የነገሥታት ልዩ ምናባዊ የመልዕክታት መድብል ለዛሬው ተመካካሪ ትውልድ

ሀ- ግዕዝ

ስመ መንግሥቴ ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ እጓለ አንበሳ፦

የምትወደኝና የምወድህ የሀገሬ ሕዝብ ሆይ ዛሬ የምነግርህ ታላቅ ነገር አለኝና ልብ ብለህ ስማ። ለብዙ ዘመን ለማንና መች እንደምነግረው ቸግሮኝ ስኖር ይኸው ዛሬ የልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ ሆነና የልቤን ቋጠሮ የምተነፍስበት ጊዜ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ውጥኔ እንዳይጨነግፍ፣ ሕልሜም መና እንዳይቀር እሸሻለሁ፡፡

በሀገሬ ትናንት የተቸገርኩበት ችግር ዳግም እንዳይመጣ፣ አንድ አድርጎ የሚመራት መሪ ለመሆን ናፍቄ ያ ትንቢት የተነገረለት ሣልሳዊ ቴዎድሮስ የመኾን መሻቴ በልቤ ቢያይልም ስመ መንግስቴን በስሙ አደረኩ፡፡ ግን የፈጣሪ ፈቃድ አልነበረምና ሩቅ ሐሳቤ በአጭር ቀረ፡፡ ዛሬ በንጹሕ ልቦና በሀገር መውደድ ስሜት ሆናችሁ የመመካከር ጉባዔ በሀገሩ ፈጥራችሁ በልዩነታችሁ ደምቃችሁ በአንድ ሐሳብ አስባችሁ፣ በአንድ ልብ መክራችሁ ሀገራችሁን ልትታደጉ ይገባል፡፡

ዛሬም እንደ ጥንቱ አዋጅ አሳውጃችሁ፤ ነጋሪት አስጎስማችሁ፤ ለዓለም መንግስታት እንደየቋንቋቸው የተቋሰልኩበትን ታላቅ ሀገር የመገንባት ሕልሜን አሳክታችሁ የአንድነታችሁን ጦማር ለዓለም የምትሰዱበት ምስጢርን እውን አድርጉ፡፡ ይህ የሚኾነው በመመካከር እና ፍትህና ዲሞክራሲን ስታነግቡ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገሬ የምትመራው በጦር አይሁን፡፡ በፍቅር፣ በጥበብ፣ በዕውቀትና በሥልጣኔ አድርጉት፡፡

በመልካም መሪነታችሁ ሳይቀሰቀስ የሚነቃ፣ ገና ሳይታዘዝ ወዴት የሚል ሕዝብን አፍሩ፡፡ ዛሬም የቴዎድሮስ ደም አልደረቀም፣ መንፈሱም ከግዛቱም አልተለየም እንድል ሕልሜን ከመጽሐፍ ፊደል ገዝፎ፣ ከቃል ረቆ፣ በሀገሬ ሰማይ ላይ እንደደመና ረቦና እንደቀስተ ደመናም ደምቆና በመላው ዓለምም እንዲታይ አድርጉ፡፡

እኔም በነፍሴ ዓለም ሆይ እወቂ ዛሬ የሀገሬ ትንሳኤ ነው፤ ከዛሬ በኋላ እንደግመል ሽንት ወደ ኋላ መጓዝ የለም፡፡ እንደቀደመ ታሪካችን እንገዝፋለን፤ እንደዛሬ አይደለም እንደትናንቱ ታውቁናላችሁ። ብርቱ ክንዳችን እንጂ የምጽዋት መዳፋችንን አታዩትም፡፡ እንደፊደላችን ርቀን እንዘምናለን። እንደአኀዛችን ጠልቀን እንቀምራለን፡፡ እንደኪነ- ጥበባችን አሸብርቀን እንዋባለን፡፡ የዕድገታችን መንገድ ይተለማል ብዬ የልቡናዬን መሻት ልምከር፡፡

ከራሴ በላይ በምወዳት ራሴን አሳልፌ በሰዋሁላት ውድ ሀገሬ ዛሬም እንዳልሞትኩና እንዳልተረሳሁ መኖር እፈልጋለሁ፡፡ የጋፋት የሥልጣኔዬ እርሾ የሚብላላበትና የመዘመን ሕልሜን በልጆቼ የማይበት ሀገርን እናፍቃለሁ፡፡ ጥንት እኔ ለመድፍ ደክሜአለው፡፡ ዛሬ የመንፈስ ልጆቼ እንደመድፍ ጠንክራችሁ፣ ሀገራችሁን የምትጠብቁ ሁኑ፡፡ ንጉሥ ቢሞት፣ ሕዝብ ቢያልፍ መንፈስ እንደማይሞት እኔና ይህ ትውልድ ምስክር እንሁን፡፡

የምወዳት ሀገሬ ኢትዮጵያ ትንሳኤዋን ከምድር ያይደለ ከላይ ከአባቶቼ አምላክ ከጸባዖት እንዲኾን እኔም እማልዳለሁ፡፡ በዚህች ታላቅ ሀገር ያላችሁ ሁላችሁ የአባቶቻችሁን መንፈስ እንደካባ ደርቡና ሀገር ታደጉ፡፡ ሕዝቤ ሆይ ልንገርህ በጦር ሜዳ መሸለል፣ በደጋፊዎች ድምጽ መመካት ዋጋቢስ ነው፡፡ ለፍትሕና ለርትሕ ስሩ፤ እንደዛ ሲሆን አንድነት ይነግሳል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ለሀገር የሚጠቅመው አንድነት ነው፡፡

ሀገሬ ሆይ ታስታውሺ የለ በመቅደላ ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ገጥሜ ሕዝቤን እንተባበር፣ አንድ እንሁን ብለው አሻፈረኝ አለ፡፡ የሞኝ ነገር በአንድ ሀገር ሁሉም መሪ ሆኖ ስልጣን ይጨብጥ ይመስል እኔንም የጎዳ እየመሰለው ሀገሩን በደለ። ሕቅታዬ ሲደርስ የልጄ እናት ጥሩወርቅ ‹‹እኔንና ልጅዎን ለማን ጥለው ነው የሚሄዱት›› ብላ አልቅሳ ብትለምነኝ ያንቺና የልዑል ዓለማየሁ ጉዳይ ኢምንት ነው አልኳት፡፡

ምክንያቱም በዛ መከራ ጊዜ እንኳን ሐሳቤና ጭንቀቴ ሁሉ ከነፍሴ በላይ ሳስቼ ለምወዳት አንዲት ሀገር ኢትዮጵያ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል እንደልቤ አልሆነልኝም፤ እንዳሰብኩት አልተሳካልኝም እንጂ። ያው ግራ ቢገባኝ፣ ልመናዋ አንጀቴን ቢበላኝ፣ ቢያጽናናትም ባያጽናናትም እናንተማ እንደሌላው ሕዝብ ትኖራላችሁ፤ ልጄ ሲደርስ አባቱን መጠየቁ አይቀርምና አድጎ ሲጠይቅሽ አንዲት ኢትዮጵያ፣ የተባበረች ኢትዮጵያ በዐይኑ እንደዞረች ቀረ ብለሽ ንገሪው ነበር ያልኳት፡፡

የደስታዬ ጥግ፣ የጸሎቴ መልስ የተባበረችና አንድ የሆነች ኢትዮጵያዬን፣ ሀገሬን፣ እምዬን ማየት ነበር፡፡ ከዚያም የእኔን አርአያነት ይዞ ራሱን ለመስዋዕትነት ለሀገሩ የሰዋው ወንድሜ ዮሐንስ የጀመረውን እና ምኒሊክም ከነጭ አሞራ ጋር ተናጥቆ ሀገሬን ዳር ድንበር አስክብሮና አጽንቶ ባየው መንፈሴ እረፍት አገኘች፡፡

ከዘመናት በኋላ ያ ሁሉ ለሀገር የተከፈለው መስዋዕትነት ጠይሞ የሀገር ፍቅርና አንድነት ቀስ በቀስ ብል እንደበላው ጨርቅ እየሳሳና እየነተበ ሄዶ ልዩነቶች ሰፍተው ሳይ ምነው የመመካከርና የመወያየት ባህላችን የት ጠፋ አልኩ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ጠቢቡ የፈጣሪ ፈቃድ የደረሰ ይመስለኛል፡፡

በሀገሬ ሰማይ ላይ ለዓለም የሚበቃ ተዓምር፣ ሁሉን የሚያነጋግር ዜና፣ ሁሉን ያስደመመ ድርጊት የሚፈጽም ከዚህ ትውልድ በመመካከር ይፈጠር ዘንድ ፍጹም ምኞቴ ነው፡፡ ሀገር የምትሰለጥነውና የምትጀግነው በተባበረ ክንድ፤ አንድ በሆነ የሕዝብ ልብና ውይይት እንደሆነ አውቃለሁና ልጆቼ ሆይ ምክሬን ስሙ፤ አንድ ኾናችሁም በመመካከርና  በመደራደር ሀገር አቅኑ፡፡

ሁ- ካዕብ

ስመ መንግሥቴ ራባዊ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ስዩም

እግዚአብሔር ወንጉሠ ጽዮን፦

እንኳን በዚህች ሀገር ተወለድኩ፡፡ እንኳንም ለዚህ ሕዝብ ኖሬ በመስዋዕትነት አለፍኩ። በየትኛውም ዓለም የማንም ዜጋ አድርጎ ያልፈጠረኝ ጌታ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ከኢትዮጵያዊ ተወልዶ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ፣ ለኢትዮጵያ ኖሮ መሞት ለካስ ክብርና ኩራት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ይሄን አበክረህ ታውቃለህ፤ እኔ የእግዚአብሔር የትህትና ደካማ እንጂ የሰው ደካማ እንዳይደለሁም፡፡ እውነት እውነት ነው የምልህ ጥንት በዘመኔ ባሳለፍኩት በአንዳች ነገር አልተቆጨኹም፡፡ በጊዜው ሁሉ በእጄ ነበር፡፡ በጌታ ፈቃድ ማድረግ የፈለኩትን ሁሉ በመንግሥቴ ለሕዝቤ የሚበጀውን አድርጌ አልፌአለው፡፡ በቃሌ አይደለም ሕዝቤም በጠላቶቼ ዘንድም የታመነ፣ የታፈረና የተከበረ እንደነበር ከአንተ ከምወድህና ከምትወደኝ ወገኔ የተደበቀ እንዳልሆነ አስረግጠህ ታውቃለህ። መንግሥቴን ለማቅናት፣ ሀገሬን ለመታደግ የከፈልኩት መስዋዕትነት ለሕዝቤና ለውድ ሀገሬ ቢያንሳት እንጂ አይበዛባትም፡፡

አንድ መሪ በመንግስቱ እንዲጸና፣ በሕዝቡ እንዲወደድ፣ በፈጣሪም እንዲታመን ምንም ሥልጣን በእጁ ቢሆን፣ ክንዱንም ኃያልና ብርቱ ቢያደርግ፣ ዕውቀትና ሀብትም ቢኖረው፤ ትሑት ልብ ከሌለው መንግስቱ አይፀናም፡፡ በታሪክም አይታወስም፡፡ ዘመኑም ቢረዝምም እንኳን ከሕዝብ ልብ ርቆ ነው የሚኖረው፡፡ ከሕዝብ የተፋታ መንግስት ትዳሩን የፈታ አባት ያህል ነው። ከሚስቱ ተለይቶ ከልጆቹ ተራርቆ የሚኖር ፈት ባል ማን ያከብረዋል? ቤቱን የበደለ መሪ ማን ቦታ ይሰጠዋል?

አሁንም በሀገራችን የፍትሕ መዛባት ድህነት፣ እርዛት፣ መከራ፣ ኋላ ቀርነት ዋና ጠላት ነውና ዛሬም እንደትናንቱ ኢትዮጵያ የተባለችው እናትህ፣ ዘውድህ፣ ሚስትህ፣ ልጅህና መቃብርህ ናትና እንግዲህ የእናት ፍቅር፣ የዘውድ ክብር፣ የሚስት ደግነት፣ የልጅ ደስታን እና የመቃብር ከባቲነት እንዲህ መሆኑ አውቃችሁ ሀገርን በጋራ ለመታደግ የሥራ፣ የልማት፣ የሰላም ዝናራችሁን አጥብቃችሁ ለዕድገትና ለሥልጣኔ የምትነሱበት ዘመን ዛሬ ይሁን፡፡ ያለፈው የመለያትና የጥላቻ ዘመን ይብቃ። ዛሬአችሁን ተጠቀሙበት። በዛሬአችሁ ለነገ የሚተርፍ ስራ ሰርታችሁ እለፉበት፡፡ በታላቅ ሀገር ላይ ታላቅ ስም ትከሉ፡፡ ከአባቶቻችሁ መሰረት አትናወጹ፡፡

ውድ ልጆቼ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያላችሁና ሕዝብ ለማገልገል አደራ የተቀበላችሁ ሁሉ በሥርዓት ሀገር ካልመራችሁ ምንም ብታተርፉ በሀገርና በሕዝብ ከከሰራችሁ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው፡፡ ከሕዝብ ተለይታችሁ ደብቃችሁ ያከማቻችሁት ሀብት ብትይዙ፣ ሥልጣን ላይ ብትቆናጠጡ፣ ዝናን ብታተርፉ ነዋያችሁ ባዶ በረሃ ላይ እንዳገኛችሁት በዋጋ የማትገዙበት፣ ለብሳችሁ የማትደምቁበት፣ ጠጥታችሁና በልታችሁ የማትረኩበትና ጥማችሁን የማትቆርጡበት ያህል ከሆንባችሁ ምን ይረባችኋል? ሰው ሆናችሁ፣ በሰው ልክ ኖራችሁ እንደሰው ከዚህ ምድር በሕዝብ ፍቅር መሸኘት የመሰለ ምን በረከት አለና? ዛሬ ለዚህ ክብር የሚያበቃ ስራ የምትሰሩበት ውጥን አዘጋጁ፡፡ በሕዝብ ታምናችሁ በመስራት ታሪክን የምትቀይሩበት መመካከርና የመወያት ዕድል በእጃቹ ነውና ተጠቀሙበት፡፡

የመንፈስ ልጆቼ ሆይ ሀገር ልትመሩ ልታሳድጉ የሚያስችላችሁ ነገር ሁሉ አላችሁ፤ ሁሉም ነገር በእጁ ሆኖ ሳለ ለምን ምንም እንደሌለው ትሆናላችሁ? ቀና ሕሊና፣ ትሑት ልቦና እና አፍቅሮተ ሕዝብ ገንዘብ አድርጉ፡፡ ፈጣሪ የመረጣትና የባረካት ሀገር ናት ያላችሁ ክፉ ልቦች መክረው አያፈርሷትም፡፡

በቃ ከዛሬ በኋላ ደስታን እንጂ የሚያስቆጭ ነገር አትስሩ፡፡ ለዕድገትና ለሥልጣኔ እንጂ ለውርደትና ለድህነት አትድከሙ፡፡ መሪዎች ሆይ ለሕዝቡ ነቅታችሁና ተግታችሁ በመስራት የሀገርን ብርሃን አብሩ፡፡ በመመካከር፣ በመወያየትና በመደራር በአንድነት፣ በፍቅር፣ በሰላም መኖር ሲባል ቀላል ቃላት እንዳይመስላችሁ ሐሳቡ ገብቷችሁ በአኮቴት ከተቀበላችሁ ተገብቷችሁ ትኖራላችሁ፡፡ ያ ሕይወት ደግሞ የገነት ያህል ናት፡፡ ልብ በሉ ሁሉም በእጃችሁ አለ፡፡ በጎ ነገርን በቅንነት ተጠቀሙበት፡፡ ይህን ማድረግና በእንዲህ ዐይነት ዕድል መጠቀም የመሰለ ታላቅነት የለምና፡፡

ሂ- ሣልስ

ስመ መንግስቴ ዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ፦

ከቀደሙ አባቶቼ ያወረሱኝን ሀገር ዳር ድንበሯን አስከብሬ ነጻነቷን ለዓለም አሳውጄ ያጸናሁት በዕውቀቴ፣ በገንዘቤ፣ በጉልበቴ ብቻ አልነበረም፡፡ እንደወደድኩት የወደደኝ ሕዝብ በማርያም ብዬ ብምል እንኳን መሀላዬን ተቀብሎ በፍቅር ከመንግስቴ ጎን ፀንቶ ስለቆመ ጭምር ነበር፡፡ በነበርኩበት የንጉሥና የንጉሠ ነገሥት ዘመን በሀገሬና በመንግስቴ ደስታዬ ፍጹም እንደነበር ፈጣሪዬና ሕዝቤ ምስክር ናቸው፡፡

ዕድሜዬን ሙሉ ከአባቶቼ ርስት ፈጣሪዬ ይሁን ብሎ በሰጠኝ ከቤተ መንግሥቴ የፈጣሪዬ በረድኤት ሳይርቀኝ፣ ከሕዝቤ ሳልለይ፣ የወደድኩት ሕዝብ ወዶኝና ወድጄ ሁሉም ዜጋ እንደአባቱ አይቶኝ እንጂ እንደባላንጣ ፊቱን ሳያጠፋብኝ፣ ክፉ ቃልም ሳይወጣው፣ በፍስኃና በሐሴት በተሞላ ዘመኔን ኖርኩ።

ውድ የምወድህና የምትወደኝ ሕዝቤ ሆይ ከምንም ጊዜ በላይ ዛሬ በዓላማህ ኑር፤ ዓላማህ ከተሰረቀ እንደእንስሳ በሥጋ ብቻ መኖር ምን ይበጃል? ዛሬ የሚፈለገው ዓላማ ያለው ብርቱ ታዳጊ፣ ዓላማ ያለው ሕልመኛ ወጣት፣ ዓላማ ያለው አርአያ ጎልማሳ፣ ዓላማ ያለው መካሪ ሽማግሌ ነው፡፡ በምንም ሚዛን ቢለካ ፍሬቢስ ያልሆነ፤ ባለመክሊት መነሻውን የተለመ፣ መድረሻውን ያወቀ፣ ሰው የሆነ፣ ለሰው የሚተርፍ ሙሉ ሰው፣ ንጹሕ ኢትዮጵያዊ የሆነ ነው ዛሬ ለዚህች ሀገር የሚያስፈልጋት፡፡

ታላቁ በሥጋና በመንፈስ ኃያልና ብርቱ የነበሩት አባቴ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ የሞቱት በዘመናቸው የነበሩት ባላባቶች አንዱ አንዱን ገድዬ በመብለጥ፣ በግዛቴ ላይ ሌላ ግዛት ደርቤ መንግስቴን አሰፋለሁ ሲሉ ላይረባ ነገር ብዙ ጀግኖች ተላልቀው ቀሩ፡፡ ልጆቼና ወዳጆቼ አሁንም እኔ በዘመኔ ሀገሬንና ሕዝቤን በፍቅርና በሰላም እንዳኖርኩ እናንተም በአንድነት ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ፡፡

ዛሬ እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ የዘመኔን የዐድዋ ጀግንነት በሥልጣኔና በዕድገት ጀብደኝነት ድገሙት፡፡ አልያ እንደአላዋቂ በተንኮልና በምቀኝነት እርስ በእርሳችሁ ተጋጭታችሁ ከተዳከማችሁና ከተፍረከረካችሁ የጠላት መሳቂያና መሳለቂያ ትሆናላችሁ፡፡ ሰላማችሁ እንዳይጎድል፤ ይህን ምክር ለእናንተ መስጠቴ ይጠቅማችኋል በሚል ነው፡፡ እኔማ በእግዚአብሔር ቸርነት ያን ያህል ዘመን ገዝቼ የለምን? ነገር ግን ሰውነኝና እንግዲህ ስንት ዘመን እኖራለሁ?

የመንፈስ ልጆቼ ሆይ በምወዳትና በምሳሳላት በኢትዮጵያ ሀገሬ ታላቅ በረከትና ፀጋ ተገብቷችሁ እንድትኖሩ በጋራ፣ በጥንቃቄ፣ በፍቅር፣ በሰላም ለመኖር ልትዘጋጁ ይገባል፡፡ ዛሬ የአባቶቼ አምላክ በቃሽ፣ ትንሳኤሽ ደርሷል የሚላት ጊዜ ይሁንላችሁ። ለዚህ ደግሞ በመመካከር፣ በመደራደር፣ በመዌት፣ በሰላም፣ በፍትሕና በርትሕ ልትኖሩ ይገባል፡፡

ሃ-ራብዕ

ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ

ከማንም በላይ በእልፍኛቸው አድጌ የላመ የጣመ ከማዕዳቸው ተቋድሼ በቤተ መንግሥታቸው ጥበብን ቀስሜ ያደኩበት የቅርቡ አባቴ ንጉሥ ሚኒሊክ ሰፊ ዘመን በፍቅርና በሰላም ታልፏል፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ከታሪካዊ የአድዋ ጀግንነት ጋር ይህችን ውድ ሀገር ለረዥም ዘመናት መርተው በፈጣሪ ፈቃድ ለእኛ ደረሰ፡፡ እኛም በዘመናችን ከአባቶቻችን የተቀበልነውን አደራ ለመወጣት የጀመሩትን በማበልጸግና አዳዲስ ተግባራትን በማምጣት ለሕዝባችን ሰፊ ልማት አበርክተናል፡፡ በአርበኝነት ተዋድቀናል፣ በትምህርት ከፍተኛ ተቋም መስርተናል፣ የአፍሪካን ሕብረት በመዲናችን በመመስረት በአህጉሩና በዓለም ላይ ደማቅ ታሪክ አስተይበናል….

እኛ በዘመናችን ንግሥናን ከሰው አናገኘውም፤ ከፈጣሪ ነው የሚገኘው ብለን በጽናት እናምን ነበር። በዘመናችን የበራላቸው ሀገር የሚታደጉ ወጣት መሪዎች ሲገጥሙን እንኳን ሀገራችን ላይ የመጣባት ፈተና መስሎን በራሳችን መንገድ ተወጣነው፡፡ ጥንት የእስራኤል አምላክ ሕዝብን እንደሚጠብቅ፣ በመልካም መንገድ እንደሚሰራ፣ የመረጠውን እንደሚያነግስ የዓለም ታሪክም እንደሚነግረን እናውቃለን፡፡ ዳሩ የዚህ ዓይነቱን እውነት ችላ ብንልም በድርጊታችን ስህተት አልጠፋብንም።

እኛም ምንም እንኳን በሀገራችን መልካም ነገር ብንሰራም ሰው ነንና ስህተት አላጣንም። የዛሬው ትውልድ በጋራ፣ በሰላምና በፍቅርና በመመካከር፣ በመወያየትና በመደራደር ኖራችሁ በዓለም ከፍ ያላችሁ የሕዝብ ምሳሌ ልትሆኑ ይገባል፡፡ ዘመናችሁ አንዳች ታሪክ ጠባሳ ሳታኖሩ ታሪኳን ልታድሱላት፣ ቁስሏን ልታክሙላት፣ ስብራቷን ልትጠግኑላት፣ ፍትሕ ልታሰፍኑ ተግታችሁ ስሩ፡፡ ፈጣሪ አሁንም ሕዝቡን መጠበቁና ዐይኑን ከሚወዳት ሀገር አለማንሳቱን ሕዝብ ሁሉ ለምስክር ልትበቁ ይገባ ዘንድ በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ ለመልካም ስራ ፍሬ ትጉ፡፡

ይህ በምግባርና በሥርዓት የሚታወቅ ሕዝብ እሴቱን ሳይለቅ፣ በደመቀ ታሪክ አሸብርቆ፣ ሀገሪትዋን ከውርደትና ከድቀት ለመታደግ በጋራ አንድ በመሆን የቀደመች የአባቶቻችንን ሀገር ዳግም ትሰሯት ዘንድ ዕድሉ በእጃችሁ ነው፡፡ ያሳለፍናቸው የጦርነት ታሪካችን ሀገር የሚወር፣ ሕዝብ የሚፈጅ ጠላት ሲመጣ ለሀገር ክብር ያደረግነው ነበር፡፡ ዛሬ ዘመኑ የትምህርት፣ የጥበብ፣ የሥልጣኔ፣ የብልጽግና እና እራስን አሸንፎ በመኖር በሚገኝ ድል ነው የበላይ ሆኖ መኖር የሚቻለው እንጂ ጋሻ በመመካት፣ ጦር በመምዘዝና ምንሽር በመተኮስ የሚመጣው ድል ጊዜው አልፎበታል፡፡

ይህ ትውልድ በንጹሕ ልቡ ተመካክሮ፣ ተወያይቶና ተደራድሮ ሕዝብ መርቶ ሀገር ሊያቀና የአባቶቹ አደራ አለበት፡፡ የተሻለች ሀገር ፈጥራችሁ ታኖሩበት ዘንድ ጊዜው አሁን ነው። ለዚህም ፍትሓዊና ሰላማዊ የኾነ ምክክርና ድርድርን ገንዘብ አድርጉ፡፡ ፍትሓዊና ሰላማዊ የኾነ ምክክርና ድርድርን ገንዘብ አድርጉ!።

መኩሪያ አለማየሁ

አዲስ ዘመን የካቲት 19/2016

Recommended For You