የጉባኤው ውሳኔና የአፍሪካ ትምህርት የወደፊት አቅጣጫ

ከሁለት ሳምንት በፊት “ትምህርት በአፍሪካ” በሚል ርዕስ አንድ ዳሳሽ ጽሑፍ አቅርበን እንደነበር ይታወሳል። በጽሑፉም በአህጉረ አፍሪካ ትምህርት ያለበትን ሁኔታና ይዞታ፣ በወፍ በረርም ቢሆን ዳስሰናል። ያሉበትን ችግሮች ቃኝተን፤ ከምሑራን ጥናት ተነስተን መፍትሔውን ጠቁመናል፤ መደረግ ያለበትን ከሌለበት ለይተን አሳይተናል።

ይህን ያደረግነውና የአፍሪካ አሕጉርን ትምህርት የኋላ ታሪክ የገመገመውን የዘንድሮው 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዐቢይ የመወያያ አጀንዳ ይህንኑ የአፍሪካን ትምህርት የወደ ፊት አቅጣጫ ያስቀመጠ በመሆኑ ነው።

ዛሬም፣ ከጉባኤው መጠናቀቅና ካስተላለፈው ውሳኔ አኳያ አንዳንድ ሀሳብ ለመለዋወጥ በመሻት ጉዳዩን ወደዚሁ ገጽ እንደገና ይዘነው መጥተናል።

የዘንድሮው የኅብረቱ ጉባኤ መሪ ቃሉ “Educate an African fit for the 21st Century: Building Resilient Education Systems for Increased Access to In­clusive, Lifelong, Quality, and Relevant Learning in Africa”. የሚል ነው፡፡ በእኛ ትርጉም “21ኛውን ክፍለ ዘመን ያገናዘበና ለአፍሪካ የሚስማማ ማስተማር፤ አይበገሬ የትምህርት ሥርዓት መገንባት ለአካታችነት፣ ጥራት፣ እና ተገቢነት በአፍሪካ እንደማለት ነው።

ይህ መሪ ቃል በአጀንዳ 2063 ለማሳካት ከተያዙት እቅዶች አንዱ ሲሆን፣ እሱም “በአካታች እድገትና ቀጣይነት ያለው ልማትን መሠረት ያደረገ የበለፀገ አፍሪካ” የሚለውና አፍሪካን ለመለወጥና ወደ ብልፅግና ለማምጣት ትምህርት ላይ በከፍተኛ ደረጃ መዋዕለ ንዋይን በማፍሰስ፤ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርትን ለአፍሪካውያን በተለይም ለወጣቱ ተደራሽ በማድረግ ወዘተ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራትን፤ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ አብዮት ማቀጣጠልን፤ ከዛም አፍሪካን ወደ ብልፅግና ጉዞን ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረገ ነው።

በአጀንዳው መግቢያና አንዳንድ ገፆችም ሆነ ሌሎች ሰነዶች ላይ እንደሰፈረው፣ በአፍሪካ እንደ ሌሎቹ ሁሉ የትምህርቱ ሴክተርም በተግዳሮት የተሞላ ነው። በደል እየደረሰባቸው ካሉት ዘርፎች ቀዳሚው እንኳን ባይሆን፣ ከፊት መሪዎቹ ውስጥ አንዱ ነው – ትምህርት።

እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 2024፣ “ሴቭ ዘ ችልድረን “EDUCATION IN AFRICA: VIOLENT ATTACKS AGAINST SCHOOLS ROSE 20% IN 2023 በሚል ርዕስ በተጠና ጥናት በአፍሪካ በሚደረጉ የእርስ በእርስ ግጭቶች ምክንያት፣ በተጠናቀቀው 2023 ብቻ ካሉት አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች መካከል 20 በመቶ ያህሉ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ወድመዋል።

ይህ፣ በ411 የመስክ እና ጥናታዊ ሪፖርቶች የተገለፀው አደጋ በትምህርት ሴክተሩ ላይ ትልቅ ጉዳትን ያደረሰ ሲሆን፤ የመማር-ማስተማሩን ሥራ በመግታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ አድርጓል። ስለዚህ ይህ ይቆም ዘንድ አስቸኳይ እርማትን ይፈልጋል ማለት ነው፡፡

ጥናቱ የመሪዎቹ ውሳኔ በትምህርቱ ዘርፍ ያለውን ማነቆ በአፍሪካ አንድ አራተኛ የመጀመሪያ ደረጃ፤ ከሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 50 በመቶ ብቻ ናቸው በሙያው የሠለጠኑ መምህራን፡፡ ስለሆነም በመምህራን፣ በተማሪዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና ተያያዥ ወገኖች ላይ እየደረሱ ያሉትን ችግሮች ይፈታል፤ የመማር-ማስተማር መሰናክሎቹንም ያስወግዳል ተብሎ ይጠበቃል።

መሪዎቹንም ቃልና ውሳኔያቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ፤ የትምህርት ተቋማትንም ለልጆች ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን በጥብቅ ያሳስባል።

በዚሁ የካቲት 9 እና 10/2016 ዓ.ም የተካሄደውን 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ አስታኮ ይፋ በተደረገው የሴቭ ዘ ችልድረን ጥናት ላይ ልዩ ትኩረትን ካገኙት መካከል በሕፃናት ጉዳይ ላይ ሁሉም አካል እጅ ለእጅ ተያይዞ ይህችን ዓለም ለልጆች ምቹ ማድረግ የሚገባ መሆኑን የሚያስገነዝበው ክፍል ነው፡፡

በዚሁ ክፍል በትምህርት ቤቶች ላይ የጦር መሣሪያ መተኮስ፤ መምህራንን መግደልና ማሰቃየት፤ በተማሪዎች ላይ አስለቃሽ ጋዝ መርጨት እና የመሳሰሉት ባስቸኳይ ቆመው ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው፤ መምህራንም ሠላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ የመማር ማስተማሩ ተግባር መቀጠል እንደሚገባው ተጠቅሷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የእርዳታ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በትምህርት ቤቶች ላይ የአየር ድብደባ መፈፀም፣ የትምህርት ቤቶችን ጥበቃ ኃይላት መግደልና ማሰር፤ የትምህርት ተቋማትን ለወታደራዊ ማሠልጠኛነት መጠቀም ወዘተ በአስቸኳይ መቆም ያለበት መሆኑን የሚገልፀው ይህ ጥናት፤ ችግሩ በመቆም ፋንታ በየዓመቱ እየጨመረ የመሄዱን ጉዳይ “alarming rise in attacks year-on-year ሲል የገለፀው ሲሆን፣ የአሕጉሪቱ መሪዎች ይህንን ችግር ለመፍታት ሲረባረቡ አለመታየታቸውን፤ እንዲሁም የየሀገራቱን የተቀናጀ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚጠይቀውን፣ በዓለም ላይ 119 ሀገራት ያላቸውን (አፍሪካ ውስጥ ከ55ቱ 35ቱ ሀገራት አላቸው)፤ እና የትምህርት ቤቶች ደኅንነት መጠበቅ ያለበት መሆኑን የሚደነግግ አዋጅ (Safe Schools Declaration) የሌላቸው ሀገራት መኖራቸውንና ያላቸውም ቢሆኑ ወደ ተግባር መለወጥ አለመቻላቸውን በማንሳት ይወቀሳል።

ሌላውና በዚሁ በአፍሪካ የትምህርት ይዞታና ሁኔታ ላይ የተደረገ ለየት ያለ ጥናት እንደሚያሳየው የአፍሪካ ትምህርት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው። ይኸው የSilas Nka­la ጥናት እንደሚለው ከሆነ፣ በአፍሪካ የሴቶች ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ በአፍሪካ ከ19 ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ነው። የዚህ ትልቁ ምክንያት በቂ በጀት አለመመደብ ሲሆን፣ ይህም አሕጉሪቱ ለትምህርት ልታውለው ከምትችለው በጀት ላይ 29 ቢሊዮን ዶላርን በታክስ ማጭበርበር (tax abuse) ምክንያት እንድታጣ መደረጉ ነው።

በአፍሪካ ሥርዓተ-ፆታን ማመጣጠን ላይ ያለው ክፍተት አስደንጋጭ ነው። በአፍሪካ 38 ሚሊዮን 904 ሺህ 483 ልጆች ከትምህርት ቤት ውጪ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 18 ሚሊዮን 846 ሺህ 517 ያህሉ ልጃገረዶች ናቸው። እንደ ሌሎች በተለይ፣ የአፍሪካን ትምህርት ቅድመ- እና ድህረ- ቅኝ አገዛዝ በማለት ያጠኑቱ ጥናቶች ግኝት ከሰሐራ በታች ባሉት ሀገራት ሴቶች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳን ቢያጠናቅቁ (ተደራሽ ቢሆንላቸው) በቀጣናው ያለው የእናቶች ሞት 70 በመቶ ይቀንስ ነበር።

በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነው 55 አባል አገራትና ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት አፍሪካ ያለው የትምህርት ተደራሽነት በራሱ ችግር ያለበት ነው። ተደራሽ ሆኗል የተባለው ትምህርት እራሱ በጥራት ችግር የተተበተበ ሲሆን፣ በዚህ በኩል በከፍተኛ ደረጃ መሥራት የአሕጉሪቱ ኃላፊዎች ኃላፊነት ይሆናል።

ሌላው ችግር ለትምህርት የሚጠየቀው ክፍያ ነው። በአሕጉሪቱ ያሉና ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ከትምህርት ገበታቸው ውጪ የሚያደርገው ከባድ ችግር ከጣራ በላይ የሆነው ክፍያ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት በዚህ ችግር ምክንያት ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆች እየተማሩ አይደለም። ይህ በቀጥታ በትላልቅ ኩባንያዎች አማካኝነት በታክስ ማጭበርበር የሚጠፋውና ከላይ የተጠቀሰው የ29 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ውጤት ነው።

አፍሪካ በየዓመቱ ይህንን ያህል ገንዘብ ባታጣ ኖሮ በክፍያ ማጣት ምክንያት ሚሊዮኖች ከትምህርት ቤት ውጪ ሆነው እቤታቸው አይውሉም ነበር። አፍሪካ በአጀንዳ 2023 እና ስትራቴጂክ እቅድ (CESA 2016–2025) ውስጥ “አሳካዋለሁ ብላ የያዘችው እቅድም በተሳካ ሁኔታ በሄደም ነበር።

ከላይ በጠቀስናቸው ጥናቶች ግኝት መሠረት በአሕጉሪቱ ትምህርትን ለማዳረስና በተገቢው መንገድ ለማስኬድ ተጨማሪ 20 ከመቶ 29 ቢሊዮን ዶላር መመደብን ግድ ይላል። ይህ ደግሞ 25 ሚሊዮን ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ መሠረታዊ ትምህርት የማግኘት ሰብዓዊ መብታቸውን እንዲያረጋግጡ ያስችላቸዋል።

ወደ መፍትሔው እየመጣ ያለው ይህ ባለ ብዙ ማጣቀሻዎች ጥናት እንደሚለው ከሆነ ሁሉም ነገር ከአሕጉሪቱ መሪዎች አናት ላይ የሚወርድ አይደለም። “መሪዎቻችን ይላል ጥናቱ “መሪዎቻችን ትምህርትን በተመለከተ ያላቸው አተያይ ግራ የሚያጋባ ነው። በቂ የሕግ ማዕቀፍ የላቸውም፤ በአህጉሪቱ በፖሊሲ የተደገፈ አሠራር ማየት ብርቅ ነው፤ በቂ በጀት አይመድቡም፤ ለሙስና የተጋለጡ አሠራሮችን አይቆጣጠሩም ወይም ለሙስና በራቸው በጣም ክፍት ነው።

በዚህ ጥናት ላይ በዋቢነት የተጠቀሱት የትምህርት ዓለም አቀፍ አፍሪካ (EIA) ዳይሬክተር ዴኒስ ሲንየሎ እንደሚሉት በአፍሪካ የመምህራን ልማት ላይ ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ እጥረቱ ሰማይ ነው። የአፍሪካ መሪዎች በአስቸኳይ እነዚህን ችግሮች በመፍታት የአሕጉሪቱን የትምህርት ሕመም መታደግ አለባቸው።

እንደ ዳይሬክተር ዴኒስ አስተያየት የአፍሪካ መሪዎች በድርጅታቸው (AU) አማካኝነት እያንዳንዱ የአፍሪካ ልጅ ተገቢ የሆነ ትምህርት በተገቢና የሠለጠኑ መምህራን አማካኝነት እያገኘ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥና ካላገኘ እንዲያገኝ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን መፈተሽ አለባቸው። ሲፈትሹም የመምህራኑን የሥልጠና ደረጃ፣ ባለሙያነት፣ ምቹ የትምህርት አካባቢ ስለ መኖሩ ሁሉ ማካተት ይኖርባቸዋል፡፡

ጥናታዊ ሪፖርቱ በመውጫ አንቀፆቹ ላይ አንድ ለየት ያለ ጉዳይ ያነሳ ሲሆን፣ እሱም የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች፣ በተለይም ግብ 4 (MDGs 4)ን ለማሳካት በዓለም አቀፍ ደረጃ 44 ሚሊዮን የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን እንደሚያስፈልጉና ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብዛኛው ለአፍሪካ መሆኑን ነው።

ይህ ብቻም አይደለም፣ የጥናት ሪፖርቱ በመዝጊያ አንቀፁ ላይ አፍሪካን ብቻ የተመለከተ ሀሳብ የሰነዘረ ሲሆን፣ እሱም “አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግዴታ የሆነውን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በ2030 እውን ማድረግ ካለባት አሕጉሪቱ ብቁ የሆኑ 17 ሚሊዮን መምህራን ያስፈልጓታል ያለው ነው። እነዚህ መምህራን ብቃት ብቻ አይደለም ሊኖራቸው የሚገባው ብቃትና ጥራታቸውን ተከትሎ ፅድት ያለ ደመወዝና ምቹ የሥራ አካባቢዎች ያስፈልጓቸዋል፡፡

ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ አኳያ ብቻ በማየት በጉባኤው ላይ ስለ አፍሪካ ትምህርትና ሥርዓተ ትምህርት፤ እንዲሁም ትምህርትና የነገዋ አፍሪካ ምን ምን ጉዳዮች ተነስተው ነበር የሚለውን በጨረፍታ እናያለን።

በናይጄሪያ የሕፃናት ፓርላማ ምክትል አፈጉባኤ ኢብራሂም ዛና በተጠናቀቀው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደ ተናገሩት በአገራቸው በከፋ ጦርነት ምክንያት ትምህርት ቤቶች ሲወድሙና ሕፃናት ላይ አደጋ ሲደርስ ተስተውሏል፡፡ የአሕጉሪቱ መሪዎች ለዚህ ለዘንድሮው ‹‹2024 year of education›› የሚል ስያሜ ለተሰጠው ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተገዥ በመሆን ውሳኔውን ያለ ምንም መሸራረፍ ወደ መሬት ሊያወርዱ ይገባል።

ይህ ድርጊት በዚህ ከቀጠለ በአሕጉሪቱ የሚከተለው የትምህርት ተቋማት መውደም፣ መዘረፍ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ሌሎች በትምህርት ዙሪያ የሚሠሩ ሁሉ ሳይቀሩ መገደል፤ በመጨረሻም የትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መዘጋት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የሚቀረው ነገር የአፍሪካን መጪውን የጭለማ ዘመን መጠበቅ ነው።

ሌላው አስተያየት ሰጪ በ“ሴቭ ዘ ችልድረን የፓን አፍሪካ ጽሕፈት ቤት ጊዜያዊ ዳይሬክተር እና የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ መሐሙድ መሐመድ ሀሰን በአፍሪካ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንደሚገደሉ፣ የሽብር ወንጀል እንደሚፈፀምባቸው፣ ትምህርት ቤቶች በቦምብ እሩምታ እንደሚወድሙ የገለፁ ሲሆን፣ ሀሳባቸው በጉባኤተኞች ድጋፍን አግኝቶ አስቆዝሟል።

በአሕጉር አቀፍ የትምህርት ስትራቴጂ ለአፍሪካ (Continental Education Strategy for Africa (CESA)) አማካኝነት ወደ ተግባር ይቀየሩ ዘንድ የተዘረዘሩ አስራ ሁለት ነጥቦች ይፋ የተደረጉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በአሕጉሪቱ በየደረጃው የትምህርትን ተደራሽነትና ጥራትን ማረጋገጥ፣ የትምህርት መሠረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የተማሪና መምህራንን ጤና መጠበቅ፣ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን መሥራት፣ ቴክኖሎጂን ማስፋፋትና መጠቀም፤ የመምህራንን ሥልጠና ማካሄድ፣ ጥራት ያለው የትምህርት አመራርን መስጠት ፣ጥራትን መሠረት ያደረገ የሥልጠና ሥርዓት መዘርጋት ይገኙበታል፡፡

የትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ መሐይምነትን ከአሕጉሪቱ ለማጥፋት አሕጉር አቀፍ ዘመቻ ማድረግ፣ ሳይንሳዊና እውነተኛ መረጃዎችን ለመላው አፍሪካ ኅብረተሰብ በማሰራጨት ተደራሽ ማድረግ፣ የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶችን በተጠናከረ ሁኔታ ማስተማር፣ ሙያና ቴክኒክ (TVET) ተቋማትን ማስፋፋትና በተለያዩ ሙያዎች የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማስፋፋትና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በስፋትና በጥራት ማከናወን የሚሉትም ከአስራ ሁለቱ ነጥቦች ውስጥ ይካተታሉ፡፡

ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት፣ በሁሉም የትምህርት እርከኖች የሰላም ትምህርትን ማስፋፋት፣ ግጭት አፈታትን ማስረፅ፣ የትምህርት ባለ ድርሻ አካላትን በሙሉ ማሳተፍ የሚሉትም በአስራ ሁለቱ ነጥቦች ውስጥ ተካተዋል፡፡

የአፍሪካ ትምህርትን ወቅታዊ ሁኔታና አጠቃላይ ይዞታ በተመለከተ በአንዲት የጋዜጣ ገጽ ላይ ሁሉንም ማስተናገድ አይቻልም። የሚቻለው የዘንድሮውንና ሰሞኑን የተካሄደውን፤ መላው አፍሪካውያንን የሚወክለውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቅድሚያነትን ይዞ የነበረው የአሕጉሪቱ የትምህርት ጉዳይ እንደ መሆኑ መጠን እሱን አስመልክቶ ለትኩረት ያህል ጥቂት ማለት ብቻ ነው። በመሆኑም፣ መሪዎቹ በ2050 ከ2 አፍሪካውያን 1ዱ እድሜው ከ25 ዓመት በታች፤ እድሜያቸው ከ0-18 የሆኑ ልጆችና ወጣቶች 1 ቢሊዮን የሚደርስ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የዩኒሴፍ “Transforming Education in Africa: An evidence-based overview and recom­mendations for long-term improvements” ጥናት አመላክቷል፡፡

ስለዚህ እ.ኤ.አ 1800ዎቹና ከዛ በፊት እንደነበረው ትምህርት መዝናኛ (luxury) አለመሆኑን ከልብ በመገንዘብ መሪዎቹ ባሉት፣ በወሰኑት መሠረት እንደሚከውኑና በቃላቸው እንደሚፀኑ ይታመናል፡፡

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You