የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ ባለፈው ሳምንትም ስድስተኛውን ዙር የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሀ ግብር አካሂዷል፡፡በዚህም 66 ኩባንያዎች በፕላቲኒየም፣ 165 ኩባንያዎች በወርቅ፣ 319 ኩባንያዎች ደግሞ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፤ ባለፉት አራት ዓመታት በታማኝነት ከፍተኛ ግብር በመክፈላቸው ተሸላሚ የሆኑ 20 ኩባንያዎች ደግሞ ልዩ ተሸላሚ በመባል ተሸልመዋል።
በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የታማኝ ግብር ከፋዮች ሽልማት ተቋዳሾችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል፡፡‹‹የዜግነት ግዴታችሁን ለመወጣት ያደረጋችሁት ቁርጠኝነት ምስጋና ሊቸረው ይገባል›› ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ግብር መክፈል ለታማኝ ግብር ከፋዮች ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ዐሻራ ማኖር ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ታማኝ ግብር ከፋዮች የኢትዮጵያን ክብር የሚያስጠብቁና ብልጽግናዋ እውን እንዲሆን የሚተጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ግብር የመሰብሰብ መጠንና የግብር ከፋዮች ቁጥር እያደገ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ይህን ገቢ ይበልጥ ለማሳደግና የሀገርን ግንባታ ለማፋጠን በታማኝነት ግብር የመክፈል ባሕል እየዳበረ ሊመጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡በግብር አሰባሰቡ ላይ እየታዩ ያሉ አዎንታዊ ለውጦች ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡በመንግሥት በኩል የገቢ አሰባሰብ አሰራር ማሻሻያን በማጠናከር ሌብነትን በመቀነስና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን በማስፋፋት ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥተው ጠቅሰዋል፡፡ወደ ግብር መረቡ ያልገቡትን እንዲገቡ በማድረግ እንዲሁም አዳዲስ የታክስ ዓይነቶችን በመተግበር፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመንና ታክስ በመሰብሰብ ሂደት የሚወጣውን ወጪ ውጤታማ በማድረግ፣ በፌዴራል ደረጃ ያሉትን የታክስ ማሻሻያ ሥራዎች ወደ ክልሎችም በማውረድና በክልል ደረጃ የሚሰበሰበውን ገቢ በማሳደግ የመንግሥትን የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመንና በማሻሻል፣ ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ከግብር የሚገኘውን ገቢ የመሰብሰብ እቅምን በማሳደግ አስፈላጊነት ላይ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባሮች ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ይታወቃል፡፡የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ ሚኒስቴሩ በ2015 በጀት ዓመት 442 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህ አሀዝ በ2016 በጀት ዓመት 512 ቢሊየን ብር ደርሷል፡፡የ70 ቢሊየን ብር ጭማሪ አለው ማለት ነው፡፡ቀደም ባሉት ዓመታት የተሰበሰበው ገቢም እንዲሁ እያደገ ነው የመጣው፡፡
መንግሥት በየዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ በመሰብሰቡም ሆነ ገቢ የመሰብሰብ አቅሙ እያደገ በመምጣቱ አልተኩራራም፡፡ለተገኘው ለውጥ በየዓመቱ እውቅና እየሰጠ ግብር የመሰብሰቡን አቅም እያሳደገ የበለጠ ገቢ መሰብሰብ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡
በሀገር ደረጃ ሰሞኑን የተካሄደውን እውቅናና በዚያው መድረክ ላይ ከግብር የሚገኘውን ገቢ ለመሰብሰብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸበት ሁኔታ እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ያስቀመጡት አቅጣጫም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡ሽልማቱ ተሸላሚዎቹ ብቻ እንዲበረታቱ የተደረገበት ሳይሆን ሌሎች ታማኝ ግብር ከፋዮች እንዲፈጠሩ የተሰራበትም ነው፡፡
የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሀ ግብሩ ግብር ከፋዮቹ በታማኝነት ግብር በመክፈላቸው የተመሰገኑበትና የተሸለሙበት ነው፡፡ከእዚህ ሽልማት ሌሎች ትምህርት እንዲቀስሙ መልእክት የተላለፈበትም ነው፡፡ በሁሉም የግብር ከፋይነት ደረጃ ግብር የሚከፍሉ አካላት ከዚህ አርአያነት ያለው ተግባር በመማር ገቢ ሳይሰውሩ ያገኙትን ገቢ ታሳቢ ያደረገ ግብር ወደ መክፈል እንዲገቡ፣ ሌሎች ግብር የማይከፍሉ አካላትም ካደፈጡበት ወጥተው ግብር የመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ይህ ሲሆን ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ገቢ የሚጠበቀውን ግብር መሰብሰብ መቻል ይጀመራል፡፡
መንግሥት እየተሰበሰበ ባለው ገቢ ረክቶ አልተቀመጠም፡፡ከግብር የሚሰበሰበው ገንዘብ በብዙ ቢሊየን ብር እያደገም መሰብሰብ ያለበትን ያህል ገቢ እንዳልተሰበሰበ ሁሌም ይገልጻል፡፡የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ነው፤ ሀገር ከሚያስፈልጋት ሀብትና ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት አንጻር ሲታይ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ በቂ አለመሆኑ አንዱ ነው፡፡ገቢ የመሰብሰብ ሥራው በላቀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ታምኖበት ሲሰራ የቆየውና ተጨባጭ ለውጥ እየታየ ያለውም በእዚህ መልኩ በመሰራቱ ነው፡፡
በቀጣይም በዚሁ መልኩ እንደሚሰራ መንግሥት አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ለእዚህም ግብር በመሰብሰብ በኩል ውጤታማ መሆን ያስቻሉትን ይዞ መቀጠል አንድ ነገር ሆኖ፣ ውጤታማ ያልሆኑት ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ በመፈለግ መሥራት፣ አዳዲስ መንገዶችንም መቀየስ ያስፈልጋል፡፡
ግብር መረብ ውስጥ ከገቡት የሚሰበሰበው ግብር ኢኮኖሚያቸው ከሚያመነጨው ሀብት አኳያ ሲታይ በቂ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡ በተለይ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ገቢን አሳውቆ ግብር በመክፈል በኩል ሊጠቀሱ የሚችሉ ታማኝ ግብር ከፋዮች ቢኖሩም፣ ጥቂት የማይባሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገቢ የሚደብቁበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል፡፡እነዚህ ግብር ከፋዮች ታማኝ ግብር ከፋይ እንዲሆኑ ማድረግም ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርበታል፡፡
ግብር ከፋዮች ታማኝ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ምንድነው ብሎ አጥንቶ ርምጃ መወሰድ ይገባል፡፡ይሄኔ ግብር ሰብሳቢው አካል በሚያሰማራቸው ሠራተኞች ታማኝነት ላይ የመሥራት አስፈላጊነት ይመጣል፡፡ብዙ ነገሮች እዚህ አካባቢ ሲበላሹ ነው የኖሩት፡፡ይህን ጉያ ውስጥ ይዞ ስለግብር በአግባቡ አለመሰብሰብ መናገር ትክክል አይሆንም፡፡
በእነዚህ ሁለት ወገኖች መካከል በሚፈጸም መሞዳሞድ ሀገር ብዙ ገቢዋን ስትቀማ ኖራለች፡፡ብዙ ሚሊየን ብር ግብር እንዲከፈል እየጠየቁ ይህን ያህሉን ሚሊየን ብር ከሰጠኸኝ ይህን ያህሉን አቅንስልሃለሁ ብለው ቀብድ ሲቀበሉ የተያዙ ግብር ተማኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ሌሎች በርካታ የመሞዳሞድ ዓይነቶችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡እንዲህ ዓይነቱን ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን አጥምዶ መያዝ፣ የሚወሰድባቸው ርምጃም ጠንካራና አስተማሪ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም ርምጃው ሌሎች እንዲማሩበትም በመገናኛ ብዙሃንንና በመሳሰሉት ላይ መገለጽ ይኖርበታል፡፡
አዳዲስ የግብር ዓይነቶችን ማምጣት ወይም ወደ ግብር መረቡ ያልመጡትን ማምጣት ሌላው በሰፊው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ርግጥ ነው ቀደም ሲል ግብር የማይከፍልባቸው ወይም ጥቂት ግብር ብቻ ይከፈልባቸው የነበሩና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግብር ይከፍልባቸው የጀመሩ እንደ መኖሪያ ቤት ግብር ያሉት አዳዲስ የግብር ዓይነቶች ማምጣታቸው አበረታች ተግባር ነው፡፡ከዚያም ቀደም ብሎ የቤት ባለቤቶች ከሚያከራዩት ቤት ግብር መሰብሰብ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
በዚህ ዓይነት መልኩ ግብር ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ በርካታ የንግድ፣ የአገልግሎትና የመሳሰሉት ሥራዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡እነዚያ ላይም መድረስ ያስፈልጋል። ሁለት ሺ ብር ደሞዝ የሚከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ግብር እየከፈሉ ብዙ ሺ ብር ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን የሚሰሩ ምንም ዓይነት ግብር የማይከፍሉበት ሁኔታ ብዙ ነው፡፡
ከዚህ መሰሎቹ ገቢዎች ላይ ግብር መሰብሰብ ላይ ገና ብዙም ባልተሰራበት ሁኔታ ሌሎች አዳዲስ ግብር ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ የሥራ ዘርፎች እየተወለዱ ናቸው፡፡ ዘመኑ የዲጂታል እንደመሆኑ በቴክኖሎጂ መኖሪያ ቤት ቁጭ ተብሎ የሚሰሩ ሥራዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ይነገራል፡፡እንደዚህ ዓይነቶቹ ሥራዎች ባደጉትና በማደግ ላይ ባሉት ሀገሮች ተለምደዋል፡፡ሥራዎቹ ባህር ማዶ ድረስ የተዘረጉና የውጭ ምንዛሬ የሚገኝባቸውም ናቸው፡፡ዜጎች በእዚህ ዓይነቶቹ ሥራዎች መሰማራታቸው ሊበረታታ ይገባል፡፡ከዚህ ገቢ ለሀገራቸው ግብር ሊከፍሉ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር ግን ይኖርበታል፡፡ ለእዚህም መንግሥት ባደጉት ሀገሮች እንዲህ ዓይነቱ ሥራ እንዴት ክትትል እንደሚደረግበትና ግብር እንዲከፈልበት ማድረግ እንደሚቻል አጥንቶ በኢትዮጵያም መተግበር ይገባል፡፡
እነዚህን ግብር ሊሰበሰብባቸው የሚችሉ የሥራ ዘርፎች አጥንቶ፣ አሰራር ቀይሶ ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ ላይ በስፋትና በትኩረት መሥራት ሲገባ ከግብር የሚገኝ ገቢን ለማሳደግ በስፋት የሚሰራበት ሥራ አንዴ ግብር መረብ ውስጥ በገቡት ላይ ጭማሪ ማድረግ ነው፡፡አንዱ ነጋዴ ተሞዳሙዶ ዝቅተኛ ግብር እንዲከፍል እየተደረገ፣ ሌላው ደግሞ ግብር መረብ ውስጥ እንዲገባ ባልተደረገበት ሁኔታ ግብር መረብ ውስጥ የገባው ነጋዴ ላይ ከልክ ያለፈ ጭማሪ እንዲከፍል የሚደረግ ከሆነ አሰራሩ ፍትሃዊ ካለመሆኑ በተጨማሪ ታማኝ ግብር ከፋዮችን ማማረርም ይሆናል፡፡ በዚህች ሀገር እየሆነ ያለው ይሄው ነው፡፡
በዚህ ዓይነቱ የግብር አሰባሰብ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ክፉኛ እየተጎዳ ነው፡፡እንዲህ ዓይነቱ ግብር ከፋይ ላይ መንግሥት ብቻም ሳይሆን የሚበረታው ግብር ተማኞችም ናቸው፡፡እነሱ ይብሳሉ፤ ጥቂት አይደሉም፡፡ጥቂት ቢሆኑ ጩኸቱ ብዙ አይሆንም ነበር፡፡
እነዚህ ግብር ከፋዮች ግብር ሲጨመርባቸው ወይ አቤቱታ ያቀርባሉ፤ አልያም ይከፍላሉ፡፡ሶስተኛው አማራጫቸው ከግብር ተማኞች ጋር ተሞዳሙደው ግብሩን ማስቀነስ ነው፡፡ይህ ችግር የነበረ፣ ያለ፣ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራበት በቀጣይም ሊኖር የሚችል የገቢ ጠንቅ ነው፡፡
በግብር ከፋዩ ላይ በየጊዜው የሚጫን ተጨማሪ ክፍያ ሀገሪቱን ግብር ተጨመረብኝ እያለ የሚያማርር እንጂ ግብር እንድከፍል ተጠየቅሁኝ የሚል ብዙም የማይሰማባት ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ይህ በስፋት እየተፈጸመ ባለበት ሁኔታ የግብር መሰረት ማስፋት ሥራ ተሰርቶበታል የሚያሰኝ ሁኔታ አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፤ የግብር መሰረት ሲሰፋም ነው የግብር ገቢ እየጨመረ የሚመጣው፡፡ የግብር መረብ እንዲሰፋ ሲደረግም የመጀመሪያው አላማ መሆን ያለበት ወደ ግብር መረብ ማምጣት መሆን ነው ያለበት፡፡ተያዘ ተብሎ እዚህም ላይ ግብር መቆለል ተገቢ አይደለም፤ ቀስ በቀስ ግብሩን መጨመር ይቻላል፡፡
በዜጎች ዘንድም ስር የሰደደ የግንዛቤ እጥረት ችግር አለ፡፡ግብር ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ተግባሮች ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡መንገዱም፣ ትምህርቱም ጤናውም ወዘተ ያለ ግብር ሊሰራ፣ ሊታደስ፣ የመንግሥት ሠራተኛውም ባለደሞዝ ሊሆን አይችልም። በመሰረቱ ዝም ብሎ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋም አይጠየቅም፤ በደረቁ የውሃ አገልግሎት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ወዘተ መጠየቅ የለበትም፡፡በኛ ሀገር ግን እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡ ግብር እንዲከፍሉ ሲጠየቁ ወገቤን ማለት፤ ግብር ሲጨመርብም እንዲሁ መታመም፤ መሰረተ ልማት ግን መጠየቅ፡፡
ግንዛቤው እያለም በግብር ጉዳይ ላይ ድብብቆሽ መጫወቱ ብዙም ነው፡፡የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ግብር እንዲከፈል የግድ የሚል ሆኖ እያለ፣ ሀገር ወደ ልማት እንድትገባ አስቀድሞ መሠረተ ልማት መዘርጋት ያለበት መሆኑን እየታወቀ የግብር ነገር ሲነሳ ፊት ማዞር ይስተዋላል፡፡‹‹አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንዲሉ የግብር መክፈልን ፋይዳ እየተገነዘቡ ግብር ለመክፈል ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው፣ ፍላጎት እንዲያድርባቸው በተለያዩ መንገዶች ተቀስቀሰውም፣ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸውም ወደ ግብር መክፈሉ ያልገቡ ጥቂት አይደሉም፡፡ለእዚህም ነው መንግሥት በእዚህ ላይ በስፋት እንዲሰራ እየጎተጎተ ያለው፡፡
በዚህች ሀገር ግብር መክፈል ሲገባቸው ጨርሶ የማይከፍሉ ሞልተዋል፡፡እነዚህ በአነስተኛ ንግድ ሥራዎች፣ በድርጅቶችና በመሳሰሉት ተቀጥረው የሚሰሩ ነገር ግን ምንም ዓይነት ግብር የማይከፍሉ፣ ቤት እያከራዩ የኪራይ ግብር የማይከፍሉ፣ በአንድ ምርት የንግድ ፈቃድ አውጥተው በተጓዳኝ ብዙ ነገሮችን የሚነግዱ፣ ወዘተ፣ ግብር ግን የማይከፍሉ በርካታ ናቸው፡፡
መክፈል ያለባቸውን ያህል የማይከፍሉትም ጥቂት አይደሉም፡፡እነዚህ ግብር ከፋይ ተብዬዎች ብዙ ገቢ እያገኙ ትንሽ እንዳገኙ አርገው ሂሳብ አሰርተው በማቅረብ መንግሥትን ያጭበረብራሉ፡፡ይህ ዓይነቱ ሕገ ወጥነት በትላልቆቹ የንግድ ድርጅቶች ሳይቀር የተለመደ ነው፡፡የሚያገኙት ገቢና የሚከፍሉት ግብር ጨርሶ እንደማይደራረስ ይነገራል፡፡
በተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈል ገንዘብ መንግሥት ዘንድ የማይደርስበት ሁኔታም ብዙ ነው፡፡ደረሰኝ ሳይቀበሉ ገንዘብ አይክፈሉ ቢባልም ክፍያው ያለ ደረሰኝ የሚፈጸምበት ሁኔታ እጅግ ብዙ ሆኗል፡፡ነጋዴዎቹ ደረሰኝ አልቆረጡም ማለት ተጨማሪ እሴት ታክስ አልሰበሰቡም ማለት አይደለም፡፡ሰብስበው ለራሳቸው ያውላሉ፡፡ በዚህም ለመንግሥት ገቢ መደረግ ያለበት ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ለሕገ ወጦች እየዋለ ይገኛል፡፡
ሀገሪቱ የምትሰበስበውን ገቢ ከትሪሊየን ብር በላይ ለማድረስ ታቅዷል፡፡ይህን ሁሉ ለማሳካት ሙሉ አቅምን ግብር መሰብሰብ ላይ ማድረግ ይገባል፡፡ በሀገሪቱ ግብር በስፋት ለመሰብሰብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ በተደጋጋሚ ተገልጸል፡፡በአጭበርባሪዎች ወይም ገቢ ደባቂዎች የተነሳ ያልተሰበሰበ፣ አዳዲስ የገቢ ምንጮችንና ከእነዚህ ምንጮች ገቢ አንዴት መሰብሰብ አንደሚቻል ባለማወቅ ሳቢያ ያልተሰበሰበ ሀብት ብዙ ነው፡፡
ከሌለ ነገር አይደለም ግብር መሰብሰብ የተፈለገው። ይህን ሀብት ለመሰብሰብ የሚያስችል አቅም መፍጠር ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚገልጸውም ዘንድሮም እንደገለጸው ይህን አቅም ማሳደግ ላይ ይሰራል፤ ግብር የመሰብሰብ አቅም የማሳደጉ ሥራ የራሱን የግብር ቀበኞች ቆርጦ እስከ መጣል ገቢ ሰዋሪ እንዳይኖር እስከ ማድረግ መዝለቅ የሚደርስ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሀገራችን በአፍሪካ ዝቅተኛ የግብር ገቢ ከሚሰበሰብባቸው ሀገሮች መካከል መሆኗ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ በግብር አሰባሰቡ እነዚህ ሀገሮች ላይ መድረስ ባይቻል እንኳ ለመቀራረብ መሰረት ይኖርበታል፡፡ የእነዚህ ሀገሮች ግብር አሰባሰብ ግብር በሚገባ ለመሰብሰብ ሌላ መነሻ ሆኖ ማገልገል ይችላልና ተሞክሯቸውን ቀስሞ መተግብርም ያስፈልጋል፡፡
ሀገር ለምታካሂደው ልማትና የመሳሰሉት ተግባሮች የውጭ ገንዘብ ሊገኝ ይችላል፡፡ ዋናው ሀብት ግን በሀገር የሚሰበሰበው ገቢ መሆኑ ስለመሆኑ ለዜጎች ማስተማር ላይ አጥብቆ መሰራት ይኖርበታል፡፡ ከውጭ የሚገኝ ሀብት አስተማማኝ ሊሆን ስላለመቻሉ ያለፉት ዓመታት የሀገራችን ተሞክሮ ያመለክታል፡፡
አስተማማኝ ገቢ ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ሊሰብሰብ የሚችለው ገቢ ብቻ ነው፡፡ ይህን ገቢ ዜጎችን በማስተማር፣ በማስገንዘብ፣ ግብር በታማኝነት ለከፈሉት ደግሞ በቅርቡ እንደተደረገው እውቅና በመስጠት ፣ ይህን እውቅና በየደረጃው አውርዶ ከትንሽ ገቢ ጥሩ ግብር ለከፈሉትም እውቅና በመስጠት ዜጎች በግብር አሰባሰቡ አምነው፣ ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑን ተረድተው ግብር በታማኝነት የሚከፍሉበትን አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም