
የአሜሪካ እና የዩናይትድ ኪንግደም ተዋጊ አውሮፕላኖች በየመን ውስጥ በሚገኙ 18 የሁቲ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን አስታወቀ።
ሁለቱ ሀገራት በጋራ ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ኢላማ ያደረጉትም የሁቲ መጋዘኖችን፣ የድሮን እና የአየር ጥቃት መከላከያ መዋቅሮችን እንዲሁም ታጣቂዎቹ የሚንቀሳቀሱበትን ሄሊኮፕተር መሆኑን አሜሪካ አሳውቃለች።
ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) በበኩሏ የምዕራባውያን ሀገራቱ እርምጃውን የወሰዱት የሁቲ ታጣቂዎችን ጥቃት የመፈጸም አቅምን “የበለጠ ለማዳከም” ነው ብላለች።
በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ለባሕር ንግድ እንቅስቃሴ ወሳኝ በሆነው በቀይ ባሕር በሚንቀሳቀሱ በመርከቦች ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን ጨምሮ ሰፊ የሀገሪቱን ግዛት የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች ጋዛ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ለፍልስጤማውያን ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት የእስራኤል እና የምዕራባውያን የሚሏቸውን መርከቦች ኢላማ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በቀይ ባሕር ላይ ሁቲዎች በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት ታላላቅ የመርከብ ጭነት አጓጓዥ ኩባንያዎች የጉዞ መስመራቸውን በመቀየራቸው፣ በዓለም ንግድ ላይ የአቅርቦት መስተጓጎል ከመፍጠሩ በላይ የዋጋ ጭማሪም አስከትሏል።
የዩኬ እና የአሜሪካንን ጥቃት በተመለከተ ፔንታጎን ባወጣው የጋራ መግለጫ፣ የቅዳሜው ጥቃት “ከመሬት በታች ያሉ የጦር መሳሪያ እና የሚሳኤል ማከማቻዎች፣ የድሮን መዘዣ፣ የአየር ጥቃት መከላከያ እና የራዳር ማዕከሎች እንዲሁም ሄሊኮፕተር” ላይ ጥቃት መፈጸሙን አሳውቋል።
“አስፈላጊ እና ተመጣጣኝ ነው” በተባለው በዚህ ጥቃት በየመን የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ስምንት ቦታዎች ላይ ባሉ 18 ኢላማዎች ላይ መፈጸሙንም የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት አመልክቷል።
ኢላማዎችን ብቻ ነጥሎ ለመምታት በተወሰደው እርምጃ “ሁቲዎች በዚህ ወሳኝ በሆነው የባሕር እንቅስቃሴ መስመር በዓለም አቀፍ ንግድ፣ በባሕር ኃይል መርከቦች እና በመርከቦች ሕይወት ላይ የሚደቅኑትን ስጋት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ያለመ ነው።”
መግለጫው ጨምሮም “ከኅዳር ወር አንስቶ ሁቲዎች ከ45 በላይ በሚሆኑ የንግድ እና የባሕር ኃይል መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸም ለዓለም አቀፉ ምጣኔ
ሀብት፣ ለአካባቢው ደህንነት እና መረጋጋት አደጋ በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል” ብሏል።
የቅዳሜ ምሽቱ ጥቃት የተፈጸመውም “ከአውስትራሊያ፣ ከባህሬን፣ ከካናዳ፣ ከዴንማርክ፣ ከኔዘርላንድስ እና ከኒውዚላንድ” በተገኘ ድጋፍ አማካይነት ነው ተብሏል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአጭር ጊዜ በኋላ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን “የዓለም ወሳኝ በሆነው የባሕር መስመር ላይ የሚደረግን ነጻ የሰዎች እና የንግድ እንቅስቃሴ ለመጠበቅ አሜሪካ አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ከመውሰድ አታመነታም” ሲሉ ተናግረዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ በበኩላቸው “የሰዎችን ሕይወት እና የባሕር ላይ ነጻ እንቅስቃሴ ደህንነትን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለብን አየር ኃይላችን የመን ውስጥ ባሉ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ሆኗል” ብለዋል።
ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት እንዳስታወቀው፤ ጥቃት ለመፈጸም የተዘጋጁ ናቸው ያላቸውን ሰባት የሁቲ ተንቀሳቃሽ ፀረ መርከብ ሚሳኤሎችን ማውደሙን አስታውቆ ነበር።
ባለፉት ሳምንታት በቀይ ባሕር በኩል በመርከቦች ጭነት ማጓጓዝ ፈታኝ ሆኗል። በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጽያን በሰው አልባ አውሮፕላን እና በሚሳኤል መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።
ታጣቂዎቹ በተጨማሪም በጀልባ እና በሄሊኮፕተርም ጥቃት አድርሰዋል።
አብዛኛውን የመን የሚቆጣጠሩት ሁቲዎች “በጋዛ እና በዌስት ባንክ ላሉ ፍልስጤማውያን ወንድሞች” ድጋፍ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ወደ እስራኤል የሚጓዙ የንግድ መርከቦችን ዒላማ እንዳደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ባጣራው መረጃ መሠረት ሁቲዎች ጥቃት የሰነዘሩት በደቡባዊ ቀይ ባሕር ነው። ይህም በየመን ባሕር ዳርቻ በባብ ኤል-ማንዳብ መተላለፊያ ላይ ነው።
ወደ ኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚጓዙ መርከቦች ላይም ጥቃት ተሰንዝሯል።
ነገር ግን በጥቃቱ ዒላማቸውን የመቱት የተወሰኑት ብቻ ናቸው። ከእነዚህም መካከል እአአ ጥር 17 የተፈጸመው ጥቃት ይገኝበታል።
በዚህም በአሜሪካ መርከብ ላይ ነበር ጥቃቱ የተቃጣው። ነገር ግን መርከቡ በሁቲዎች ድሮን ጎኑ ላይ ቢመታም ጉዞውን ቀጥሏል።
ጥቃቱን የሚያሳይ ምስል ያነሳው የሕንድ የባሕር ተዋጊ መርከብ ነበር። ይህም የሁቲዎችን ጥቃት ለመመከት ያለውን ትብብር ማሳያም ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም