የዓድዋ ዘመን የአንድነት መንፈስ – ስለምን ተሸረሸረ?

ኢትዮጵያ ምንም እንኳ በራሷ ተነሳሽነት አንድን ሀገር ለመበደል አሊያም ለመውረር ስትል ጦር ሰብቃ ባታውቅም፤ ብዙዎቹ ሀገራት ግን ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር ድንበሯን ደጋግመው ማንኳኳታቸው አልቀረም፡፡ በተለያየ ጊዜም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች መደረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ለሙከራዎቹ ሁሉ ተገቢ ምላሾች በጀግንነት የተሰጡ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ አይነኬ ሆና ቆይታለች፡፡

ለዚህ ትልቁ ማሳያ እና የጥቁር ሕዝቦች ያለመሸነፍ ጽኑ መሠረት የሆነው የዓድዋ ድል ነው፡፡ ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው ዓድዋ በራሱ የቆመ ታላቅ ጀብድ ነው፡፡ ይህ ታላቅ ጀብድ አምሳያ አለው ተብሎ አብነት ሊቀርብለት አይችልም፡፡ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት ነጭ በጥቁር ተሸንፏል፡፡ በእስካሁኑም ሒደት እሱን ማሳያ ድል የትም አልተደገመም፡፡ ይህ ደግሞ የማይታበል እውነታ ነው፡፡

የዓድዋ ድል፣ ጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ ‹‹ለካ ነጭንም ማሸንፍ ይቻላል!?›› ያስባለ ነው፡፡ ብርቱዋንም ኢትዮጵያ ተከትለው ከተጠፈነጉበት የቅኝ ግዛት ውስጥ ሰንሰለታቸውን በጣጥሰው ቀስ በቀስ ነፃነታቸውን ማወጅ የቻሉበት ታላቅ ድል ነው፡፡

ይህ የኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል፣ በአጼ ምኒልክ ዘመን ተከስቶ በኢትዮጵያውያን ትብብር የተገኘ ታላቅ ድል ሲሆን፣ ይህ የኢትዮጵያውን ጀብድ ግን እዚያው ዘመን ላይ የቆመ አይደለም፡፡ ከዚያን ጊዜ በኋላም ኢትዮጵያን በተለያየ ጊዜ ለመውረር የቃጡ ሀገራት አልታጡም፤ ይሁንና በየዘመኑ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊዳፈር የመጣን ወራሪ ሁሉ ሕዝቧ በተለመደው ወኔ እና በሀገር ወዳድነት መንፈስ ተነሳስቶ ድል እያደረገ እዚህ ላይ መድረስ ችሏል፡፡

ዓድዋ፣ ብዙዎች እንደሚያውቁት የትብብር፣ የኅብረትና የአንድነት ምሳሌ ነው፡፡ ዛሬስ? ኢትዮጵያውያኑ የዓድዋ ልጆች ናቸው ማለት ይቻላልን? ከሆኑስ ስለምን አንድነታቸውን ማስጠበቅ አቃታቸው? ስለምንስ እርስ በእርስ መግባባታቸው ተሳናቸው? ስንል ካነጋገርናቸው የታሪክ ተመራማሪና ምሁራን አንዱ የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የዓድዋ ልጆች መሆን ያቃተን በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው የዓድዋን ድል እንደ ባለቤትነት አለመውሰድ፣ አለመያዝ እና አለመቀበል ያመጣው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከአንድነት ይልቅ የእኔነት መንፈስ በመጉላቱ ነው፡፡

ይህን በማሳያነት ሲጠቅሱ እንደሚሉት፤ ለአብነት ያህል በዓድዋ ጊዜ አንድነትና ኅብረት እንደነበረው ዛሬ ላይ ያለመታየቱ ምስጢር የትብብር አለመኖር ነው። በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የውጭ ጠላት መጣ፤ ያንን የውጭ ጠላት ደግሞ «ሀገሬን አላስደፍርም» በሚል የክተት አዋጅ ታወጀ፤ በዚያን ሰዓት ከሁሉም አቅጣጫ በመምጣት ጠላትን ድል ማድረግ ተቻለ፡፡ በዚያ የአብሮነት ድርጊታቸውም ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ እንዳላቸው ማስመስከር ቻሉ፡፡

አንድነት ላለመኖሩ ዋና ችግር እርስ በእርሳችን ያለመስማማታችንና ያለመግባባታችን ጭምር ነው የሚሉት አየለ (ዶ/ር) የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ መሰማራታችን እና ታሪካችንን በአግባቡ ያለመገንዘባችን ያመጣው ነው ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ ምክንያቱም ታሪካችንን በአግባቡ ብንገነዘብ ኖሮ ቶሎ ወደእርቅና ወደሰላም ብሎም ወደመግባባት እንመጣ እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት እያየን ያለነው ሽኩቻ ነው፤ ይህ ሽኩቻ ደግሞ የግል ጥቅም ከማሳደድ ፍላጎት የመነጨ እንጂ የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም ይላሉ፡፡

ሌላው በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የታሪከ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መምህር ሰማኸኝ ጋሻው ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ዓድዋ ከሰው ልጅ ታሪክ ታላላቅ የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም።

የሰው ልጅን የእርስ በእርስ ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት መልክ ካስያዙ ክስተቶች መካከል ምናልባት የታላላቅ ሃይማኖታዊ አስተምርሆዎች መነሳት በዋናነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖቶቹ በአስተምርሆዎቻቸው የሰው ልጆችን እኩልነት በመርህ ደረጃ ማስተማር መቻላቸው ነውና ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንን አንድ ከሚያደርጉን ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ ዓድዋ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ነገር ግን የዓድዋ ዘመን ትውልድ የአንድነት መንፈስ በዛሬው ትውልድ ላይ ጎልቶ አይታይም፤ ይህ ደግሞ የራሱ መሠረታዊ ምክንያቶች አሉት፡፡ በእርግጥ የዛሬው ትውልድም በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳለው በተለያዩ ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ በተግባር አሳይቷል። በቅርቡ እንኳ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ አሰጣጥ ላይ አንድነቱን በሚገባ ማሳየቱና እያሳየም እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ያልተለመዱ፤ ለአብሮነታችን እንቅፋት የሚሆኑ ድርጊቶች ሲከሰቱ መታየታቸውን መምህር ሰማኸኝ ይናገራሉ፡፡

ዓድዋ የጋራ አምድ እንደመሆኑ መጠን እንደ ዓድዋ ጀግኖች አባቶቻችን የአንድነት ማሰሪያ ፅኑ ቃልኪዳን ልናደርገው ይገባ ነበር ሲሉ በቁጭት የሚገልጹት መምህሩ፣ ነገር ግን በፊት ለፊት ጦርነት ዓድዋ ላይ የተሸነፉት ኢምፔሪያሊስቶች ስልታቸውን በመቀየር ሊያግባባን በማይችል የፖለቲካ ሪዕዮትዓለም ውስጥ ከትተውናል ይላሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት፤ በሽንፈታቸው ጥርስ የነከሱት አውሮፓውያን፤ ኢትዮጵያን በምን መልኩ ማፍረስ እንደሚችሉ ዘዴ ከመፈለግ አላረፉም ነበር። ለምሳሌ ባሮን ፕሮቻዝካ የተባለው ጸሐፊ “Abys­sinia: The Powder of Barrel” በተሰኘውና በእ.ኤ.አ በ1935 ባሳተመው መጽሐፉ፤ ኢትዮጵያውያን አንድ እንዳይሆኑ አዳዲስ የሀሰት ትርክቶችን ጠቅሷል። ከነዚህ መካከል የ«ብሔር» ጭቆና እንደነበር፤ ሀገሪቱም ቅኝ መገዛት እንዳለባት፤ ነባር ተቋማት በጠላትነት እንዲፈረጁ አቅጣጫ ሰጥቷል። እንዳለመታደል ሆኖ የ1960ዎች ትውልድ ይህንን የተዛባ ትርክት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ማዕዘን አድርጎ አስቀጠለው፡፡ ይህም ዛሬ ያለንበትን ፖለቲካዊ ስብራትን ፈጠረ፡፡

በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን ጦር መዝዞ የመጣውን ኃይል ቀደም ብሎ ዶጋሊ ላይ በመቀጠል ደግሞ ዓድዋ ላይ ፊት ለፊት ተጋፍጠን ማሸንፍ ቻልን እንጂ፤ መልኩን ቀይሮ በእኛ ሰዎች በኩል የመጣውን የቅኝ ገዥዎች ድብቅ ሴራ ማሸነፍ አልቻልንም ሲሉ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ የዛሬው ትውልድ እንደ ዓድዋ ትውልድ በተሟላ መልኩ በአንድነት እንዳይቆም እንቅፋት የፈጠረበት ይመስልኛል ሲሉም ያስረዳሉ።

መምህር ሰማኸኝ፣ የዛሬው ትውልድ እንደ ዓድዋ አባቶች መሆን ያልቻለው በአስተሳስብ ጦርነት መሸነፉ ነው ይላሉ። የግንባር ጦርነቱን በድል ከተወጣ በኋላ ፖለቲካዊ አይዶሎጅካል ጦርነቱን ግን ተሸንፏል።ትውልዱ የራሱ የሆነ ሀገር በቀል ፖለቲካዊ ተቋማትን ከመገንባትና ከማጠናከር ይልቅ በዴሞክራሲ ሽፋን የተመረዘ «አብዮታዊ» ዴሞክራሲን ተከለ። ይህ መልካም የሚመስል ግን ደግሞ አደገኛ የሆነው እሳቤ ተቋማዊ ቅርፅ በመያዝ መሠረታዊ የአብሮነትን መርህ ማናጋት ቻለ ሲሉም ይናገራሉ።

መፍትሔው ሊሆን የሚችለው ከዚህ አንጻር ብዙ ሥራ መሥራት ነው የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰር (ዶ/ር) አየለ፣ የቀድሞ ታሪካችንን ወጣቱ በአግባቡ ይረዳው ዘንድ ግንዛቤ ማስያዝ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በዓድዋ ጦርነት ጊዜ ድል ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ሁሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ የመጡና የተለያየ ብሔር እና ሃይማኖት ያላቸው ሲሆኑ፣ የተዋደቁትም ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታቸውንም በሚገባ የተገነዘቡ ዜጎች ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረው የኢትዮጵያዊነት ግንዛቤ ዛሬ ላይ ግን የተሸረሸረ ሆኗል፡፡ ይህ ጉድለት በመሆኑ መሟላት ያለበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመንግሥት የሚጠበቀው የሀገር ፍቅርን የሚቀሰቅስ፣ የሚያፈልቅና የሚያመነጭ አቅጣጫን ሁል ጊዜ መስጠት መቻል ነው፡፡ በተለይ ዜጋው ከእርስ በእርስ ጦርነት የሚወጣበትን መንገድ ማበጀት የግድ ይላል፡፡ ይህንን የእርስ በእርስ ግጭት አካሔድ ማስቆም ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው። እንዲህ ሲባል ጉዳዩ የመንግሥት ብቻ ነው ማለት ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሰላም መስፈን ማሰብ እንዳለበት ሊዘነጋ አይገባም ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር) ለሁሉም የምትበቃ መሆኗን ይገልጻሉ፡፡ በመካከል ልዩነት የሚኖር ከሆነ ያንን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ተገቢነቱ ላይ አጽንኦት ሰጥተው፤ ይህም በመወያየትና በመነጋገር ሊከናወን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ልዩነትን ለመፍታት መሞከርም ትልቅነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መምህር ሰማኸኝ ልክ እንደ ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ (ዶ/ር) ሁሉ እርሳቸውም ወደ አባቶቻችን የአብሮነት ስሜት ለመመልስ ከተፈለገ መነጋገር፤ መወያየትና መደማመጥ ያስፈልጋል ይላሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ሰው ከስሜትና ሆደ ባሻነት መላቀቅ ይኖርበታል። መንግሥትም ሕዝብ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሰከነ መልኩ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ግዴታው ነው ብለው እንደሚያስቡ አብራርተዋል።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ታሪክን የምንመረምር ካለፈው ድርጊታችን ትምህርት ለመቅሰም ነው። ሰዎች በግለሰብም ይሁን በማኅበረሰብ ደረጃ የታሪካዊ ክስተቶች ድምር ውጤት ናቸው። ሀገርም እንዲሁ የታሪኳ ድምር ውጤት ናት። እንደ ሀገር ካለፉ ድርጊቶቻችን ትምህርት የማንወስድ ከሆነ የከፋ አደጋ ሊገጥመን ይችላል። በእርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ ያውቃል፤ ዛሬ የገጠመውንም ከዓድዋ ጀግኖች በወረሰው ጥበብ ይሻገረዋል የሚል እምነት አላቸው።

በመሠረቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተጋጭቶ አያውቅም። መሪዎቹ ግን በተለያዩ የውጭና የውስጥ ግፊቶች ምክንያት ሽኩቻ ውስጥ ይገባሉ። በዓድዋ ጦርነት ወቅት፤ ጣሊያን ትከተለው በነበረው የማግባባት ፖሊሲ ምክንያት በትግራይና «መረብ ምላሽ» አካባቢ የነበሩ ገዢዎች ጣሊያንን ሊተባበሩ ሞክረው የነበረ ቢሆንም፤ የጣሊያንን መሰሪ አካሄድ በመገንዘብ ከወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ ጋር ታርቀው ጠላትን በጋራ ተጋፈጠው ድልን አውርሰውናል ይላሉ።

ዛሬም ቢሆን ሕዝብ እንደ ሕዝብ አልተጋጨም። የችግሩ ምንጭ ዓድዋ ላይ ያሸነፍናቸውን ቅኝ ገዥዎችን ሥነ ልቦና ከወረሱት ጥቁር ኮሎኒያሊስት «ምሁራን» ነው። እነርሱም የፖለቲካ ስብራታችን ውጤቶች እንደሚመስሏቸው ተናግረዋል፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ አንድነታችን መጠበቁ አይቀሬ ነው የሚሉት ደግሞ ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ነገር ግን ብዙ መስዋዕትነት ያስከፍላል፡፡ ያንን መስዋዕትነት ከመክፈላችን በፊት እኛው ራሳችን ለአንድነታችንም ሆነ ለሰላማችን ዘብ መቆም አለብን ይላሉ፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ዋጋ አስከፍሎን ከመምጣቱ በፊት ግን ከወዲሁ አንድነታችንን ብንጠብቅ ተመራጭ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድነት መጠበቁ አይቀርም።

እንደ እርሳቸው ግምት እና አስተሳሰብ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሰላም ሀገሩን ለመገንባት እና ሀገሩን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያልምና የሚጥር ነው። እንደዚህ ዓይነት ኢትዮጵያዊ መኖሩ የሚታበል አይደለም፡፡ ስለመኖሩ ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ሁሉም ጨለማ ነው ብሎ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡

እንደ ታሪክ ምሁራኑ አባባል ከሆነ፤ መልካሙ ነገር እንዲመጣ ሰላም እንዲሰፍን ዳር ቆሞ መጠበቅ ግን አያዋጣም፡፡ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ለሰላም ያለውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ አንድነቱና ኅብረቱ ይመጣ ዘንድም ኃላፊነት ወስዶ የድርሻን መወጣት ያስፈልጋል። ዜጋው፣ በጦርነት የሚመጣ ሰላም እና አንድነት እንደማይኖር መረዳት ይጠበቅበታል፡፡ ምክንያቱም ጦርነት መልሶ ቁርሾ ውስጥ የሚከትና ቂም የሚያሲይዝ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ እየበጠበጠን ያለው ከ30 እና ከ40 ዓመት በፊት የተቋጠሩ ቂሞች ናቸውና እዚህ ላይ ብልሆች ልንሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ትዕግስት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

አስቴር ኤልያስ

 አዲስ ዘመን የካቲት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You