የደራው የልመና ገበያ!

ዓይን ሲያይ ልብ ይፈርዳል። የተመለከትነውን ተመልክተን የሰማነውንም ሰምተናል። ነገር ግን ግብር የማይጣልበት፣ ቀረጥ የማይቀረጥበት አዲስ የሥራ መስክ ያለ ምንም የንግድ ፈቃድ ስለመምጣቱ ያስተዋልን ግን ስንቶቻችን ነን? ብቻዬን ተመልክቼ ብቻዬን የምፈርድ እንደሆን በመፍረዴ ይፈረድብኛልና ጥቂት ስለ ሀቁ አስበን ስለመፍትሔው ብናሰላስል ይሻላል ባይ ነኝ።

ከብጣሽ ጽሑፌ መግቢያ እስከ መደምደሚያ የማውራት ፍላጎቴ አጥተው ነጥተው ስለሚለምኑት የኔ ቢጤዎች ሳይሆን በሌላኛው አቅጣጫ ልመናን እንደ አዲስ ቢዝነስ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ነድፈው እየሠሩበት ስላሉት ነውረኞች ነው። የትም ሳንሄድ፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ብቻ ሳትሆን የለማኞች መዲናም ጭምር ሆናለች።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በእግር ከመራመድ በላይ የሚያደክመውና የሚያስጨንቀው ከዚም ከዚያም ከሚታዩት የሚሰማው የሰለሉ የልመና ድምጾች ናቸው። አሁን አሁን ከንፈር ከመምጠጥ የልብ ስብራት ወደ ጥያቄ አጫሪነት ተሸጋግሯል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባልተለመደ መልኩ እንደ አሸን እየፈሉ፤ ከመጽዋቹ ተመጽዋቹ ለመብለጥ የቀረው የለም። ልመና ሳይሆን የልመና ፌስቲቫል የሚካሄድ መስሎ ሲታይ ከዚህ በላይ ሊያሳስበን የሚገባ ምን አለ?

ምንዱባን፣ የጎዳና ሰው፣ የኔ ቢጤ በየትኛውም የሠለጠኑና ሀብታም ሀገሮች ውስጥ ያለና የሚኖር ነው። በሀገራችንም የተቸገረውን መርዳት ለዘመናት የቆየው ባሕላችን ነው። እኛ ጣል አድርገናት የምናልፋት ሳንቲም ለኛ በረከትን ስለማምጣቷ እንጂ ከበስተጀርባዋ ያላትን አንመለከትም።

ከተባረኩበት ማንም ይሁን ለማን እኔ ምን አገባኝ እሳቤያችንን ለጽድቅ ሳይሆን ለኩነኔ እየተደረገብን ነው። ምጽዋት የሚገባቸው ምስኪኖች ዳር ላይ ተረስተው በሌላ የበግ ለምድ በለበሱ ምንደኞች ተሸፍነዋል። ዞረን ለምዱን ብንገልጥ በየርምጃው የተሰገሰጉ ተኩላዎች ለጉድ ናቸው።

የበጎቹን ሳር ቅጠል የሚለቅሙትን እኚህን ተኩላዎች መንጥሮ ርምጃ መውሰዱ የሕግ አካላት የቤት ሥራ ሊሆን አይገባም ወይ? አስመሳዮች የሚያደርጉትን ተመልክቶ፤ በሞት አፋፍ ቆሞ የርዳታ ጥሪውን ሲያስተጋባ “ውሸታም!” ብሎ ማለፍ የጀመረው ማህበረሰብስ በአረሙ ምክንያት አዝመራውን ረግጦ ማለፉ ተመችቶት ይሆን? አይመስለኝም። ሁላችንም መፍትሔውን እንፈልጋለን። ግን ሰጪና አምጪው ማነው? ከእኛ ሌላ ማንስ ይምጣ?

በፊት በፊት በልመና ውስጥ የምንመለከታቸው ጧሪ ደጋፊ ያጡ፣ ወላጅ አልባ፣ የአካል ጉዳተኛ፣ ለሥራ አቅምና አካል አጥተው በችጋር ሳማ የተገረፉ ነበሩ። ሀፍረት ተከናንበው አማራጭ ስላጡ ብቻ የሚገቡበት ነበር። ዘንድሮ ግን ልመና የእነዚህ ብቻ አይደለም። ጠብ ለማይል ኑሮ ሠርቶ ከእጅ ወደ አፍ ከማለት ልመናው አዋጭ የሥራ ዘርፍ መሆኑን ተመልክተው ያለ ሀፍረት በጥበብ የገቡበት ቁጥር የላቸውም።

አሳፋሪ የነበረው ልመና ያለ ድካም የሚያበላና ዓይን የማይታሽበት ተደርጎ ከዘመኑ ጋር አዘምነውታል። መለስ ብለን ካስተዋልን በሴተኛ አዳሪነት የነበረው ታሪክ ነው። አማራጭ በማጣት ካለመሞት መሰንበት ተብሎ የሚገባበት አስነዋሪ ተግባር ነበር። ቆይቶ ግን ከተማሪ እስከ ዕውቅ ቆነጃጅት በደላሎች እየተመለመሉ ዘመናይ ሴተኛ አዳሪዎች ተፈጠሩ። ከባለገንዘቦች ጭን ስር መገኘት፤ ደህና ሰንብት ድህነት ተብሎ የሀብት ቁልፍ መረካከቢያ አደባባይ ሆነ። ዛሬ የምንመለከተውም ይኼው ነው። ዳግም በልመናው ታሪክ እየተደገመ ነው።

ዛሬ ላይ በየአደባባዩ በምንመለከተው በደራው የልመና ገበያ ውስጥ መሆን ሳይሆን መስሎ መታየት ትልቁ ጥበብ ነው። በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ እንኳን ያልተመለከትነውን የትወናና የሜካፕ ጥበብ በልመናው ውስጥ እየተመለከትን ነው። እንኳን አዋቂው ሕፃናቱ ሳይቀር በደህና ደራሲ ተቀርጸው፣ በድንቅ ዳይሬክተር በመመራት አጃኢብ ነው! የሚያስብል የትወና ብቃታቸውን ያሳያሉ።

የተሰረቁና መሰል ሕፃናትን በየጎዳናው ላይ የሚያሰማሩ የበስተጀርባ ዘዋሪዎች ቀድሞም የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን ከዘመኑ ጋር አዘምነው እረቀቅ አድርገውታል። ውስጡን ብንፈትሽ፤ በዝርፊያው ዓለም ውስጥ ከአሸባሪ ባልተናነሰ የተደራጁ የማፍያ ቡድኖች እንዳሉ ሁሉ ከልመናውም በስተጀርባ ፈርጣማ ቡድኖችን መቆም ጀምረዋል።

ከዝርፊያው የሚለየው በበጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ ዘረፋ መሆኑ ብቻ ነው። የታማሚን ምስልና ማሞኛ ቃላትን የያዙ ትልልቅ ባነሮች ይሠራሉ። የኪራይ መኪና የኪራይ ጀነኔተር ይዘጋጃል። ስፒከር ተሰቅሎ ድምጽ ማጉያ ይጨበጣል። አንጀት መብያ የመለመኛ ሙዚቃና ክላሲካሎች ከፍ ተደርገው ይደመጣሉ።

ከሆድ አደር የህክምና ባለሙያዎችና ተቋማት የውሸት ማስረጃዎችን በማጻፍ ይለጣጠፋሉ። በጥሩ ሜካፕ አርቲስት የተሠራው ተዋናይ በመርሀ ተውኔቱ እየተመራ ይተውናል። እንግዲህ ሙዚቃዊ ተውኔት መሆኑ ነው። ከዚህ ቀደም በመርካቶና በሌሎች ጥቂት በማይባሉ ስፍራዎች በጥቆማ የተያዙት ለዚህ ማሳያ ናቸው። ይሄም ከብዙ የልመና ስልቶች መካከል አንደኛው እንጂ ብቸኛው አይደለም። በግልና በቡድን ሌላውም ዓይነት ይቀጥላል።

የልመናውን አዋጭነት በማመን ከሥራ አምልጠው የገቡ ሁሉ ምክንያታቸው የተትረፈረፈ ብልጽግናን ፈልገው አይደለም። ራሳቸውን ለማኖር ሥራ ያጡ ይሆናሉ። ሥራ ቢኖራቸውም ገቢያቸው የማያኖራቸው ሆኖ ያገኙታል። የያዘ ይዞት እንጂ በልመናው ጠንክሮ ከማንም የወር ደመወዝተኛ የተሻለ ገቢ የሚያገኝ እንዳለ አይካድም።

በወሬም ይሁን በእውን እሱ የሚመጸውተው ተመጽዋች ከእርሱ የተሻለ እንደሚያገኝ ያሰበበት ዕለት ብድግ ብሎ ከሥራው ልመናውን ይመርጣል። በኛ በሦስተኛው ዓለም ውስጥ ርካሹ ነገር ጉልበት ነው። አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ ጥሮ ግሮ የሚኖረው በጉልበቱ ነው። ይኼው ትኩስ ኃይልና ጉልበትም ራሱን ለማኖር ሲል በተስፋ መቁረጥ የልመናውን ቢዝነስ ይቀላቀላል።

ችግሩ ያለው ልመናው ላይ ሳይሆን የሚሠራው የሰው ኃይል በመቀነሱ በተዘዋዋሪ ሀገር የምታጣው ብዙ መሆኑ ነው። ኢኮኖሚው ለሁሉም በቂ እንዲሆን ሁሉም መሥራት ይኖርበታል። የሚለምነው በዛ ማለት የአንዱን ሰው ገቢ ለሁለትና ለሦስት እየተሻማንበት ነው ማለት ነው። ሳይሠራ ቁጭ ብሎ ገንዘብ የሚሰበስበው ግለሰብ እያገኘ ነው ብንልም፤ በኢኮኖሚ እሳቤ ግን ከግለሰቡ ገቢ በብዙ እጥፍ ሀገር እያጣች ነው እንደማለት ነው።

ስለዚህ የደራው የልመና ገበያ ውስጥ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ትልቅ የኢኮኖሚ ማገርም ጭምር እየተመዘዘ ነው። የእውነትም ተቸግረውም ይሁን ታዘው ምንም የማያውቁ ሕፃናት ፊደል በመቁጠሪያ ዕድሜያቸው የልመናን ሀሁ ያጠናሉ። ምንም ሳያውቁ በፊት ነጭ ወረቀት የመሰለው ጭንቅላታቸው በልመና ተቀርጾ ነገ ላይ ምን ወርቅ ብናነጥፍላቸው ነገ ላይ ምን ዓይነት ትውልድ ነው የሚሆኑት? በልመና የታሸ ትውልድ ይዘን የምንገነባት ሀገርስ የነገው መልኳ ምን መሳይ ይሆን?

ከቅርብ ዓመታት በፊት በገጠሩ የሀገራችን ክፍል የሚኖረው ማህበረሰብ እንደ ልመና አምርሮ የሚጠላውና እንደ አሳፋሪ የሚያየው ነገር አልነበረም። ‹‹ነፍሴ እያለች…›› እያለ ልመናን አምርሮ የሚጸየፍ ነበር።

‹‹ሰው እንዴት ሙሉ አካል ይዞ ይለምናል?›› እያለ የሚገረም ነበር። አብዛኛው የገጠር ሥራ ከአካላዊ ጤንነት ጋር የሚያያዝ የጉልበት ሥራ በመሆኑ ጤንነት አስካለው ድረስ ልመናን አያስበውም። ለሱ ጤነኛ ሆኖ መለመን እጅግ በጣም ነውር ነበር።

የችግሩ ክፋት ደግሞ ሕፃናት እና ታዳጊዎች ልመናን እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ እያዩት እና እየተቀበሉት መሄዳቸው ነው። አሁን አሁን በየመንገዱ ሕፃናት ልጆች የአዋቂዎችን ልብስ እየያዙ ሲለምኑ ማየት ተለምዷል። እነዚህ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር እየለመኑ ነው። የልመናን ነውርነት እየሰሙ ሳይሆን እንደ ሥራ እያዩት እያደጉ ነው። የነዚህ ሕፃናት ልጆች ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አይቸግርም።

ችግሩ አሁን ባለበት ደረጃ እየቀጠለ ከሄደ እንደ ሀገር ሊፈጥረው የሚችለው አደጋ የቱን ያህል የገዘፈ ሊሆን እንደሚሆን መገመት አይከብድም፤ የከተሞች መንገድ ብቻ ሳይሆን ገጠሮቻችንም በተመሳሳይ መልኩ ልመናን ሥራ ባደረጉ ዜጎች መሞላታቸው የማይቀር ነው ።

ምጽዋት ሽቶ የወጣውን አትለምንም ተብሎ ሊከለከል አይችልም። ለደራው ገበያ የሥራ ፈቃድ አውጣ ልንለው አንችልም። የውሸቱን ይሆናል ብለን ምጽዋታችንን ሳንሰጥ ስለማለፍም ማሰብ የለብንም። ተኩላውን ከበጎቹ መለየት አንዱ መፍትሄ ቢሆንም፤ በዚህ ወንጀልን እንከላከል ይሆናል እንጂ ለችግረኛው ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም።

ምጽዋታችንን ከኪስ አውጥተን ጣል ማድረጋችን መልካም ቢሆንም በቂ ግን አይደለም። መንግሥት እንደ መንግሥት የሥራ ዕድሎችን ከጥሩ ገቢ ጋር ለመፍጠር መሥራት ይኖርበታል። የኑሮ ውድነቱን በመቆጣጠር ከዜጎች ገቢ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ማድረግ ግድ ነው።

በችግር ለወደቁ ሕፃናትና አረጋውያን እንዲሁም አካል ጉዳተኞች ትኩረት በመስጠት ከጊዜያዊነት ያለፈ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል። ከሀገር በቀልም ሆነ ከውጭ የርዳታ ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት የወደቀውን ማንሳት መረሳት የለበትም። ችግሩ ላይ ብቻ ከማተኮር ወደኋላ ምንጩን ለማድረቅ ባንጠራራ እንኳን ለመቀነስ መሥራት ነው። አሳሳቢውን የደራ ገበያ ማጥራቱ ግን፤ ፋታ የማያሰጠው ወሳኙ ጉዳይ ነው።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You