አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻው የዕገታ ወንጀል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 61/177 እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 20 ቀን 2006 በመወያየት አንድ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ አጽድቋል። ድንጋጌው ‘Disappearance Convention’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ የሰው ልጅ በአስገዳጅ ሁኔታ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጣ ነው። ከሚያዝያ 23 ቀን 2010 ጀምሮ በሥራ ላይ ውሏል፡፡

በድንጋጌው መሠረት፤ ሰውን በአስገዳጅ ሁኔታ መሰወር ማለት፤ እስራት፣ በጥበቃ ሥር መዋል፣ ጠለፋ ወይም አፈና ወይም ማናቸውም ዓይነት የነፃነት መነፈግ ተግባር ነው። ነፃነትን የመንፈግ አድራጎት ሁኔታውን ለሌሎች ሰዎች አለማሳወቅን ወይም የታፋኞችን ወይም የተሠወሩትን ሰለባዎች ዕጣ ፈንታ ከሕጋዊ ጥበቃ ውጪ በመደበቅ ሰዎችን ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ፣ አስገድዶ መሰወር እንደሆነ ይቆጠራል፡፡

የአንድ ሰው መሰወር የበርካታ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት መሆኑንና የቤተሰቦችን መብቶች ጭምር የሚጥስ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ሆነ በሀገር የውስጥ ሕጎች ላይ በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፍጡርን የማገት አድራጎት ለየትኛውም ዓላማ ተፈጽሞ ቢገኝ በምንም ዓይነት አመክንዮ ሊደገፍ ወይም ቅጣቱ ሊለዝብ የማይችል ደረቅ ወንጀል ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 90 (1) ሥር በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል በአስገዳጅ ሁኔታ ሰውን መሰወር ይገኝበታል፡፡ የወንጀሉ ደረጃ ከባድና ከነ ጭራሹ አንዳች መንግሥታዊ ምህረትን ወይም ይቅርታን የማያሰጥ እንደሆነም ሕገ መንግሥቱ ላይ በማያሻማ ቋንቋ ተቀምጧል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር (Enforced Disappearance) ወንጀል እየጨመረ መጥቷል። የሰዎች በታጣቂዎች የመታገት ዜና እንግዳ መሆኑ ከቀረ ሰነባብቷል። ክስተቱም በተወሰኑ መጥፎ ዕጣ በገጠማቸው ሰዎች ላይ የሚከሰት ሳይሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እና በብዛት የሚያጋጥም ስጋት ሆኗል።

እንደ ሀገር ዕገታ ተፈጸመ ሲባል መስማት የተለመደ ወደ መሆን ተሻግሯል፡፡ የጭነትም ሆነ የሰው መጓጓዣዎች የዕገታ ሰለባ ስለመሆናቸው በሰፊው ይሰማል፡፡ ከኢንዱስትሪዎች እስከ ቤተ እምነቶች የዕገታ ወንጀል ተቃጣባቸው መባሉ ተለ ምዷል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከፋና ቴሌቪዥን ጋር አድርገውት በነበረ ቆይታ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ይህ ድርጊት ተባብሶ መቀጠሉን አረጋግጠዋል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅ እየተለመደ መጥቷል።

ከዕገታ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ለገንዘብ ወይም ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚውሉ ናቸው። የፀጥታ መዋቅሩን በገንዘብ በመደለል የራሳቸውን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚያደርጉ ግለሰቦች አሉ፤

ወንጀሉ በመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ግለሰቦች ተሳትፎ የሚያደርጉበት መሆኑን ተደጋግሞ የሚነሳ ነው። ይህም ወንጀሉን ለመከላከል የሚደረገውን ሂደት ፈታኝ እንዳደረገው መገንዘብ ይቻላል። ሌላው የዕገታ ድርጊቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ላይ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ሰዎች የእገታ ሰለባ እስከመሆን ደርሰዋል። በሚታገቱበትም ወቅት ባገታቸው አካል የመብት ጥሰት፣ ጭካኔ የተሞላበት አዋራጅ አያያዝ ወይም ቅጣት ይደርስባቸዋል። እንዲሁም ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባሉ ሰዎች ሕይወታቸው እስከማለፍ ደርሷል።

በዚህም ዜጎች ደህንነት እንዳይሰማቸው፤ በነፃነት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን እንዲቸገሩ እና ኑሯቸው ስጋት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል። በተጨማሪም ድርጊቱን የሚፈጽሙት ሽፍቶች ከመከላከያ ወይም ከፖሊስ ጋር ፊት ለፊት የሚታኮሱ አይደሉም። ተደብቀው ሕዝብ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ስለሆኑ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎታል።

ይሁንና ፌዴራል ፖሊስ ሆነ መከላከያ የኅብረተሰብ ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር ኃላፊነቱን ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የሚካድ አይደለም። በዚህም የጸጥታ አካላት ወንጀሎቹን ለመከላከል በቅንጅት ውጤታማ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ በተጨባጭ አሳይተዋል።

ለምሳሌ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ክስተት እናንሳ። የሀገር መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ገጹ አንድ መረጃ ይፋ አደርጓል። መነሻውን ከአዲስ አበባ በማድረግ ወደ ደዱ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ ሀገር አቋራጭ አውቶቡስ በሆሮ ጉድሩ ሀቦቦ ከተማ በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ታግቶ ነበር። የሀገር መከላከያ ሠራዊት ባደረገው ተጋድሎ ተሽከርካሪውን ጨምሮ ሰዎችን ማስለቀቅ ችሏል።

ይህን ጠቀስን እንጂ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ተከታትሎ በመያዝ ተጠያቂ ሲሆኑ አይተናል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ወንጀሉ እየተስፋፋ ካለበት ደረጃ አንጻር ገናብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ መገመት የሚከብድ አይደለም። ወንጀሉን የመከላከል እና መቆጣጠር ተግባር የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ፣ ቁርጠኝነት እና የጋራ ርብርብ ይጠይቃል።

በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተቀመጠው የወንጀሉ ደረጃ ከባድና ከነ ጭራሹ አንዳች መንግሥታዊ ምህረትን ወይም ይቅርታን የሚያሰጥ አይደለም። በዚህ የወንጀል ድርጊቱ ተሳትፎ የሚያደርግን ማንኛውንም አካል መንግሥት ለሕግ ማቅረብ ግዴታ አለበት። የጸጥታ መዋቅሩንም በመፈተሽ ውስጡን ማጥራት ይጠበቅበታል። ለዚህ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም።

የፌዴራል መንግሥት ሆነ የክልል የጸጥታ አካላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈጸሙ እገታዎችን ለመከላከል የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉ፤ ኅብረተሰቡም መንግሥት ወንጀሉን ለመከላከል እና በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት ሊደግፍ ይገባል። ወንጀሉ በሚፈጸምበት ጊዜ ድርጊቱ የተፈፀመባቸው ግለሰቦች መረጃውን በሰዓቱ ለፖሊስ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ወንጀለኞችን ተከታትሎ የመያዝ ጥረቱን አስቸጋሪ እንዳይሆን ያደርገዋል።

በአጠቃላይ ድርጊቱ « እቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም » እንደሚባለው በተለያዩ አካባቢዎች ብቅ ብቅ እያለ የሚገኘውን የዕገታ ድርጊት መንግሥት በፍጥነት መቆጣጠር ካልቻለ፤ የወንጀሉ መስፋት በማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰ ካለው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና አልፎ በሀገር ገጽታ ላይ ከፍተኛ የሆኑ ተጽእኖ መፍጠሩ የማይቀር ነው።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን የካቲት 20 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You