‹‹ሽፎን›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ሴቶች የአለባበስ ልማድና ባሕል ጋር ተስማምቶ ቀርቧል። ጥሬ እቃው ከውጪ ይገባል። በትከሻ ልክ ተሠርቶ፣ ከወገብ ጥንቅቅ ተደርጎ በልብስ ስፌት ባለሙያዎች ይስተካከላል፣ ከጉልበት እስከ እግር ጣት ዝርፍፍ ብሎ ቁርጭምጭሚትን ጭምር የሚሸፍን ነው። በላዩ ላይ ደግሞ አጠር ያለ ነጭ ነጠላ ሲደረብበት ልዩ ውበትን ያላብሳል። እድሜም ገደብ ሳይኖረው የሚለበሰው ሽፎን ሴቶች በእምነት ቦታ፣ የሠርግ ዝግጅት ላይ፣ ለአዘቦት ቀንም ጭምር ተመራጭ ያደርጉታል። ሽፎን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በስፋት የባሕል አልባሳት ገበያው ውስጥ በስፋት ይታያል።
አብዱልከሪም አብዱልሰመድ ይባላል፤ ዜድ ኬ የሽፎን ዲዛይን ሱቅ ባለቤት ነው። ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን በጨርቆስ የገበያ ማዕከል የሀገር ባሕል ልብስ፣ በዘመናዊ መልክ የሚሠራ ‹‹ሽፎን›› እና ሌሎች ቀሚሶችን በመሥራት ለገበያ ያቀርባል፡፡ በሥራው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያለፈ ጊዜን አስቆጥሯል፡፡ ወቅቱ ከሽፎን ጨርቅ የሚሠሩ ልብሶች ተቀባይነት እያገኙ የመጡበት ጊዜ በመሆኑ ሙያውን ለወራት ከተማረ በኋላ ወደ ገበያው ተቀላቅሏል፡፡
ባለሙያው እንደሚናገረው ሽፎን ልብስ የሚሠራበት ጥሬ እቃ የሚመጣው ከዱባይና ከሕንድ ነው። ብዙ ሴቶች ከእነዚህ የሻማ ይዘት ካላቸው ጨርቅ የሚሠሩ አልባሳትን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ብትን ጨርቁን (ጥሬ እቃ) ከእነዚህ ሀገራት በማስመጣት የሚሸጡ እና በስፌት ሥራ ለተሠማሩ ባለሙያዎች የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ያሉ ሲሆን አብዱልከሪም ብትን ጨርቁን ከሚያስመጡ ነጋዴዎች ተቀብሎ ይሠራል ፡፡
እንደ አብዱልከሪም ገለፃ፤ ሽፎን የሚሠራበት ጥሬ እቃ የማኅበረሰቡን አለባበስ እንዲመች ተደርጎ በመሠራቱ ብዙዎች እንዲመርጡት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ፋሽን በተዋወቀበት ወቅት በተለምዶ እናቶች ‹‹ሽንሽን›› እያሉ የሚጠሩት ቀሚስ አይነት ተደርጎ ይሠራል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ወጣት ሴቶች የተለያየ ዘመናዊ ዲዛይን በመምረጥ ይጠቀሙታል።
‹‹ሽፎን በጨርቆስ ገበያ በብዙ አማራጭ ይገኛል›› የሚለው አብዱል ከሪም፤ ይህንን አልባስ ደንበኞች በሚፈልጉት ዲዛይን የሚሠሩ ባለሙያዎችም በስፋት እንደሚገኙ ይገልፃል፡፡
ሽፎን የተለያየ ስያሜ ያለው መሆኑን በመግለፅም በብዛት ከኢትዮጵያ የሀገር ባሕል ልብስ ዲዛይን ጋር ተመሳስሎ እንደሚሠራ ያስረዳል፡፡ ሽፎን በባሕሪው ዘርፋፋና ረዥም መሆኑን፤ በዚህ መልክ ሲሠራም ይበልጥ ውበት እንደሚኖረውም ይናገራል፡፡ አንገቱ ላይ በአራት ማዕዘን እና በ ‹‹ቪ›› ቅርፅ ይሠራል። ወገብ ሽንሽን፣ አስመራ ክሽ ክሽ ወይንም በጉልበት አካባቢ የሚጨመር በዲዛይን ተመጥኖ የሚሠራ ጨርቅ፣ በዘመናዊ መንገድ ከሚሠሩ ደግሞ ሬድሜድ ቅድ በአሁን ሰዓት ደግሞ በአዘቦት ቀን መለበስ እንዲችሉ ቀለል ያለ ዲዛይን እንዲኖረው ይደረጋል፡፡
አብዱልከሪም ወደ ሱቁ መጥተው ትእዛዝ ከሚሰጡት ደንበኞቹ ባሻገር በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚይዘውን የጨርቅ አማራጭ ያስተዋውቃል፡፡ የሽፎን ጨርቁ ከመሠራቱ በፊት እና ተሠርቶ ቀሚስ ሲሆን የሚኖረው ውበት የተለያየ በመሆኑ አዳዲስ ዲዛይኖችን አስቀድሞ ሠርቶ የተለያዩ የፎቶ ሞዴሎች፣ አርቲስቶች እንዲያስተዋውቁት በማድረግ ደንበኞችን ለመሳብ እንዲሁም ለማስተዋወቅ ይጠቀምበታል። ደንበኞችም የተለያዩ ገጾችን በመመልከት የራሳቸውን ዲዛይን እና የጨርቅ አይነት ይዘው ወደ ሱቁ ጎራ ይላሉ፡፡
በአብዛኛው በበዓላት ወቅት፣ ጥምቀት፣ ሠርግ ሲሆን እንስቶች በቤተሰባቸው አንድ አይነት የሽፎን ቀሚስን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ በኅብረት ሲለበስም የተለየ ውበትን ይሰጣል፡፡ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ደንበኛ የሚያስተናግዱበት ወቅትም የጥምቀት በዓል ሲቃረብ መሆኑን አብዱልከሪም አንስቷል፡፡ ሽፎኑ ብትን ጨርቅ ሆኖ ወደ ሀገር የሚገባ ሲሆን በአብዛኛው ስድስት ሜትር፣ አልያም አራት ሜትር ተደርጎ ወደ ሀገር ይገባል፡፡ ለአንድ ሰው ከሦስት ሜትር እስከ ስድስት ሜትር የሽፎን ጨርቅ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ጨርቁ በባሕሪው የመሳሳት ባሕሪ ስላለው ሲለበስ ተጨማሪ ገበር ከውስጡ የሚደረግበት ሲሆን የገበሩ አይነትም የልብሱ ውበት ላይ የራሱ አስተዋፅዖ አለው፡፡ ከተመረጠው የጨርቅ ቀለም ጋር አብሮ የሚሄድ የውስጥ ገበር እንዲሁም ልብሱን ይበልጥ እንዲያምር የሚያደረገው አንጸባራቂ የውስጥ ገበር በባለሙያዎች እይታ እና ምርጫ ይጠቀማሉ፡፡ የጨርቆቹ አይነት ወጥ የሆነ ቀለም እና በአብዛኛው ደግሞ ይህ ነው ተብሎ ሊለይ በሚችል ቀለም ላይ የተለያዩ አበባዎች አንጸባራቂ ፈርጦች ያሏቸው ናቸው፡፡
የሽፎን ጨርቅ በአንድ ሱቅ ውስጥ በሜትር ተለክቶ ከእነመሥሪያው እና ተጨማሪ ነጭ ነጠላ አብሮት ይዘጋጃል።፡ በአብዱልከሪም ሱቅ ከሦስት ሺህ 500 ብር ጀምሮ ለገበያ ቀርቧል፡፡ ልብሱን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ሳምንት ጊዜን ብቻ ቢወስድም ተጨማሪ የቀን ቀጠሮ ለደንበኞች የሚሰጠው አስቀድመው የተሰጡ ትዕዛዞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ የሽፎን ጨርቅ መለመድ በሀገር ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ኢንዱስትሪ ላይ ተሠማርተው ለሚገኙ ባለሙያዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭን እንደፈጠረም የልብስ ስፌት ባለሙያው ይናገራል፡፡ አብዱልከሪም በሱቁ ውስጥ ከሽፎን ውጪ የሐገር ባሕል ልብስን አጣምሮ ይይዛል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ለልብስ ስፌት ባለሙያው ‹‹የሽፎን ጨርቅ መለመድ ደንበኞች ፊታቸውን ወደ ሀገር ባሕል ልብስ እንዳያዞሩ አላደረገም›› በማለት ላቀረበለት ጥያቄ ‹‹በሁለቱ የልብስ አይነቶች መካከል ውድድር እንዲፈጠር እና የሀገር ባሕል ልብሶች በተሻለ መልኩ ተሠርተው እንዲቀርቡ ያደርጋል›› ሲል ያመጣውን ጥሩ እድል ገልፆልናል፡፡ ደንበኞች ከሀገር ባሕል ልብስ ይልቅ ሽፎንን የመረጡበት ምክንያት ምናልባት ያልተዘጋጁበት ቀጠሮዎች ቢኖርባቸው በፍጥነት ተሠርቶ ማለቅ የሚችል እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችሉት ስለሆነ ነው ይላል፡፡
በጨርቆስ አካባቢ ባሉ የገበያ ማዕከሎች አብዛኛዎቹ ሱቆች የሽፎን ጨርቆች የሚይዙ ሲሆን የልብሱ መለመድ እና በሀገር ውስጥ ባለው የአለባበስ አይነት የሚስተካከል እና የሚመች ተደርጎ መሠራቱ ‹‹የሀገር ባሕል ልብስ ገቢው እና በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳድር ይሆን›› የሚል ጥያቄ መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡
ወይዘሮ ዓለምፀሐይ መብራቴ የሀገር ባሕል አልባሳት በተለያየ መልኩ ዲዛይን በማድረግ በመሸጫ ሱቃቸው ለደንበኞች ያቀርባሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ተጠቃሚዎች ሽፎንን የሚመርጡት በሀገር ባሕል አልባሳት ላይ ፍላጎት አጥተው ሳይሆን በሁለቱ መሐከል ያለው የዋጋ ልዩነት ሰፊ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹ሰዎች አሁንም ቢሆን የሀገር ባሕል ልብስን ይመርጣሉ፡፡ ነገር ግን የዋጋው መወደድ ወደ ሽፎን እንዲዞሩ ያደርጋቸዋል›› የሚሉት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ምክንያቱን ይገልፃሉ። የሀገር ባሕል ልብስ ለመሥራት የሚያገለግሉ ግብዓቶች መወደድ ለዋጋው መናር ሚና ስላላቸው ደንበኞች በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረበውን የሽፎን ጨርቅን እየመረጡ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የአልባሳት ገበያ ውስጥ ሽፎን ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ ነው። ይህ ፋሽን ከመለመዱ አስቀድሞ በገበያዎች ላይ የሀገር ልብስን ከቻይና በማሽን ተሠርቶ በሚመጣ ልጥፍ ጥበብ (በአቡጀዴ) ማቅረብ በተመሳሳይ ተለምዶ ነበር። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያን የሴቶች የባሕል ልብስ ሽፎን በቀዳሚነት እየመራው ይመስላል። ሰላም!!
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም