሙ ይለቃቸዋል። አንዳንድ ሰዎች ህመሙ የሚጀምራቸው በተወሰነ የዓመት ወቅት ሲሆን ለረጅም ዓመታት ብቻ ወይም ሙሉ ሕይወታችንን ሊዘልቅብን ይችላል።
ህመሙን እንዴት መቆጣጠር ይችላል?
አስምን የሚያድን መድኃኒት የለም። ነገር ግን በሽታውን ለመቆጣጠር የሚረዱ መድኃኒቶች አሉ። ህመሙ ሲከሰት ስሜቱን የሚያስታግሱ መድኃኒቶች እና በህመሙ ወቅት ለመተንፈስ የሚረዳ «ኢንሄለር» በመጠቀም የህመሙን ስሜት ማስታገስ እንችላለን።
ምንጭ፡– Tenegna.Com
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ1/2011