የፍጻሜው ጅማሬ እውን እየሆነ ነው

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ተደጋግሞ ከብዙዎቻችን አንደበት የሚደመጥ አንድ ዓረፍተ ነገር አለ፤ ይኸውም “ሠላም ጠፋ!” የሚል ነው። በእርግጥም በሀገራችን ካሉ ጥቂት ከማይባሉ አካባቢዎች ውስጥ ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ቦታ ለማቅናት በመጀመሪያ ወደአዕምሯችን የሚመጣው ስለአካባቢው ሁለት ሦስቴ ማሰብና ቀጥሎም “እዛ አካባቢ ምን አለ? ማን አለ?” የሚል ጥያቄ እንደሆነ እገም ታለሁ።

“ምን” እና “ማን” የተባሉት አካላት ደግሞ በየአካባቢው መሣሪያ አንግተው የአካባቢውን ነዋሪ፣ ዘመድ ጥየቃም ሆነ ለግል ጉዳዩ ወደ አካባቢው የሚመጣውን፤ ከዛም አልፎ አካባቢውን አቋርጦ የሚያልፈውን ተጓዡ ሳይቀር አበሳ እያሳዩት ነው። የአካባቢው ነዋሪ በሠላም ወጥቶ በሠላም መግባት ብርቅ እንዲሆንበት እያደረጉ ነው።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ እንደሚያመለክተው፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት እንዳለው ይደነግጋል።

እነዚህ አካላት ለሕግ እና ሥርዓት ተገዥ የሆነ ማንነት የላቸውም። ዋነኛ ባሕሪያቸው ሽፍትነት ነው፤ ለዚህ ተራ ባሕሪያቸው ብዙዎችን አሰቃይተዋል፤ ገድለዋል፤ ዘርፈዋል፤ አሰጨንቀዋል። እትብታቸው ከተቀበረበት አካባቢ ጥለው እንዲኮበልሉ ምክንያት ሆነዋል።

እነዚህ ገድሎ/ዘርፎ አደር የሆኑ ኃይላት፤ የገዛ ሕዝባቸውን የእለት ተእለት ሕይወት ከማክበድ ባለፈ፤ በብዙ ዋጋ የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን አፍርሰዋል፤ እያፈረሱም ነው። በተጨማሪ ልማቶች እንዳይከናወኑ ፈተና እየሆኑ ነው። በዚህም ተግባራቸው ደግሞ ደስተኞች መሆናቸው በየወቅቱ ከሚያሰሟቸው ፉከራዎች እና ቀረርቶዎች መረዳት ይቻላል።

በርግጥ ለነዚህ ኃይሎች በአንድም ይሁን በሌላ፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አቅም የሆናቸው በእነሱ እኩይ ተግባር ሕይወቱ የተጎሳቆለው ሕዝብ ስለመሆን ለመገመት የሚከብድ አይደለም። በተራ ፕሮፖጋንዳው ብዙዎችን የዓላማቸው መጠቀሚያ ማድረግ ችለዋል። በዚህም እድሜውን ማራዘም ችሏል።

አሁን ግን ሁኔታው መልኩን እየቀየረ ነው፤ ሕዝቡ የቡድኖቹን እውነተኛ ማንነት መረዳት ከጀመረ ውሎ አድሯል። በዚህም ሠላምን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች የተሻለ ውጤት እያስገኙ ነው። በዚህም እየተገኘ ያለው አዎንታዊ ሠላም ሕዝቡ ከትናንት ዛሬ የተሻለ የሠላም አየር እንዲተነፍስ እያስቻለው ነው።

ይህንን አንጻራዊ ሠላም አስተማማኝ እና ዘላቂ ለማድረግ፤ ሕዝቡ የነዚህን ኃይሎች ማንነት በአግባቡ በመረዳት፤ አንድነቱን አጠናክሮ ለሠላሙ ዘብ መቆም ይጠበቅበታል። ሕዝቡ ለሠላሙ እርስ በእርስ መደጋገፍ ከቻለ የትኛውም አካል ሠላሙን ሊያውክ፤ አደጋ ውስጥ ሊከተው አይችልም ።

ሕዝቡ ስለሠላሙ መጠበቅ ያለበት ከቀበሌው ሊቀመንበር ወይም ደግሞ ከወረዳው ሠላምና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት፤ እልፍ ሲልም ከክልሉ የሠላምና የፀጥታ ቢሮ መሆን የለበትም። እያንዳንዱ ለአካባቢው ሠላም መስፈን የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት ይጠበቅበታል። በዙሪያው ያሉ ሠላም ነሺዎችን አምርሮ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል።

ገና ከጅምሩ፣ ከአንድ ገጠር ቀበሌ ተነስቶ ወደ አንድ ወረዳ የሚሔድን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ እዛው እበራችን ላይ ማስፈራራትና ማገት ሲጀምሩ ዝም! ያልነው ራሳችን ነን፤ መሠረተ ልማቱን ሲያበላሹና ዘርተን እንዳናጭድ እንቅፋት ሆነው ሲደነፉ ጭጭ! ያልነው እኛው ነን።

ይህ ነገር ውሎ አድሮ የራሳችንን ልጆች እንደሚሰለቅጥ መገመት የተሳነን ከእኛ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል? አሁን አሁን እንደልብ ወጥተን ማረስ፣ መዝራት፣ መጎልጎል፣ ማጨድና መሰብሰብ የተሳነን ሁኔታ ተፈጥራል። ልጆቻችንም ቢሆኑ ወደትምህርት ቤት ሔደው እንዳይማሩ ዕድሉ እየጠበበ መጥቷል።

ከዚህ በኋላ ለሠላማችን የምናባክናት አንዲትም ደቂቃ ልትኖር አይገባም። እስከዛሬ ድረስ በብዙ ቆስለናል፤ ይህ የደረሰብን ቁስል ወደማመርቀዙ ሔዶ መድኃኒቱ ከመታጣቱ በፊት ከሠላማችን ጋር ልንስማማ ይገባል። ለሠላም ዘብ የቆሙ ወንድሞቻችንንና ልጆቻችንን ማገዝ ይጠበቅብናል።

ሠላም ከምንም ነገር በላይ ነው። አምርተን እንዳንበላ እንቅፋት፤ ወጥተን እንዳንገባ ጋሬጣ የሆኑብንን የሠላም ጠንቆች ከመካከላችን እናስወግድ። ወደንም ሆነ ተገድደን በጉያችን ታቅፈናቸው የነበሩት የሠላም ቀበኞች ጉያችን እንዲሞቃቸው አናድርግ።

ከሰሞኑን አዲሱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ “ዘላቂ ሀገራዊ ሠላምን ማስፈንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው” ብለዋል። ለሚገነባው ዘላቂ ሠላም ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።

የትኛውም ጥያቄ ያለው አካል ጥያቄውን በሕግ አግባብ ማቅረብ ይችላል፤ ይሕ ሕገመንግሥታዊ መብት ነው። ፍላጎቶቹን በጠብመንጃ አማካይነት በሕዝብ እና በመንግሥት ላይ ለመጫን የሚደረግ ጥረት ግን ሀገር እና ሕዝብን የሚጎዳ፤ በዚህ ዘመን ጥፋት እንጂ ለጥያቄ መልስ ሊያመጣ የሚችል አይደለም።

መንግሥት፤ ከየትኛውም ኃይል ጋር በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ በችግሮች ዙሪያ ለመወያያት ፈቃደኛ መሆኑን ደጋግሞ አስታውቋል። “እንነጋገር፤ እንወያይ” ሲል የሠላም እጁን ዘርግቶ ሲጠብቅ ሰንብቷል። አሁንም ቢሆን በሩ አልተዘጋም። ለሕዝቡና ለሀገር ሠላም ሲል መንግሥት ልቡን አስፍቶ እየጠበቀ ነው።

አዲሱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው። እንዲያውም በተናጠልም ይሁን በጋራ መንግሥት በሠላማዊ መንገድ ለመነጋገር ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኑንም በመክፈቻ ንግግራቸው ጠቅሰዋል።

ኅብረተሰቡም ከመነሻው የሚፈጠር የሠላም መደፍረስ ማን እንደፈጠረው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሠላም አደፍራሹን አካል “ሃይ” ሊለው ይገባል። ምንጩ ላይ በመሆን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ከተሠራ ችግሩን በእንጭጩ መግታት ይቻላል። ይህ ደግሞ ከግጭት ለማትረፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን አቅም የሚያሳጣ ነው ።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢትዮጵያ ጥቂቶቹ ከፈጠሩት ውጥንቅጥ መውጣቷ አይቀሬ ነው። በተለያየ አቅጣጫ ጦር የሚያነሱና የሕዝቡን የመልማት ተስፋ የሚናጠቁ ኃይሎች ጊዜያቸው ያበቃል። የገዛ ወገኖቻቸውን እያስጨነቁና እያሰቃዩ አይቀጥሉም። ለዚህም የፍጻሜው ጅማሬ እውን እየሆነ ነው።

ወጋሶ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You